ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፲፬—የኋለኞቹ የእንግሊዝ ተሐድሶ አራማጆች
ሉተር የተከደነውን መጽሐፍ ቅዱስ ለጀርመን ሲከፍት ሳለ ቲንዳልም ለእንግሊዝ ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈጽም በእግዚአብሔር መንፈስ ተገፋፍቶ ነበር። የዋይክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ስህተት ከነበረበት ከላቲን ጽሑፍ የተተረጎመ ነበር። ታትሞም ስለማያውቅ በእጅ የተፃፈውን ቅጂ ማግኘት በጣም ውድ ከመሆኑ የተነሳ ማግኘት የቻሉት ሃብታምና የከፍተኛው መደብ አባላት ብቻ ነበሩ። በተጨማሪም በቤተ ክህነት ተከልክሎ ስለነበር ብዙም አልተሰራጨም ነበር። በ1516 ዓ.ም ማለትም የሉተር የጥናት ጽሁፎች ከመድረሳቸው ከአንድ ዓመት በፊት ኢራስመስ አዲስ ኪዳንን በላቲንና በግሪክ ቋንቋ አትሞ ነበር። አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል መጀመሪያ በተፃፈበት ቋንቋ ታተመ። በዚህ ሥራ በቀድሞዎቹ ትርጉሞች ውስጥ የነበሩ ብዙ ስህተቶች ታረሙ፣ የተሻለና ግልጽ የሆነ ስሜት የሚሰጥ ትርጉምም ተዘጋጀ። እውነትን በማወቅ ረገድ ብዙ የተማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ተሻለ ደረጃ መራቸው፣ የተሐድሶውን ሥራ በተመለከተም አዲስ ጉልበት ለገሰ። ተራው ሕዝብ ግን በአብዛኛው ከእግዚአብሔር ቃል እንደተገለለ ነበር። ለአገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማደል ዋይክሊፍ የጀመረውን ሥራ ቲንዳል ይፈፅም ዘንድ ነበረው። GCAmh 181.1
ትጉህ ተማሪ፣ እውነትን ከልቡ ይሻ የነበረው ቲንዳል ወንጌሉን የተቀበለው ኢራስመስ ወደ ግሪክ ከተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። የተቀበላቸውን እውነቶች ያለ አንዳች ፍርሃት በመስበክ ሁሉም አስተምህሮዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲመዘኑ አስገነዘበ። መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠችው ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ ልታብራራ የምትችለውም እርስዋ ብቻ መሆንዋን ስለሚያሳስበው ጳጳሳዊ መጠይቅ ቲንዳል ሲመልስ፦ “ንስሮች ምግባቸውን እንዲያገኙ ማን እንዳስተማራቸው ታውቃላችሁ? ያ፣ ራሱ እግዚአብሔር የተራቡ ልጆቹ አባታቸውን በቃሉ ውስጥ እንዲያገኙት ያስተምራቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለኛ መስጠት አይደለም ከኛ የደበቃችሁት እናንተው ናችሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩትን ያቃጠላችሁ እናንተ ናችሁ፤ ቢቻላችሁስ መጽሐፍ ቅዱስን ራሱን ባቃጠላችሁት ነበር።” ብሏል።-D’Aubigné, History of the Reformation of the Sixteenth Century, b. 18, ch. 4። GCAmh 181.2
የቲንዳል ስብከት ጥልቅ ፍላጎትን ቀሰቀሰ፣ ብዙ ሰዎችም እውነትን ተቀበሉ። ሆኖም ሥራውን ቀሳውስቱ ልብ ብለውት፣ ማሳውን እንደለቀቀ ከኋላው እየተከተሉ በማስፈራራት ያልሆነውን ሆነ በማለት የእርሱን ሥራ ለማፈራረስ ለፉ። በአብዛኛው ተሳካላቸው። “ወይኔ!” ብሎ በመደነቅ “ምንድን ነው መደረግ ያለበት? በአንድ ስፍራ እየዘራሁ ሳለ ልክ የሄድኩበትን መስክ ጠላት ያወድመዋል። በሁሉም ስፍራ በአንድ ጊዜ መሆን አይቻለኝም። ኦህ! ክርስቲያኖች በራሳቸው ቋንቋ የተፃፈ መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸው ኖሮ እነዚህን ማጭበርበሪያዎች በራሳቸው መቋቋም ይችሉ ነበር። ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ተራውን ምዕመን በእውነት ላይ መመስረት ፈጽሞ የማይቻል ነው።”-Ibid., b. 18, ch. 4። GCAmh 181.3
አሁን ደግሞ አዲስ አላማ አዕምሮውን ተቆጣጠረው። “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መዝሙሮች ይዘመሩ የነበሩት” አለ “በእሥራኤል ቋንቋ ነበር፤ እናስ ወንጌሉ የእንግሊዝን ቋንቋ በመካከላችን ሊናገር አይገባውምን?…. ቤተ ክርስቲያንዋ ከንጋት ያነሰ ብርሐን በቀትር ይኖራት ዘንድ ይገባልን?…. ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳንን አፍ በፈቱበት ቋንቋ ማንበብ አለባቸው።” የቤተ ክርስቲያን ዶክተሮችና አስተማሪዎች እርስ በርሳቸው መስማማት አቃታቸው። ሰዎች ወደ እውነት መድረስ የሚችሉት በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ብቻ ነው። “አንዱ ይህንን አስተምህሮ ይይዛል፤ ሌላው ያኛውን…. አሁን እያንዳንዱ ፀሐፊ ሌላኛውን ይቃረናል።እና ታዲያ እውነት የሚናገረውን ስህተት ከሚናገረው እንዴት አድርገን እንለየዋለን?…. እንዴት?…. በእርግጥ በእግዚአብሔር ቃል ነው።”-Ibid., b. 18, ch. 4። GCAmh 181.4
ከዚህም በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር አንድ የተማረ የካቶሊክ ዶክተር ሲከራከረው፣ “የሊቀ ጳጳሱ ሕግ ከማይኖረን የእግዚአብሔር ሕግ ባይኖረን ይሻለን ነበር” በማለት የተናገረው። ቲንዳል ሲመልስ “ሊቀ ጳጳሱንና የእርሱን ሕጎች እገዳደራቸዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሕይወቴን ካተረፋት ዓመታት ሳይቆጠሩ እርፍ ይዞ የሚያርሰው ለጋ ወጣት ከናንተ የተሻለ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያውቅ አደርገዋለሁ።” አለ።-Anderson, Annals of the English Bible, ገጽ 19። GCAmh 182.1
አዲስ ኪዳንን በራሳቸው ቋንቋ አዘጋጅቶ ለመስጠት በማለም የተነሳበት፣ እየወደደው የመጣው አላማው አሁን ተረጋገጠ፤ ወዲያውኑም ወደ ሥራ ገባ። በስደት ምክንያት ከቤቱ ተፈናቅሎ ወደ ለንደን ሄደ፤ እዚያም ለተወሰነ ጊዜ ሳይረበሽ ሥራውን መቀጠል ቻለ። ሆኖም አሁንም እንደገና የጳጳሳውያኑ ነውጠኝነት እንዲኮበልል አስገደደው። እንግሊዝ በአንድነት በተቃውሞ በሩን የዘጋበት ሲመስል በጀርመን መጠለያ ለመሻት ወደዚያ ሄደ። በዚህ ስፍራ በእንግሊዝኛ የተተረጎመውን የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ጀመረ። ሁለት ጊዜ ሥራው እንዲቆም ተደረገ፤ ሆኖም በአንዱ ከተማ እንዳያሳትም ሲከለከል ወደ ሌላኛው ይሄድ ነበር፤ በመጨረሻም ከጥቂት ዓመታት በፊት ሉተር በጉባኤው ፊት ወንጌሉን ደግፎ ወደ ተከራከረበት ወደ ዎርምስ መጣ። በዚያች ጥንታዊት ከተማ የተሐድሶው ብዙ ወዳጆች ነበሩና ቲንዳል ያለምንም መከልከል ሥራውን መቀጠል ቻለ። ብዙም ሳይቆይ ሶስት ሺህ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ታትመው፣ በዚያው ዓመት ሌላ እትም መቀጠል ቻለ። GCAmh 182.2
