የልጅ አመራር
ምዕራፍ 45—በፍቅር እና በጽናት
ሁለት መንገዶች እና መጨረሻቸው— ልጆችን ለመያዝ ሁለት መንገዶች አሉ — እነዚያም በመሠረታዊ መርህ እና በውጤቶች በጣም የሚለያዩ መንገዶች ናቸው። በእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮ መሠረት ተማኝነት እና ፍቅርን ከጥበብ እና ጽኑነት ጋር ማጣመር፣ ለዚህም ሆነ ለመጻኢው ህይወት ደስታን ያመጣል፡፡ ኃላፊነትን ችላ ማለት፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ፍላጎትን ማርካት፣ የወጣትነት ስህተቶችን መግታት ወይም ማረም አለመቻል፣ በልጆች ላይ ሐዘን እና የመጨረሻ ጥፋትን እና በወላጆች ላይ ተስፋ መቁረጥ እና ጭንቀትን ያስከትላል። 501 CGAmh 244.1
ፍቅር መንታ እህት አላት፣ እርሷም ተግባር ናት። ፍቅር እና ተግባር ጎን ለጎን ይቆማሉ፡፡ ተግባር ችላ ተብሎ የሚገለጥ ፍቅር ልጆችን ሀሳበ ግትር፣ አስቸጋሪ፣ ጠማማ፣ ራስ ወዳድ እና የማይታዘዙ ያደርጋቸዋል፡፡ እንዲራሩ እና እንዲሸነፉ ከሚያደርግ ፍቅር ውጭ ጥብቅ ተግባር ብቻውን እንዲተው ሲደረግ፣ ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል። ልጆች በትክክል እንዲታረሙ ተግባር እና ፍቅር መዋሀድ አለባቸው።2 CGAmh 244.2
ያልታረሙ ስህተቶች ደስተኛ አለመሆንን ያመጣሉ— የሕፃናትን ምኞት መከልከል ወይም የልጁን ፍላጎት መቃወም አስፈላጊ በሚመስልበት ጊዜ ይህ ለወላጆች እርካታ፣ ወይም አምባገነናዊ ስልጣናቸውን ለማስፈፀም ሳይሆን ለእርሱ ጥቅም መሆኑን በልጁ ውስጥ በጥልቀት መስረጽ አለበት፡፡ ያልታረመ ስህተት ሁሉ ደስተኛ አለመሆንን ወደ ራሱ እንደሚያመጣ እና እግዚአብሔርን እንደማያስደስት መማር አለበት፡፡ ልጆች በእንደዚህ ዓይነቱን ሰልጠና ሥር የራሳቸውን ፈቃድ ለሰማያዊ አባታቸው ፈቃድ በማስገዛት ከፍተኛ ደስታ ያገኛሉ። 502 CGAmh 244.3
የራሳቸውን ስሜት እና ዝንባሌ የሚከተሉ ወጣቶች በዚህ ሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ የላቸውም፣ በመጨረም የዘላለም ሕይወት ያጣሉ፡፡ 503 CGAmh 244.4
ትህትና የቤቱ ሕግ መሆን አለበት — የእግዚአብሔር አገዛዝ ዘዴ ልጆች እንዴት መሰልጠን እንዳለባቸው የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡ በጌታ አገልግሎት ውስጥ ጭቆና የለም፣ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ጭቆና ሊኖር አይገባውም፡፡ ሆኖም ግን ወላጆችም ሆኑ አስተማሪዎች ቃላቶቻቸው ችላ እንዲባሉ መፍቀድ የለባቸውም። ልጆች ስህተትን ሲሰሩ እነርሱን ከማረም ችላ ካሉ እግዚአብሔር ስለ ቸልተኝነታቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ተግሳጽ በልኩ ይሁን፡፡ ትህትና የቤትና የትምህርት ቤት ሕግ ይሁን። ልጆቹ የጌታን ህግ እንዲጠብቁ ይማሩ፣ እናም ጽኑ እና የፍቅር ተጽዕኖ ከክፉ እንዲርቁ ያድርጓቸው። 504 CGAmh 245.1
