ታላቁ ተጋድሎ

12/45

ምዕራፍ ፱—የስዊዝ ተሐድሶ አራማጅ

ቤተ ክርስቲያንን ለማቋቋም የሚሰራው ያው መለኮታዊ እቅድ የቤተ ክርስቲያንን ተሐድሶ ለመተግበር በሚወከሉ መሳሪያዎች ምርጫ ላይም ይታያል። በሕዝብ መሪነታቸው ምስጋናና ክብር መቀበል የለመዱትን ስመጥር ሃብታም የሆኑ የምድር ታላላቅ ሰዎችን የሰማያዊ መምህር አለፋቸው። የተሻሉ እንደሆኑ በሚናገሩበት ኩራታቸውና በራስ መተማመናቸው ውስጥ ሆነው፣ ለመሰሎቻቸው ርኅራኄ ማሳየት የሚችሉ ሆነው፣ ከትሁቱ የናዝሬት ሰው ጋር የሥራ ተባባሪ ይሆኑ ዘንድ መቀረጽ የሚችሉ ሳይሆኑ ቀሩ። ላልተማሩ፣ ጥረው ግረው ለሚያድሩ የገሊላ አሳ አጥማጆች ጥሪው ቀረበ “ተከተሉኝ ሰው አጥማጅ አደርጋችኋለሁ።” [ማቴ 4÷19]። እነዚህ ደቀ-መዛሙርት ትሁትና ትምህርት ለመቀበል የተዘጋጁ ነበሩ። በዘመናቸው በነበረው የሃሰት ትምህርት ተፅዕኖ ስር መሆናቸው አናሳ ሆነ ማለት ክርስቶስ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለአገልግሎቱ ሊያስተምራቸውና ሊያሰለጥናቸው ይችላል ማለት ነበር። በታላቁ የተሐድሶ ዘመናትም የሆነው እንዲሁ ነው። የተሐድሶ መሪዎቹ ተራ ከሚባል ሕይወት የመጡ በዘመናቸው ከነበረው የማዕረግ ኩራት፣ እንዲሁም ከንቀትና የስልጣን የበላይነትን ለመቆናጠጥ ከሚለፉ የቅስና ተፅዕኖ የፀዱ ነበሩ። ታላላቅ ውጤታማ ክንውኖችን ይፈጽም ዘንድ ተራ የሚባሉ መሳሪያዎችን መጠቀም የእግዚአብሔር ንድፍ ነው። ይህም ሲሆን የራሱ መልካም ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ መፈለግንና ማድረግን በውስጣቸው ለሚሰራው ለእርሱ እንጂ ክብር ለሰዎች የሚሰጥ አይሆንም። GCAmh 127.1

በማዕድን ሰራተኛ ጎጆ ውስጥ ሉተር በሳክሶኒ ከተወለደ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በእንስሳት አርቢ ጎጆ ውስጥ በአልፕስ መካከል ኧርሊክ ዝዊንግል ተወለደ። ገና በልጅነቱ ዝዊንግል፣ በዙሪያው የነበሩት ነገሮችና በህጻንነቱ ያገኛቸው ስልጠናዎች ለወደፊት ተልዕኮው የሚያዘጋጁት ነበሩ። በተፈጥሮአዊ ታላቅ ግርማ፣ ውበትና አስገራሚ ልዕልና ውስጥ ያደገው ዝዊንግል ከልጅነቱ ጀምሮ በእግዚአብሔር ታላቅነት ኃይልና ግርማዊነት አዕምሮው ተነክቶ ነበር። በዚህ ባደገባቸው ተራራዎች ጀግኖች የፈፀሟቸው የጀብዱ ታሪኮች የወጣትነት ህልሙን አቀጣጠሉት። ኃይማኖተኛ ከሆነቸው አያቱ አጠገብ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያንዋ ቀደምት ታሪኮችና ወጎች መካከል ለቃቅማ ያሰባሰበቻቸውን ወርቃማ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ይሰማ ነበር። አበውና ነብያት የፈጸሟቸውን ታላላቅ ተግባራት፤ በፍልስጤም ኮረብታዎች በጎቻቸውን ሲጠብቁ ስለነበሩት፣ መላዕክት ስላነጋገሯቸው እረኞች፣ ስለ ቤተልሔሙ ህፃንና ስለ ቀራንዮ ሰው በጥልቅ ፍላጎት ያደምጥ ነበር። GCAmh 127.2

እንደ ጆን ሉተር ሁሉ የዝዊንግል አባትም ልጁ ይማር ዘንድ በመፈለግ ገና በልጅነቱ ከአደገበት ሸለቆ እንዲወጣ ሆነ። አእምሮው በፍጥነት በማደጉ በማስተማሩ ረገድ የሚመጥኑት አስተማሪዎች የት ይገኛሉ የሚለው ጥያቄ ብዙም ሳይቆይ ብቅ አለ። በአሥራ ሶስት አመቱ በስዊዘርላንድ በስመጥርነቱ በዚያን ወቅት ተወዳዳሪ ወዳልነበረው ወደ በርን ሄደ። ሆኖም በዚህ ስፍራ የሕይወቱን ተስፋ የሚያጨልም አደጋ አጋጠመው። ወደ ገዳም ይሄድ ዘንድ ለማባበል የማያባራ የመነኩሴዎች ጥረት ተነጣጠረበት፤ የዶሚኒካንና የፍራንሲስካን መነኩሴዎች ሕዝባዊ ተቀባይነት ለማግኘት ይቀናቀኑ ነበር። የተንቆጠቆጡ የቤተ ክርስቲያናቸውን ጌጣጌጦች፣ የሥነ-ሥርዓታቸውን አንፀባራቂነት፣ የታሪካዊ ቅርሶቻቸውንና ተዓምር ሰሪ ስዕሎቻቸውን በማሳየት ይህንን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ለፉ። የበርን ዶሚኒካኖች [በቅዱስ ዶሚኒክ የተመሰረቱ የመነኩሴ ሰባኪዎች] ይህንን ተሰጥኦ ያለውን ወጣት ተማሪ የራሳቸው ማድረግ ከቻሉ ሀብትና ክብር ያለ ጥርጥር እንደሚጠብቃቸው ተመለከቱ። የእድሜ ለጋነቱ በፀሐፊነትና በተናጋሪነት ያለው ተፈጥሮአዊ ተሰጥኦው፣ የሙዚቃና የግጥም ልቀቱ፣ ከታይታና አጀባቸው ይልቅ ሰዎችን ወደ አገልግሎታቸው በመሳብና ገቢያቸውን በመጨመር ረገድ የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን አመኑበት። በማታለያና በሐሰት ሙገሳ ዝዊንግል የገዳማቸውን መነኮሳት እንዲቀላቀል ለማግባባት ጣሩ። ሉተር ተማሪ እያለ በመነኩሴ ጎጆ ውስጥ ራሱን ቀብሮ ነበር፤ የእግዚአብሔር አቅርቦት ባያወጣው ኖሮ በዓለም ጠፍቶ በቀረ ነበር። ተመሳሳይ አደጋ ውስጥ ይሆን ዘንድ ለዝዊንግል አልተፈቀደም። በአምላክ እርዳታ አባቱ ስለ መነኩሴዎቹ ዓላማ ቀድሞ መረጃ ደርሶት ነበር። የመነኩሴዎቹን የስንፍናና እርባና-ቢስ ሕይወት ልጁ እንዲመራ ለመፍቀድ ሃሳቡም አልነበረውም። የወደፊት ጠቀሜታው አደጋ ውስጥ እንደሆነ በመመልከት ሳይዘገይ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ልጁን አዘዘው። GCAmh 127.3