በታላቅ ቅንነትና በጽናት ሥራዎቹን ቀጠለ። የእንግሊዝ ባለስልጣናት ወደቦቻቸው እጅግ ከባድ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ቢለፉም የእግዚአብሔር ቃል በተለያዩ ምስጢራዊ መንገዶች ወደ ለንደን እንዲገባ ተደርጎ በአገሪቱ በሞላ ተሰራጨ። ጳጳሳውያኑ እውነትን ለመጨምደድ ብዙ ደከሙ፤ ልፋታቸው ግን መና ሆነ። በአንድ ወቅት የዱርሃም ጳጳስ የቲንዳል ወዳጅ ከነበረው መጻሕፍት ሻጭ ላይ የነበሩትን መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ ገዛና ተግባሩ የወንጌሉን ሥራ ክፉኛ ያደናቅፈዋል ብሎ ተስፋ በማድረግ ሊያወድማቸው አቅዶ ተንቀሳቀሰ። ሆኖም በተቃራኒው ከዚህ ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ለአዲስና የተሻለ እትም ጥሬ እቃ በማቅረብ፣ ያለዚህ ገንዘብ ሊከናወን አይችል የነበረው ሥራ እንዲሰራ አደረገ። በኋላ ቲንዳል እስረኛ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሶቹን ለማሳተም ይችል ዘንድ ወጭውን የሸፈኑት እነማን እንደሆኑ ከተናገረ ነፃነቱን እንደሚያገኝ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦለት ነበር። ሲመልስም የቀሩትን መጻሕፍት ሁሉ በርከት ባለ ገንዘብ በመግዛቱ፣ በተነቃቃ መንፈስ ሥራውን እንዲቀጥል እንዳስቻለው፣ እንደ ዱርሃሙ ጳጳስ የረዳው ሰው እንዳልነበር ተናገረ። GCAmh 182.3
ቲንዳል የመከዳት ሴራ ተፈጽሞበት ወደ ጠላቶቹ እጅ ተላልፎ ተሰጥቶ በአንድ ወቅትም ለብዙ ወራት በእስር ቤት ተንገላቷል። በመጨረሻም የሰማዕትነት ሞት በመሞት ለእምነቱ ምስክርነቱን ሰጥቷል። እርሱ ቢያልፍም ያዘጋጃቸው መሳሪያዎች፣ በዘመናት ሁሉ፣ እስከ እኛ ጊዜ ድረስ፣ ሌሎች ወታደሮች እንዲዋጉባቸው አስችለዋቸዋል። GCAmh 183.1
መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቡ ቋንቋ መነበብ አለበት በማለት በመድረክ የሚናገረው ላቲመር በሃሳቡ እንደፀና ነበር። “የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊ” አለ፣ “እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይህም መፅሐፍ የፀሐፊው ኃያልነትና ዘላለማዊነት ባህርይ ተካፋይ ነው። ይታዘዘው ዘንድ የማይገባው ንጉሥ ወይም ንጉሠ ነገሥት የለም። ድንጋዮች፣ ቁጥቋጦዎችና የተነቀሉ ዛፎች ከሞሉበት ከፍጡር የወግና የባህል ተቀጥላ (ያልተለመዱ) መንገዶች እንጠንቀቅ። ቀጥ ያለውን የቃሉን መንገድ እንከተል። ሊያሳስበን የሚገባው አባቶች የፈፀሙት ተግባር ሳይሆን መፈፀም የነበረባቸው ነው።” GCAmh 183.2
የቲንዳል ታማኝ ወዳጆች፣ ባርነስና ፍሪዝ፣ እውነትን ከጥቃት ለመከላከል ተነሱ። ሪድሊዎችና ክሬመር ዱካቸውን ተከተሉ። በእንግሊዝ ተሐድሶ የተሳተፉት እነዚህ ሰዎች የተማሩ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ በካቶሊክ ማህበር ውስጥ በቀናኢነታቸውና በቅዱስነታቸው ስመ ጥር የነበሩ ናቸው። የ”ቅዱስ መንበረ-መንግሥቱን” ስህተቶችን ማወቃቸው ጳጳሳዊ ሥርዓትን እንዲቃወሙ ምክንያት ሆነላቸው። ከባቢሎንም ምስጢራዊ ባህርያት ጋር መተዋወቃቸው እርስዋን ተቃውመው ለሰጡት ምስክርነት ኃይል ያጎናፀፈ ነበር። GCAmh 183.3
“በእንግሊዝ አገር ተወዳዳሪ የሌለው ትጉህ ጳጳስ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” አለ ላቲመር “እየሰማችሁኝ እንደሆነ፣ በስምም ስጠቅሰው ለማዳመጥ እንደተዘጋጃችሁ አያለሁ። እነግራችኋለሁ፣ ዲያብሎስ ነው፤ ከሚያስተዳድረው ደብር ፈቀቅ ብሎ አያውቅም። በፍጹም ሥራ ፈቶ አታገኙትም። ስትፈልጉ ጥሩት፣ ሁልጊዜም በቤትና በእርሻ ቦታ አለ። ዲያብሎስ ነዋሪ በሆነበት ስፍራ ሁሉ መፅሐፎች ተወርውረው ሻማዎች ከፍ ይላሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ተገፍትሮ ዶቃዎች ከፍ ይላሉ፣ አዎ በእኩለ ቀን የወንጌሉ ብርሐን ተዳፍኖ የጧፍ መብራት ይለኮሳል፤ የክርስቶስ መስቀል ተጥሎ፣ ኪስ አውላቂ የሆነው የሙታን ጊዜያዊ ማረፊያ (pulgatory) ከፍ ይደረጋል፤ የታረዘውን፤ ድሃውንና አቅመ ደካማውን በማልበስ ፈንታ ምስሎች ማስጌጥ፣ ድንጋዮችንና ቁሳቁሶችን ያለመጠን ማንቆጥቆጥ ተይዟል። እግዚአብሔርና ቅዱስ መፅሐፉ ወደ ታች፤ ወጎችና ባህሎች፣ የፍጡር ምክሮችና የታወረው ሊቀ-ጳጳስ ወደ ላይ። ኦህ! ሰይጣን የአረም ዘርን በሚዘራበት ትጋት የቤተ ክህነት ሰዎች የመልካም አስተምህሮን ማሽላ ቢዘሩ ኖሮ!” GCAmh 183.4
በዋልደንሳውያን፣ በዋይክሊፍ፣ በጆን ኸስ፣ በሉተር፣ በዝዊንግልና በአበሮቻቸው ሲጠበቅ የነበረው፣ በአሁኖቹም የተጠበቀው ታላቁ መርህ፣ ስህተት መሥራት የማይቻለው የመጽሐፍ ቅዱሳት ስልጣን የእምነትና ሥራ መመሪያ መሆኑ ነበር። ሊቀ ጳጳሳት፣ ጉባኤዎች፣ አባቶችና ነገሥታት፣ ኃይማኖትን በተመለከቱ ጉዳዮች ህሊናን ይቆጣጠሩ ዘንድ መብት እንዳይሰጣቸው ከለከሉ። የእነርሱ የበላይ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፣ በእርሱም ትምህርት አማካኝነት ሁሉንም አስተምህሮዎችና መጠይቆች ፈተኑ። GCAmh 183.5
እነዚህ ቅዱሳን ሰዎች ሕይወታቸውን በማቃጠያ ስፍራው ሲሰጡ በእግዚአብሔርና በቃሉ የነበራቸው እምነት በጽናት አቆማቸው። “በመልካምም ጽናት ተጽናና” አለ ላቲመር ለሰማዕት ጓደኛው፣ የእሳቱ ነበልባል ላንቃቸውን እየዘጋው ሳለ፦ “አምናለሁ፣ በእግዚአብሔር ፀጋ እርዳታ፣ ዛሬ በእንግሊዝ ፈፅሞ ሊጠፋ የማይችል ሻማ እናቀጣጥላለን።”-Works of Hugh Latimer, vol. 1, ገጽ xiii። GCAmh 183.6
በስኮትላንድ በኮሉምባ እና በግብረ አበሮቹ የተበተኑት የእውነት ዘሮች ሙሉ በሙሉ አልተደመሰሱም ነበር። የእንግሊዝ አብያተ ክርስቲያናት ለሮም ከተንበረከኩ በኋላ ለብዙ ዓመታት ስኮትላንዶቹ ነፃነታቸውን እንደጠበቁ ቆይተዋል፤ በአሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ጳጳሳዊ ሥርዓት እዚህም ተመስርቶ፣ በሌላ አገር ያልታየ የማያፈናፍን ሥርዓት መዘርጋት ተቻለ። የጽልመቱ ጥልቀት ከዚህ ስፍራ የባሰበት ሌላ ምድር አልነበረም። ሆኖም የሚመጣውን ቀን ተስፋ የሚያበስር፣ ጨለማውን የሚበሳ የብርሐን ጮራ መጣ። ከእንግሊዝ መጽሐፍ ቅዱሳቸውንና የዋይክሊፍን ትምህርቶች ይዘው የመጡ ሎላርዳውያን(the Lollards)፣ የወንጌሉ እውቀት ሳይጠፋ እንዲቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እያንዳንዱ ምዕተ ዓመትም የራሱ ምስክሮችና ሰማዕታት ነበሩት። GCAmh 184.1
ታላቁን ተሐድሶ ተከትሎ የሉተር ጽሁፎችና የቲንዳል የአዲስ ኪዳን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ መጡ። እነዚህ ድምጽ የሌላቸው መልዕክተኞች በመዋቅሩ ልብ ሳይባሉ ተራራውንና ሸለቆውን በመጓዝ በስኮትላንድ ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረውን የእውነት ችቦ ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ የሮም የአራት መቶ ዓመት ጭቆና የሰራውን ሥራ በመቀልበስ ታላቅ ሥራ ሰርተዋል። GCAmh 184.2
