ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፵—የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነፃ መውጣት
የእግዚአብሔርን ሕግ ከሚያከብሩት ዘንድ የሰብአዊ ፍጡር ሕግጋት ጥበቃ በሚነሳበት ጊዜ፣ በተለያዩ የምድር ክፍሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚደረግ ለእነርሱ ጥፋት የሚሆን እንቅስቃሴ ይኖራል። በአዋጅ የተወሰነው ጊዜ ሲቃረብ የተጠላውን [ኃይማኖታዊ] ወገን መንግሎ ለማጥፋት ሕዝቡ ይመሳጠራል። የተቃውሞንና የዘለፋን ድምጽ ዝም የሚያሰኝ ወሳኝ ጥቃት በአንድ ሌሊት ለመፈፀም ይወሰናል። GCAmh 458.1
በሁሉም የምድር ነፋሳት፣ በክፉ መላእክት ሰራዊት እየተገፋፉ፣ በብርጌድ የተደራጁ የታጠቁ ሰዎች ለሞት ሥራ ሲዘጋጁ ሳለ፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ገሚሶቹ በእስር ቤት ክፍሎች፣ ገሚሶቹ ደግሞ በጫካዎችና በተራሮች ፀጥ ረጭ ባሉ ስፍራዎች ተደብቀው አሁንም ለመለኮታዊ ጥበቃ ይቃትታሉ። አሁን ለምርጦቹ መበዤት የእሥራኤል አምላክ ጣልቃ የሚገባው በዚህ የመጨረሻ፣ ጫፍ በደረሰ የክስተት ሰዓት ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ አመት ሌሊት እንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላችኋል….ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እሥራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ….እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፣ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቁጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል በአውሎ ነፋስም በወጨፎም በበረዶ ጠጠር ይገልጣል።” [ኢሳ 30÷29፣30]። GCAmh 458.2
በድል ጩኸት፣ በፌዝ ሳቅና በእርግማን የክፉ ሰዎች ቡድን በታዳኞቻቸው ላይ ግር ሊል ሲል፣ እነሆ፣ ጥቅጥቅ ያለ ጥቁረት፣ ከውድቅት ጽልመት የባሰ ድቅድቅ ጨለማ በምድር ላይ ሰፈነ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ዙፋን በሚወጣው ክብር ያሸበረቀ ቀስተ-ደመና ሰማያትን አቋርጦ እያንዳንዱን የሚፀልይ ቡድን የሚከብ መሰለ። የተቆጡ እልፍ አዕላፋት በድንገት ተያዙ፤ የፌዝ ጩኸታቸው ሞተ። በቁጣ የገነፈለው የገዳይነት ዓላማቸው ተረሳ። ሊሆን ያለውን አስፈሪ ነገር በመገመት በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ምልክት ላይ አፍጥጠው ከአቅም በላይ ከሆነው ነፀብራቁ እንዲከለሉ ተመኙ። GCAmh 458.3
በእግዚአብሔር ሕዝቦች አጠገብ ግልጽና መረዋ የሆነ ድምጽ ተሰማ፤ እንዲህ ሲል፦ “ወደ ላይ ተመልከቱ”፤ ወደ ሰማያት ሲመለከቱም የተስፋውን ቀስተ ደመና አዩ። የተቆጡ፣ ጠፈርን የሸፈኑት ጥቁር ደመናዎች ተከፈሉ። እንደ እስጢፋኖስም ያለማቋረጥ ወደ ሰማይ አንጋጠው የእግዚአብሔርን ክብር፣ የሰውንም ልጅ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አዩ። በመለኮታዊ ገጽታው ሆኖ የውርደቱን ምልክቶች (ጠባሳዎች) አዩ። በአባቱና በመልአክቱ ፊት የሚያቀርበውን፣ ከከንፈሩ የአክብሮት ጥያቄን ሰሙ፦ “እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” [ዮሐ 17÷24]። እንደገናም የሙዚቃ ቃና ያለው የድል ድምጽ እንዲህ ሲል ተሰማ፦ “መጡ! መጡ! ቅዱስና ያለተንኮል፣ ያለነውርም። የትዕግስቴን ቃል ጠብቀዋል፣ በመላእክትም መካከል ይመላለሳሉ።” እምነታቸውን የጠበቁ እነርሱ፣ የገረጡና የሚንቀጠቀጡ ከናፍሮች፣ የድል ጩኸት አሰሙ። GCAmh 458.4
እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ ነፃ መውጣት ኃይሉን የሚገልጠው በእኩለ ሌሊት ነው፤ ፀሐይ በኃይልዋ እያንፀባረቀች ወጣች። ምልክቶችና ተዓምራት በፍጥነት ተከታተሉ። ፃድቃን የመዳናቸውን ምልክቶች በጥልቅ ሐሴት ሲመለከቱ ሳለ ኃጥአን በፍርሃትና በመደነቅ በትዕይንቱ ላይ አፈጠጡ። በተፈጥሮ ውስጥ ያለ [የተለመደ] ነገር ሁሉ ስርዓቱን የሳተ መሰለ። ጅረቶች መፍሰሳቸውን አቆሙ። ጥቁርና ከባድ ደመናዎች ወጡ፣ እርስ በርስም ተጋጩ። በተቆጡ ሰማያትም መካከል በአንድ ጥርት ባለ ቦታ ሊገለጽ የማይችል ክብር ታየ፤ ከእርሱም እንደ ብዙ ውኆች ድምጽ፣ የእግዚአብሔር ድምጽ ወጣ፤ እንዲህ ሲል፦ “ተፈጽሞአል።” [ራዕይ 16÷17፣18]። GCAmh 458.5
