ቀደምት ጽሑፎች

2/73

1—የግል ተሞክሮና አመለካከት

የግል ተሞክሮዬንና አመለካከቴን ለሌሎች አጋራ ዘንድ በውድ ወዳጆቼ የቀረበልኝ ጥያቄ ትሁት ልብ ያላቸውንና በእርሱ የሚተማመኑ የጌታን ልጆች ያበረታታል ብዬ ተስፋ በማድረግ እነሆ እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርቤአለሁ:: EWAmh 5.1

አሥራ አንድ ዓመት በሞላኝ ጊዜ ጌታን ተቀበልኩ፤ በ12 ዓመቴ ተጠምቄ የሜቶዲስት ቤተክርስቲያን አባል ሆንኩ፡፡ በአሥራ ሦስት ዓመቴ ዊልያም ሚለር ሁለተኛውን መልእክቱን በፖርትላንድ ሜይን ሲያስተላልፍ የመካፈል ዕድል አገኘሁ፡፡ ከመልእክቱ በኋላ ቅዱስ አለመሆኔና የሱስን ለማየት ዝግጅት እንደሚጎድለኝ ተሰማኝ፡፡ የቤተክርስቲያን አባላትና ኃጢአተኞች በሙሉ ወደ ፊት ለጸሎት እንዲመጡ ግብዣ በተደረገ ጊዜ እራሴን ለሰማይ ገጣሚ ለማድረግ አያሌ ተግባራት እንደሚጠበቁብኝ በማሰብ ይህን የመጀመሪያ ዕድል አሳለፍኩ፡፡ EWAmh 5.2

በ1842 ላይ በፖርትላንድ ሜይን የተካሄደውን የዳግም ምጽአት ጉባዔ ያለማቋረጥ ከተከታተልኩ በኋላ ጌታ እንደሚጣ ሙሉ በሙሉ አመንኩ፡፡ እራሴን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ ለሙሉ በማስማማት በሙላት የሚገኝ ደኅንነትን እራብና እጠማ ነበር፡፡ የምድር ሁሉ ሐብት ሊገበየው የማይችለውን ይህን እጅግ የከበረ ሐብት አገኝ ዘንድ ቀንም ሆነ ሌት አጥብቄ እታገል ነበር: በጌታ ፊት እራሴን ዝቅ አድርጌ ይህን በረከት እንዳገኝ እጸልይ በነበረበት ወቅት ከምዕመናን ጋር በኅብረት የመጸለይ ኃላፊነት ተገለጸልኝ:: ከዚህ ቀደም በመንፈሳዊ ስብሰባ ላይ ጸልዬ የማላውቅ በመሆኑ በጉባዔ ላይ ለመጸለይ ብሞክር ግራ ልጋባ እችላለሁ በሚል ፍርሃት ከዚህ የሞራል ግዴታ አፈገፈግኩ፡፡ በየጊዜው በስውር በጸሎት ወደ ጌታ ፊት በምቀርብበት ወቅት፤ ይህ ተግባራዊ ላደርገው ያልቻልኩት ኃላፊነት መጸለይ እስካቆም ድረስ እየመጣብኝ በመጨረሻ የሚያስከፋ ስሜት ከፈጠረብኝ በኋላ ነበር መረጋጋት የማገኘው፡፡ EWAmh 5.3

በዚህ ልኩ ከብቦኝ የነበረውን ጽልመት ሰንጥቆ የሚያልፍ አንድ እንኳ የብሃን ጨረር ሳይኖር ለሦስት ሣምንታት ቆየሁ:፡ ከዚህ በኋላ ድብዝዝ ያለ የብርሃን ጨረርና ተስፋ መመልከት የቻልኩባቸውን ሁለት ሕልሞች አለምኩ፡፡ አእምሮዬን---እራሷን ለመንፈሳዊው ነገር አሳልፋ ለሰጠችው እናቴ ከፈትኩ፡፡ እርሷም የጠፋሁ አለመሆኔን በመንገር፤ በዚያን ወቅት በፖርትላንድ ለነበሩ አድቬንቲስቶች ይሰብክ ወደነበረው ወንድም ስቶክማን በመሄድ እርሱን እንድገናኘው መከረችኝ፡፡ ይህ ሰው እራሱን ለክርስቶስ አሳልፎ የሰጠ አገልጋይ በመሆኑ በእርሱ ላይ ከፍ ያለ መተማመን ነበረኝ፡፡ ከአንደበቱ ይወጡ የነበሩ ቃላት በእኔ ላይ ተጽእኖ በማሳደር ወደ ተስፋ አመሩኝ፡፡ ወደ ቤቴ ከተመለስኩ በኋላ እንደገና በጌታ ፊት በመቅረብ፤ የየሱስን ፈገግታ ማየት ከቻልኩ ማንኛውንም ነገር ለማድረግም ሆነ የሚመጣውን ሥቃይ ለመቀበል ቃል ገባሁ፡፡ አሁንም ያው ኃላፊነት ተመልሶ መጣ በዚያን ምሽት የሚካሄድ የኅብረት ጸሎት ፕሮግራም ስለ ነበር ተካፈልኩ፡፡ ሰዎቹ ለጸሎት ሲንበረከኩ እኔም እየተንቀጠቀጥኩ አብሬያቸው እራሴን ለጸሎት ዝቅ አደረግኩ፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ሰው ከጸለየ በኋላ ሳላስበው ለመጸለይ አንደበቴ ተከፈተ፤ እርሱን በጸሎት በመጠየቅ ብቻ አያሌ የከበሩ ነገሮች መቀበል እንደምንችል አምላካዊው ተስፋ ተገለጠልኝ፡፡ እየጸለይኩ እያለ ረዘም ላሉ ጊዜያት ነፍሴን ተጭኗት የነበ ረው የህመምና ሸክም ስሜት ሲለቀኝ ተሰማኝ፡፡ የእግዚአብሔር በረከትም ልክ እንደ ጤዛ በላዬ ሲሰፍር ታወቀኝ፡፡ ለተሰማኝ ነገር ለእግዚአብሔር ውዳሴ ባቀርብም ነገር ግን የበለጠውን ናፈቅኩ፡፡ በመሆኑም በአምላካዊው ሙላት እስከምጥለቀለቅ ድረስ መርካት አልቻልኩም ነበር፡፡ በቃላት ሊገለጽ የማይቻል የየሱስ ፍቅር ነፍሴን ሞላው፡፡ የአምላካዊው ክብር ሞገድ አካሌ እስኪጠነክር ድረስ ደጋግሞ ሲያልፍብኝ ተሰማኝ፡፡ በወቅቱ ከየሱስና ከእርሱ ክብር በቀር ሌላው ሁሉ ከእኔ በመወገዱ በአካባቢዬ የሚያልፈው ማንኛውም ነገር አይታወቀኝም ነበር፡፡ EWAmh 5.4