ከዚያም የሰማዕታት ደም ለእንቅስቃሴው አዲስ ጉልበት ለገሰ። ጳጳሳዊ መሪዎች አላማቸውን ስጋት ላይ ለጣለው አደጋ በድንገት በመንቃት እጅግ ስመ ጥር የሆኑትንና ስኮትላንድ አላት ከተባሉት ልጆችዋ መካከል እጅግ የተከበሩትን የተወሰኑትን በእሳት አቃጠሉዋቸው። ያደረጉት ነገር ቢኖር ግን የስብከትን መድረኮች መትከል ነበር፤ ከእነዚህ ከሚሞቱ ምስክሮች የሚወጡ ቃላት በምድሩ ሁሉ ተሰሙ፣ የሰዎችንም መንፈስ በማይሞት ዓላማ በማነሳሳት የሮምን የእግር ብረት ያራግፉ ዘንድ ምክንያት ሆኑ። GCAmh 184.3
በርካታ ትሁትና መልካም ስነ ምግባር የነበራቸው እንደ ትውልዳቸው ሁሉ ልዑላዊ ባህርይ የነበራቸው ሃሚልተንና ዊሻርት፣ ሕይወታቸውን ለእሳት አሳልፈው ሰጡ። ሆኖም ከዊሻርት ቅሪተ-አካል፣ የሚነድ ነበልባል ዝም የማያሰኘው፣ የጳጳሳዊ ሥርዓትን ሞት በስኮትላንድ የሚያበስረውን ደወል በእግዚአብሔር ምሪት የሚደውለው ሰው ተነሳ። GCAmh 184.4
ከቤተ ክርስቲያን ወግና በተመስጦ አምላክን ለመገናኘት ከሚሞክር ተግባር ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነቶች ያዞረው ጆን ኖክስ የዊሻርት አስተምህሮ ከሮም ጋር ያለውን ህብረት እንዲያቋርጥና ከተሳዳጆቹ ተሐድሶ አራማጆች ጎራ እንዲሰለፍ አደረገው። GCAmh 184.5
የስብከት አገልግሎትን እንዲወስድ ከወዳጆቹ የቀረበለት ጥያቄ ኃላፊነቱ ከብዶት በመሸማቀቅ ጥቂት ቀናት የተገለለ ቆይታ ካደረገና ከራሱ ጋር ሲታገል ከቆየ በኋላ በመጨረሻ የአዎንታ ምላሹን ሰጠ። ኃላፊነቱን ከተቀበለ በኋላ ግን ፍንክች በማይል ቆራጥነትና በማይታጠፍ ጉብዝና ሕይወቱ እስካለ ድረስ ወደፊት ገሰገሰ። ይህ ልባዊ ተሐድሶ አራማጅ የፍጡርን ፊት የሚፈራ አልነበረም። በዙሪያው የሚንቀለቀሉት የሰማዕትነት ነበልባሎች ቅናቱ በበለጠ ኃይል እንዲጠነክር አደረጉት እንጂ አላስፈሩትም። አስፈሪ የአምባገነንነት መጥረቢያ ጭንቅላቱ ላይ ቢቀሰርም በጀግንነት፣ የጣዖት አምልኮን የግራና ቀኝ እጆች በሚያሽመደምድ ምት በመምታት ከስፍራው ንቅንቅ ሳይል ፀንቶ ቆመ። GCAmh 184.6
በአካል መገኘትዋ የብዙ ፕሮቴስታንት መሪዎችን ከፍተኛ ኃይማኖታዊ ተነሳሽነት በምታቀዘቅዘው በስኮትላንድዋ ልዕልት ፊት ሲቀርብ እንኳ ጆን ኖክስ ለእውነት ያለውን የማይናወጥ ምስክርነት አሳይቷል። በመደባበስ ሊሸነፍ፣ በዛቻም ሊሸማቀቅ አልቻለም። ልዕልቷ በመናፍቅነት ወነጀለችው። በመንግሥት የተከለከለን እምነት ሕዝቡ እንዲቀበል በማስተማሩ ተገዥዎች ጌቶቻቸውን እንዲታዘዙ የሚደነግገውን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ተላልፏል በማለት አወጀች። ኖክስም ፈርጠም ብሎ እንዲህ አለ፦ GCAmh 185.1
“ትክክለኛ ኃይማኖት ምንጩን ወይም ስልጣኑን የተቀበለው ከዘላለማዊ አምላክ ብቻ እንጂ ከልዑላን ባለመሆኑ ተገዥዎችም በልዑላኖቻቸው ምርጫ ላይ ተመርኩዘው ሐይማኖታቸውን ቅርጽ ያስይዙ ዘንድ አይገደዱም። ብዙ ጊዜ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ልዑላን ለእግዚአብሔር እውነተኛ ሐይማኖት ገልቱዎች ናቸው። የአብርሐም ዘሮች የፈርኦንን ሐይማኖት ተከትለው ቢሆን ኖሮ፤ እለምንዎታለሁ እሜቴ፣ በዓለም ምን አይነት ሐይማኖት ይኖር ነበር? በሐዋርያት ዘመን የነበረው ኃይማኖትስ የሮም ንጉሠ ነገሥታት ቢሆን፣ እሜቴ፣ ምን አይነት ሐይማኖት አሁን በዚህ ምድር ላይ የሚኖር ይመስልዎታል? ስለዚህም እሜቴ ተገዥዎች ለጌቶቻቸው አክብሮት እንዲሰጡ የሚገባቸው ቢሆንም የአለቆቻቸውን ሐይማኖት እንዲከተሉ ግን የማይገደዱ መሆኑን ሊረዱት ይገባል።” GCAmh 185.2
ማሪያም ስትመልስ፦ “አንተ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ መንገድ ስትተረጉመው እነርሱ ደግሞ [የሮም አስተማሪዎች] በሌላ መንገድ ይተረጉሙታል፤ ማንን ልመን፤ ማንስ ፈራጅ ይሁን?” አለች። GCAmh 185.3
“እርስዎ በቃሉ አማካኝነት በግልጽ የሚናገረውን እግዚአብሔርን ይመኑ” አለ ተሐድሶ አድራጊው፤ “ቃሉ ከሚያስተምረው ውጪ ይህንንም ያንንም ያምኑ ዘንድ አይገባዎትም። የእግዚአብሔር ቃል በራሱ ግልጽ ነው። ግልጽ ያልሆነ ነገር በአንድ ስፍራ ቢኖር እንኳ፣ በድንቁርናቸው መቀጠል ከሚፈልጉት በስተቀር፣ ምንም አይነት መጠራጠር እንዳይኖር ከራሱ ጋር የማይቃረነው መንፈስ ቅዱስ፣ ግልጽ ያልሆነውን ያንኑ ሃሳብ በሌላ ስፍራ የበለጠ ግልጽ ይሆን ዘንድ ያብራራዋል።”-David Laing, The Collected Works of John Knox, vol. 2, ገጽ 281, 284። GCAmh 185.4
የተሐድሶ አራማጁ ሕይወቱን እውን አደጋ ላይ ጥሎ ለንጉሣዊያን ጆሮ እንዲህ ይናገር ነበር። እየፀለየና የጌታን ውጊያ እየተፋለመ አላማውን በጠበቀበት ፍርሃት-የለሽ ጀግንነት ስኮትላንድ ከጳጳሳዊ ሥርዓት ነፃ እስክትሆን ድረስ ለፋ። GCAmh 185.5
በእንግሊዝ አገር የፕሮቴስታንት እምነት እንደ ብሄራዊ ኃይማኖትነት መመስረቱ ቀነሰ፣ ስደቱን ግን ሙሉ ለሙሉ አላስቆመውም። ብዙ የሮም አስተምህሮዎች ቢሻሩም ጥቂት የማይባሉት አሁንም ቀርተው ነበር። የሊቀ ጳጳሱ የበላይነት ተቀባይነት አጣ፤ ሆኖም በቦታው ንጉሠ ነገሥቱ የቤተ ክርስቲያንዋ ራስ ሆኖ ተሾመ። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥም ከወንጌሉ ንጽህናና ቀጥተኛነት ያፈነገጡ አካሄዶች በስፋት ይተገበሩ ነበር። ታላቅ መመሪያ የሆነው የኃይማኖት መቻቻል ገና በውል መረዳት አላገኘም ነበር። ሮም በሥራ ላይ ያዋለችው፣ ኑፋቄን በመቃወም የፈፀመችው አሰቃቂ ድርጊት በፕሮቴስታንት መሪዎች ዘንድ የተተገበረበት ሁኔታ እጅግ አናሳ የነበረ ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው እንደራሱ ህሊና መረዳት እግዚአብሔርን ማምለክ ይችል ዘንድ ያለው መብት ግን እውቅና አልተሰጠውም ነበር። የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችውን የአምልኮ ሥርዓትና አስተምህሮ ሁሉም ሰው ይቀበል ዘንድ ይጠበቅበት ነበር። ተቃዋሚዎች፣ አንዳንዴ በከፋ ሁኔታ አንዳንዴም በመጠኑ፣ ለምዕተ ዓመታት በስደት ተሰቃይተዋል። GCAmh 185.6
በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ፓስተሮች ከያዙት ቦታ ተባረሩ። ቤተ ክርስቲያንዋ ካልፈቀደች በስተቀር ሕዝቡ ምንም አይነት ሐይማኖታዊ ስብሰባ እንዳያደርግ በከባድ የገንዘብ ቅጣት፣ በእሥራትና ከስፍራው በማስወገድ ቅጣት ተከለከለ። እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ ከመሰብሰብ መቆጠብ የተሳናቸው እነርሱ በጨለማ ጠባብ መንገዶች፣ በተደበቁና በማይመቹ ትናንሽ ክፍሎች፣ በአንዳንድ ወቅት ደግሞ በጫካ በእኩለ ሌሊት እንዲገናኙ ተገደው ነበር። የእግዚአብሔር የራሱ የእጅ ሥራ በሆነው፣ ጥቅጥቅ ባለው ጫካ ውስጥ ሆነው፣ የተበታተኑትና የተሰደዱት የእግዚአብሔር ልጆች ነፍሳቸውን በፀሎትና በምስጋና ለማፍሰስ ይሰበሰቡ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ተጠንቅቀው ቢያመልኩም እንኳ ብዙዎች ስለ እምነታቸው ተሰቃይተዋል። እስር ቤቶች ጥቅጥቅ አሉ፤ ቤተሰቦች ተነጣጠሉ፤ ብዙዎች ወደ እንግዳ አገራት ተጋዙ። ሆኖም እግዚአብሔር ከሕዝቦቹ ጋር ነበረ፤ ምስክርነታቸውን ዝም ያስብል ዘንድ ስደት አቅም አልነበረውም። ብዙዎች ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አሜሪካ እንዲሰደዱ፣ የዚህች አገር [የአሜሪካ] ጋሻና ክብር የሆኑትን የሕዝባዊና ሐይማኖታዊ ነፃነት የመሰረት ድንጋይ እንዲጥሉ ተገደዱ። GCAmh 186.1