የአባቱ ትዕዛዝ አዎንታን አገኘ፤ ሆኖም ወጣቱ በተወለደበት ስፍራ ረክቶ ለረዥም ጊዜ መቆየት አልተቻለውምና ወደ ትምህርቱ በመመለስ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በባሰል ተቀመጠ። ዝዊንግል የእግዚአብሔር የነፃ ፀጋን ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው በዚህ ስፍራ ነበር። የጥንታዊ ቋንቋዎች መምህር የነበረው ዊተምባች የግሪክና የዕብራይስጥን ቋንቋዎች ሲመረምር ሳለ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመመራቱ በእርሱ አማካኝነት የመለኮታዊ ብርሐን ጮራ በተማሪዎቹ አዕምሮ ላይ ፈነጠቀ። መምህራንና ፈላስፋዎች ከሚያስተምሩት ፅንሰ-ሃሳብ የበለጠ መጠን የለሽ ዋጋ ያለው ጥንታዊ እውነት እንዳለ ተናገረ። ይህ ጥንታዊ እውነትም የክርስቶስ ሞት የኃጢአተኛው ብቸኛ ቤዛ (የተከፈለ ዋጋ) እንደሆነ የሚናገረው ነበር። እነዚህ ቃላት ለዝዊንግል፣ ጎህ እንደሚቀዱት እንደ መጀመሪያዎቹ የማለዳ የፀሐይ ጮራዎች ነበሩ። GCAmh 128.1

ወደ ተጠራበት የሕይዎቱ ሥራ ይገባ ዘንድ ብዙም ሳይቆይ ዝዊንግል ከባሰል ተጠራ። የመጀመሪያ የሥራ መስኩም ከተወለደበት ብዙም ያልራቀ በአልፓይን የሚገኝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነበር። በቄስነት ከተቀባ በኋላ “የክርስቶስ መንጋ አደራ የተሰጠው እርሱ” አለ አንድ አጋር የተሐድሶ አራማጅ “ምን ያህል ማወቅ እንዳለበት በውል ስለተረዳ ሕያው ነፍሱን ሙሉ በሙሉ መለኮታዊ እውነትን ለመመርመር አሳልፎ ሰጠ።”-Wylie, b. 8, ch. 5። መጽሐፍ ቅዱሳትን የበለጠ በመረመረ ቁጥር በእነርሱ እውነቶችና በሮም ኑፋቄዎች መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ ግልጽ እየሆነለት መጣ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል፣ በብቸኝነት ሙሉ እና ስህተት የሌለበት መርህ እንደሆነ ተቀበለ። መጽሐፍ ቅዱስ የራሱ [የመጽሐፍ ቅዱስ] አብራሪ መሆን እንዳለበት ተረዳ። ቀድሞ የነበረን ፅንሰ-ሃሳብ ወይም አስተምህሮ ለማጠናከር ሲል መጽሐፍ ቅዱስን ያብራራ ዘንድ መሞከር አልደፈረም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛና ግልፅ ትምህርት ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ምግባሩ አደረገው። ሙሉና ትክክለኛ ትርጓሜውን መረዳት ይችል ዘንድ ሊያግዘው የሚችለውን እርዳታ ሁሉ በመሻት በታማኝነትና በፀሎት ለሚለምኑ ሁሉ መገለጥን ይሰጣል ብሎ የተናገረለትን የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለመነ። GCAmh 128.2

“መጽሐፍ ቅዱሳት” አለ ዝዊንግል “የመጡት ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነው፣ የእግዚአብሔር ቃል …. ውጤት አልባ ሊሆን አይችልም፤ ብሩህ ነው፤ ራሱን ያስተምራል፣ ራሱን ይገልጻል። ነፍስ ራስዋን በመርሳት ብሎም ራስዋን አሳልፋ በመስጠት እግዚአብሔርን ትቀበል ዘንድ በእግዚአብሔር መጽናናት ያፅናናታል፣ ትሁት ያደርጋታል፣ በአርነትና በፀጋ ሁሉ ያፈካታል።” ለእነዚህ ቃላት እውነትነት ራሱ ዝዊንግል ምስክር ነበር። በዚህ ጊዜ ስለነበረው ልምምድ ሲጽፍ፦ “ለመጽሐፍ ቅዱሳት ሙሉ ለሙሉ ራሴን አሳልፌ ስሰጥ ፍልስፍናና የስነ-መለኮት ትምህርት (በመደበኛ ትምህርት የሚሰጠው) ሁሌም ተቃራኒ ነገር ይሰነዝሩብኝ ነበር። በመጨረሻም ‘ሌላውን ሁሉ ትተህ የእግዚአብሔርን ማንነት ራሱ ከተናገረው ቀላል (ያልተወሳሰበ) ቃል ተማር’ የሚለውን አባባል አጤንኩ ከዚያም እግዚአብሔር ብርሐን እንዲሰጠኝ መለመን ጀመርኩ፣ መጽሐፍ ቅዱሳትም እየቀለሉኝ መጡ።” GCAmh 129.1

