ቀደምት ጽሑፎች
71—ሁለተኛው ትንሳኤ
የሱስ፣ መላእክቱና መላው የዳኑ ቅዱሳን በአንድ ላይ ከተማዋን ለቅቀው ወጡ፡፡ መላእክት አዛዣቸውን በመክበብ አጅበውት ሲወጡ ከእነርሱ በመቀጠል የዳኑት ቅዱሳን ተከተሉ: ከዚያም በሚያስፈራ ግርማ የሱስ የሞቱትን ኃጥአን ተጣራ፡፡ እነርሱም ያንኑ ወደ መቃብር ይዘውት የወ ረዱትን ሟችና ታማሚ አካል ይዘው ተነሱ፡፡ ምን ዓይነት ትዕይነት ነው! በመጀመሪያው ትንሳኤ ሁሉም የማይሞተውን አካል ለብሰው ነበር የተነሱት፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው ትንሳኤ በተነሱት ላይ የእርግማን ምልክት ይታይ ነበር፡፡ የምድር ነገሥታትና ታላላቅ ሰዎች፣ ጨካኞችና ጸለምተኞች ፣ የተማሩና ያልተማሩ ሁሉም በአንድነት ተነሱ፡፡ በቅዱስ አናቱ ላይ የእሾህ ጉንጉን በማድረግ የናቁት የተሳለቁበትና የተፉበት ሁሉ የሰውን ልጅ በንጉሣዊ ክብሩ ተመለከቱት፡፡ እነዚያ በሸንጎ የተፉበት አሁን ግን ውስጥን ሰንጥቆ ከሚያልፈው አስተያየቱና በግርማ ከተሞላ ገጽታው ፊታቸውን ሸሸጉ፡፡ እነዚያ እጆቹንና እግሮቹን የቸነከሩ አሁን እነዚያን የተሰቀለባቸውን ምልክቶች ይመለከታሉ፡፡ ጎኑን በጦር የወጉ የጭካኔአቸውን ምልክት በአካሉ ላይ ያያሉ፡፡ ይህ አሁን በታላቅ ግርማ የሚያዩት እነርሱ የሰቀሉትና በከፋ ህማም ውስጥ ሆኖ የተሳለቁበት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ከነገሥታት ንጉሥና ከጌቶች ጌታ ለመሸሸግ በሚያደርጉት መፍጨርጨር ከፍ ያለ ሥቃይና መከራ ይቀበላሉ:: EWAmh 216.3
እነዚያ በአንድ ወቅት የናቁት ሁሉ አሁን ከአስፈሪ ግርማው በመሸሽ በዐለቶች ውስጥ ለመሸሸግ ይሞክራሉ፡፡ በንጉሣዊ ግርማውና ኃያልነቱ በመደነቅና በመታወክ ሁሉም ድምፆቻቸውን በአንድነት ከፍ አድርገው «በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” ብለው ይጮኻሉ፡፡ EWAmh 217.1
ከዚያም የሱስ በመላእክቱና በቅዱሳን ታጅቦ እንደገና ወደ ከተማዋ ሲሄድ የኃጥአን የመረረ ልቅሶና ዋይታ አየሩን ይሞላዋል፡፡ ከዚያም ሰይጣን ሥራውን መጀመሩን ተመለከትኩ፡፡ ሰይጣን ባሳታቸው ኃጥአን ዙሪያ በመሽከርከር ደካሞችን እያበረታና እያጠነከረ እርሱና መላእክቱ ብርቱ መሆናቸውን ይለፍፍ ነበር፡፡ ሰይጣን ለቁጥር ወደሚያታክቱት አያሌ ሚሊዮኖች ያመላክት ነበር፡፡ ከእነዚህ ህዝቦች መሃል በውጊያ ተሸንፈው የማያውቁ ታላላቅ የጦር ሰዎችና ነገሥታት ነበሩባቸው፡፡ ነገሥታትን ያንቀጠቅጥ የነበረው ኩሩውና ብርቱው ናፖሊዮን ከመካከላቸው ነበር እንዲሁም በውጊያ ላይ የተሰዉ ግዙፍ ቁመናና የከበረ ማንነት