ልክ እንደ ጥንቱ የሐዋርያት ዘመን፣ በዚህ ጊዜም ስደት ያደረገው ነገር ቢኖር የወንጌሉን መስፋፋት ማገዝ ነበር። ከባለጌዎችና ከወንጀለኞች ጋር በሚያንገሸግሽ የተጨናነቀ የመሬት ውስጥ እስር ቤት ሆኖ ጆን በንያን የሰማይን ትንፋሽ ተነፈሰ፤ በዚህም ስፍራ የኃይማኖት ስደተኛው ግሩም የሆነውን፣ ከጥፋት ምድር ወደ ዘላለማዊቷ ከተማ የሚያደርገውን ጉዞ የሚተርከውን መጽሐፍ ፃፈ። ከቤድፎርድ እስር ቤት የወጣው ያ ድምጽ ለሁለት መቶ ዓመታት በሚደንቅ ኃይል ለሰዎች ልብ ሲናገር ቆይቷል። የበንያን “ፒልግሪምስ ፕሮግረስ/Pilgrim’s Progress” እና “ግሬስ አባውንዲንግ ቱ ዘ ችፍ ኦፍ ሲነርስ/Grace Abounding to the Chief of Sinners” ብዙ እግሮችን ወደ ህይዎት ጎዳና መርተዋል። GCAmh 186.2
ባክስተር፣ ፍላቨል፣ አለይንና የመሳሰሉት፣ ተሰጥኦ ያላቸው፣ የተማሩና የጥልቅ ክርስቲያናዊ ልምድ ባለቤት የነበሩ በአንድ ወቅት ለቅዱሳን የተሰጠውን እምነት በጀግንነት በመደገፍ ፀንተው ቆሙ። በዚህ ዓለም ገዥዎች እንዳይተገበር የታዘዘውና ህገ ወጥ የተደረገው የእነዚህ ሰዎች ሥራ ፈጽሞ ሊጠፋ አይችልም። የፍላቨል “ፋውንቴይን ኦፍ ላይፍ/Fountain of Life” እንዲሁም “ሜተድ ኦፍ ግሬስ/Method of Grace” የሚሉት መጻሕፍቱ ይጠብቃት ዘንድ ነፍሳቸውን ለክርስቶስ እንዴት አሳልፈው እንደሚሰጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ አስተምረዋል። የባክስተር “ሪፎርምድ ፓስተር/Reformed Pastor” የሚለው መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማነቃቃት ለሚፈልጉ ብዙዎች በረከት መሆኑን አስመስክሯል፤ “ሴይንትስ ኤቨርላስቲንግ ሬስት/Saint’s Everlasting Rest” የሚለው ደግሞ “እረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ቀርቶላቸዋል/rest that remains for the people of God” [ዕብ 4÷9] ወደሚለው ነፍሳትን በመምራት ሥራውን ሰርቷል። GCAmh 186.3
ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ፣ በታላቅ የመንፈሳዊ ጽልመት ዘመን ዋይትፊልድና ዌስሊዎች የእግዚአብሔር ብርሐን ተሸካሚዎች ሆነው ብቅ አሉ። በቤተ ክርስቲያንዋ ሕግ ስር የነበሩት የእንግሊዝ ሕዝቦች ከእምነት የለሽ ሕዝቦች ጋር ምንም ልዩነት እስከማይታይባቸው ድረስ ሐይማኖታዊ ማሽቆልቆል ደርሶባቸው ነበር። ተፈጥሮአዊ ኃይማኖት (Natural religion) የቤተ ክህነት ባለስልጣናት ተወዳጅ ጥናት ሲሆን የስነ መለኮት አስተምህሮአቸውን አብዛኛውን ክፍል የያዘ ነበር። በከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበሩት፣ በቅድስና የሚያላግጡ፤ አክራሪነት ብለው ከሚጠሩትም ውጪ በመሆናቸው ኩራት የሚሰማቸው ነበሩ። የበታች መደቦች ደግሞ ድንቁርና የወረሳቸው፣ ለአስነዋሪ ምግባር የተተዉ፣ ቤተ ክርስቲያንም የወደቀውን የእውነት ዓላማ ለመደገፍ የእምነት ጉብዝና ያልነበራት ነበረች። GCAmh 187.1
ሉተር ፍንትው ባለ ሁኔታ ያስተማረው ታላቁ የጽድቅ በእምነት አስተምህሮ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ፣ ጠፍቶ፣ ድነት በመልካም ሥራ ይገኛል የሚለው የሮማውያን መመሪያ በቦታው ተተክቶ ነበር። የዋናው ቤተ ክርስቲያን አባላት የነበሩት ዋይትፊልድና ዌስሊዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከልባቸው የሚጥሩ ነበሩ። ይህንንም ለማሳካት ግብረ ገብ ሕይወት መኖርና ኃይማኖት የሚያስቀምጠውን ሕግ መታዘዝ እንዳለባቸው ተምረው ነበር። GCAmh 187.2
በአንድ ወቅት ቻርለስ ዌስሊ ታመመና እንደማይተርፍ ተገምቶ የዘላለም ሕይወት ተስፋውን በምን ላይ እንዳደረገ ተጠየቀ። መልሱም፦ “እግዚአብሔርን ለማገልገል አቻ የሌለውን ጥረት አድርጌአለሁ” የሚል ነበር። ጥያቄውን ያነሳው ወዳጁ በመልሱ ሙሉ ለሙሉ አለመርካቱን ሲመለከት ዌስሊ፣ “ምን! ጥረቶቼ ሁሉ የተስፋዬ መሰረት ይሆኑ ዘንድ በቂ አይደሉምን? ልፋቴን ሁሉ ይቀማኛል ማለት ነው? ሌላ ምንም ተስፋ የማደርግበት ነገር የለኝም።” አለ።-John Whitehead, Life of the Rev. Charles Wesley, ገጽ 102። ስርየትን በመደበቅ፣ ክርስቶስንም ክብሩን በመንጠቅ፣ ከብቸኛው የመዳን ተስፋቸው፣ ከተሰቀለው አዳኝ ደም የሰዎችን አእምሮ ፈቀቅ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን የወደቀው ድቅድቅ ጨለማ ይህንን ይመስል ነበር። GCAmh 187.3
እውነተኛ ኃይማኖት በልብ ውስጥ እንደሆነ፣ የእግዚአብሔር ሕግ መጠይቅም ሃሳብን፣ ንግግርንና ተግባርን እንደሚያጠቃልል ዌስሊና ጓደኞቹ ያስተውሉ ዘንድ ተመሩ። የልብ ቅድስናና የውጫዊ ባህርይ ትክክለኛ አስፈላጊነትን በመረዳት በቅንነት አዲስ ሕይወት ፍለጋ ተያያዙት። በከፍተኛ ትጋትና ፀሎት በተሞላበት ጥረት የተፈጥሮአዊ ልብን ክፋት ለማንበርከክ ደከሙ። ራስን የካደ የፍቅርና ራስን ዝቅ ያደረገ ሕይወት በመኖር ከሁሉም በላይ የሚፈልጉትን፣ የእግዚአብሔርን ተቀባይነት የሚያረጋግጥላቸውን ቅድስና ለማግኘት ያስችለናል ብለው ያሰቡዋትን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በታላቅ ጥንቃቄና ውልፍት በማያደርግ ሁኔታ ይፈጽሙ ነበር። በጥረታቸው ግን የፈለጉትን ያሳኩ ዘንድ አልተቻላቸውም። ከኃጢአት እርግማን ራሳቸውን ነፃ ለማድረግም ሆነ ሃይሉን ለመስበር ያደረጉት ጥረት መና ሆነ። በኤርፈርት ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ሉተር ያለፈበት ተመሳሳይ ትግል ነበር። ነፍሱን ያሰቃየው የነበረው ያ ተመሳሳይ ጥያቄ ነበር፦ “ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ፃድቅ መሆን እንዴት ይችላል? [እዮብ 9÷2]። GCAmh 187.4
ከጥቂት ጊዜ በፊት በፕሮቴስታንትነት መሠውያ ላይ የተዳፈነው የመለኮታዊ እውነት ነበልባል በቦሄሚያዊያን ክርስቲያኖች አማካኝነት ለዘመናት ሲተላለፍ የመጣው የጥንቱ ችቦ እንደገና ይቀጣጠል ዘንድ ነበረው። ከተሐድሶው በኋላ በቦሄሚያ የነበረው ፕሮቴስታንትነት በሮም የሕዝብ መንጋ ተረግጦ እንዲጠፋ ተደርጎ ነበር። እውነትን ይክዱ ዘንድ እምቢ ያሉት ሁሉ መሰደድ ግድ ሆኖባቸው ነበር። ከእነዚህ የተወሰኑት ወደ ሳክሶኒ (ጀርመን) ኮብልለው በዚያ መጠጊያ በማግኘት የጥንቱን ኃይማኖት መጠበቅ ቻሉ። ወደ ዌስሊና አጋሮቹ ብርሐን የመጣው ከእነዚህ ክርስቲያኖች ትውልድ ዘንድ ነበር። GCAmh 188.1
ጆን ዌስሊና ቻርለስ ዌስሊ፤ ለአገልግሎት ከተቀቡ በኋላ ለሚስዮናዊ ተልዕኮ ወደ አሜሪካ ተላኩ። በሚጓዙበት መርከብ ውስጥ የሞራቫዊያን ቡድን ነበር። በጉዞው አደገኛ የሚባሉ የባህር ማዕበሎች ተከስተው ጆን ዌስሊ ከሞት ጋር ፊት ለፊት ሲፋጠጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ሰላም ማረጋገጫ እንደሌለው ተሰማው። ሆኖም በተቃራኒው ጀርመናዊያኑ የተረጋጋ መንፈስና እምነት ይንፀባረቅባቸው ነበር፤ ይህ ሰላም ለእርሱ እንግዳ ነበር። GCAmh 188.2