ዝዊንግል ያስተምረው የነበረው አስተምህሮ ከሉተር የተወሰደ አልነበረም፤ የክርስቶስ አስተምህሮ ነበር። “ሉተር ክርስቶስን የሚሰብክ ከሆነ” አለ የስዊሱ ተሐድሶ አራማጅ፣ “እኔ የምሰራውን ይሰራል ማለት ነው። ከእኔ ይልቅ ብዙ ነፍሳትን ወደ ክርስቶስ መርቷል፤ እንደዚያው ይሁን። ነገር ግን ወታደሩ ከሆንኩለት፣ እርሱም ብቸኛ አለቃዬ ከሆነው ከክርስቶስ ስም በቀር ሌላ እሸከም ዘንድ አይቻለኝም። በእኔ ወደ ሉተር የተጻፈ በሉተርም ወደ እኔ የመጣ አንድ መስመር ጽሁፍ እንኳ የለም። ለምንድን ነው? እኛ እርስ በርሳችን ፈጽሞ ተነጋግረን የማናውቀው በየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ እጅግ እንስማማለን፤ ይህም የእግዚአብሔር መንፈስ ምስክርነት ወጥ መሆኑ ለሁሉም ይታወቅ ዘንድ ነው።”-D’Aubigné, b. 8, ch. 9። GCAmh 129.2

በ1516 ዓ.ም ኢንሲደልን በሚገኘው የመነኮሳት መኖሪያ ሰባኪ ይሆን ዘንድ ዝዊንግል ተጋበዘ። በዚህ ስፍራ የሮምን ብልሹነት በቅርበት ይመለከት ዘንድ፣ እንደ ተሐድሶ አራማጅነቱም ከአገሩ ከአልፕስ አልፎ የሚታወቅ ተጽዕኖ ያደርግ ዘንድ ነበረው። በኢንሲደልን ከነበሩ፣ ከሚጎበኙ ስፍራዎች አንዱ ተዓምር የመሥራት ኃይል አለው የሚባልለት የድንግል ምስል ነበር። በመግቢያው ዋና በር ላይ “እዚህ ሙሉ የኃጢአት ይቅርታ ይገኛል” ይል ነበር። የኃይማኖት ጎብኚዎች በሁሉም ወራት ወደዚህ ቅዱስ የድንግል ስፍራ ይመጡ ነበር። በታላቁ ዓመታዊ የቅዳሴ በዓል ደግሞ ሰዎች ከመላው ስዊዘርላንድ፣ ከፈረንሳይና ከጀርመን አገራት ሳይቀር ይመጡ ነበር። በትዕይንቱ እጅግ በማዘን ዝዊንግል አጋጣሚውን ተጠቅሞ የአጉል አምልኮ ባሪያ ለሆኑት በወንጌሉ የሚገኘውን አርነት አወጀላቸው። GCAmh 129.3

“ሌሎቹ ፍጥረታት ካሉበት ስፍራ ይልቅ እግዚአብሔር በዚህ ቤተ መቅደስ ይገኛል ብላችሁ” አለ “ልታስቡ አይገባም። በየትኛውም ስፍራ መኖሪያችሁን የወሰነላችሁ ብትሆኑ እግዚአብሔር ይከባችኋል፤ ይሰማችኋልም … ትርፍ በሌለው ሥራ፣ በአድካሚ የኃይማኖት ጉዞ፣ በስጦታዎች፣ ለድንግል እና ለቅዱሳን በሚቀርብ ፀሎት ውስጥ ምን ኃይል አለና ነው የእግዚአብሔር ሞገስ የሚያስገኝላችሁ? በፀሎት ቃላትን ማብዛት ምን ይጠቅማል? በቆብ ወይም በመላጣ ዘውድ፣ በወርቅ ባጌጡና በተንዘረፈፉ የቀሳውስት አልባሳት ዘንድ ምን ውጤታማነት አለ? እግዚአብሔር የሚያየው ልባችን ነው - ልባችንም ከእግዚአብሔር እጅግ የራቀ ነው። “ክርስቶስ” አለ “አንድ ጊዜ ለሁሉም በመስቀል ላይ የተሰዋ፣ እርሱን ለሚያምኑ ኃጥአን ሁሉ፣ ለዘላለም የሚበቃ መስዋዕትና ተጠቂ ነው።”-Ibid., b. 8, ch. 9። GCAmh 129.4

ለብዙሃኑ አድማጮች እነዚህ ትምህርቶች ተቀባይነት ያገኙ አልነበሩም። እጅግ አድካሚው ጉዟቸውን በከንቱ እንዳደረጉት ሲነገራቸው መራራ የሆነ ሃዘን ተሰማቸው። በክርስቶስ የሚያገኙትን የነፃ የኃጢአት ይቅርታ ሊረዱት አልቻሉም። ሮም በቀየሰችላቸው ወደ ሰማይ በሚወስደው የቀድሞ መንገድ ረክተው ነበር። የተሻለ ነገር ከመፈለግ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው ግራ መጋባት ራሳቸውን ሰበሰቡ። የልብን ንጽህና ከመፈለግ ይልቅ የመዳናቸውን ጉዳይ ለቀሳውስቱና ለሊቀ-ጳጳሱ አደራ መተው ለእነርሱ ቀላል ነበር። GCAmh 130.1

ሆኖም ሌላው መደብ በክርስቶስ የሚገኘውን የድነት የምሥራች በደስታ ተቀበለው። በሮም የተቀመጡት ስነ ስርዓቶች ለነፍስ ሰላም ያመጡ ዘንድ ተስኖአቸው ነበርና የአዳኙን ደም በዋስትናነት በእምነት ተቀበሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያገኙትን ወርቃማ ብርሐን ለሌሎች ያካፍሉ ጀመር። እውነቱ ከሰፈር ሰፈር፣ ከከተማ ወደ ከተማ እየተስፋፋ ሲሄድ ወደ ድንግሏ ቅዱስ ስፍራ የሚመጡት የሐይማኖች ጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ መጣ። የሚሰጡ ስጦታዎች እየቀነሱ ሄዱ፣ ከስጦታዎቹ ተቀንሶ የሚከፈለው የዝዊንግል ደሞዝም እንዲሁ ቀነሰ። ነገር ግን የወግ አጥባቂነትና የአጉል አምልኮ ኃይል ሲንኮታኮት ማየቱ ደስታ እንጂ ሌላ ሊፈጥርበት አልቻለም። GCAmh 130.2

የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለስልጣናት ዝዊንግል እያከናወነ ስለነበረው ተግባር እውቀት የሌላቸው አልነበሩም። ወዲያው ጣልቃ መግባት ግን አልፈለጉም። ዓላማቸውን ይደግፍላቸው ዘንድ ተስፋ በማድረግ አሁንም ይደልሉት ጀመር። እነርሱ ይህንን ጥረት ሲያደርጉ ሳለ እውነቱ በሕዝቡ ልብ ስር እየሰደደ ነበር። GCAmh 130.3