ያ ድምጽ ሰማያትንና ምድርን አነጋነገ። ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ። “ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ” [ራዕይ 16÷17፣18]። ጠፈር የሚከፈትና የሚከደን መሰለ። ከእግዚአብሔር ዙፋን የሚወጣው ክብር ቦገግ እያለ የሚነጉድ ይመስላል። ተራሮች በነፋስ እንደሚወዛወዝ ቄጤማ ተንቀጠቀጡ፤ የተሰባበሩ ቋጥኞች በሁሉም አቅጣጫ ተበተኑ። ውሽንፍር እንደሚመጣ አይነት የሚያጓራ ድምጽ አለ። ባህር በኃይልና በቁጣ ይማታል። ዲያብሎሶች በማጥፋት ተልዕኮ ላይ ሲሆኑ እንደሚያሰሙት ድምጽ ያለ፣ ታላቅ የአውሎነፋስ ድምጽ ይሰማል። መላዋ ምድር ልክ እንደ ባህር ሞገድ ከፍ ዝቅ፣ አበጥ ጎደል ትላለች። ውጫዊ ገጽታዋ እየተሰባበረ ነው። መሰረቶችዋ ራሳቸው እየሸሹ ይመስላሉ። የተራራ ሰንሰለቶች እየሰጠሙ ናቸው። ሰው የሚኖርባቸው ደሴቶች ጠፉ። በክፋታቸው ልክ እንደ ሰዶም የሆኑት የባህር ወደቦች በተቆጡ ውኃዎች ተዋጡ። ታላቂቱም ባቢሎን “የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ ይሰጣት ዘንድ” በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች [ራእይ 16÷19፣21]። “ታላቅ በረዶ፣ እያንዳንዱ አንድ ታለንት የሚመዝን”፣ የማውደም ሥራቸውን እየሰሩ ናቸው። በኩራት ተወዳዳሪ የሌላቸው የምድር ከተሞች ፈራርሰው ወደቁ። የዓለም ታላላቅ ሰዎች፣ ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ ሲሉ ሐብታቸውን በገፍ ያፈሰሱባቸው ባለ ግርማ ቤተ መንግሥታት በፊታቸው ወደ ውድመት እየተናዱ ናቸው። የወህኒ ቤት ግንቦች ተተረተሩ፤ ስለ እምነታቸውም የታሰሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነፃ ሆኑ። GCAmh 459.1
መቃብሮች ተከፈቱ፣ “በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ነቁ፣” “እኩሌቶች ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኩሌቶቹም ወደ ዘላለም እፍረትና ጉስቁልና” [ዳን 12÷2]። ሕጉን ከጠበቁቱ ጋር የእግዚአብሔርን የሰላም ቃል ኪዳን ይሰሙ ዘንድ በሶስተኛው መልአክ መልእክት አምነው ያንቀላፉ ሁሉ በክብር ከመቃብራቸው ወጡ። “የወጉት” [ራዕይ 1÷7]፣ በክርስቶስ የሞት ስቃይ የተሳለቁና ያፌዙ እነርሱ፣ የእውነቱና የሕዝቦቹ እጅግ ጨካኝ ጨቋኞች እነርሱ፣ በታማኞችና በታዛዦች ላይ ያረፈውን ክብር፣ እርሱንም በክብሩ ይመልከቱ ዘንድ ተነሱ። GCAmh 459.2
ጥቁር ደመና አሁንም ህዋን እንደሸፈነው ነው፤ ሆኖም የያህዌን ተበቃይ አይን መስላ፣ ፀሐይ፣ደመና እየሰበረች ወጣ ገባ ትላለች። ኃይለኛ መብረቆች ከሰማያት እየዘለሉ ምድርን በነበልባል አንሶላ ጀቦኑአት። ከአስደንጋጩ የነጎድጓድ ድንፋታ በላይ፣ ምስጢራዊና አስፈሪ ድምፆች የኃጥአንን ጥፋት አወጁ። የተነገሩት ቃላት በሁሉም ዘንድ አይስተዋሉም፤ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ግን አንድ በአንድ፣ ልቅም ብለው ተስተዋሉ። ከጥቂት ጊዜ በፊት በእግዚአብሔር ትዕዛዛት ጠባቂ ሕዝቦች ላይ ባሳዩት ጭካኔ፣ ንዝህላል፤ ተንቦጥራሪ፣ እምቢተኛ እንዲሁም ፈንዳቂ የነበሩ አሁን በሽብር ተሸንፈው በፍርሃት ተርበደበዱ። በስቃይ ሲጮሁ ከተፈጥሮ የአየር ንብረት ክስተቶች [ከወጀቡ፣ ከበረዶው…] ድምጽ በላይ ይሰማሉ። ሰዎች በሚያሸንፍ ፍርሃት እየተንፏቀቁ ምሕረት ሲማፀኑ ሳለ አጋንንት ለክርስቶስ መለኮትነት እውቅና ሰጡ፤ በኃይሉም ፊት ተንቀጠቀጡ። GCAmh 459.3
የእግዚአብሔርን ቀን በቅዱስ ራዕይ የተመለከቱ የጥንት ነብያት እንዲህ ብለዋል፦ “የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል” [ኢሳ 13÷6]። “ወደ ደንጋይ ዋሻ ግባ በመሬትም ተሸሸግ ከእግዚአብሔር ግርማ ፊት ከታላቅነቱም ክብር። ከፍ ያለችው የሰው አይን ትዋረዳለች የሰዎችም ኩራት ትወድቃለች በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኩራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፤ እርሱም ይዋረዳል።” “በዚያ ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል፤ እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሳ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሳ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ።” [ኢሳ 2÷10-12፤21]። GCAmh 460.1
በተገመሠው ደመና መሐል ከጨለማው ጋር ሲነፃፀር ብሩህነቱ አራት እጥፍ የሚጨምር አንድ ኮከብ አበራ። ለታማኞች ተስፋና ደስታ፣ ለእግዚአብሔር ሕግ ተላላፊዎች ደግሞ ጭቆናና ቁጣ ተናገረ። ሁሉን ለክርስቶስ የሰዉ እነርሱ፣ በእግዚአብሔር ድንኳን ማጀት ውስጥ እንደተደበቁ ሆነው፣ አሁን ከአደጋ የተጠበቁ ናቸው። ተፈትነዋል፤ በዓለምና እውነትን በሚንቁ ፊት፣ ለሞተላቸው ለእርሱ ታማኝነታቸውን በግልጽ አሳይተዋል። የሞት ፊት አፍጥጦባቸው ኃቀኝነታቸውን በጠበቁ በእነርሱ ላይ ግሩም መለወጥ መጥቷል። ወደ ዲያብሎስነት ከተቀየሩ ሰዎች ከባድና አስፈሪ ፈላጭ ቆራጭነት በድንገት እንዲተርፉ ተደርገዋል። ከአፍታ በፊት የገረጡት፣ የደነገጡትና የኮሰሱት ፊቶቻቸው አሁን በአድናቆት፣ በእምነትና በፍቅር ፈኩ። በአሸናፊ መዝሙርም ድምፃቸው ከፍ አለ፦ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም፤ ውኆቻቸው ቢጮኹ ቢናወጡም፣ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሳ ቢናወጡ [አንፈራም]።” [መዝ 46÷1-3]። GCAmh 460.2