“ገና ቀደም ብዬ” አለ “ፀባያቸው የምር እንደሆነ አስተውያለሁ። ማንም እንግሊዛዊ የማያደርገውን እንደ ባርያ ሆነው ለሌሎች ተጓዦች ጥቅም ሲሉ ሲሰሩዋቸው የነበሩት ተራ ሥራዎች ለትሁትነታቸው ቋሚ ማስረጃዎች ነበሩ። ይህ ዝቅተኛ ሥራ ለኩሩው ልባቸው መድሃኒት እንደሆነና አፍቃሪ አዳኛቸው ከዚህ የበለጠ ለእነርሱ እንዳደረገላቸው በመግለጽ ለልፋታቸው ክፍያ መሻት ወይም መቀበል አይፈልጉም ነበር። እያንዳንዱ ቀን ጉዳት የማይበግረው ትህትና ያሳዩ ዘንድ ዕድል የሚሰጣቸው ነበር። ቢገፈተሩ፣ ቢመቱ ወይም ተገፍተው ቢወድቁ [ፀብ ሳያነሱ] እንደገና ተነስተው ይሄዱ ነበር እንጂ አንዳች ምሬት ከአፋቸው አትወጣም ነበር። ከፍርሃት እንዲሁም ከኩራት፣ ከቁጣና ከበቀል መንፈስ በእርግጥ ተላቀው እንደሆነ መፈተኛ ዕድል ተገኘ። አገልግሎታቸውን የሚጀምሩበት መዝሙር እየዘመሩ ሳለ፣ ጥልቁ የዋጠን በሚመስል ሁኔታ ባህሩ ወደ ላይ ተነስቶ ዋናውን የመርከብ ሸራ ሰንጥቆ መርከብዋን በመሸፈን በወለልዋ መካከል ፈሰሰ። እንግሊዞቹ ጩኸታቸውን አቀለጡት፤ ጀርመኖቹ በእርጋታ መዘመራቸውን ቀጠሉ። በኋላ አንደኛውን ጠየኩት ‘አልፈራህም ነበር?’ ‘አልፈራሁም፣ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ’ ብሎ መለሰልኝ። ‘ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁስ አልፈሩም?’ ብዬ ጠየቅሁት፤ ‘አይ ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ለመሞት አይፈሩም’ ብሎ በለሆሳስ መለሰልኝ።”-Whitehead, Life of the Rev. Charles Wesley, ገጽ 102። GCAmh 188.3
ወደ ሳቫናህ ሲደርሱ ዌስሊ ከሞራቪያውያን ጋር ለአጭር ጊዜ ቆየ፤ በክርስቲያናዊ ባህሪያቸው እጅግ ተነክቶ ነበር። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከምትከተለው ምውት ሥርዓተኝነት ጋር ፍጹም ተቃራኒ ስለሆነው ስለ አንዱ አምልኮአቸው ሲጽፍ፦ “ሁሉም ነገር ያልተወሳሰበና የተረጋጋ መሆኑ በመካከል ያለፉትን ሺህ ሰባት መቶ ዓመታት ረስቼ፣ ታይታና ደረጃ ባልነበሩበት፣ ከጉባኤዎቹ በአንዱ ውስጥ እንዳለሁ አሰብኩ፤ ድንኳን ሰፊው ጳውሎስ ወይም አሳ አጥማጁ ጴጥሮስ በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ያህል መሰለኝ። ያ መንፈስና ኃይል ግን በሥራ ላይ ነበረ።”-Ibid., ገጽ 11, 12። GCAmh 188.4
ዌስሊ ወደ እንግሊዝ ሲመለስ በአንድ የሞራቪያን ሰባኪ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን እምነት በተሻለ መረዳት ቻለ። ለመዳን በራሱ ሥራ መደገፉን ሙሉ በሙሉ መተው እንዳለበት፣ እምነቱንም ሙሉ በሙሉ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” [ዮሐ 1÷29] ላይ ማድረግ እንዳለበት ተረዳ። በለንደን በተደረገ በአንድ የሞራቪያን ማህበር ስብሰባ ላይ በአንድ አማኝ ልብ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሚሰራው ሥራና ስለሚመጣው ለውጥ የሚገልፅ የሉተር ፅሁፍ ተነበበ። ዌስሊ ይህንን ሲሰማ እምነት በውስጡ ተጸነሰ። “ልቤ እንግዳ በሆነ ሁኔታ ሲሞቅ ተሰማኝ” ይላል “ለመዳኔ ክርስቶስንና ክርስቶስን ብቻ እንዳመንኩ ተሰማኝ። የእኔን፣ ያውም የእኔን ኃጢአት ወስዶ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ እንዳተረፈኝ ማረጋገጫ ተሰጠኝ።”-Ibid., ገጽ 52። GCAmh 188.5
ረጅም ዓመታትን በፈጀ አድካሚና ጎርባጣ በሆነ ጥረት፤ ዓመታትን ባስቆጠረ ንቅንቅ በማያደርግ ራስን መካድ፣ ወቀሳና ውርደት ውስጥ በመሆን ዌስሊ እግዚአብሔርን የመፈለግ ብቸኛ ዓላማውን ግራ ቀኝ ሳይል ቀጥሎበት ነበር። አሁን አገኘው፤ በፀሎትና በጾም፣ በምፅዋትና ራስን በመናቅ ለማግኘት ሲማስንበት የነበረው ፀጋ “ያለ ገንዘብና ያለ ክፍያ”፣ ስጦታ ሆኖ አገኘው። GCAmh 189.1
በክርስቶስ እምነት ላይ ከተመሠረተ ጀምሮ የእግዚአብሔርን የነፃ የከበረ ወንጌል እውቀት ወደ ሁሉም ስፍራ ለማሰራጨት ከነበረው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ነፍሱ ትቃጠል ነበረች። “እኔ ዓለምን ሁሉ የምመለከተው የራሴ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ አድርጌ ነው” አለ፤ “በየትኛውም ስፍራ ብሆን መልካሙን የድነት የምሥራች መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ አውጅ ዘንድ ገጣሚ፣ ትክክልና እፈጽመው ዘንድ የሚገባኝ ኃላፊነት እንደሆነ አድርጌ እወስደዋለሁ።”-Ibid., ገጽ 74። GCAmh 189.2
የማያወላዳና ራስን-የካደ ሕይወቱን ቀጠለበት፤ አሁን ግን የዕምነቱ መሰረት አድርጎ ሳይሆን የእምነት ውጤት፣ የቅድስና ስሩ ሳይሆን ፍሬው አድርጎ ነበር። በክርስቶስ ያለው የእግዚአብሔር ፀጋ የክርስቲያን ተስፋ መሰረት ነው፤ ያም ፀጋ በመታዘዝ የሚገለጽ ይሆናል። የዌስሊ ሕይወት፣ የተቀበላቸውን እውነቶች ለመስበክ የተሰጠ ነበር - በሚያነጻው በክርስቶስ ደም በማመን መጽደቅን፣ የክርስቶስን ምሳሌ በሚከተል ሕይወት ውስጥ ፍሬ የሚያመጣ፣ ልብን የማደስ ኃይል ስላለው መንፈስ ቅዱስ መስበክ የሕይወቱ አላማ ነበር። GCAmh 189.3
ዋይትፊልድና ዌስሊዎች ጠፋን ብለው ባመኑበት ሁኔታቸው ውስጥ ሆነው በወሰዱት ረጅምና በሚያሳምም ግላዊ ውሳኔያቸው አማካይነት ለሥራቸው ተዘጋጅተው ነበር። እንደመልካም የክርስቶስ ወታደርነታቸውም ስቃይን ለረጅም ጊዜ ተቋቁመው ይዘልቁ ዘንድ በዩኒቨርስቲ እያሉም ሆነ ወደ አገልግሎቱ ሲገቡ በንቀት፣ በፌዝና በስደት ከባድ አበሳ ተቀብለው ነበር። እግዚአብሔርን የማያውቁ አብረዋቸው የሚማሩ ተማሪዎች እነርሱንና ጥቂት ደጋፊዎቻቸውን፣ በንቀት “ሜተዲስት” ብለው ይጠሯቸው ነበር። ይህ ስም በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካና በእንግሊዝ ካሉ ታላላቅ የኃይማኖት ማህበራት አንዱ በመሆን ክቡር ሆኖ የሚታይ ሆኖአል። GCAmh 189.4
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንደመሆናቸው ከአምልኮ ሥርዓትዋ ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ቢሆኑም እግዚአብሔር ግን በቃሉ አማካይነት ከፍ ያለ ደረጃን አቅርቦላቸው ነበር። ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ ይሰብኩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጎሰጎሳቸው። ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ጥረታቸውን ያግዝ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ጥፋተኛነታቸው ገብቶአቸው ከልብ ተለወጡ። እነዚህ በጎች ደግሞ ከነጣቂ ተኩላዎች መጠበቅ ነበረባቸው። ዌስሊ አዲስ የሐይማኖት ወገን (ድርጅት) የማቋቋም ሃሳብ አልነበረውም፤ ሆኖም ሜተዲስት ኮኔክሽን (Methodist Connection) በሚል ስም ሥር አደራጃቸው። GCAmh 189.5