በኢንሲየደልን ሲያከናውነው የነበረው ተግባር ዝዊንግልን በቅርቡ ወደሚገባበት ሰፊ የሥራ መስክ አዘጋጀው። በዚህ ስፍራ ለሶስት ዓመት ከቆየ በኋላ በዙሪክ ወደሚገኘው ካቴድራል የሰባኪነት ቦታ ተጠራ። በዚያን ጊዜ ዙሪክ የስዊዝ ህብረት ቀዳሚ ከተማ ነበረች፣ በመሆኑም በዚህ ስፍራ የሚመነጨው ተጽእኖ ዳርቻው ሰፊ ነበር። ወደ ዙሪክ ጋብዘው ያመጡት የቤተ-ክህነት መሪዎች ግን አዳዲስ ሃሳቦችን ለመግታት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ማከናወን ያለበትን ኃላፊነቶች ከመዘርዘር ወደ ኋላ አላሉም። GCAmh 130.4

“ጥቃቅንዋን ነገር እንኳ ሳይቀር ሳትንቅ በጣም ተጠንቅቀህ” አሉ “የዚህን ቅርንጫፍ ገቢ ትሰበስባለህ። መክፈል የሚገባቸውንና አሥራትን እንዲከፍሉ በመድረክና በኑዛዜ ክፍሉ አማኞችን አጥብቀህ ታሳስባለህ፤ በስጦታቸውም ለቤተ ክርስቲያንዋ ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲመሰክሩ ታደፋፍራለህ። ከህሙማን፣ ከጉባኤዎችና አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ከሚፈፀሙ ስነ-ስርዓቶች ገቢን ለመጨመር በጥንቃቄ ትሰራለህ።” “ሐይማኖታዊ በዓላትን በማስተዳደር፣ ስብከትንና ምዕመናንን በመንከባከብ ረገድ” አሉ አዛዦቹ “እነዚህም የቄሱ ሃላፊነቶች ናቸው። ሆኖም እነዚህን ጉዳዮች ለማከናወን፣ በተለይም ደግሞ ለስብከት፣ አንተን ወክሎ በምትክ የሚሰራ ቄስ መቅጠር ትችላለህ። በእነዚህ ስነ-ስርዓቶች ላይ አገልግሎት የምትሰጠው ለተከበሩ ሰዎች ብቻ ነው፤ በተለይም በምትፈለግ ጊዜ ብቻ፤ እነዚህን ስነ-ስርዓቶች ሳትመርጥ ለሁሉም መደቦች ማድረግ አይፈቀድልህም።”-Ibid., b. 8, ch. 6። GCAmh 130.5

ዝዊንግል ይህንን ትዕዛዝ በዝምታ ካዳመጠ በኋላ ወደዚህ አስፈላጊ ስፍራ ሄዶ እንዲሰራ በመጋበዙ ለተቸረው ክብር አመስግኖ የሚከተለውን መንገድ ማብራራት ቀጠለ። “የክርስቶስ ታሪክ” አለ “ለብዙ ዘመን ከሕዝቡ ተደብቆ ኖሯል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ ብቻ በመውሰድ ጥልቀቱን ሁሉ በመግለጽ አንዱን ጽሁፍ ከሌላው ጽሁፍ ጋር በማወዳደር የማቴዎስን ወንጌል በሙሉ ለማስተማር ወስኛለሁ። የመንፈስ ቅዱስ ሃሳብ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይፈቀድልኝ ዘንድም ልባዊና የማያቋርጥ ፀሎት አደርጋለሁ። አገልግሎቴን ልቀድስ የምፈልገው ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለአንድያ ልጁ ውዳሴ፣ ለነፍሳት መዳንና በእውነተኛው እምነት ይሆኑ ዘንድ ምሪት መስጠት ይሆናል።”-Ibid., b. 8, ch. 6። አንዳንድ የቤተ-ክህነት ሰዎች እቅዱን ባያፀድቁለትም፣ ብሎም ሃሳቡን እንዲተው ቢያግባቡትም ዝዊንግል ግን ንቅንቅ አላለላቸውም ። በጥንት ዘመን፣ ንጽህና በነበረበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ስትከተለው የነበረውን አካሄድ ከመከተል በቀር አዲስ አሰራር ሥራ ላይ እንደማያውል ተናገረ። GCAmh 130.6

ከአስተማራቸው እውነቶች የተነሳ ፍላጎቶች ማንሰራራት ጀምረው ነበር፤ አስተምህሮውንም ለመስማት ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ይጎርፍ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም መከታተል ካቋረጡ ብዙ ጊዜ የሆናቸው በርካታ ሰዎች ወደርሱ ከሚመጡት መካከል ነበሩ። አገልግሎቱን በወንጌላቱ ጀመረ፤ ስለሕይወቱ አስተምህሮውና ሞቱ የሚገልጹትን የክርስቶስ ታሪኮች ለአድማጮቹ ያነብና ያብራራ ነበር። በኢንሲየደልን እንዳደረገው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ሊሳሳት የማይችል ስልጣን እንደሆነ፣ የክርስቶስ ሞትም ብቸኛው ሙሉ መስዋዕትነት እንደሆነ አስተማረ። “ልመራችሁ የምፈልገው” አለ “ወደ ክርስቶስ ነው። የድነት እውነተኛ ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ።”-Ibid., b. 8, ch. 6። ከመንግሥት መሪዎችና ከተማሩ ሰዎች ጀምሮ እስከ የእጅ ባለሙያዎችና ጭሰኞች ድረስ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የመጡ ሰዎች በሰባኪው ዙሪያ ተሰብስበው ነበር። ቃላቶቹን በጥልቅ ፍላጎት ያዳምጡ ነበር። የነፃ ድነት ስጦታውን ማወጅ ብቻ ሳይሆን የጊዜውን ክፋትና ብልሹነት ያለ አንዳች ፍርሃት ይነቅፍ ነበር። ብዙዎቹ ከቤተ-መቅደሱ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይመለሱ ነበር። “ይህ ሰው” አሉ፦ “የእውነት ሰባኪ ነው። የኛ ሙሴ ይሆናል። ከዚህ የግብፅ ጽልመትም አውጥቶ ይመራናል።”-Ibid., b. 8, ch. 6። GCAmh 131.1