የልጅነት አላዋቂነትን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ— አባቶች እና እናቶች ቤት ውስጥ የእግዚአብሄርን ባህሪይ መወከል አለባችሁ፡፡ ታዛዥነትን እንደመጠይቅ ስታቀርቡ በቃላት ማዕበል ሳይሆን በትህትና እና ፍቅር መሆን አለበት፡፡ ልጆቻችሁ ወደ እናንት እንዲሳቡ ርህራሄ የተሞላችሁ ሁኑ፡፡ 505 CGAmh 245.2
ቤት ውስጥ ደስተኞች ሁኑ፡፡ ቁጣ የሚያስነሳውን ቃል ሁሉ ተቆጣጠሩ። “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው” የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ልጆቻችሁ በዕድሜያቸው እና ተሞክሮአቸው ገና ለጋ እንደሆኑ አስታውሱ። እነርሱን በመቆጣጠር እና በመገሠጽ ረገድ ጽኑ፣ ነገር ግን ሩህሩህ ሁኑ፡፡ 506 CGAmh 245.3
ልጆች ሁልጊዜ ትክክለኛውን ከስህተት ለይተው አይገነዘቡም እናም ስህተት ሲሰሩ በርህራሄ እነርሱን ከማስተማር ይልቅ ብዙውን ጊዜ የጭካኔያዊ አያያዝ ይይዟቸዋል። 507 CGAmh 245.4
በልጆች አለመታዘዝ ምክንያት ወላጆች እንዲጎዷቸው እና እንዲጨቁኗቸው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ምንም ፈቃድ አልተሰጠም። በቤት ውስጥ ሕይወት እና በብሔራት መስተዳድር ውስጥ፣ የእግዚአብሔር ሕግ፣ ከልብ ውስጥ ወሰን የሌለው ፍቅር ይፈስሳል፡፡9 CGAmh 245.5
ጥሩ ላልሆነ ልጅ ሩህሩህ መሆን — ወላጆች ስህተት የሚሰሩ ልጆቻቸውን በክርስቶስ ጥበብ የመያዝን አስፈላጊነት አያለሁ…፡፡ ታላቅ ትዕግሥትና ርህራሄ፣ እጅግ እንዲታዘንለት የሚገባቸው ጥሩ ያልሆኑ ልጆች ናቸው፡፡ ነገር ግን ብዙ ወላጆች ስህተትን ወደ ንስሃ የማይመራውን ቀዝቃዛ፣ ርህራሄ ያሌለው መንፈስን ያሳያሉ። የወላጆች ልብ በክርስቶስ ፀጋ ይራራ፣ እናም ፍቅሩ ወደ ልብ ለመግባት መንገድ ያገኛል። 508 CGAmh 245.6
የአዳኙ ሕግ — “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” (ሉቃስ 6፡ 31) - የልጆችን እና የወጣቶችን ስልጠና ለሚያከናውኑ ሁሉ ሕግ መሆን አለበት። እነርሱ ከእኛ ጋር የሕይወት ጸጋ ወራሾች የሆኑ የጌታ ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡ የክርስቶስ ሕግ ለቀርፋፋው፣ ለታናሹ፣ እጅግ ጅል ለሆነው አልፎ ተርፎም ለሚሳሳተው እና ለዓመፀኛው እንኳን ሳይቀር የክርስቶስ ህግጋት በቅድስና መከበር አለበት።11 CGAmh 246.1