የሚስተዋልባቸው ሰዎችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ህዝቦች ከመቃብር ሲነሱ፤ በሞት ተቋርጦ የነበረውን አስተሳሰባቸውን እንደያዙ ይቀጥላሉ፡፡ በመሆኑም በወደቁ ጊዜ አንግበውት የነበረው ያው ዓላማና ምኞት አብሯቸው ይሆናል፡፡ ሰይጣን በመጀመሪያ ከመላእክቱ ጋር ከመከረ በኋላ በመቀጠል ከነገሥታት፣ ከገዢ ዎችና ከኃያል ሰዎች ጋር ምክክር ያደርጋል: ከዚህ በኋላ ሰይጣን ለቁጥር ወደሚያታክተው ሠራዊት በመመልከት በከተማዋ ያሉት ቁጥራቸው ኣነስተኛና ደካሞች መሆናቸውን ይለፍፋል፡፡ ወጥተው ከተማዋን መውረስ እንደሚችሉም ይነግራቸዋል፡፡ EWAmh 217.2
ሰይጣን ኃጥአንን በማሳት አንቅስቃሴው ውጤታማ በመሆን ሁሉም እራሳቸውን ለጦርነት ማዘጋጀት ይጀምራሉ፡፡ በዚያ ለቁጥር የሚያታክት ሰራዊት ውስጥ ብዙ ችሎታ ያላቸው ሰዎች በመኖራቸው ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያዎች ይሠራሉ ከዚያም ሰይጣን ከበላያቸው ሆኖ ሲመራ ሁሉም ወደ ፊት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሰይጣንን ተከትለው የተሰለፉት ነገሥታትና ጦረኞች ሲሆኑ እነርሱን ተከትሎ ለቁጥር የሚያታክት ሕዝብ ነበር እያንዳንዱ ቡድን የየራሱ መሪ የነበረው ሲሆን ሁሉም አዛዡን ተከትሎ ወደ ቅድስት ከተማ በሚወስደው ሽንቁር ምድር ይተም ነበር፡፡ የሱስ የከተማዋን በሮች ዘጋ ግዙፉ ሰራዊት የከፋ ውጊያ እንደሚኖር ተስፋ በማድረግ ከተማዋን ከበበ:፡፡ የሱስና ሁሉም የመላእክት ሰራዊት እንዲሁም ቅዱሳን የሚያብረቀርቁ አክሊሎቻቸውን በአናቶቻቸው ላይ እንደ ደፉ ወደ ከተማዋ ቅጥር ጫፍ ወጡ፡፡ የሱስ በታላቅ ንጉሣዊ ክብር ‹እናንት ኃጥአን የጻድቃኑን ሽልማት ተመልከቱ! እናንተ ቅዱሳን ደግሞ የኃጥአንን ዋጋ እዩ!” በማለት ተናገረ፡፡ በዚህን ወቅት ስፍር ቁጥር የሌለው ኃጥን በከተማዋ ቅጥር ውስጥ ያሉትን ህዝቦች ግርማ ተመለከተ፡፡ ቅዱሳኑ የተዋቡ አብ ረቅራቂ አክሊሎቻቸውን ደፍተውና ፊታቸው በክብር አብርቶ የየሱስን አምሳል ሲያንጸባርቁ አዩ: ከዚያም ወደርየለሹን የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ክብር ሲመለከቱ ብርታታቸውና ጥንካሬአቸው ሟሸሽ፡፡ የግላቸው ሊሆን ይችል የነበረውን የከበረ ነገር ያጡ መሆናቸውንና የኃጢአት ዋጋ ሞት መሆኑን ተገነዘቡ እነርሱ ንቀዋቸው የነበሩ አሁን ቅዱስና ደስተኞች፣ የማይሞቱና በክብር የተሞሉ ሆነው ይመለከቷቸዋል፡፡ እራሳቸው የሚገኙበት ሁናቴ ግን ከከተማዋ ቅጥር ውጪ በጨካኝና አስፈሪ ሁናቴ ውስጥ ይሆናል፡፡ EWAmh 217.3