ጥረቶቹ በመጀመሪያ በከፍተኛ ፍላጎት ተቀባይነት ቢያገኙም እየቆየ ግን ተቃውሞ መቀስቀሱ አልቀረም። ሥራውን ለማደናቀፍ ትምህርቱንም ለማውገዝ መነኮሳቱ ቆርጠው ተነሱ። ብዙዎች በሹፈትና በፌዝ ያላግጡበት ጀመር። ሌሎች ደግሞ ወደ ክብርን የሚነካ ንግግርና ማስፈራራት ዞሩ። ዝዊንግል ግን “ለክርስቶስ ነፍሳትን የምንማርክ ከሆነ በመንገዳችን ላይ ለሚገጥሙን ብዙ ነገሮች ዓይናችንን መክደን አለብን” በማለት ሁሉንም ነገር በትዕግስት ይሸከም ነበር።-Ibid., b. 8, ch. 6። GCAmh 131.2

በዚህ ጊዜ ገደማ አዲስ ወኪል የተሐድሶውን ሥራ ወደፊት ለማራመድ ሥራውን ጀመረ። በባሰል ያለው የተሐድሶ እምነት ወዳጅ በሆነ ሰው አማካኝነት አንድ ሉሲያዊ የሉተርን ጽሁፎች ይዞ ወደ ዙሪክ ተላከ። የላከው ሰው የእነዚህ መጻሕፍት መሸጥ ብርሐንን ለማስፋፋት ጠንካራ መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ለዝዊንግል ሲጽፍም “ይህ ሉሲያዊ (Lucian) በቂ የመወሰን ችሎታና የንግግር ብቃት እንዳለው አረጋግጥ። እነዚህ ባህርያት ያሉት ከመሰለ ከትልቅ ከተማ ወደ ትልቅ ከተማ፣ ከመለስተኛ ከተማ ወደ መለስተኛ ከተማ፣ ከመንደር መንደር፣ እንዲያውም ቤት ለቤት በመላው ስዊዘርላንድ የሉተርን ጽሁፎች በተለይም ለምዕመናን የተፃፈውን የጌታን ፀሎት የሚያብራራውን ይዞ ይዙር። የበለጠ ሲታወቅ፣ ብዙ ገዥዎች ያገኛል።” አለ።-Ibid., b. 8, ch. 6። በዚህም ሁኔታ ብርሐን መግቢያ ቀዳዳ አገኘ። GCAmh 131.3

እግዚአብሔር የድንቁርናንና የአጉል አምልኮን ሰንሰለት ለመበጠስ በሚዘጋጅበት ጊዜ ሰይጣን በታላቅ ኃይል በመሥራት ሰዎችን በጽልመት በመሸፈን የእግር ብረታቸውን የበለጠ ያጠብቅባቸዋል። ሰዎች በተለያዩ ሃገራት እየተነሱ ይቅርታንና ጽድቅን በክርስቶስ ደም በኩል ለሕዝብ ሲያቀርቡ፣ ሮም በታደሰ ጉልበት ተነስታ ይቅርታን በገንዘብ የመሸጥ ገበያዋን በክርስቲያኑ ዓለም የመክፈት ተግባርዋን በስፋት ተያያዘችው። GCAmh 132.1

እያንዳንዱ ኃጢአት ዋጋ ተተምኖለት ነበር፤ የቤተ ክርስቲያን ግምጃ ቤት ጢም ብሎ እስከሞላ ድረስ ሰዎች ወንጀል የመፈጸም ነጻነት ተሰጥቷቸው ነበር። እንዲህም ሁለቱ ንቅናቄዎች መስፋፋት ቀጠሉ፦ አንደኛው የኃጢአት ይቅርታን በገንዘብ አማካኝነት ሲያቀርብ ሌላኛው ደግሞ ይቅርታን በክርስቶስ በኩል አቀረበ። ሮም ለኃጢአት ፈቃድ ሰጥታ የገቢ ምንጭዋ ምክንያት ስታደርገው፣ የተሐድሶ አራማጆቹ ደግሞ ኃጢአትን በማውገዝ ክርስቶስ ማስተሰሪያና ነፃ አውጪ እንደሆነ በመስበክ ወደ እርሱ ይጠቁሙ ነበር። GCAmh 132.2

በጀርመን አገር ስርየት የመሸጥ ሃላፊነቱ ለዶሚኒካኖች መነኮሳት ተሰጥቶ የሚካሄደውም አስከፊ ስም ባለው ቴትዘል ነበር። በስዊዘርላንድ ደግሞ ግብይቱ ለፍራንሲስካውያን እጅ ተላልፎ የሚቆጣጠረውም የኢጣልያው መነኩሴ ሳምፕሶን ነበር። ከጀርመንና ከስዊዘርላንድ ከፍተኛ ገቢ በማስገባትና የጳጳሳዊውን ግምጃ ቤት በመሙላት ሳምፕሶን ቀደም ብሎም ለቤተ ክርስቲያንዋ ሰናይ አገልግሎት ያበረከተ ሰው ነበር። አሁን ደግሞ በስዊዘርላንድ እየተዘዋወረ ብዙ ሕዝብን በመሳብ ያላቸውን ጭላጭ ገቢ በመውሰድ ድኃ ጭሰኞችን ሲበዘብዝ ከሃብታም መደቦች ደግሞ ብዙ ስጦታ ይጠይቅ ነበር። ሆኖም ግብይቱን ሙሉ በሙሉ ባያቆመውም የተሐድሶው ተጽዕኖ [ሥራውን] በመገደቡ በኩል ያለው ሚና ታውቆ ነበር። ሳምፕሶን ወደ ስዊዘርላንድ እንደገባ የሽያጭ ቁሳቁሱን ይዞ በአቅራቢያው በምትገኝ ከተማ ሲደርስ ዝዊንግል እዛው በኢንሲየደልን ነበር። የተልዕኮው መረጃ ስለደረሰው የተሐድሶ አራማጁ ይቃወም ዘንድ ወዲያውኑ ወደ ስፍራው ሄደ። ሁለቱ በአካል ባይገናኙም የመነኩሴውን አስመሳይነት በማጋለጥ ዝዊንግል ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ የነበረበትን ስፍራ ለቆ ወደ ሌላ ለመሄድ ተገድዶ ነበር። GCAmh 132.3

በዙሪክ ዝዊንግል ይቅርታ(ስርየት) ለፋፊዎችን በመቃወም ከልቡ ይሰብክ ነበር፤ ሳምፕሶን በስፍራው ሲደርስም ከጉባኤው የተላከ አንድ ሰው ወደርሱ በመቅረብ አልፎ ይሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አይነት ያለ መልእክት ነገረው። በመጨረሻም ማታለያ ተጠቅሞ መግባት ቢችልም አንድም የኃጢአት ይቅርታ ሽያጭ ሳያከናውን ተባረረ፤ ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ስዊዘርላንድን ለቆ ሄደ። GCAmh 132.4