ልጆች እንዲያሸንፉ እርዷቸው — እግዚአብሔር ለልጆቹ ሩህሩህ ነው፡፡ እርሱ በየቀኑ ድሎችን እንዲያገኙ ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም ልጆች አሸናፊዎች እንዲሆኑ ለመርዳት እንትጋ፡፡ አናዳጅ የሆኑ ሁኔታዎች ከገዛ የቤተሰባቸው አባላት እንዲመጣባቸው አትፍቀዱ። ድርጊቶቻችሁ እና ቃላቶቻችሁ የልጆቻችሁን ቁጣ የሚቀሰቅስ አይነት ባህሪይ እንዲኖረው አትፍቀዱ፡፡ ሆኖም ግን ስህተት ሲሰሩ በታማኝነት ተግሣጽ እና እርማት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ 509 CGAmh 246.2
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጊዜ ሁሉ አመስግኗቸው — ልጆች ጥሩ በሚሰሩበት ጊዜ አመስግኗቸው፣ ምክንያቱም ፍትሃዊ አመስጋኝነት በዕድሜ ለገፉት እና ለአስተዋዮች እንደሚረዳ ሁሉ ለእነርሱም በጣም ጠቃሚ ነው። ቤት ውስጥ በሚገኝ ቤተ መቅደስ ውስጥ በጭራሽ ብልሹ አትሁኑ፡፡ ክርስቲያናዊ ጨዋነትን እያሳያችሁ፣ ልጆቻችሁ ለሚሰጧችሁ ድጋፎች አመስጋኝ በመሆን ደጎችና እና ርህሩሆች ሁኑ፡፡13 CGAmh 246.3
ደስተኛ ሁኑ። በጭራሽ ስሜታዊ ቃላትን በጩኸት አትናገሩ፡፡ ልጆቻችሁን በመገደብ እና በመገሠጽ ረገድ ጽኑ፣ ነገር ግን ሩህሩህ ሁኑ። የቤተሰቡ ድርጅት አባላት እንደመሆናቸው ተግባራቸውን እንዲሰሩ አበረታቷቸው፡፡ የተሳሳተ ነገር የመስራት ዝንባሌያቸውን ለማስቀረት ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆታችሁን ግለጹላቸው። 510 CGAmh 246.4
ከራሳቸው ቤተሰቦች ትዕዛዝ ሲኖርባቸው ልጆቻችሁ እንዲሆኑ የምትፈልጉት አይነት ሁኑ፡፡ እነርሱ እንዲናገሩ እንደምትፈልጉት ተናገሩ፡፡ 511 CGAmh 247.1
የድምጻችሁን ቃናዎችን ተቆጣጠሩ— የትኛውም የስሜታዊነት ምልክት በማይገለጽበት ሁል ጊዜ በእርጋታ እና በጸኑ ድምፅ ተናገሩ፡፡ ፈጣን ታዛዥነትን ለማረጋገጥ ስሜት አስፈላጊ አይደለም።16 CGAmh 247.2
አባቶችና እናቶች፣ ለልጆቻችሁ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ በምን ተጽዕኖዎች ሥር እንደምታደርጓቸው በማወቅ ተጠንቀቁ፡፡ በመንቀፍ ወይም በማበሳጨት በእነርሱ ላይ ለጥቅማቸው መሆን የነበረበትን ተጽዕኖአችሁን እንዳታጡ። እንድትመሯቸው እንጂ የአዕምሯቸውን ስሜት እንድታነሳሱ መሆን የለበትም። የሚያስቆጣችሁ ነገር ምንም ይሁን ምን የድምጻችሁ ቃና ምንም ዓይነት ቁጣ እንደማያበርድ እርግጠኛ ሁኑ፡፡ የሰይጣን መንፈስ መገለጽን በውስጣችሁ እንዲያዩ አታድርጉ፡፡ ይህ ልጆቻችሁን ለመጪው ዘላለማዊ ሕይወት ብቁ እንድታደርጓቸው እና እንድታሰለጥኗቸው አይረዳችሁም፡፡ 512 CGAmh 247.3
ጽድቅ ከምህረት ጋር መዋሀድ አለበት— እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን እና ንጉሣችን ነው፣ ወላጆችም እራሳቸውን ሕጉ ስር ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ ሕግ በወላጆች በኩል የሚደረገውን ማንኛውንም ጭቆና እና በልጆች በኩል ያለውን አለመታዘዝ ይከለክላል። ጌታ በፍቅር ርህራሄ፣ በምሕረት