የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
በእግዚአብሔር ታመኚ - በእርሱ ተደገፊ
ውድ እህት ኤን ኤስ ሃሰከል ሆይ፣
…ብዙ ተንቀሳቅሰሽ መስራት በማትችይበትና ድካም እየተጫጫነሽ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር የሚፈልግብሽ ነገር ቢኖር በእርሱ እንድትታመኚ ነው፡፡ እንደ ታማኝ ፈጣሪ አድርገሽ በመመልከት የነፍስሽን ጥበቃ ለእርሱ አሳልፈሽ ስጪ፡፡ ምህረቱ የታመነና ቃልኪዳኑም ዘላለማዊ ነው፡፡ ተስፋው እውነትን ለዘላለም በሚጠብቅ በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው፡፡ አእምሮሽ ተስፋዎቹን ያስታውሳቸውና የሙጥኝ ይበላቸው፡፡ በከበሩ ቃል ኪዳኖቹ ውስጥ ያሉትን የበለጸጉ መተማመኛዎች እንዳሉ አእምሮሽ ማስታወስ ካልቻለ ከሌላ ሰው ከናፍር ስሚ፡፡ ለሚጠነቀቅላቸው ልጆቹ ያለውን ፍቅሩን፣ ርህራሄውንና ፍላጎቱን በሚያውጁ ከራሱ ከናፍር በሚወጡ በእነዚህ ቃላት ውስጥ ያለው እንዴት ያለ ሙላት፣ እንዴት ያለ ፍቅርና መተማመኛ ነው! Amh2SM 231.1
«እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሃሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” (ዘፀ. 34፡ 6፣ 7)፡፡ Amh2SM 231.2
ጌታ በስቃይ ውስጥ ላሉት ልጆቹ በርኅራኄ የተሞላ ነው፡፡ እርሱ ይቅር ሊላቸው የማይችላቸው እጅግ ትልልቅ ኃጢአቶች ምንድን ናቸው? እርሱ መሃሪ ስለሆነ ከመኮነን ይልቅ ይቅር ለማለት ሁልጊዜ ዝግጁና ደስተኛ ነው፡፡ ስህተት የማይፈልግብን ደግ አምላክ ነው፤ ከምን እንደተሰራን ያውቃል፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል፡፡ ገና ኃጢአተኞች ሳለን በነጻ በመውደዱ ስለ ክርስቶስ በማለት ብርሃኑን ሳይነፍግብን እያበራልን ገደብ የለሽ በሆነው ርኅራኄውና ምህረቱ ማፈግፈጋችንን ሁሉ ይፈውሳል፡፡ Amh2SM 231.3
እህቴ ሆይ፣ ጽድቅሽ የሆነውን ኢየሱስን ሁልጊዜ ትተማመኝበታለሽን? በልግስና በተሰጠሽ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልብሽ ፈሷል፡፡ ከክርስቶስ ጋር አንድ ነሽ፡፡ እንድትታገሺ ጸጋን ይሰጥሻል፣ እረፍት የለሽነትን ማሸነፍ እንድትችዪ ጸጋ ይሰጥሻል፣ በራሱ ጣፋጭ መንፈስ ልብሽን ያሞቀዋል፣ ነፍስሽ ደክሞ ሳለ ያነቃቀዋል፡፡ ሰማያዊ የሆነ የተሻለ አገር በመሻት እንግዳና ተንከራታች ለመሆን የቀሩት ቀናት ጥቂት ናቸው፡፡ ቤታችን በሰማይ ነው፡፡ ነፍስሽ በእግዚአብሔር ትታመን፡፡ ሸክሞችሽን በሙሉ በእርሱ ላይ አድርጊ፡፡ Amh2SM 231.4
እነሆ ልብሽ በአዳኙ ፊት ውበት የተነካው፣ በእርሱ ባሕርይ ማማር የተሳበው፣ እና የእርሱን ሥቃይ በማሰብ የተገዛው ስንት ጊዜ ነው! አሁን መላው ሸክምሽን በእርሱ ላይ እንድታሳርፊ ይፈልጋል፡፡ ሁልጊዜ እንዲያጽናናሽ አንድ ምዕራፍ እሰጥሻለሁ፡፡ «በዚያም ቀን አቤቱ፣ ተቆጥተኸኛልና፣ ቁጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፣ አጽናንተኸኛልና አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔም አምላኬ መድሃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፣ መድሃኒትም ሆኗልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ፡፡ ውኃንም ከመድሃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ» (ኢሳ. 12፡ 1-3)፡፡ Letter 146, 1891. Amh2SM 232.1