እነዚህ የተቀደሱ የመተማመን ቃላት ወደ እግዚአብሔር ሲወጡ ሳለ፣ በሁለቱም በኩል ካለው ጥቁርና ቁጡ ጠፈር ጋር ሲነፃፀር ለመግለጽ በማይቻል ግርማ ያሸበረቀ፣ ደመናዎቹ ወደ ኋላ ተገልጠው፣ ከዋክብታማ ሰማይ ታየ። ገርበብ ካለው በሮችዋ የሚወጣ የዘላለማዊቷ ከተማ ክብር ይወርዳል። ከዚያም በህዋው ላይ አንድ ላይ የታጠፉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች የያዘ አንድ እጅ ታየ። ነብዩ እንዲህ አለ፦ “ሰማያት ክብሩን ይናገራሉ፤ እግዚአብሔር [ራሱ] ፈራጅ ነውና” [መዝ 50÷6]። በነጎድጓድና በነበልባል መሃል ከሲና እንደ ሕይወት መመሪያ የታወጀው ያ፣ ቅዱስ ሕግ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ አሁን የፍርድ ሕግ ሆኖ ተገለጠ። እጁ ጽላቶቹን ከፈተ፣ በእሳት ብዕር እንደተፃፈ የአሥርቱ ትዕዛዛት መመሪያዎች ታዩ። ቃላቱ እጅግ ግልጽ ናቸው፤ ሁሉም ሊያነባቸው የሚችሉ ናቸው። ትውስታ ተቀሰቀሰ፤ የአጉል እምነትና የኑፋቄ ጽልመት ከእያንዳንዱ አዕምሮ ተገለጠ፤ እጥር ምጥን ያሉ ሁሉን ያካተቱ፣ ባለ ስልጣን የሆኑ የእግዚአብሔር አሥርቱ ቃላት የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ይመለከቷቸው ዘንድ ተገለጡ። GCAmh 460.3
በእግዚአብሔር ቅዱስ ትዕዛዛት ላይ ሲረማመዱ የነበሩት ሰዎች የሚደርስባቸውን ታላቅ ድንጋጤና ተስፋ መቁረጥ ለመግለጽ ፈጽሞ አይቻልም። ጌታ ሕጉን ሰጣቸው፤ ለንስሐና ለመለወጥ ገና እድሉ እያለ ባህርያቸውን ከእርሱ [ከሕጉ] ጋር አነፃጽረው፣ ጉድለታቸውን ማወቅ ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን የዓለምን ሞገስ ለማትረፍ ሲሉ መመሪያዎቹን ወደ ጎን አድርገው ሌሎችም እንዲጥሱት አስተማሩ። ሰንበቱን ያረክሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማስገደድ ሲጥሩ ኖረዋል። አሁን በዚህ በናቁት ሕግ ተኮነኑ። በሚገርም፣ ቁልጭ ባለ ግልጽነት ስለታየ ማሳበቢያ ምክንያት እንደሌላቸው ተመለከቱ። ማንን እንደሚያገለግሉና እንደሚያመልኩ መርጠዋል። “ተመልሳችሁም በፃድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።” [ሚል 3÷18]። GCAmh 461.1
የእግዚአብሔር ሕግ ጠላቶች፣ ከአገልጋዩ ጀምሮ ከሁሉም እስከሚያንሰው ድረስ፣ ስለ እውነትና ስለ ኃላፊነት አዲስ መረዳት አገኙ። የአራተኛው ትዕዛዝ ሰንበት [ቅዳሜ] የሕያው እግዚአብሔር ማህተም መሆኑን ጊዜ ካለፈ በኋላ ተመለከቱ። እውነተኛ ያልሆነውን ሰንበታቸውን ትክክለኛ ሁኔታ፣ ሲገነቡበትም የኖሩትን የአሸዋ መሰረት ጊዜ ካለፈ በኋላ አስተዋሉ። እግዚአብሔርን ሲዋጉ እንደነበረ አወቁ። ወደ ገነት በር እየመሯቸው እንደነበረ ሲመሰክሩ ሳለ ኃይማኖታዊ መምህራን ነፍሳትን ወደ ጥፋት ሲመሩ ኖረዋል። በቅዱስ ስፍራ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ኃላፊነት፣ የእምነት የለሽነታቸውም ውጤቶች እንዴት ዘግናኝ እንደሆኑ እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ አይታወቅም። የአንድን ነፍስ ጥፋት በትክክል ልንገምት የሚቻለን በዘላለም ዘመናት ውስጥ ብቻ ነው [የአንድን ነፍስ ኪሳራ በትክክል ለመገመት እንችል ዘንድ የሚወስድብን ጊዜ ዘላለም ነው]። እግዚአብሔር አንተ ክፉ ባርያ ውጣ( ራቅ) የሚለው የእርሱ ጥፋት እጅግ አስፈሪ ይሆናል። GCAmh 461.2
የሱስ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ሲናገር፣ ዘላለማዊውን ቃል ኪዳንም ለሕዝቦቹ ሲያደርስ የእግዚአብሔር ድምጽ ከሰማይ ተሰማ። ልክ እንደ ታላቅ የነጎድጓድ ደወል ሆነው ቃላቱ በምድር ላይ አስተጋቡ። አይኖቻቸው ወደ ላይ ተቀስረው የእግዚአብሔር እሥራኤሎች እያዳመጡ ቆሙ። ገጽታቸው በክብሩ ፈካ፤ ሙሴ ከሲና ሲመለስ እንደነበረው አንፀባረቁ። ኃጥአን ይመለከቷቸው ዘንድ አይችሉም። ሰንበቱን ቅዱስ አድርገው በመጠበቅ እግዚአብሔርን ባከበሩት ላይ በረከት በሚወርድበት ጊዜ ታላቅ የድል ጩኸት ተሰማ። GCAmh 461.3
ብዙም ሳይቆይ የሰውን እጅ ግማሽ የምታህል ትንሽ ጥቁር ደመና ከምሥራቅ በኩል ብቅ አለች። በርቀት ሲታይ በጨለማ የተከበበ የሚመስለው አዳኙን የከበበው ደመና ነው። ይህ የሰው ልጅ ምልክት እንደሆነ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ያውቃሉ። ታላቅ ነጭ ደመና መሰረቱም እንደሚፋጅ እሳት የከበረ፣ በላዩም የቃል ኪዳኑ ቀስተ ደመና እስኪታይ ድረስ፣ ወደ ምድር እየቀረበ፣ የበለጠ እየፈካና ውብ እየሆነ ሲሄድ ሳለ፣ በታላቅ ፀጥታ ይመለከቱታል። የሱስ ኃያል ድል አድራጊ ሆኖ ወደፊት መጣ። አሁን እንደ “የህማም ሰው” የኃፍረትንና የመከራን መራራ ጽዋ ሊጠጣ ሳይሆን፣ ነገር ግን በሰማይና በምድር ድል ነሺ ሆኖ፣ በሕያዋንና በሙታን መካከል ሊፈርድ መጥቶአል። “የታመነና እውነተኛ” “በጽድቅም ይፈርዳል፣ ይዋጋልም።” “የሰማይም ጭፍሮች.. ይከተሉታል” [ራዕይ 19÷11፣14]። በሰማያዊ ጥዑመ-ዜማ የምስጋና መዝሙር የሚዘምሩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው አያሌ መላእክት ሲመጣ አጀቡት። ጠፈር በሚያንፀባርቁ ምስሎች የተሞላ መሰለ። “አዕላፋት ጊዜ አዕላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበሩ።” የሰብአዊ ፍጡር ብዕር ክስተቱን ይገልፀው (ይስለው) ዘንድ፣ የሟች አዕምሮም ድምቀቱን ይረዳው ዘንድ ብቁ አይደለም። “ክብሩ ሰማያትን ከደነ፤ ምስጋናውም በምድር መላ። ብልጭታውም እንደ ብርሐን ነበረ።” [እንባ 3÷3፣4]። ሕያው ደመና አሁንም እየቀረበ ሲሄድ እያንዳንዱዋ አይን የሕይወትን ልዑል አየች። አሁን ያንን ቅዱስ (sacred) ራስ የሚያውከው የእሾህ አክሊል የለም። በቅዱስ (holy) ግንባሩ የክብር ዘውድ አርፎአል። የፊቱ ነፀብራቅ እጅግ የደመቀ የቀትር ብርሐንን ያስንቃል። “በልብሱና በጭኑም የተፃፈበት፦ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶችም ጌታ የሚል ስም አለው” [ራዕይ 19÷16]። GCAmh 461.4
በእርሱ መገኘት “ፊትም ሁሉ ወደ ጥቁረት [መገርጣት] ተለወጠ።” በእግዚአብሔር ምሕረት እምቢ ባዮች ላይ አስፈሪ ዘላለማዊ ተስፋ መቁረጥ ወደቀ። “ልብ ቀልጦአል፣ ጉልበቶችም ተበረክርከዋል ፊትም ሁሉ ወደ ጥቁረት ተለወጠ” [ኤር 30÷6፤ ናሆም 2÷10]። ፃድቃን እየተንቀጠቀጡ “ማንስ ሊቆም ይችላል?” ብለው ጮኹ። የመላእክት ዝማሬ ቆመ፤ ከባድ ፀጥታም ሰፈነ። ከዚያም የየሱስ ድምጽ ተሰማ እንዲህ ሲል፣ “ፀጋዬ ይበቃችኋል።” የፃድቃን ፊቶች አበሩ፤ ደስታም እያንዳንዱን ልብ ሞላ። ወደ ምድርም የበለጠ እየቀረቡ ሲሄዱ መላእክት ከፍ ያለ ኖታ ደረደሩ፤ እንደገናም ዘመሩ። GCAmh 462.1
በነበልባል እሳት ተከቦ በደመናው ላይ ሆኖ የነገሥታት ንጉሥ ወረደ። ሰማያት እንደወረቀት ተጠቀለሉ፤ ምድርም በፊቱ ተንቀጠቀች። እያንዳንዱ ተራራና ደሴትም ከስፍራው ሸሸ። “አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፤ በዙሪያውም ብዙ አውሎ አለ። በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል” [መዝ 50÷3፣4]። GCAmh 462.2
“የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለጠጋዎችም ኃይለኛዎችም፣ ባርያዎችም፣ ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራሮች ዓለቶች ተሰወሩ፤ ተራሮችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣ ቀን መጥቶአልና ማንስ ሊቆም ይችላል?” [ራዕይ 6÷15-17] አሉ። GCAmh 462.3
የንቀት ቧልቶች አቁመዋል። የሚዋሹ ከናፍሮች ጭጭ ብለዋል። የጦር መሳሪያዎች ቁርቁስ፣ የጦርነት ግርግር “የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፣ በደምም የተለወሰ ልብስ” [ኢሳ 9÷5] እረጭ አለ። ከፀሎት ድምጽ፣ ከለቅሶና ዋይታ ጩኸት በቀር የሚሰማ ነገር የለም። ከጥቂት ጊዜ በፊት ሲያላግጡ ከነበሩ ከንፈሮች የለቅሶ ድንፋታ ይሰማል “ታላቁ የቁጣ ቀን መጥቶአልና ማንስ ሊቆም ይችላል?”፤ ኃጥአን፣ የጠሉትን፣ አንቀበልም ያሉትን፣ የእርሱን ፊት ከመገናኘት ይልቅ በተራሮች ቋጥኞች ስር ይቀበሩ ዘንድ ለመኑ። GCAmh 462.4
የሙታንን ጆሮ ሰርስሮ የሚገባውን ያንን ድምጽ ያውቁታል። [የድምጹ] ኃዘንተኛና ለስላሳ ቃናዎች፣ ምን ያህል ጊዜ ወደ ንስሐ ጠርተዋቸዋል። ልብ በሚነካ የጓደኛ፣ የወንድም፣ የአዳኝ፣ ልመና ድምፁ ስንት ጊዜ ተሰምቶአል። ፀጋውን አሻፈረኝ ላሉ “ተመለሱ፣ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ፤ ስለምንስ ትሞታላችሁ?” [ሕዝ 33÷11] እንደሚለው ለረጅም ጊዜ እንደተማፀነው ያለ በውግዘት ሊሞላ የሚችል፣ የኩነኔም ቀንበር ሊጫንበት የሚችል ድምጽ የለም። የእንግዳ ሰው ድምጽ ቢሆንላቸው ኖሮ መልካም ነበረ። የሱስ አለ፦ “እኔም ስለፀራሁ እምቢ አላችሁ፤ እጄን ዘረጋሁ ማንም አላስተዋለም። ነገር ግን ምክሬን ሁሉ ፀላችሁ ዘለፋየንም ናቃችሁ” [ምሳሌ 1÷24፣25]። ድምፁ፣ ቢደመስሷቸው ደስ የሚሏቸውን ትውስታዎች ቀሰቀሰ - የተናቁ ማስጠንቀቂያዎች፣ እምቢ የተባሉ ግብዣዎች፣ የተቃለሉ እድሎች። GCAmh 462.5
በውርደቱ ጊዜ በክርስቶስ የተሳለቁ በዚያ አሉ። በሊቀ ካህኑ በተጠየቀ ጊዜ ረጋ ብሎ የመለሰበት የተሰቃዩ ቃላት በሚያነቃ ኃይል ወደ አዕምሮአቸው መጣ “ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ እንድታዩ በሰማይም ደመና ሲመጣ” [ማቴ 26÷64]። አሁን በክብሩ ተመለከቱት፤ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥም ገና ያዩታል። GCAmh 463.1
የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ያለበቱን ንግግር መቀለጃ ያደረጉት እነርሱ አሁን የሚሉትን አጡ። በንጉሣዊ ማዕረጉ (ንጉሥ ነኝ በማለቱ) የጮኸበት፣ የሚያሾፉ ወታደሮቹንም ንጉሥ አድርገው ዘውድ እንዲደፋለት ያዘዘ፣ እብሪተኛው ሄሮድስ አለ። በንቀት እጃቸው ሐምራዊ ልብስ ያለበሱት፣ እሾሃማውን አክሊል በቅዱስ ግንባሩ ያኖሩት፣ እምቢ የማይል እጁ ላይ የንጉሥ ዘንግ የሚመስል በትር አስይዘው ስምን በሚያጎድፍ ፌዝ በፊቱ የሰገዱለት እነዚያው ሰዎች እዚያ አሉ። የመቱት፣ በሕይወት ልዑል ላይ የተፉ ሰዎች አሁን ከሚሰረስረው፣ ትኩር ያለ እይታው ዘወር ብለው ከአቅም በላይ ከሆነው ከመገኘቱ ክብር ለመሸሽ ጣሩ። በእጆቹና በእግሮቹ ካስማ የከተቱ እነርሱ፣ ጎኑን የወጉት ወታደሮች በፍርሃትና በፀፀት እነዚህን ጠባሳዎች ተመለከቷቸው። GCAmh 463.2