ከዋናው ቤተ ክርስቲያን በኩል እነዚህን ሰባኪዎች የገጠማቸው ተቃውሞ ምስጢራዊና ፈታኝ ነበር፤ ሆኖም እግዚአብሔር በጥበቡ ሁኔታዎችን በመለወጥ በዚያው ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ እንዲጀምር አደረገ። ለውጡ ሙሉ በሙሉ ከውጪ የመጣ ቢሆን ኖሮ በተለይ ወደተፈለገበት ስፍራ ሰርስሮ መግባት ይሳነው ነበር። የመነቃቃቱ ሰባኪዎች የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሆነው በዛው በቤተ ክርስቲያኑ ክበብ ውስጥ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየተጉ በሩ እንደተዘጋበት ይቀር የነበረው እውነት መሹለኪያ ደጃፍ አገኘ። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ካህናት ከሥነ-ባህርያዊ ድንዛዜ ተላቀው በራሳቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ንቁ ሰባኪዎች ለመሆን በቁ። በወግ አጥባቂነት ፍርሃት ደርቀው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ነፍስ ዘራባቸው። GCAmh 190.1
በዌስሊ ዘመን፣ እንደ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ዘመናት ሁሉ፣ የተለያየ ክህሎት የነበራቸው ሰዎች የተሰጣቸውን ሥራ አከናወኑ። በእያንዳንዱ የአስተምህሮ ነጥብ ላይ ባይስማሙም ሁሉም ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ተነሳስተው ነፍሳትን ለክርስቶስ መማረክ በሚለው የሚያስተሳስር ዓላማ ስር ተባበሩ። በዋይት ፊልድና በዌስሊዎች መካከል የነበሩት ልዩነቶች በአንድ ወቅት የመቃቃር ስሜትን ለመፍጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም የዋህነትን ከክርስቶስ ትምህርት ቤት ውስጥ እየተማሩ ሲሄዱ የእርስ በርስ መቻቻልና ፍቅር እንደገና አስታረቃቸው። ስህተትና ኃጢአት በየስፍራው ተትረፍርፎ፣ ኃጢአተኞች ወደ ጥፋት እየወረዱ እያለ ለንትርክ ጊዜ አልነበራቸውም። GCAmh 190.2
የእግዚአብሔር አገልጋዮች አባጣ ጎርባጣ መንገድ ላይ ተጓዙ። የተማሩና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይቋቋሟቸው ዘንድ ኃይላቸውን ተጠቀሙ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የቤተ ክህነት ባለስልጣናት ያላሰለሰ ጥላቻ በማንፀባረቃቸው የአብያተ ክርስቲያናት በሮች በንፁሁ እምነትና ባወጁት ላይ ተዘጋ። ካህናቱ መድረክ ላይ ቆመው የፈፀሙት የውግዘት ድርጊት የጽልመትን፣ የድንቁርናንና የአመጽን ኃይላት ቀሰቀሰ። በእግዚአብሔር የምሕረት ተዓምር፣ ጆን ዌስሊ በተደጋጋሚ ሞትን አመለጠ። የሕዝቡ ቁጣ በእርሱ ላይ ሲገነፍልና ምንም አይነት ማምለጫ የጠፋ ሲመስል መልአክ በሰው አምሳል ሆኖ ከጎኑ ቆመ፤ አመፀኛው ሕዝብ ወደኋላ አፈገፈገ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይም ከአደገኛው ስፍራ በሰላም አለፈ። GCAmh 190.3
ይህን ከመሰሉ አጋጣሚዎች ውስጥ በአንዱ፣ በቁጣ ከነደደው ሕዝብ ባመለጠ ጊዜ ዌስሊ እንዲህ አለ፣ “በሚያንዳልጥ መንገድ ወደ ከተማ ቁልቁለት ስንወርድ አንዴ ከወደቅሁ ተመልሸ የመነሳቴ ጉዳይ የማይታሰብ እንደሆነ በመገመት ብዙዎች ገፍትረው ሊጥሉኝ ሞከሩ፤ ሆኖም ግን ፈጽሞ አልተደናቀፍኩም። ከእጃቸው ሙሉ በሙሉ እስክወጣ ድረስ ትንሽም አልተንሸራተትኩም። ብዙዎች [ጎትተው ሊጥሉኝ…] ኳሌታዬን ወይም ልብሴን ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም መጨበጥ ግን በጭራሽ አልቻሉም። አንደኛው ብቻ ከኮቴ ስር የለበስኩትን የልብስ ዘለበት መያዝ ችሎ ነበር። ጨርቁ ግን ተቀዶ እጁ ጋር ቀረ። በውስጡ የባንክ ቼክ የነበረበት ኪስ በኩል የነበረው ዘለበት በግማሽ ብቻ ተቀደደ። አንዱ ኃይለኛ ሰው በኋላዬ ሆኖ በዋርካ ዱላ በተደጋጋሚ ይደበድበኝ ነበር። በዚያ ብትር አንድ ጊዜ የኋላ አናቴን ቢያገኘኝ ኖሮ ከብዙ ልፋት ይተርፍ ነበር። በሞከረ ቁጥር ግን ምቱ ወደ ጎን ዘወር ይል ነበር፤ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አላውቅም፣ ምክንያቱም ግራዬንም ሆነ ቀኝ እጄን ማንቀሳቀስ አልችልም ነበር። ሌላኛው ከሕዝቡ መካከል እየበረረ መጣና ሊመታኝ ክንዱን ከዘረጋ በኋላ መለሰው፤ ራሴን ብቻ ነካ አደረገኝና ‘ምን አይነት ለስላሳ ፀጉር ነው ያለው’ አለ…. ልባቸው ከተለወጠው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ውስጥ የከተማዋ ጀግኖች፤ በሁሉም ክስተቶች ላይ የብጥብጥ መሪዎች፣ እንዲያውም ከመካከላቸው አንዱ በውድድር ለሽልማት የሚፋለም፣ ሰዎች ነበሩ። GCAmh 190.4
“በምን አይነት፣ ጥንቃቄ በተሞላበት እግዚአብሔር ለፈቃዱ ያዘጋጀናል! ከሁለት ዓመት በፊት የጡብ ስባሪ ትክሻዬን ጋጠኝ። ይህ የሆነው ድንጋይ በአይኖቼ መካከል ከመታኝ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ባለፈው ወር አንድ ጊዜ፣ በዚህ ምሽት ደግሞ ሁለት ጊዜ ተመትቻለሁ፤ አንዱ ወደ ከተማዋ ከመግባታችን በፊት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከወጣን በኋላ ነበር። ሁለቱም ግን ምንም ያህል አልነበሩም። ምክንያቱም አንደኛው ሰው ያለውን ኃይል ተጠቅሞ ደረቴን ቢመታኝም፣ ሌላኛው ደግሞ በኃይል አፌን ሲለኝ ደሙ ወዲያውኑ ቢንቦለቦልም፣ ሁለቱም ምቶች በሰንበሌጥ ነካ ከመደረግ ያህል የበለጠ ህመም አልነበራቸውም።”-John Wesley, Works, vol. 3, ገጽ 297, 298። GCAmh 191.1
በእነዚያ በጥንት ዘመናት የነበሩ ሜተዲስቶች - ሰባኪዎቹም ሆኑ ምእመናኑ - የሚወክሉት ነገር የተሳሳተ ነው ብለው ከሚበሳጩ፣ ከቤተ ክርስቲያን አባላትም ሆነ በግልጽ ኃይማኖተ-ቢስ ከሆኑ ሰዎች ዘንድ፣ መሳለቂያ መደረግና ስደት ይደርስባቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በፍርድ ቤት ትክክለኛ ፍርድ ማግኘት ያልተለመደ በሆነበት፣ ለስም ብቻ በቆሙ ፍርድ ቤቶች ፊት ይቀርቡ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በአሳዳጆቻቸው የኃይል እርምጃ ይፈፀምባቸው ነበር። ሰዎች ተሰብስበው ቤት ለቤት በመዞር የቤት ቁሳቁስና ሌሎች ሸቀጦችን በማውደም፣ የፈለጉትን በመዝረፍ፣ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ህጻናትን ያሰቃዩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ መስኮቶቹን በመስበር የሜተዲስት ቤቶችን ለመዝረፍ መተባበር የሚፈልጉ ሰዎች በተወሰነ ጊዜና ቦታ እንዲሰበሰቡ ማስታወቂያ ይለጠፍ ነበር። እንዲህ አይነቶቹ የሰውንና የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጥሱ ግልጽ ወንጀሎች ያለምንም ነቀፌታ በዝምታ ይታለፉ ነበር። ብቸኛ ጥፋታቸው የኃጢአተኞችን እግሮች ከጥፋት መንገድ ወደ ቅድስና ጎዳና ለማምጣት ፍላጎት ማሳየታቸው በሆኑት ላይ የተቀናጀ የማሳደድ ተግባር ይፈፀምባቸው ነበር። GCAmh 191.2