እና በእውነት የተሞላ ነው፡፡ ሕጉ ቅዱስ፣ ጻድቅ እና መልካም ነው፣ በወላጆች እና በልጆችም መከበር አለበት። የወላጆችን እና የልጆችን ሕይወት መቆጣጠር ያለባቸው ህጎች ወሰን ከሌለው ፍቅር ልብ የሚፈስ እና የእርሱን ሕግ በቤታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉ ወላጆች እና ይህን ሕግ በሚታዘዙ ልጆች ላይ የእግዚአብሔር የተትረፈረፉ በረከቶች ያርፋሉ። የምህረት እና የጽድቅ ጥምር ተጽዕኖ ስሜት መኖር አለበት። “ምህረት እና እውነት ተገናኙ፣ ጽድቅ እና ሰላም ተስማሙ።” በዚህ ስነ-ስርዓት ስር ያሉ ቤቶች ጽድቅ እና ፍርድን ለማድረግ በጌታ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ 513 CGAmh 247.4
አገዛዙ ጨቋኝ እንዲሆን የሚፈቅድ ወላጅ ከባድ ስህተት እየሠራ ነው፡፡ በልጅነት ልባቸው ውስጥ በተግባር እና በፍቅር ቃላት የሚፈሰውን ፍቅር እያጠፋ በልጆቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ራሱም ላይ ስህተት ይሰራል፡፡ ለልጆች የሚገለጽ ርህራሄ፣ ይቅር ባይነት እና ፍቅር ተመልሶ ለወላጆቹ ይንፀባርቃል። የዘሩትን እንዲሁ ያንኑ ያጭዳሉ…፡፡ CGAmh 248.1
ጽድቅን ተግባራዊ ለማድረግ በምትሹበት ጊዜ፣ መንትያ እህት እንዳላት አስታውሱ፣ እርሷም ምህረት ናት፡፡ ሁለቱ ጎን ለጎን ይቆማሉ፣ መለያየትም የለባቸውም። 514 CGAmh 248.2
ኃይለኝነት ጠበኛ መንፈስን ያነሳሳል። ኃይለኛ ለሆኑ ወላጆች የተሰጠ ምክር — ጥብቅነትና ጽድቅ ከፍቅር ጋር ያልተጣመረ እንደሆነ፣ ልጆቻችሁ ትክክለኛውን ነገርን እንዲያደርጉ አይመራቸውም። ጠበኛ መንፈስ በውስጣቸው ምን ያህል በፍጥነት እንደሚነሳ ልብ ይበሉ፡፡ አሁን በግዴታ ሳይሆን እነርሱን ለማስተዳደር የተሻለ መንገድ አለ፡፡ ጽድቅ መንታ እህት አላት፣ እርሷም ፍቅር ናት፡፡ ፍቅር እና ጽድቅ በአስተዳደርዎ ሁሉ ውስጥ እጃቸውን ያጨብጭቡ፣ እና በእርጥጠኝነት የእግዚአብሔር ድጋፍ ከጥረታችሁ ጋር ይተባበራል፡፡ እግዚአብሔር የሚቀበለው ባህሪይ ይኖራችሁ ዘነድ፣ ባለጸጋ የሆነው ቤዛችሁ ሊባርካችሁ ይፈልጋል፣ አዕምሮውን፣ ፀጋውን እና ማዳኑን ሊሰጣችሁም ይፈልጋል።20 CGAmh 248.3
የወላጆች ስልጣን ፍጹም መሆን አለበት፣ ሆኖም ግን ይህ ኃይል አላግባብ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም። ልጆቹን በመቆጣጠር ረገድ አባት በስሜት ቁጥጥር ሳይሆን ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት መመራት አለበት፡፡ የእራሱን መጥፎ ባህሪዎች እንዲመራው ከፈቀደ፣ ጨቋኝ ይሆናል፡፡ 515 CGAmh 248.4