ካህናትና አለቆች የቀራንዮን ትዕይንት ልቅም አድርገው አስታወሱ። በሰይጣናዊ ፍንደቃ ራሳቸውን እየነቀነቁ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእሥራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአልና….ከወደደውስ አሁን ያድነው” [ማቴ 27÷42፣43] ብለው የጮኹ አሁን በሚያርበደብድ ድንጋጤ አስታወሱ። GCAmh 463.3
የወይኑን ፍሬ ለጌታቸው ለመስጠት እምቢ ስላሉት፣ ሰራተኞቹን ስለመቱት ልጁንም ስላረዱት፣ አዳኙ የተናገረውን ምሳሌ ጥርት አድርገው አስታወሱ። ራሳቸው ስላስተላለፉት ውሳኔም እንዲሁ አስታወሱ፦ የወይኑ ጌታ እነዚያን ክፉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠፋቸዋል። በነዚያ እምነት የጎደላቸው ሰዎች ኃጢአትና ቅጣት፣ ካህናትና ታላላቆች የራሳቸውን አካሄድ የራሳቸውንም ልክ ጥፋት ተመለከቱ። አሁን እጅግ አደገኛ የሆነ የህመም ጩኸት ወጣ። “ስቀለው!” ስቀለው!” ከሚለው በየሩሳሌም ጎዳናዎች ሲያስተጋባ ከነበረው ጩኸት የደመቀ፣ “እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! እርሱ እውነተኛ መሲህ ነው!” የሚል የስቃይ ሲቃ የተሞላበት ጩኸት ገነነ። ከነገሥታት ንጉሥ መገኘት ፊት ይሸሹ ዘንድ ፈለጉ። የምድር ነፋሳት በተጋጩ ጊዜ በተፈጠሩ ዋሻዎች ይደበቁ ዘንድ በከንቱ ደከሙ። GCAmh 463.4
እውነትን አንቀበልም በሚሉ ሰዎች ሁሉ ሕይወት ውስጥ፣ ንቃተ ህሊና የሚነቃባቸው፣ ትዝታ የግብዝነት ሕይወትን ገራፊ ትውስታ የሚያቀርብበት፣ ነፍስም በከንቱ የፀፀት [ድግግሞሽ] የምትዝልበት አፍታዎች አሉ፤ ነፍስም በከንቱ ፀፀት ትታወካለች። ነገር ግን “ድንጋጤ እንደ ጎርፍ” በደረሰ ጊዜ “ጥፋትም እንደ አውሎ ነፋስ” በመጣ ጊዜ በዚያን ቀን ከሚሆነው ፀፀት ጋር ሲነፃፀሩ እነዚህ ምንድን ናቸው! [ምሳሌ 1÷27]። እነዚያ ክርስቶስንና ታማኝ ሕዝቦቹን ያጠፉ የነበሩ እነርሱ፣ አሁን በላያቸው ያለውን ክብር ተመለከቱ። በድንጋጤያቸው መሃል የቅዱሳንን ሐሴታዊ መዝሙር ሰሙ፣ እንዲህ ሲል፦ “እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ ያድነንማል” [ኢሳ 25÷9]። GCAmh 463.5
በሚንገዳገደው መሬት፣ በመብረቅ ብልጭታው፣ በነጎድጓድም ጉርምርምታ መካከል የእግዚአብሔር ልጅ ድምጽ ያንቀላፉትን ቅዱሳን ጠራቸው። ወደ ቅዱሳን መቃብር ተመለከተ፤ ከዚያም እጁን ወደ ሰማይ አንስቶ “ንቁ፣ ንቁ፣ ንቁ እላንት በአፈር ውስጥ የተኛችሁ ተነሱ!” በምድር እርዝመትና ወርድ ሁሉ ሙታን ያንን ድምጽ ይሰማሉ። የሚሰሙትም እነርሱ በሕይወት ይኖራሉ። ከእያንዳንዱ መንግሥት፣ ወገን፣ ቋንቋና ሕዝብ ከወጣ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ኮቴ የተነሳ መላዋ ዓለም ታስተጋባለች። በማይሞት ክብር ተላብሰው፦ “ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታለ?” እያሉ [1ኛ ቆሮ 15÷55] ከሞት እስር ቤት ይመጣሉ። በሕይወት ያሉ ፃድቃንና ከሞት የተነሱ ቅዱሳን ረጅም፣ ተድላ የተሞላበት፣ የአሸናፊነት ጩኸታቸውን በአንድ ላይ ያደርጋሉ። GCAmh 464.1
ወደ መቃብር ሲገቡ በነበሩበት በዚያው ቁመና ሆነው ሁሉም ከመቃብር ወጡ፤ ከተነሳው ሕዝብ መካከል ያለው አዳም ረጅም ቁመና እና ግዙፍ አቋም ያለው፤ ከእግዚአብሔር ልጅ [ከየሱስ] ግን ትንሽ ዝቅ ያለ ነው። በኋላው ከመጡት ትውልዶች የሚስተዋል ልዩነት አለው፤ በዚህ በአንዱ ሁናቴ ዘሩ ታላቅ መቆርቆዝ ታይቶበታል። ነገር ግን በዘላለም ወጣትነት ለጋነትና ጥንካሬ ሁሉም ተነሱ። በመጀመሪያ፣ በባህርይ ብቻ ሳይሆን በቅርጽና በመለዮ ጭምር ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ። ኃጢአት የመለኮትን መልክ አበላሽቶ ሙሉ ለሙሉ ሊያጠፋው ተቃርቦ ነበር፤ ነገር ግን የጠፋውን ያድስ ዘንድ ክርስቶስ መጣ። የተዋረደውን (ግሙን) ሰውነታቸውን ይለውጠዋል፤ ውብ በሆነው አካሉ አምሳያም ያበጃቸዋል። ደም ግባቱ የጠፋበት፣ በአንድ ወቅት በኃጢአት ተበክሎ የነበረው ሟቹና ተበላሹ አካል ፍፁም፣ ውብና ዘላለማዊ (immortal) ይሆናል። ሁሉም እንከንና ጎዶሎነት እዛው መቃብር ይቀራሉ። ለረጅም ጊዜ ጠፍታ በቆየችው ኤደን ወደ ሕይወት ዛፍ ተመልሰው፣ የዳኑት፣ የሰው ዘር ጥንት ወደነበረው ክብሩ ወደ ሙላቱ ልክ “ያድጋሉ” [ሚል 4÷2]። የተቀሩት የኃጢአት እርግማን ምልክቶች ሁሉ ይወገዳሉ፤ በአዕምሮ፣ በነፍስና በአካል የጌታቸውን ፍፁም መልክ እያንፀባረቁ የክርስቶስ ታማኞችም “በአምላካችን በእግዚአብሔር ሞገስ [ውበት]” ሆነው ይታያሉ [መዝ 90÷17]። ኦህ ግሩም መቤዠት! ረጅም ጊዜ የተወራበት፣ ለረጅም ጊዜ ተስፋ የተደረገበት፣ በጉጉት የተንሰላሰለበት ሆኖም ሙሉ ለሙሉ መስተዋል ያልቻለ ድነት፤ ኦ ግሩም መቤዠት! GCAmh 464.2