በመላው ስዊዘርላንድ በ1519 ዓ.ም የመጣው “ታላቁ ሞት” ተብሎ የተጠራው ወረርሽኝ ለተሐድሶው ጠንካራ ጉልበት ሆነው። ሰዎች ከዚህ አጥፊ ጋር ፊት ለፊት በተፋጠጡ ጊዜ በቅርቡ የገዙት የኃጢአት ማስተሰርያ ምን ያህል ጥቅመ-ቢስና ከንቱ እንደሆነ ተረዱት፤ ለእምነታቸው የተሻለ፣ እርግጠኛ የሆነ መሰረትም ይመኙ ጀመር። በዙሪክ የነበረው ዝዊንግል ክፉኛ ታመመ። እጅግ ከመድከሙ የተነሳ ይሻለዋል የሚል ተስፋ ሁሉ ተሟጦ እንዲያውም ሞቷል የሚለው ወሬ በስፋት ይናፈስ ነበር። በዚያ ፈታኝ ሰዓት ተስፋውና ጥንካሬው አልተነቃነቀም ነበር። ለኃጢአት ስርየት ሙሉ በሙሉ በቂ በሆነው ተማምኖ በእምነት ወደ ቀራንዮ መስቀል ተመለከተ። ከሞት አፋፍ ደርሶ ሲመለስ ከምን ጊዜውም በበለጠ ተነሳሽነት ወንጌሉን ሊሰብክ ነበረው፤ ንግግሩ የተለየ ኃይል ነበረው። ከመቃብር አፋፍ የተመለሰውን ተወዳጁን ፓስተራቸውን ሕዝቡ በደስታ ተቀበሉት። እነርሱም ራሳቸው የመጡት በጣዕረ-ሞት ያሉትን ሲደርሱ፣ ህሙማኑን ሲጠይቁ ቆይተው ነበርና ከምን ጊዜውም በላይ የወንጌሉ ዋጋ ተሰማቸው። GCAmh 132.5

ዝዊንግል [የወንጌሉን] እውነቶቹን በተሻለ ጥራት ወደ መረዳት ደርሶ አዳሽ ሃይሉን በራሱ ላይ በበለጠ ሙላት ተለማምዶት ነበር። የሰው ውድቀትና የድነት እቅድ ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ነበሩ። “በአዳም ውስጥ” አለ ሲናገር “ሁላችንም የሞትን ነን፣ በኃጢአትና በኩነኔ የዘቀጥን።”-Wylie, b. 8, ch. 9። “ክርስቶስ ግን ዘላለማዊ ነፃነትን(ድነትን) ገዝቶልናል።” “ፍላጎቱ ሁሉ ዘላለማዊ መስዋትነት ነው፤ ዘላለማዊ ውጤትም ያለው ነው። በጠንካራና በማይነቃነቅ እምነት ለሚደግፉት ሁሉ በምትካቸው መለኮታዊ ፍርድን ለዘላለም የሚያሟላ ነው።” ሰዎች በክርስቶስ ፀጋ ስር ከመሆናቸው የተነሳ፣ ኃጢአት በቀጣይነት ለመሥራት ነፃ አይደሉም [በፀጋው ስር መሆን ኃጢአት መሥራትን ለመቀጠል ነፃነት አይሰጥም] የሚለውን ትምህርት ግን በግልፅ አስተምሯል ። “በእግዚአብሔር ላይ እምነት ባለበት ሁሉ በዚያ እግዚአብሔር ራሱ ይኖራል፤ እግዚአብሔር ባለበት ደግሞ ወደ መልካም ሥራ ሰዎችን የሚገፋፋና የሚያደፋፍር ፍላጎት ይመነጫል።”አለ።-D’Aubigné, b. 8, ch. 9። GCAmh 133.1

የዝዊንግል ትምህርት ከመወደዱ የተነሳ ሊሰሙት የሚመጡ ሰዎች ቤተ-መቅደሱን ሞልተው ይተርፉ ነበር። እንደሚችሉት መጠን በጥቂት በጥቂቱ እያደረገ ለሚያዳምጡት እውነቱን ከፈተላቸው። በመጀመሪያ የሚያስደነግጡ ነጥቦችን አቅርቦ ሚዛናዊ ያልሆነ ስሜትን እንዲያጎለብቱ እንዳይገፋፋቸው በማሰብ በጥንቃቄ ያስተምር ነበር። የመጀመሪያ ተግባሩ የሰዎችን ልብ ወደ ክርስቶስ በመሳብ በፍቅሩ አለዝቦ ምሳሌነቱን በፊታቸው ማቅረብ ነበር፤ የወንጌሉን መርሆዎች ሲቀበሉ አጉል እምነታቸውና ልምምዶቻቸው ያለ ጥርጥር ይገረሰሳል። GCAmh 133.2

በዙሪክ የነበረው ተሐድሶ ደረጃ በደረጃ እድገት ያሳይ ጀመር። አደጋውን በማስተዋልም የተሐድሶው ጠላቶች ለንቁ ተቃውሞ ተነሳሱ። አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር የዊተንበርጉ መነኩሴ ለሊቀ-ጳጳሱና ለንጉሠ ነገሥቱ በዎርምስ “እምቢ” ያለው፤ አሁን ደግሞ በዙሪክ የሊቀ-ጳጳሱን መጠይቆች በመቃወም ተመሳሳይ ትዕይንት በሙሉ የሚደገም መሰለ። በዝዊንግል ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈፀሙ። የጳጳሳዊ ሥርዓት ባለባቸው ክፍለ ሃገሮች የወንጌሉ ደቀ-መዛሙርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ማቃጠያ ስፍራ ይወሰዱ ነበር፤ ይህ ግን በቂ አልሆነም፤ የኑፋቄ ትምህርት አስተማሪው ዝም መሰኘት አለበት። በመሆኑም የኮንስታንስ ጳጳስ ሶስት ምክትሎቹን ወደ ዙሪክ ጉባኤ በመላክ ዝዊንግል ሰዎች የቤተ ክርስቲያንዋን ሕግጋት እንዲጥሱ በማስተማር የህብረተሰቡን ሰላምና አደረጃጀት አደጋ ላይ የሚጥል ትምህርት ያስተምራል በማለት ከሰሰው። የቤተ ክርስቲያንዋ ስልጣን ወደ ጎን ከተተወ ዓለምአቀፋዊ ብጥብጥ እንደሚከሰት ተናገረ። ዝዊንግል ሲመልስ ላለፉት አራት ዓመታት ሲያስተምር እንደነበርና ዙሪክ “በህብረቱ ካሉ ከተሞች ሁሉ ፀጥታና ሰላም የሰፈነባት” እንደሆነች ተናገረ። “ታዲያ እንዲህ ከሆነ” አለ ሲናገር “ለአጠቃላይ ፀጥታ ክርስትና አይነተኛ መፍትሄ አይደለምን?”-Wylie, b. 8, ch. 11። GCAmh 133.3