ገስጹ፣ ነገር ግን ከልብ ከመነጨ ርኅራሄ ጋር ይሁን— ልጆቻችሁ ላይ ስህተቶች እና አስቸጋሪነትን እንደምትመለከቱ ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንደሚነጋገሩ እና እንደሚቀጧቸው ይነግሯችኋል፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ተጨባጭ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ማየት አይችሉም፡፡ እንደነዚህ ያሉ ወላጆች አዳዲስ ዘዴዎችን ይሞክሩ፡፡ ርህራሄ እና ፍቅርን ከቤተሰባቸው አስተዳደር ጋር ያዋህዱ፣ ሆኖም ግን ለትክክለኛ መርሆዎች እንደ ዐለት የጸኑ ይሁኑ፡፡ 516 CGAmh 248.5
ከወጣቶች አያያዝ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው እንደ ብረት የጠነከረ ልብ ያለው ሳይሆን፣ ነገር ግን አፍቃሪ፣ ርኅሩኅ፣ አዛኝ፣ ትሑት፣ የሚማርክ እና ጓደኝነትን የሚያውቅ መሆን አለበት፤ ሆኖም ግን ዘለፋ መሰጠት እንዳለበት፣ እና ተግሳጽም ቢሆን እንኳን ክፋትን ለማስወገድ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። 517 CGAmh 249.1
ወላጆችን በገዛ ቤታችሁ ውስጥ የባህሪይን አርማ ከፍ አድርጉ እንድላቸው ትእዛዝ ተሰጥቶኛል፡፡ ልጆቻችሁ እንዲታዘዙ አስተምሯቸው፡፡ በፍቅርና የክርስቶስ ዓይነት ሥልጣን ጥምር ተጽዕኖ ግዟቸው። ሕይወታችሁ ለቆርኔሌዎስ “እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚፈራ” ተብሎ እንደ ተነገረለት የምስጋና ቃል እንዲነገርላችሁ ይሁን። 518 CGAmh 249.2
መጉዳትንም ሆነ ከልክ ያለፈ ምኞትን ማርካትን አትለማመዱ— ልጆችን ተስፋ የሚያስቆርጥ የወቀሳ ተግሳጽ ወይም ስሜታዊ እርምት ማድረግ እና ከዚያ ስሜት በሚቀየርበት ጊዜ፣ በመሳም ወይም ጎጂ በሆኑ እርካታዎች እነርሱን ማረጋጋትን አንደግፍም፡፡ ከልክ በላይ ምኞታቸውን ማርካትም ሆነ አላስፈላጊ ጉዳት በተመሳሳይ ሁኔታ መወገድ አለባቸው። ንቁነት እና ጽኑነት አስፈላጊዎች ቢሆኑም እንኳ አዛኝነት እና ርኅራሄም እንዲሁ ናቸው። ወላጆች፣ ከፈተና ጋር ከሚታገሉ ልጆች ጋር እንደምትሰሩ፣ እና እነዚህ ክፉን የሚያነሳሱ ሁኔታዎች ጎልማሳ ዕድሜ ያላቸውን ሲያጠቋቸው ለመቋቋም አስቸጋሪዎች እንደ ሆኑ ሁሉ ለእነርሱም በጣም ከባድ እንደሆኑ አስታውሱ። ቀና የሆነውን ለማድረግ የሚመኙ ልጆች ደጋግመው ይወድቃሉ፣ እናም ብዙ ጊዜ ለኃይል እና ለጽናት ማበረታቻ ይፈልጋሉ። የእነዚህ ወጣት አእምሮዎች ሥራን በጸሎት በማሰብ ተመልከቷቸው። እያንዳንዱን ጥሩ ስሜትን አጠናክሩ፤ እያንዳንዱንም መልካም ተግባር አበረታቱ። 519 CGAmh 249.3
ወጥ ጽኑነትን፣ ስሜታዊ ያልሆነ ቁጥጥር ይኑራችሁ— ልጆች ትብ እና አፍቃሪ ተፈጥሮ አላቸው። እነርሱ በቀላሉ ይደሰታሉ፣ በቀላሉም ያዝናሉ፡፡ በፍቅር ቃላት እና ድርጊቶች አማካይነት በሚደረግ የእርጋታ ተግሣጽ እናቶች ልጆቻቸውን በልቦቻቸው ላይ ሊያስሩ ይችላሉ፡፡ ወጥ ጽኑነት እና ስሜታዊነት የሌለው ቁጥጥር ለእያንዳንዱ ቤተሰብ እርማት አስፈላጊ ነው። ለማለት የፈለጋችሁን በረጋ መንፈስ ተናገሩ፣ በአሳቢነት ተንቀሳቀሱ፣ የተናገራችሁትን ያለ ዝባት አከናውኑ፡፡ CGAmh 250.1