በሕይወት የቆዩት ፃድቃን “በድንገት በቅጽበተ አይን” [1ኛ ቆሮ 15÷52] ይለወጣሉ። በእግዚአብሔር ድምጽ ከብረዋል፤ አሁን ዳግም የማይሞቱ ይደረጋሉ፤ ጌታቸውን በአየር ይቀበሉ ዘንድ ከሙታን ከተነሱት ጋር ተነጠቁ። መላእክት “ከአራቱ ነፋሳት ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን” [ማር 13÷27] ሰበሰቡ። ህፃናት በመላእክት ወደ እናቶቻቸው እቅፍ ተወሰዱ። ከአሁን ወዲያ ፈጽሞ ላይነጣጠሉ ለረጅም ጊዜ በሞት ተለይተው የነበሩ ወዳጆች ተገናኙ፤ በተድላ (በሐሴት) መዝሙርም አንድ ላይ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወጡ። GCAmh 464.3
በእያንዳንዱ ደመናማ ሰረገላ ጎን ክንፎች አሉ፤ በሥርም ሕያው መንኮራኩሮች አሉ። ሰረገላው ወደ ላይ ሲሽከረከር መንኮራኩሮቹ “ቅዱስ” ብለው ጮኹ። ክንፎቹም ሲንቀሳቀሱ “ቅዱስ” እያሉ ጮኹ። የመላእክት ቡድንም “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔር” እያሉ ጮኹ። ሰረገላው ወደ ላይ ወደ አዲሲቱ የሩሳሌም ሲገሰግስ የተዋጁትም “ኃሌ ሉያ” ብለው ጮኹ። GCAmh 465.1
ወደ እግዚአብሔር ከተማ ከመግባቱ በፊት፣ አዳኙ ለተከታዮቹ የድል አርማ ሰጠ። ከንጉሣዊ መንግሥታቸው ማዕረግ አበረከተላቸው። የሚያብረቀርቁት ደረጃዎች፣ በክፍት አራት ማዕዘን ቅርጽ፣ በግርማ ሞገስ ከቅዱሳንና ከመላእክት በላይ ገዝፎ በሚታየው፣ ፊቱ በደግነት ፍቅር በሙላት በሚያበራባቸው፣ በንጉሳቸው ዙሪያ ተሰለፉ። በማይቆጠረው፣ በዳነው ሰራዊት በሞላ፣ የእያንዳንዱ እይታ “ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፣ መልኩም ከሰው ልጆች ይልቅ” በተጎሳቆለው በእርሱ ላይ አረፈ፤ እያንዳንዱ ክብሩን ተመለከተ። የሱስ ራሱ በአሸናፊዎች ራስ ላይ በቀኝ እጁ የክብር ዘውድ አስቀመጠ። ለእንዳንዱ “የራሱን አዲስ ስም” የያዘ [ራዕይ 2÷17] “ቅድስና ለእግዚአብሔር” [ዘፀ 28÷36] የሚል ጽሁፍ ዘውድ አለ። በእያንዳንዱ እጅ የአሸናፊነት ዘንባባና የሚያንፀባርቅ በገና ተደረገ። ከዚያም መሪ መላእክት ኖታውን ሲደረድሩ እያንዳንዱ እጅ ክሮቹን በጥበብ እየነካካ ግሩም ጥዑመ-ዜማ አፈለቀ። ሊነገር የማይችል ሀሴት እያንዳንዱን ልብ ሞላው። እያንዳንዱ ድምጽ ውለታ በሚያሳይ ምስጋና ወጣ። “ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ነገሥታትና ካህናት ላደረገን ለእርሱ ክብር ይሁን፣ ችሎትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ።” [ራዕይ 1÷5፣6]። GCAmh 465.2
ቅድስቲቱ ከተማ ከተዋጀው ሰራዊት ፊት ለፊት ነች። የሱስ በሉል የተጌጡ በሮቿን ወለል አድርጎ ከፈተ፤ እውነትን የጠበቁ ሕዝቦችም ገቡ። በንጽህናው ጊዜ የአዳም ቤት የነበረችውን የእግዚአብሔርን ገነት እዚያ ተመለከቱ። ከዚያም በሟች ጆሮ ተሰምቶ ከሚያውቀው ሙዚቃ ይልቅ እጅግ ጣፋጭ የሆነው ድምጽ እንዲህ ሲል ተሰማ፦ “ትግላችሁ አብቅቷል”፤ “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” [ማቴ 25÷34]። GCAmh 465.3
አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ የፀለየው ፀሎት አሁን ፍጻሜ አገኘ፣ “እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” [ዮሐ 17÷24]። “ያለ ነውር በክብሩ ፊት በደስታ” [ይሁዳ 24]። “እነሆኝ እኔ አንተም የሰጠኸኝ ልጆች፤ የሰጠኸኝን ጠብቄያለሁ” ብሎ ክርስቶስ በደሙ የተገዙትን ለአባቱ አቀረበ። ኦህ የሚያነፃው ፍቅር አስገራሚነት! መጠን የለሹ አባት የኃጢአት ጥል ጠፍቶ፣ መቅሰፍቱ ተወግዶ፣ ሰው እንደገና ከመላእክት ጋር ተስማምቶ፣ ወሰን የለሹ አምላክ ሲመለከት የዚያ የደስታ ሰዓት እንዴት ግሩም ነው! GCAmh 465.4
ሊነገር በማይችል ፍቅር ወደ “ጌታቸው ደስታ” የሱስ ታማኞቹን እንኳን ደህና መጣችሁ አላቸው። የአዳኙ ደስታ፣ በስቃዩና በውርደቱ የዳኑት ነፍሳት በክብር መንግሥት ውስጥ ሆነው ማየት ነው። በፀሎታቸው፣ በልፋታቸው በፍቅር መስዋዕትነታቸው አማካኝነት ለክርስቶስ የተማረኩትን ባዩ ጊዜ የተዋጁትም የዚህ ደስታ ተካፋይ ይሆናሉ። ዘውዳቸውን በየሱስ እግር ስር አኑረው ማብቂያ በሌለው በዘላለም ድግግሞሽ ሲያመልኩት፣ በነጩ ዙፋን ዙሪያ ሲሰበሰቡ ሳለ ለየሱስ የማረኳቸውን ሲያዩ፣ አንዱ ሌሎቹን አትርፎ፣ የተረፉትም ሌሎችን ማርከው፣ ወደ ሰማያዊ እረፍት ሁሉም ገብተው ሲያዩ፣ ልባቸው በማይነገር ደስታ ተሞላ። GCAmh 465.5
የተዋጁት ወደ እግዚአብሔር ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚባሉበት ጊዜ ከፍተኛ የአድናቆት፣ የደስታና የሐሴት ድምጽ በአየሩ ውስጥ አስተጋባ። ሁለቱ አዳሞች ሊገናኙ ነው። እርሱ የፈጠረውን ፍጡር፣ በሠራው ጌታው ላይም ኃጢአት የፈጸመውን፣ ስለ ኃጢአቱም ምክንያት በአዳኙ አካል ላይ የስቅላት ምልክቶች እንዲኖሩ ያደረገውን፣ የዘራችንን አባት ይቀበል ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ እጆቹን ዘርግቶ ቆሞአል። አዳም የሚስማሮቹን ጠባሳ ባስተዋለ ጊዜ በጌታው እቅፍ ውስጥ አልወደቀም፤ ነገር ግን ራሱን ቅዝ አድርጎ በእግሮቹ ስር በመውደቅ “የታረደው በግ ይገባዋል፣ ይገባዋል” ብሎ ጮኸ። አዳኙ ቀስ አድርጎ አነሳውና ከረጅም ጊዜ በፊት የተባረረበትን፣ ኤደንን እንደገና እንዲመለከት ጋበዘው። GCAmh 466.1