በእርሱና በግብረ አበሮቹ ላይ ስለተነሳው ክስ ዌስሊ ሲናገር፣ “የእነዚህ ሰዎች አስተምህሮ ሐሰት፣ ስህተትና ከስሜታዊነት የመነጩ፣ እንዲሁም አዲስና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሰምተው የማያወቁ፣ መሰረታዊ የቤተክርስቲያን አሰራርን የማይቀበሉ ኩዋከራዊነት(Quakerism)፣ አክራሪነትና እብሪት እንደሆኑ አድርገው አንዳንዶች ይናገራሉ። የዚህ አስተምህሮ እያንዳንዱ ዘርፍ በቤተ ክርስቲያናችን የተተረጎመው የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ አስተምህሮ እንደሆነ በስፋት እንዲታይ ስለተደረገ እንዲህ አይነቱ አስመሳይነት ከሥሩ የተቆረጠ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እስከሆነ ድረስ ይህ አስተምህሮ ስህተት ሊሆን አይችልም።” GCAmh 191.3
“አንዳንዶቹ ደግሞ፣ አስተምህሮአቸው እጅግ ከመጠን ያለፈ ጥብቅ፣ ወደ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ እጅግ የሚያጠብ ነው ይላሉ። ይህ ለተወሰነ ጊዜ በብቸኝነት ሲነገር የነበረው፣ በስውር ደግሞ የተለያየ መልክ ይዞ የሺህ ተቃውሞዎች መሰረት የሆነ ዋናውና የመጀመሪያው ተቃውሞ ነው። ሆኖም ጌታችንና ሐዋርያት ካደረጉት የበለጠ የሰማይን መንገድ አጥብበውታልን? አስተምህሮዎቻቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ የባሰ ጥብቅ ናቸውን? እስኪ ጥቂት ጥቅሶችን ብቻ አጢኑ፤ ‘ጌታ አምላክህን በፍፁም ልብህ በፍፁም ነፍስህም በፍፁም ኃይልህም በፍፁም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ [ሉቃስ 10÷27] ‘ሰዎች ስለሚናገሩት ስለከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል’ [ማቴ 12÷36] ‘እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት’ [1ኛ ቆሮ 10÷31]። GCAmh 191.4
“የእነርሱ አስተምህሮ ከዚህ የጠበቀ ከሆነ ወቀሳ ይገባቸዋል። ይህ እንዳልሆነ ግን ህሊናችሁ ያውቀዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ሳያበላሽ ጥብቅነቱን በአንድ ነጥብ መቀነስ ማን ይችላል? የእግዚአብሔር ምስጢራት አገልጋይ የሆነ እርሱ የተቀደሰውን ምስክር ቢለውጥ ታማኝ ሆኖ ይገኛልን? አይችልም። ምንም ነገር ማለዘብ፣ ምንም ነገር ማለሳለስ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስን እናንተ ወደምትፈልጉት ደረጃ ዝቅ ማድረግ አልችልም ብሎ የማወጅ ኃላፊነት አለበት። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ደረጃ ከፍ ማለት አለባችሁ፣ ወይም ለዘላለም ትጠፋላችሁ። እነዚህ ሰዎች ፍቅር የሌላቸው እንደሆኑ ተደርገው በአብዛኛው ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። ፍቅር የሌላቸው ናቸውን? በምን ዓይነት መልኩ? የራበውን አያበሉም?፣ የታረዘውን አያለብሱም? አይ አይደለም። ጉዳዩ ይህ አይደለም፤ በዚህ በኩል ጎዶሎ የለባቸውም። ሆኖም ፍርድ በመስጠት በኩል ፈጽሞ ሚዛናዊ አይደሉም። እነርሱ የሚከተሉትን መንገድ የማይከተሉ ሁሉ እንደሚጠፉ ያስባሉ።”-Ibid., vol. 3, ገጽ 152, 153። GCAmh 192.1
ከዌስሊ ዘመን ትንሽ ቀደም ብሎ በእንግሊዝ አገር ሲንፀባረቅ የነበረው መንፈሳዊ ዝቅጠት ባብዛኛው የአንቲኖሚያን (Antinomian - ለመዳን እምነት ብቻ በቂ ነው፣ ሕግጋት አያስፈልጉም የሚል አስተምህሮ) ትምህርት ውጤት ነው። ክርስቶስ የግብረገብ ሕጉን (the Moral Law) እንደሻረውና ክርስቲያኖችም ይጠብቁት ዘንድ ግዴታ እንደሌለባቸው ብዙዎች በማመን አንድ አማኝ ከ“መልካም ሥራ ባርነት” ነፃ እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የሕጉን ዘላለማዊነት ቢቀበሉትም “ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር የመረጣቸው እነርሱ ይቋቋሙት ዘንድ በማይችሉት የመለኮት ፀጋ ጉትጎታ ቅድስናንና ግብረ ገብነትን ወደ መተግበር ስለሚመሩ፤ ለዘላለም በእግዚአብሔር የተጠሉት ደግሞ መለኮታዊ ሕጉን ይታዘዙ ዘንድ የሚያስችል ኃይል ስለሌላቸው፣ ሕዝቡ የሕጉን መመሪያ ይጠብቅ ዘንድ አገልጋዮች መናገራቸው አስፈላጊ አይደለም ባዮች ነበሩ። GCAmh 192.2
“የተመረጡት ከፀጋ ሊርቁ ወይም የመለኮታዊ ሞገስን ሊያጡ አይችሉም” የሚሉ ሌሎች ደግሞ የበለጠ አስከፊ ወደሆነ መደምደሚያ በመድረስ፣ የሚፈጽሙአቸው ክፉ ተግባራት በእርግጥ ኃጢአት አይደሉም፤ የመለኮታዊ ሕግን እንደጣሱ ተደርጎም ሊቆጠርባቸው አይችልም፤ በመሆኑም ኃጢአታቸውን መናዘዝ ወይም በንስሐ ማስተሰርየት አይጠበቅባቸውም ባዮች ነበሩ። ስለዚህ አሉ ሲናገሩ፣ እጅግ አፀያፊ የሆነው፣ “የመለኮት ሕግን በስፋት የጣሰ እንደሆነ በሁሉም ዘንድ የሚታመነው” ኃጢአት እንኳ የተፈፀመው በተመረጡት ከሆነ “በእግዚአብሔር እይታ ኃጢአት ሆኖ አይቆጠርም”፤ “ምክንያቱም እግዚአብሔርን የማያስደስት ወይም በሕጉ የተከለከለ ነገር መፈፀም የማይችሉ መሆናቸው፣ የተመረጡት መለያ ከሆኑት አስፈላጊና ልዩ ባህርያት ውስጥ አንዱ በመሆኑ ነው።” GCAmh 192.3
ይህ ግዙፍ(አስፈሪ) አስተምህሮ፣ “የሊቀ ጳጳሱ ከሕጉ በላይ መሆን ሕግጋትንም በመቀየር ስህተትን ትክክል በማድረግ” “ከእግዚአብሔርና ከሰው ሕግ ተቃራኒ የሆኑ ቅጣቶችንና ፍርዶችን ማስተላለፍ ይችላል” ከሚለው ከሮማዊነት አቋም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነው። ሁለቱም የሚያንፀባርቁት ኃጢአት ባልሰሩ ሰማያዊ ነዋሪዎች መካከል እንኳ ትክክለኛ መገደቢያ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ለማፈራረስ ሥራውን የጀመረውን፣ ተመሳሳይነት ያለውን፣ የዋናውን መንፈስ የማደፋፈር ተግባር ነው። GCAmh 193.1
ሰዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ የማይለወጥ ባህርይ እንዲኖራቸው የሚያደርጉት የመለኮታዊ አዋጆች አስተምህሮ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ሕግ እንዳለ እንዲቃወሙት አድርጓቸዋል። ዌስሊ የአንቲኖሚያን አስተማሪዎችን ስህተት አምርሮ በመቃወም ወደ አንቲኖሚያዊነት የመራው አስተምህሮም መጽሐፍ ቅዱስን የሚፃረር እንደሆነ አሳየ። ” ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ፀጋ ተገልጧልና”፤ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሐር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ የሱስ ነው፤ ራሱንም ለሰው [ሁሉ] ቤዛ ሰጠ።” [ቲቶ 2÷11፤ 1ኛ ጢሞ 2÷3-6]። እያንዳንዱ ሰው ለመዳን የሚያስፈልገውን አቅርቦት መጨበጥ ይችል ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ በነፃ ተበርክቷል። ክርስቶስ “እውነተኛው ብርሐን” “ለሰው ሁሉ የሚያበራ ወደ ዓለም ለሚመጣው” [ዮሐ 1÷9] ነው። ሰዎች መዳንን የማያገኙት በራሳቸው ፈቃድ የሕይወትን ስጦታ እምቢ ሲሉ ነው። GCAmh 193.2