አካሌና አእምሮዬ በዚህ ሁኔታ እንዳለ ረዘም ላሉ ጊዜያት ከቆየሁ በኋላ በአካባቢዬ ያለውን በተገነዘኩ ጊዜ ሁሉም ነገር ተለውጦ ነበር፡፡ አሁን ማንኛውም ነገር ለእግዚአብሔር ፈገግታና ምስጋና እንደሚያቀርብ ሆኖ ድንቅና አዲስ ገጽታ ተላብሶ ነበር በወቅቱ የሱስን በየትኛውም ስፍራ ለመመስከር ፈቃደኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ለስድስት ወራት ያህል አንዳችም ጽልመታዊ ደመና በአእምሮዬ አላለፈም፡፡ ነፍሴ በየቀኑ ከበቂ በላይ የደህንነትን ውሃ ትጎነጭ ነበር፡፡ የሱስን ያፈቀሩ ሁሉ የእርሱን ምጽአት እንደሚወዱ በማሰብ ወደ መንፈሳዊ ስብሰባ በመሄድ የሱስ ያደረገልኝን እንዲሁም የጌታን ምጽአት በማመኔ በሙላት የተቀዳጀሁትን ደስታ ነገርኳቸው ጉባዔውን የሚመራው ሰው «በሜቶዲስት እምነት. . .” በማለት ንግግሬን አቋረጠኝ:: ነገር ግን የዚህ ክብር ባለቤት ክርስቶስና በቅርቡ ገቢራዊ የሚሆነው የእርሱ ዳግም ምጽአት ነጻ አድርጎኝ ሳለ ይህን ክብር ለሜቶዲስት ቤተክርስቲያን መስጠት አልቻልኩም:: EWAmh 6.1

አብዛኞቹ የአባቴ ቤተሰቦች የክርስቶስ ዳግም ምጽአት መልእክት ሙሉ ለሙሉ አማኞች ነበሩ፡፡ በዚህ ውብና ባለ ክብር አስተምህሮ ምስክር መሆናችንን ተከትሎ በአንድ ወቅት ሰባት የምንሆን የቤተሰቡ አባላት ከሜቶዲስት ቤተክርስቲያን የመባረር ዕጣ ደረሰብን፡፡ በዚህ ወቅት የነቢዩ ቃላት እጅግ በተለየ መልኩ ለእኛ የከበሩ ሆነው አገኘናቸው «እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ እስቲ እግዚአብሔር ይክበርና የእናተን ደስታ እንይ አሏችሁ ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም” (ኢሳ. 66፡5)፡፡ ከዚህን ጊዜ አንስቶ እስከ ወርሃ ታህሳስ 1844 ድረስ ደስታዬ፣ ፈተናዬና ቅሬታዬ ሁሉ በዙሪያዬ ከነበሩት የዳግም ምጽአቱ መልእክት ተከታዮች ጋር አንድ ዓይነት ነበር፡፡ በዚህን ወቅት የዳግም ምጽአቱ ተከታይ እህቶችን ለመጎብኘት ወደ እነርሱ ሄድኩና ጠዋት ላይ በአንድ ላይ በቤተሰባዊው የጸሎት ስፍራ መጸለይ ጀመርን:: አጋጣሚው እምብዛም የሚያስደንቅ ባይሆንም አምስታችንም ሴቶች ነበርን፡፡ እየጸለይኩ ሳለ ከዚያ ቀደም ፈጽሞ ተሰምቶኝ የማያውቅ የእግዚአብሔር ኃይል ወረደብኝ፡፡ በአምላካዊው ራእይ ክብር ተሸፍኜ ከምድር ከፍ ከፍ እያልኩ በመውጣት የዳግም ምጽአቱ ተከታይ ሕዝቦች ወደ ቅድስት ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ ተመለከትኩ፡፡ ይህ ራእይ እንደሚከተለው ቀርቦአል፡ EWAmh 7.1

(ይህ መልእክት የተሰጠው በ1844 ዓ.ም. የዳግም ምጽአቱ ተከታዮች ላይ የደረሰውን መከፋት ተከትሎ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1846 ዓ.ም. ላይ ነው: በዚያን ጊዜ መታየት የቻሉት ክስተቶች ወደፊት ዕውን ከሚሆኑት መሃል በጣም ጥቂቶቹ ቢሆኑም ኋላ ላይ ግን ይበልጥ የተሟሉ ሆነው መቅረብ ችለዋል) EWAmh 7.2