ምክትሎቹ፣ አማካሪዎቹ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ድነት እንደሌለ የሚያስተምሩትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አጥብቀው አስጠንቅቀዋቸው ነበር። ዝዊንግል ሲመልስ፦ “ይህ ሁኔታ ሊያናውጣችሁ አይገባም። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሰረት በእምነት ስለእርሱ ስለመሰከረ፣ ጴጥሮስ ብሎ ስም የሰጠው፣ ያው ክርስቶስ፣ ቋጥኙ ራሱ ነው። በሁሉም አገር በጌታ የሱስ ማንም በሙሉ ልቡ ቢያምን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው። ከእርስዋ ውጪ ማንም ሊድን የማይችልበት ቤተ ክርስቲያን በእውነት ይህች ናት።”-Aubigné, London ed., b. 8, ch. 11። በኃይማኖት ስብሰባው (በኮንፈረንሱ) ምክንያት ከጳጳሱ ምክትሎች አንዱ የታደሰችውን ቤተ ክርስቲያን እምነት ተቀበለ። GCAmh 134.1

መማክርቱ በዝዊንግል ላይ እርምጃ መውሰድ እምቢ ስላለ ሮም ለአዲስ ጥቃት ተዘጋጀች። የተሐድሶ አራማጁ ጠላቶች እየጠነሰሱበት ያለውን ሴራ ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ይምጣ፣ የምፈራቸው ከላይ ያንዣበበው ገደል በስሩ የሚያጓራውን ማዕበል የሚፈራውን ያህል ነው።”-Wylie, b. 8, ch. 11። ይህንን ተልዕኮ ለማጥፋት የቤተ-ክህነት ሰዎች ጥረት ማከናወን የቻለው የበለጠ እንዲስፋፋ ማድረግ ብቻ ነበር። እውነት መስፋፋቱን ቀጠለ። በሉተር መሰወር ቀዝቅዘው የነበሩት የጀርመን የወንጌሉ አጋሮችም በስዊዘርላንድ ያሳየውን እመርታ በመመልከት እንደገና ተበራቱ። GCAmh 134.2

ተሐድሶው በዙሪክ ስር ሲሰድ ፍሬዎቹ በተለይ ብልሹ ስነ-ምግባርን በመጨቆን፣ ሥርዓትንና ስምምነትን በማስፋፋት ጎልተው ይታዩ ጀመር፤ “ሰላም መኖሪያዋ በእኛ ከተማ ነው” አለ ዝዊንግል ሲጽፍ፤ “ጥል የለም፣ አስመሳይነት የለም፣ ምኞት የለም፣ ብጥብጥ የለም። እንደዚህ ያለ ህብረት ከጌታ ካልሆነ፣ በሰላምና በቅድስና ፍሬዎች ከሚሞላን ከአስተምህሮአችን ካልሆነ ከየት ይመጣል?”-Ibid., b. 8, ch. 15። GCAmh 134.3

በተሐድሶው የተገኙት ድሎች ሮማውያኑን በማነሳሳት ያጠፉት ዘንድ ቆራጥ ጥረት እንዲያደርጉ ገፋፋቸው። የሉተር ሥራ እንዳይሰራጭ በመገደብ ረገድ የማሳደዱ ተግባር በጀርመን አገር ምን ያህል እዚህ ግባ የማይባል ውጤት እንዳስገኘ በመገንዘብ ተሐድሶውን በራሱ መሳሪያ ሊገናኙት ወሰኑ። ከዝዊንግል ጋር ክርክር አስነስተው፣ ነገሮችን አስተካክለው፣ የጦር ቀጠናው ስፍራ የራሳቸው እንደ ሆነ ከመናገር አልፈው በተከራካሪዎች መካከል በፈራጅነት የሚቀመጡትንም ራሳቸው እንዲመርጡ በማድረግ እርግጠኛ ባለድሎች ለመሆን ተንቀሳቀሱ። ዝዊንግልን አንድ ጊዜ ወደ መዳፋቸው ካስገቡ በኋላ እንዳያመልጣቸው በጥንቃቄ ይተገብራሉ። መሪው ዝም ከተሰኘ የተሐድሶው እንቅስቃሴም በፍጥነት ያከትማል። ሆኖም ይህ ዓላማቸው በጥንቃቄ ተደብቆ ነበር። GCAmh 134.4

ክርክሩ በባደን እንዲሆን ተወሰነ፤ ዝዊንግል ግን በዚያ አልተገኘም። የዙሪክ ጉባኤ የጳጳሳውያኑን እቅድ በመጠራጠር፣ እንዲሁም ለወንጌሉ የሚመሰክሩትን ለማቃጠል በጳጳሳውያኑ ክፍለ ሃገራት የሚንቀለቀለውን የእሳት መዓት ተመልክተው ጥንቃቄ በመውሰድ ወደዚያ ስፍራ በመሄድ ፓስተራቸው ራሱን ለአደጋ እንዲያጋልጥ አልፈቀዱለትም። በዙሪክ ሮም ልትልክ የምትችለውን ማንኛውንም አቀንቃኝ ለመገናኘት ፈቃደኛ ነበር፤ የሰማዕታት ደም እየፈሰሰበት ወዳለው ወደ ባደን መሄድ ማለት ግን ወደ እርግጥ ሞት ማምራት ማለት ነበር። ኦይኮላምፓዲየስና ሃለር የተሐድሶ አራማጆቹን ሲወክሉ ታዋቂው ዶክተር ኤክ የተማሩ ዶክተሮችንና የኃይማኖት መሪዎችን ከጎኑ አሰልፎ የሮም ልዑካን መሪ ነበር። GCAmh 134.5