ከኤደን ከተባረረ በኋላ በምድር የነበረው የአዳም ሕይወት በሃዘን የተሞላ ነበር። እያንዳንዱ የሚረግፍ ቅጠል፣ እያንዳንዱ የመስዋዕት ተጠቂ (እንስሳ)፣ በምድር መልካም ገጽታ የወረደው እያንዳንዱ ዋግ፣ በሰው ንጽህና ላይ የመጣው እያንዳንዱ እንከን፣ አዳም የሰራውን ኃጢአት ሁልጊዜ አዲስ አድርጎ ያስታውሰው ነበር። ኃጢአት ሲበዛ ሲያይ፣ ማስጠንቀቂያ ሲሰነዝርም በምላሹሰ የዚህ ኃጢዓት መንስኤ ራሱ እንደሆነ ወቀሳ ሲወርድበት፣ የፀፀት ሕይወቱ እጅግ ከባድ ነበር። ትዕግስት በተሞላበት ደግነት የመተላለፉን ቅጣት ለአንድ ሺህ ዓመት የተቃረበ ዘመን ተሸከመ። በእምነት ኃጢአቱን ተናዘዘ። ቃል ኪዳን በተገባለት አዳኝ ስጦታ አምኖና ከጥፋቱ ተመልሶ፣ ከሞት እንደሚነሳ ተስፋ አድርጎ አንቀላፋ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ግድፈትና ውድቀት አስወገደ። ስለዚህ አሁን በስርየት ሥራ ምክንያት አዳም ወደ ቀድሞ ግዛቱ ይመለሳል። GCAmh 466.2
በደስታ ስሜት ተውጦ በአንድ ወቅት የተድላው ምንጭ የነበሩትን ዛፎች - በንጽህናውና በደስታው ዘመን ፍሬ ሲለቅምባቸው የነበሩትን - ዛፎች ራሳቸውን አገኛቸው። የራሱ እጆች ያሰለጠናቸውን የወይን ግንዶች፣ በደስታ ሲንከባከባቸው የነበሩትን አበቦች አያቸው። የክስተቱን እውነትነት አምኖ አዕምሮው አስተዋለ። ይቺ፣ እርሱ ከመባረሩ በፊት ከነበረችው በላይ አምራና ደምቃ የሚያያት በእርግጥ የቀድሞዋ ኤደን እንደ ሆነች ገባው። አዳኙ ወደ የሕይወት ዛፍ መራውና ከፍሬዋ ቀጥፎ ይበላ ዘንድ ሰጠው። በዙሪያውም ሲመለከት የተዋጁት ቤተሰቦቹ በእግዚአብሔር ገነት ቆመው አያቸው። ከዚያም የሚያብረቀርቀውን ዘውዱን አውርዶ በየሱስ እግር ስር አስቀመጠና በየሱስ ደረት ላይም ወድቆ አዳኙን አቀፈው። በገናውንም ሲደረድር የሰማይ ጣሪያ በድል መዝሙር ማሚቶ አስገመገመ። “ለታደረው በግ እንደገናም ለሚኖረው ይገባዋል፣ ይገባዋል፣ ይገባዋል!” እያሉ የአዳም ቤተሰቦች ዘውዳቸውን አውርደው በአዳኙ እግር ሥር በማኖር ለአምልኮ በፊቱ ሰገዱ። GCAmh 466.3
አዳም በወደቀ ጊዜ ያለቀሱት፣ በስሙ ያመኑ ሁሉ ይድኑ ዘንድ የሱስ መቃብር ከፍቶ ከሞት በመነሳት ወደ ሰማይ ሲያርግ ሐሴት ያደረጉት መላእክት ይህንን ቅልቅል በዓይናቸው አዩ። አሁን የማዳን ሥራ ሲፈፀም አዩ። በህብረትም የምስጋና መዝሙር አሰሙ። GCAmh 466.4
በእግዚአብሔር ክብር አሸብርቆ በሚታየው፣ ከእሳት ጋር የተቀላቀለ በሚመስለው በዚያ የመስታዎት ባህር፣ በዙፋኑ ፊት ባለው በብርጭቆ ባህር ላይ “አውሬውን ድል የነሱ በምስሉም [በምልክቱም]፣ በስሙም ቁጥር ላይ ድል ነስተው የነበሩ” ተሰበሰቡ [ራእይ 15÷2]። በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ሆኖ “የእግዚአብሔርን በገና ይዘው” ከሰው መካከል የተዋጁት አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎች ቆሙ። ከዚያም ድምፁ እንደ ብዙ ውሆች እንደ ታላቅ የነጎድጓድ ድምጽ የሚመስል “ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ” ያለ ድምጽ ተሰማ [ራእይ 14÷1-5፤ 15÷3፤ 7÷14-17]። ከመቶ አርባ አራት ሺዎቹ በቀር ማንም ሊማረው የማይችል አዲስ መዝሙር ዘመሩ። የሙሴና የበጉ መዝሙር — የመዳን መዝሙር ነው። ሌላ ማንም ቡድን ያልተለማመደው፣ የራሳቸው ተሞክሮ ስለሆነ ከመቶ አርባ አራት ሺዎቹ ውጪ ሌላ ሊማረው የሚችል የለም። “በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው።” እነዚህ ከሕያዋን መካከል፣ ከምድር የተለወጡ (translated)፣ “ለእግዚአብሔርና ለበጉ የመጀመሪያ ፍሬዎች” “ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው።” [ራዕይ 14÷1-5፤ 15÷3፤ 7÷14-17]። መንግሥት ከኖረ ጀምሮ ባልታየ በመከራ ዘመን አልፈዋል፤ የያዕቆብን የመከራ ጊዜ ስቃይ ተቋቁመው አልፈዋል፤ የመጨረሻው የእግዚአብሔር ፍርድ ሲወርድ፣ ያለ አማላጅ ቆመዋል። “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም” አንጽተዋልና ዳኑ። በእግዚአብሔር ፊት “በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።” “ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን አሉ፤ ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያመልኩታል።” “በዙፋኑም የተቀመጠው ያድርባቸዋል” (shall dwell among them) [በመካከላቸው ይኖራል/ያድራል] [ራእይ 14÷1-5፤ 15÷3፤ 7÷14-17]። መሬት በረሃብና በቸነፈር ስትበላሽ፣ ፀሐይ በኃይል ሙቀት ሰዎችን ስታቃጥል አይተዋል፤ እነርሱም ራሳቸው መከራን፣ ረሃብንና ጥማትን ችለዋል። ሆኖም “ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሙም። ፀሐይም ትኩሳትም አይወርድባቸውም። በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና። ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” [ራዕይ 14÷1-5፤ 15÷3፤ 7÷14-17]። GCAmh 467.1