ከልጆቻችሁ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ውስጥ ፍቅርን ለማሳየት ይረዳችኋል፡፡ በልጆቻቸው የልጅነት ስፖርቶች፣ ደስታዎች እና ሀዘኖቻቸው ውስጥ የሀዘኔታ ስሜት በማጣት አትግፏቸው፡፡ በጭራሽ ግንባራችሁ እንዲቋጠርባቸው ወይም ክፉ ቃላት ከከንፈሮቻችሁ እንዲያመልጡ አትፍቀዱ፡፡ 520 CGAmh 250.2
ርህራሄ እንኳን ወሰን ሊኖረው ይገባል፡፡ ሥልጣን በጥብቅ ጽናት መረጋገጥ አለበት፣ አለበለዚያ ብዙዎች እንደ ፌዝ እና ንቀት ይወስዱታል። በወላጆች እና በአሳዳጊዎች ወጣቶች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ርህራሄ ተብዬው፣ መለማመጥ እና አግባብነት የሌላቸውን ምኞትን ማርካት በእነርሱ ላይ ሊመጣ ከሚችል እጅግ ክፉ ነገር ነው፡፡ ጽኑነት፣ ውሳኔ፣ አዎንታዊ መስፈርቶች በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡27 CGAmh 250.3
የራሳችሁን ስህተቶች አስታውሱ— አባትና እናት እራሳቸው ልጆች የነበሩ ነገር ግን አሁን ያደጉ መሆናቸውን ያስታውሱ፡፡ በመንገዳቸው ላይ ታላቅ ብርሃን ቢያበራ እና ረጅም ልምምድ ቢኖራቸውም እንኳ ምን ያህል በቀላሉ በምኞት፣ በቅናት እና በክፋ ጥርጣሬ ይታመሱ ነበር፡፡ ስለ ራሳቸው ስህተቶች ሲሉ የተሳሳቱ ልጆቻቸውን በእርጋታ መያዝን መማር አለባቸው፡፡ 521 CGAmh 250.4
አንዳንድ ጊዜ ልጆቻችሁ እናንተ ከነገራችኋቸው በተቃራኒ ስለሚሄዱ ልትበሳጩ ትችላላችሁ። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጌታ እንድታደርጉ ካዘዛችሁ በተቃራኒ እንደሄዳችሁ አስባችሁ ታውቃለችሁ? 522 CGAmh 250.5
ፍቅርና መተማመንን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል— ወላጆች እና አስተማሪዎች ከልጆቻቸው ወይም ከተማሪዎቻቸው ጋር በበቂ ሁኔታ ወደ ማህበራዊ ግንኙነት ሳይመጡ እጅግ ብዙ ትዕዛዝ መስጠቱ እና ማስገደዱ አደገኛ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከመጠን በላይ ቁጥብ በመሆን የልጆቻቸውን እና የተማሪዎቻቸውን ልብ ማሸነፍ በማይችል መልኩ በቀዘቀዘ እና ርህራሄ በጎደለው መልኩ ሥልጣናቸውን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ራሳቸው መሰብሰብ ቢችሉ እና እንደሚወዷቸው ቢያሳዩአቸው፣ በጥረታቸውም ሁሉ ላይ ፍላጎት እንዳላቸው ቢያሳዩአቸው፣ በስፖርታቸውም ቢሆን፣ አንዳንድ ጊዜም በመካከላቸው ልጅ በመሆን፣ ልጆቻቸውን እጅግ የሚያስደስቱ፣ ፍቅራቸውን የሚያተርፉ እና ልባቸውን የሚያገኙ ይሆናሉ፡፡ እናም ልጆች በፍጥነት የወላጆቻቸውን እና የአስተማሪዎቻቸውን ስልጣን ማክበር እና መውደድን ይማራሉ። 523 CGAmh 251.1