በክርስቶስ ሞት፣ የአሥርቱ ትዕዛዛት መመሪያዎች ከሙሴ ሕግ (the ceremonial Law) ጋር ተወግደዋል ለሚለው ዌስሊ ሲመልስ “በአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የተካተተውን ነብያትም እንዲጠበቅ ያደረጉትን የግብረ ገብነት (the moral law) ሕግ እርሱ አላስወገደውም። የዚህን ሕግ ማንኛውንም ክፍል ማፍረስም ወደዚህ የመምጣቱ እቅድ አካል አልነበረም። ይህ ሕግ በፍጹም ሊጣስ የማይችል፣ ‘ተአማኒ ምስክር ሆኖ በሰማይ የሚቆም’….ሕግ ነው። ይህ ሕግ ዓለም ሲፈጠር የነበረ፣ ‘በድንጋይ ጽላት የተጻፈ ሳይሆን‘፣ የሰው ልጆች ከፈጣሪ እጆች ሲወጡ በልባቸው ላይ የተፃፈ ሕግ ነው። በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር ጣት የተፃፉት ፊደላት በኃጢአት ምክንያት በእጅጉ መልካቸው የተበላሸ ቢሆንም ክፉና በጎን የማወቅ ህሊና እስካለን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊጠፉ አይችሉም። በጊዜ ወይም በቦታ ወይም ሊቀየር በሚችል በማንኛውም ነገር ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰው ማንነትና ሁለቱ ባላቸው የማይለወጥ ግንኙነት ተወስኖ የዚህ ሕግ እያንዳንዱ ክፍል በሁሉም ዘመናት በሰው ዘር ሁሉ ተከብሮ መቀጠል አለበት። GCAmh 193.3
“‘ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ’.... ያለምንም ጥያቄ በዚህ ስፍራ የእርሱ[የየሱስ] ትርጉም (ከሚቀድመውም ሆነ ቀጥሎ ከሚመጣው ጋር ተደጋጋፊነት ባለው ሁኔታ) የሚያስረዳው ሰዎች በብዙ መንገድ ሊሸፋፍኑት ቢሞክሩም ሙሉ በሙሉ ልፈጽመው መጣሁ፤ በውስጡ የተደበቀና የጨለመው ነገር ሁሉ በሙላትና በጥራት ይታይ ዘንድ ላስችለው መጣሁ፤ እያንዳንዱ የሕጉ አካል ያዘለውን በሙላትና በእውነት ላውጅ መጣሁ፤ በዚያ የተካተተ የእያንዳንዱን ትዕዛዝ ርዝመቱን፣ ወርዱን፣ ከነሙሉ ልኬቱ በሁሉም ቅርንጫፎቹ የተካተተውን ሊታሰብ የማይችለውን የንጽህናውንና የመንፈሳዊነቱን ቁመትና ጥልቀት አሳይ ዘንድ መጣሁ።” የሚል ነው-Wesley, sermon 25። GCAmh 193.4
ዌስሊ በሕጉና በወንጌሉ መካከል ያለውን ፍፁም ስምምነት አወጀ። “ስለዚህ በሕጉና በወንጌሉ መካከል ሊታሰብ የሚችለው ከፍተኛው ቅርበትና ቁርኝት አለ። በአንድ በኩል ሕጉ መንገድ በመምራት ወደ ወንጌሉ ይጠቁመናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌሉ ወደ ተሻለ የሕጉ ተግባራዊነት (ተፈፃሚነት) በቋሚነት ይመራናል። ለምሳሌ ሕጉ እግዚአብሔርን እንድንወድ፣ ባልንጀራችንን እንድንወድ፣ ትሁት፣ የዋህ ወይም ቅዱስ እንድንሆን ይጠብቅብናል። እኛ ለእነዚህ ነገሮች በቂ እንዳልሆንን ይሰማናል፤ አዎ፣ ይህ በሰው የማይቻል ነው፤ ሆኖም ትሁት፣ የዋህና ቅዱስ ያደርገን ዘንድ እግዚአብሔር ፍቅሩን ሊሰጠን ያለውን ተስፋ እናያለን፣ ይህንን ወንጌል እንይዛለን፣ መልካሙን ዜና እንጨብጣለን፣ እንደ እምነታችን ይደረግልናል። ክርስቶስ የሱስን በማመን [2ኛ ጢሞ 3፦15] የሕጉ ፃድቅነት በእኛ ተፈፃሚነት ያገኛል። GCAmh 194.1
“የክርስቶስ ወንጌል ጠላቶች በመሆን ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዙት” አለ ዌስሊ፣ “በገሃድና በግልጽ ራሱን ‘ሕጉን የሚገመግሙ’ና ‘የሕጉን ክፉነት የሚያወሩ’፤ አንድ ብቻ ሳይሆን፣ ትንሹንም ይሁን ትልቁን ሳይሆን፣ ሁሉንም ትዕዛዛት ሰዎች እንዲጥሱ (ያለባቸውን ግዴታ እንዲያፈርሱ) የሚያስተምሩት ናቸው።” ” ይህን ኃይለኛ ድንብርብር ከሚያሳዩ ሁኔታዎች ሁሉ የሚገርመው የተቀበሉት ሁሉ ሕጉን በመገልበጣቸው ክርስቶስን እያከበሩት እንደሆነ፣ አስተምህሮውን እያፈራረሱ ሳለ ሥራውን ከፍ ከፍ እያደረጉ እንደሆነ ከምር ማመናቸው ነው። ‘መምህር ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን’ ብሎ እንደ ‘ሳመው’፣ [ማቴ 26፦49] ልክ ይሁዳ እንዳደረገው፣ አዎ እነርሱም ያከብሩታል። እርሱም እንደሚገባው ለእያንዳንዳቸው ‘በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?’[ሉቃ 22÷48] ይላቸዋል። ወንጌሉን ማስፋፋት በሚለው ማስመሰያ ውስጥ የሕጉን የትኛውንም ክፍል ማቃጠል፤ ስለ ደሙ ማውራትና አክሊሉን መውሰድ በመሳም ከመካድ የተለየ አይደለም። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማንኛውንም የመታዘዝ ቅርንጫፍ ወደ ጎን በመተው እምነትን የሚሰብክ፤ ከእግዚአብሔር ትዕዛዛት ውስጥ እጅግ ታናሽ የተባለውን በማናቸውም ሁኔታ ይሰርዝ ወይም ያዳክም ዘንድ ክርስቶስን የሚሰብክ ማንም ከዚህ ክስ የሚያመልጥ አይሆንም።”-Ibid። GCAmh 194.2
“የወንጌሉ ስብከት ሁሉንም የሕግ መጠይቅ ሙሉ በሙሉ ያሟላል” ለሚሉት ደግሞ ዌስሊ ሲመልስ፣ “ይህንን በፍፁም እንቃወማለን፣ ሰዎችን ስለ ኃጢአታቸው የማሳመንን፣ በሲኦል አፋፍ ላይ ሆነው አሁንም የሚያንቀላፉትን የመቀስቀስ ተግባር የሆነውን የመጀመሪያውን የሕጉን ዓላማ ጥያቄ አይመልስም (አያሟላም)።” ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው “ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና” [ሮሜ 3፦20]፣ አንድ ሰው ኃጢአቱ እስኪወቅሰው ድረስ፣ የሚያነፃው የክርስቶስ ደም እንደሚያስፈልገው በትክክል አይሰማውም…. ጌታችን ራሱ እንዳስተዋለው ‘ህመምተኞች እንጂ ባለጤናዎች መድሃኒት አያስፈልጋቸውም።’ ስለዚህ ለጤነኞች ወይም ቢያንስ ጤነኛ ነን ብለው ለሚያስቡ ሐኪም ማቅረብ ዘበት ይሆናል። መጀመሪያ ማሳመን ይጠበቅባችኋል፣ ያለበለዚያ ለጥረታችሁ ምስጋና አይቸሯችሁም። በተመሳሳይ ሁኔታ ልባቸው ሙሉ ለሆኑት፣ ገና ተሰብሮ የማያውቅ ልብ ላላቸው ሰዎች ክርስቶስን ብታቀርቡላቸው የማይመስል ይሆናል።”-Ibid, sermon 35። GCAmh 194.3
እንደዚህም በማድረግ የእግዚአብሔርን የፀጋ ወንጌል እየሰበከ ሳለ፣ ዌስሊ ልክ እንደጌታው ሁሉ “ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ” ወደደ። በእግዚአብሔር የተሰጠውን ኃላፊነት በታማኝነት አከናወነ። እንዲያያቸው የተደረጉት ውጤቶችም አንፀባራቂ ነበሩ። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቤት ለቤት ወንጌል በመሥራት አሳልፎ የሰማኒያ አመት ረጅም ሕይወቱ ወደ መገባደድ ሲደርስ የታማኝ ተከታዮቹ ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን ነፍሳት በላይ ነበር። ሆኖም በእርሱ ልፋት ከኃጢአት መቆርቆዝና ጥፋት ወጥተው ከፍ ወዳለና ወደ ቅዱስ ሕይወት የመጡ እልፍ አዕላፋት፣ በእርሱ ትምህርት ምክንያት ወደ የጠለቀና የበለፀገ ልምምድ የደረሱት ሰዎች ቁጥር፣ የተዋጁት ሁሉም ቤተሰቦች በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪሰበሰቡ ድረስ በውል የሚታወቅ አይሆንም። የእርሱ ሕይወት ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ዋጋ ሊተመንለት የማይችል ትምህርት የሚለግስ ነው። የዚህ የክርስቶስ አገልጋይ እምነትና ትህትና፣ የማይዝለው ወኔው፣ የራስ መስዋዕትነቱና መሰጠቱ ምነው በዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በተንፀባረቀ! GCAmh 195.1