የልጅ አመራር

5/85

ምዕራፍ 3—የልጅ ሥልጠና መቼ መጀመር እንዳለበት

ትምህርት ከጨቅላነት ይጀምራል— “ትምህርት” የሚለው ቃል በኮሌጅ ከሚሰጥ የትምህርት ዘርፍ የላቀ ትርጉም አለው፡፡ ትምህርት የሚጀምረው ጨቅላው በእናቱ እቅፍ እያለ ነው፡፡ እናት የልጆቿን ባህርይ እየቀረጸችና እያስተካከለች ባለበት ጊዜ ትምህርት እየሰጠቻቸው ነው፡፡ 23 CGAmh 26.1

ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ይልኩና ይህንንም ከፈጸሙ በኋላ አስተምረናቸዋል ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ትምህርት ብዙዎች ከሚረዱት የላቀ ስፋት አለው፡፡ አንድ ልጅ ከጨቅላነት እስከ ልጅነት፣ ከልጅነትም እስከ ወጣትነት፣ እና ከወጣትነትም እስከ አከለ-መጠን ድረስ መምሪያ የሚቀበልበትን ሂደት ያካትታል፡፡ አንድ ልጅ ሐሳቦችን መፍጠር ከቻለበት ጊዜ ጀምሮ ትምህርቱ መጀመር አለበት፡፡ 24 CGAmh 26.2

አዕምሮ እጅግ ንቁ በሆነበት ጊዜ ይጀመር — የማስተማርና የማሰልጠን ሥራ ከልጅነት መጀመር አለበት፣ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ አዕምሮ ነገሮችን ለመቀበል ንቁ ስለሆነ የሚሰጡ ትምህርቶች ይታወሳሉ፡፡ 25 CGAmh 26.3

ልጆች ከእቅፍ ጀምሮ እስከ ጉልምስና ድረስ በቤት ትምህርት ቤት ሊሰለጥኑ ይገባቸዋል፡፡ እናም ልክ በሥርዓት እንደሚተዳደር አንድ ትምህርት ቤት፣ አስተማሪዎች ራሳቸውም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ያገኛሉ፣ በተለይም ርዕሰ-መምህር የሆነችው እናት እዚያ ለሕይወቷ እጅግ ዋጋ ያለውን ትምህርት ታገኛለች፡፡ 26 CGAmh 26.4

ተገቢ ቃላትን የመናገር የወላጅ ኃላፊነት ነው…፡፡ ወላጆች በየዕለቱ አፍቃሪያቸው ከሆነው ከክርስቶስ ትምህርት ቤት ትምህርት መቅሰም አለባቸው፡፡ ከዚያም ለጨቅላ መንጋዎች ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ፍቅር ታሪክ በቤት ትምህርት ቤት ውስጥ ይዘከራል፡፡ 27 CGAmh 26.5

ቀደም ተብሎ መሰጠት ስላለበት ሥልጠና ያጥኑ— ቀደም ተብሎ ለልጆች የሚሰጥ ስልጠና በጥንቃቄ ሊጠና የሚገባው ርዕስ ነው፡፡ የልጆች ድነት በይበልጥ በልጅነታቸው ጊዜ በሚሰጣቸው ሥልጠና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የልጆቻችንን ትምህርት እንደ አንድ ጉዳይ ማየት አለብን፡፡ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ንጹህ እንዲሆኑ የሚመኙ ከሆነ የራሳቸውን ልብና አዕምሮ በንጽህና መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ አባትና እናት እንደ መሆናችን መጠን ልጆቻችንን ራሳችን ማሰልጠንና ሥርዓት ማስያዝ ይኖርብናል፡፡ ከዚያም በኋላ ቤት ውስጥ እንዳለ መምህር ልጆቻችንን ለማይጠፋው ውርስ ይዘጋጁ ዘንድ ማሰልጠን እንችላለን፡፡ 28 CGAmh 27.1

የቀና ጅምር ያድርጉ— ልጆቻችሁ በዋጋ የተገዙ የእግዚአብሔር ንብረት ናቸው፡፡ ወላጆች ሆይ ጠንቃቆች ሁኑ፣ በክርስቶሳዊ መንገድም ተንከባከቧቸው፡፡ 29 CGAmh 27.2

ወጣቶች በጥንቃቄና በብልሃት መሰልጠን አለባቸው፣ ምክንያቱም በልጅነትና በወጣትነት የተመሰረተ ልምድ በመላው የሕይወት ጎዳን ላይ ተጣብቆ ይቀራል፡፡ የቀና ጅምር አስፈላጊነትን እንድንረዳ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ 30 CGAmh 27.3

የመጀመሪያውን ልጅ የማሰልጠን አስፈላጊነት—የመጀመሪያ ልጅ ሌሎች ቀጥሎ የሚወለዱትን ልጆችን ስለሚያስተምር በተለይ በታላቅ ጥንቃቄ መሰልጠን አለበት፡፡ ልጆች የሚያድጉት ዙሪያቸውን ከበው ባሉ ተጽዕኖ ሥር ነው፡፡ ጯኺና ሁከታም አይነት ሰው ያሳደጋቸው እንደሆነ እነርሱም እንዲሁ ጯኺና አልበገር ባይ ይሆናሉ፡፡ 9 CGAmh 27.4

በልጆች ስልጠና ተክል እንደ ምሳሌ— ተክል ከዘር ጀምሮ ቀስ በቀስ የሚያደርገው ዕድገት በልጆች ስልጠና ላይ እንደ ምሳሌ ነው፡፡ “በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች፡፡” ማርቆስ 4፡28፡፡ CGAmh 27.5

ይህን ምሳሌ የሰጠው እርሱ ራሱ ትንሽዋን ዘር በመፍጠር ልዩ ችሎታ ሰጣት፣ እድገቷን የሚቆጣጠረውንም ሕግ በውስጧ አስቀመጠ፡፡ እናም በምሳሌ ውስጥ የተስተማረው እውነት በራሱ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊነትን አገኘ፡፡ የሰማይ ግርማዊ፣ የክብር ንጉስ የሆነው የቤተልሔም ሕጻን ሆነ፣ ለጊዜውም በእናቱም እንክብካቤ ውስጥ ያለ ረዳት አልባ ልጅም መሰለ፡፡ በልጅነቱ ጊዜ ወላጆን በማክበር እና ምኞታቸውንም ጠቃሚ በሆነ ሁኔታ በመፈጸም እንደ ልጅ ተናገረ እንደ ልጅም ነገሮችን አደረገ፡፡ ነገር ግን ራሱን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በጸጋና በእውነት እውቀት ዘወትር ያድግ ነበር፡፡ 31 CGAmh 28.1