ክርስቶስን መምሰልን ተመኙ — እርሱ [ክርስቶስ] እራሱን ከዝቅተኞች፣ ከችግረኞች እና ከተቸገሩ ጋር ራሱን ቆጠረ። ትናንሽ ልጆችን በእጆቹ አቅፎ ወደ ልጅነት ራሱን አወረደ፡፡ ታላቅ የፍቅር ልቡ ችግሮቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን አስተዋለ፣ በደስታቸውም ተደሰተ። መንፈሱ በከተማው የታይታ ጉድጉድ እና ግራ መጋባት ዝሎ፣ ተንኮለኛ እና ግብዝ ከሆኑ ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ደክሞ፣ በየዋህ ሕፃናት ማህበረሰብ ውስጥ እረፍት እና ሰላም አገኘ፡፡ የእርሱ መገኘት በጭራሽ አልገፋቸው፡፡ የሰማዩ ባለ ግርማ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለመስጠት ራሱን ዝቅ አድርጓል፣ የልጅነት ግንዛቤያቸውንም ለመድረስ ወሳኝ ትምህርቶቹን ቀለል አድርጓል። በልጅነት እና እየሰፋ ባለው አዕምሮ ውስጥ በመብቀል በመከር ጊዜ ብዙ ፍሬዎችን የሚያፈራ የእውነትን ዘር ተከለ፡፡31 CGAmh 251.2
መጽናናትን የሚሻ ያልታረመ ወጣት — ደብዳቤዎችዎን በፍላጎትና በአዘኔታ አንብቤያለሁ። ልጅዎ ከዚህ በፊት አንድም ሰው በጭራሽ አስፈልጎት በማያውቅ አይነት ሁኔታ አሁን አባት ያስፈልገዋል እላለሁ፡፡ እርሱ ስህተት ሰርቷል፤ እርሶም ያውቁታል፣ እርሶም እንደሚያውቁ እርሱም ያውቃል፤ እናም በየዋህነቱ ጊዜ በሰላም መናገር የነበረብዎትእና ምንም ክፉ ውጤት የማያመጡት ቃላት፣ አሁን ርህራሄ የጎደላቸው እና እንደ ቢላ ሹል ሆነዋል…፡፡ ወላጆች እጅግ ከሚያዋርዱበት የልጃቸው ስህተት ተግባር ሀፍረት እንደሚሰማቸው አውቃለሁ፣ ነገር ግን ስህተት ሰሪው እኛ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ፍቅሩን የሰጠን እና እስከ አሁንም ድረስ እየሰጠን ያለውን፣ ከኃጢያታችን እና ከአመጻችን እንድንመለስ በመጋበዝ መተላለፋችንን ይቅር የሚለንን ሰማያዊ ወላጃችንን ከምናቆስለው በላይ የምድራዊ ወላጃቸውን ልብ ያቆስላሉን? CGAmh 251.3
ፍቅርዎን አሁን አይንፈጉት፡፡ ያ ፍቅር እና ርህራሄ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ያስፈልጋል። ሌሎች ልጅዎን በጭካኔ ሲመለከቱ እና ስህተቶቹ ላይ እጅግ ክፉ ገለጻ ሲሰጡበት፣ አባት እና እናት በርህራሄ እርምጃዎቹን ደህንነታቸው አስተማማኝ ወደ ሆኑ ጎዳናዎች ለመምራት መሻት የለባቸውምን? የልጃችሁ ኃጢአት አይነት ምን እንደ ሆነ አላውቅም፣ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን፣ ፍትህን እየሰሩ ከሚመስላቸው ከሰብአዊ ሰው ከንፈሮች የሚወጡ አስተያየቶች፣ ከሰብአዊ ሰው ተግባራት የሚመጡ ግፊቶች፣ እጅግ ስላፈሩበት እና ስለተዋረዱበት ልጅዎን ጭራሽ ማመን እና መተላለፉን መርሳት እንደማይችሉ ለልጁ ትርጉም ወደሚሰጠው አካሄድ እንዳይመራዎት ብል ደህንነት ይሰማኛል፡፡ ስህተት ለሰራው ልጅ ተስፋ እንዲቆርጡ ምንም አያድርግዎ፣ ፍቅር እና ርህራሄዎን ምንም ነገር አያጥፋ፡፡ ስሕተት በመስራቱ ብቻ፣ ይፈልግዎታል፣ ከሰይጣን ወጥመድም ለመዳን የአባትና እና የእናት እርዳታ ይፈልጋል። በእምነት እና በፍቅር አጥብቀው ይያዙት፣ ከእርሶም በላይ እንኳ በእርሱ ላይ ፍቅር ያለው መኖሩን በማስታወስ አዛኝ ከሆነው አዳኝ ጋር ይጣበቁ…። CGAmh 252.1