ዝዊንግል በኮንፍራንሱ ባይገኝም ተጽዕኖው ግን ይታይ ነበር። ፀሐፊዎቹ በሙሉ በጳጳሳዊያኑ የተመረጡ ሆነው ሌሎች ደግሞ ምንም ማስታወሻ እንዳይዙ በሞት ማስፈራሪያ ተከልክለው ነበር። ይህም ሁሉ ሆኖ በባደን የተባለው እያንዳንዱ ነገር በታማኝነት ምንም ሳይቀር በየቀኑ ለዝዊንግል ይደርስ ነበር። በክርክሩ ላይ ይሳተፍ የነበረ አንድ ተማሪ በቀን ሲቀርብ የዋለውን ንግግር ማታ ማታ ይመዘግበው ነበር እነዚህን ወረቀቶችና የኦይኮላምፓዲየስን ደብዳቤ ሁለት ተማሪዎች በዙሪክ ወደነበረው ዝዊንግል ያደርሱት ነበር። የተሐድሶ አራማጁም አስተያየትና ምክር ይሰጥ ነበር። ደብዳቤዎቹን በሌሊት ጽፎ ተማሪዎች ጧት ወደ ባደን ይዘዋቸው ይመለሱ ነበር። በከተማዋ በሮች የሚቆሙትን ዘበኞች ሳይታወቁ ለማለፍ መልክተኞቹ የዶሮ ውጤቶችን በቅርጫት ይዘው፣ በጭንቅላታቸው ተሸክመው በመሄድ ያለ ምንም ማንገራገር እንዲያልፉ ይፈቀድላቸው ነበር። GCAmh 135.1

እንደዚህም በማድረግ ዝዊንግል ከሸፍጠኛ ባላጋራዎቹ ጋር የነበረውን ትግል ማስቀጠል ቻለ። “ስለ ክርክሩ በአንክሮ በማሰብ በመከታተልና ምክሩን ወደ ባደን በማስተላለፍ” አለ ማይኮኒየስ “በጠላቶቹ መካከል ሆኖ ቢከራከር ኑሮ ከሚያከናውነው በላይ ሰርቷል።”-D’Aubigné, b. 11, ch. 13። GCAmh 135.2

ሮማውያኑ ወደ ባደን የመጡት እንደሚያሸንፉ ጠብቀው፣ ባሸበረቁ ልብሶቻቸው ተውበውና በአንፀባራቂ ጌጣጌጦቻቸው አምረው ነበር። ገበታዎቻቸው በውድ ምግብና ተመራጭ የወይን ጠጅ ሞልተው ይቀናጡ ነበር። የተሸከሙት ሐይማኖታዊ ሃላፊነት በድግሱ በመጠጡና በጭፈራው ይቃለልባቸው ነበር። በተቃራኒው፣ በሚስተዋል ልዩነት የተሐድሶ አራማጆቹ በሕዝቡ ዘንድ ሲታዩ፣ ከለማኞች ስብስብ ብዙም ያልተሻሉ በቁጠባ ያገኟትን በልተው፣ ብዙም ሳይቆዩ ከገበታቸው በቶሎ የሚነሱ ነበሩ። የኦይኮላምፓዲየስ አከራይ እርሱ በክፍሉ የሚያደርገውን ሲከታተል፣ ሲፀልይ ወይም ሲያጠና ሁል ጊዜ ያየው ነበርና በጣም ተገርሞ ሁኔታውን ሲያስተላልፍ “መናፍቁ ቢያንስ በጣም መንፈሳዊ ነበር” ብሏል። GCAmh 135.3

በኮንፍራንሱ “ኤክ በኩራት ተወጥሮ በተንቆጠቆጠ ልብስ ሆኖ ወደ ፑልፒት ወጥቶ ሳለ ትሁቱ ኦይኮላምፓዲየስ ተራ ልብስ ለብሶ እንደነገሩ በተሰራ መቀመጫ ከባለጋራው ተቃራኒ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር።”-Ibid., b. 11, ch. 13። የኤክ የሚያንባርቅ ድምጽና መጠን የለሽ ልበ ሙሉነት ፈጽሞ አልተለየውም ነበር። ከፍተኛ ተነሳሽነቱ ወርቅና ታዋቂነትን አገኛለሁ የሚለውን ተስፋ ያነገበ ነበር፤ ምክንያቱም የዚህ የእምነት ተቆርቋሪ ጠቀም ባለ ክፍያ ሊካስ ነበርና ነው። ያዋጡኛል የሚላቸው መከራከሪያዎች ውጤት ሳያመጡ ሲቀሩ ወደ ስድብና ወደ መሃላ ጭምር ይዞራል። GCAmh 135.4

ጭምቱና አንገቱን ደፊው ኦይኮላምፓዲየስ ግብግቡ አሸማቆት “ከእግዚአብሔር ቃል በቀር ለሌላ የፍርድ ሕግ እውቅና አልሰጥም”-Ibid., b. 11, ch. 13። በማለት ክርክሩን ተቀላቀለ። ለስላሳና ትሁት፣ አክብሮት የተጎናፀፈ ቢሆንም ከአቋሙ ንቅንቅ የማይል መሆኑን በተግባር አሳየ። ሮማውያኑ እንደተለመደው የቤተ ክርስቲያንዋን የተለያዩ ወጎች (ባህሎች) በመጥቀስ ስልጣን እንዳላት ቢከራከሩም የተሐድሶ አራማጁ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጎን በጽናት ቆመ። “በእኛዋ ስዊዘርላንድ” አለ “እንደ ህገ-መንግሥቱ ካልሆነ በስተቀር ባህል ተቀባይነት የለውም። እምነትን በሚመለከት ጉዳይ ሁሉ ደግሞ ህገ-መንግሥታችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው።”-Ibid., b. 11, ch. 13። GCAmh 135.5

በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል የነበረው ልዩነት ያለ ውጤት አልቀረም። በእርጋታና በትህትና የቀረበው ፀጥታ የሰፈነበት ግልጽና ምክንያታዊ የሆነው የተሐድሶ አራማጁ መከራከሪያ፣ በኤክ እብሪት የተሞላበትና በሚያንባርቅ ጩኸት በሚናገረው መላምት ያፈሩ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ቻለ። GCAmh 136.1

ውይይቱ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቀጠለ። ሲደመደም ጳጳሳውያኑ በእርግጠኝነት አሸናፊነታቸውን አወጁ። አብዛኛዎቹ ምክትሎች ሮምን ደገፉ፤ ጉባኤው የለውጥ አራማጆቹ እንደተሸነፉ፣ ከመሪያቸው ከዝዊንግል ጋርም ከቤትክርስቲያን አባልነት እንደተገለሉ አወጀ። የስብሰባው ውጤት ግን ሚዛኑ በየትኛው ወገን እንዳጋደለ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ክርክሩ ለፕሮቴስታንቱ ግብ ጠንካራ ኃይል መሆን ቻለ፣ ብዙም ሳይቆይ ወሳኝ የሆኑት የበርንና የባሰል ከተሞች ተሐድሶውን መቀላቀላቸውን አወጁ። GCAmh 136.2