ተስፋ ስለ መቁረጥ አትናገሩ፡፡ ስለ ብርታት ተናገሩ። እናንተ፣ አባቱ እና እናቱ እግሮቹ በየሱስ አስተማማኝ እርዳታ እና የማይናወጥ ብርታት እንዲያገኙ ጠንካራ ዓለት፣ ማለትም ክርስቶስ የሱስ ላይ ይተከሉ ዘንድ ከሰማይ ጋር እንዲገናኝ እንደምትረዱት፣ ራሱን መቤዠት እንደሚችልም ንገሩት፡፡ የእርሱ ጥፋት በጣም ከባድ ከሆነ፣ ዘወትር ይህንኑ በእርሱ ላይ ግፊት ማድረግ ልጃችሁን አይፈውሰውም፡፡ ነፍስን ከሞት ለማዳን እና ነፍስን ብዙ ኃጢአቶችን እንዳያደርግ ለመጠበቅ ትክክለኛ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ 524 CGAmh 252.2
ችኩል ስሜትን ለማሸነፍ መለኮታዊ እገዛን እሹ— ለእያንዳንዱ አባትና እናት፣ ችኩል ስሜት ካላችሁ ይህን ለማሸነፍ እግዚአብሔርን ፈልጉ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ትዕግሥታችሁ እንዲያልቅ ቢያስቆጧችሁ፣ ወደ ክፍላችሁ ሂዱ እና ተንበርክካችሁ በልጆቻችሁ ላይ ትክክለኛ ተጽዕኖ እንዲኖራችሁ እግዚአብሔር እንዲረዳችሁ ጠይቁት፡፡ 525 CGAmh 252.3
እናቶች ሆይ፣ ለትዕግስት ማጣት ስትሸነፉ እና ልጆቻችሁን የጭካኔ አያያዝ ስትይዟቸው፣ ከክርስቶስ ሳይሆን ከሌላ መምህር የተማራችሁ ናችሁ፡፡ የሱስ እንዲህ ብሏል:-“ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና። ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” ስራችሁ ከባድ ሆኖ ካገኛችሁት፣ ለችግሮች እና ፈተናዎች ቅሬታ ስታቃርቡ፣ ፈተናን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ የለንም፣ ትዕግሥት ማጣትን ማሸነፍ አንችልም፣ የክርስትና ሕይወት ከባድ ዳገት ነው ስትሉ፣ የክርስቶስን ቀንበር እየተሸከማችሁ እንዳልሆነ እወቁ፤ የሌላውን ጌታ ቀንበር እየተሸከማችሁ ነው። 526 CGAmh 253.1
መለኮታዊውን ምስል ማንፀባረቅ— ቤተክርስቲያኑ ትሁት እና ረጋ ያለ መንፈስ ያላቸውን ይቅር ባይ እና ታጋሽ ሰዎችን ትፈልጋለች፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት እነዚህን ባህሪዎች ይማሩ፡፡ ወላጆች ከጊዜያዊ ምቾት ይልቅ የልጆቻቸውን ዘላለማዊ ጥቅም የበለጠ ያስቡ። ልጆቻቸውን ትናንሽ የጌታ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ ይቁጠሯቸው፣ መለኮታዊውን ምስል እንዲያንጸባርቁ በሚመራቸው መልኩ ያሠለጥኗቸው፣ ይገስጿቸውም። 527 CGAmh 253.2