በዘመናት ሁሉ የአዳኙ ምርጦች በፈተና ትምህርት ቤት ተምረዋል፤ ተቀጥተዋል። በምድር ላይ በጠባብ መንገዶች ተማሩ፤ በመከራ እቶን እሳት ነጠሩ፤ ስለ የሱስ ተቃውሞን፣ ጥላቻን፣ ስም ማጥፋትን ቻሉ። ከባድ በሆኑ ጥሎች ውስጥ ተከተሉት፤ ራስን መካድን በጽናት አለፉ፤ መራራ ቅሬታዎችን ተለማመዱ። በራሳቸው የህማም ልምምድ የኃጢአትን ክፋት፣ ኃይል፣ ኩነኔና መከራን ተማሩ፤ ተጸይፈውም ይመለከቱታል። ለመፍትሄው [ለኃጢአት] የተከፈለው መጠን የለሽ መስዋዕት ስሜት፣ በራሳቸው እይታ፣ የዋህ ያደርጋቸዋል። ያልወደቁ [የኃጢአት ተጠቂ ሆነው የማያውቁ] እነርሱ ዋጋ ሊሰጡት በማይችሉት ሁኔታ ልባቸውን በምስጋናና በውዳሴ ይሞላቸዋል። ብዙ ያፈቅራሉ፤ በብዙ ይቅር ተብለዋልና። የክርስቶስ መከራዎች ተቋዳሾች ሆነው ከእርሱ ጋር የክብር ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ገጣሚ ሆነዋል። GCAmh 467.2
የእግዚአብሔር ወራሾች ከትናንሽ ክፍሎች፣ ከደሳሳ ጎጆዎች፣ ከወህኒ ቤቶች፣ ከመታረጃ ቦታዎች፣ ከተራሮች፣ ከምድረበዳ፣ ከምድር ጉድጓድ፣ ከባህርም ዋሻ መጡ። በምድር ላይ “ሁሉን ያጡ፣ መከራን የተቀበሉና የተጨነቁ” ነበሩ። ለሰይጣን አጭበርባሪ መጠይቆች እጅ አንሰጥም በማለት ፀንተው በመቆማቸው መጥፎ ስም ተሸክመው ሚሊዮኖች ወደ መቃብር ወርደዋል። በፍጡር ፍርድ ሸንጎዎች እጅግ አሰቃቂ ወንጀለኞች ተብለው ተፈርዶባቸዋል። አሁን ግን “እግዚአብሔር [ራሱ] ፈራጅ ነው [God is judge Himself]” [መዝ 50÷6]። አሁን የምድር ውሳኔዎች ተገላብጠዋል፤ “የሕዝቡን ስድብ ያስወግዳል” [ኢሳ 25÷8]። “እግዚአብሔር የተቤዣቸው የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል።” “በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በለቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፣ በሃዘንም መንፈስ ፈንታ የምስጋን መጎናፀፊያ ይሰጣቸው ዘንድ አለው” [ኢሳ 62÷12፤ 61÷3]። ከእንግደህ ወዲህ ደካሞች፣ የተጎዱ፣ የተበተኑ፣ የተጨቆኑ አይሆኑም። ከአሁን ጀምሮ ሁልጊዜ ከእግዚአብር ጋር ይሆናሉ። የምድር ቁጥር አንድ ክቡራን ከለበሱት የሚበልጥ ልብስ ለብሰው በዙፋኑ ፊት ቆመዋል። በምድር ንጉሠ ነገሥታት ከተደፋው ዘውድ ይልቅ እጅግ ያማረ ዘውድ ተደፋላቸው። የህማምና የለቅሶ ዘመናት ላይመጡ ተቋጭተዋል። የክብር ንጉሥ ከሁሉም ፊት እንባን አብሷል፤ እያንዳንዱ የኃዘን መንስኤ ተወግዷል። በሚያውለበልቡት የዘንባባ ቅርንጫፍ መሃል ጥርት ያለ፣ ጣፋጭና የተስማማ መዝሙር ዘመሩ፤ የምስጋናው መዝሙር ወደ ሰማይ ጣራ እስኪደርስ ድረስ እያንዳንዳቸው ዘመሩ። “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” ሁሉም የሰማይ ነዋሪዎችም እንዲህ ብለው መለሱ፦ “አሜን፣ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን።” [ራዕይ 7÷10፣12]። GCAmh 467.3
በዚህ ሕይወት መረዳት የምንጀምረው ግሩም የሆነውን የመዳንን ርዕሰ-ጉዳይ ብቻ ነው። በውስኑ ማስተዋላችን መስቀል ላይ የሚገናኙትን ውርደትንና ክብርን፣ ሕይወትንና ሞትን ፍርድንና ምሕረትን ከልብ እናሰላስል ይሆናል፤ ሆኖም የአዕምሯችን ኃይላት እስከ ጥግ ቢለጠጡ እንኳ አስፈላጊነቱን ሙሉ ለሙሉ መረዳት ይሳነናል። የማዳንን ፍቅር ወርዱንና ስፋቱን፣ ጥልቀቱንና ቁመቱን መረዳት ያገኘነው በድንግዝግዝ ነው። በዋጋ የተገዙት፣ እንደታዩ በሚያዩበት፣ እንደታወቁም በሚያውቁበት ጊዜም ቢሆን የማዳን እቅድ ሙሉ ለሙሉ መረዳት አያገኝም፤ ነገር ግን ማብቂያ በሌላቸው ዘመናት ውስጥ፣ ለሚደነቅና ሐሴት ለሚያደርግ አዕምሮ አዳዲስ እውነቶች በቀጣይነት ይገለጣሉ። የምድር ኃዘኖች ህማሞችና ፈተናዎች ቢያበቁም፣ መንስኤውም ቢወገድ፣ ሁልጊዜ፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መቼም ቢሆን ድነታቸው ያስከፈለው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ፣ ጥርት ያለ፣ በሳል እውቀት ይኖራቸዋል። GCAmh 468.1
የክርስቶስ መስቀል፣ ለዳኑት በዘላለም ዘመናት ሁሉ ስነ-ሕይወታቸውና (ሳይንሳቸውና) ዝማሬያቸው ይሆናል። በከበረው ክርስቶስ ውስጥ፣ የተሰቀለውን ክርስቶስን ያያሉ፤ ኃይሉ የማይቆጠሩ (በሰፊው የህዋ ግዛት ያሉትን) ዓለማትን የፈጠረና የጠበቀ፣ የእግዚአብሔር ውድ፣ የሰማይ ግርማ፣ ኪሩቤሎችና አንፀባራቂ ሱራፌሎች ያመልኩት ዘንድ ሐሴት የሚያደርጉ እርሱ፦ የወደቀውን የሰው ዘር ያነሳ ዘንድ ራሱን አዋረደ፤ የጠፋው ዓለም ሐዘን ልቡን ሰብሮ፣ በቀራንዮ መስቀል ሕይወቱን ደቁሶ እስኪያወጣው ድረስ የኃጢአትን ኩነኔ፣ ኃፍረትና የአባቱን ፊት መሰወር የቻለ እርሱ፣ ክስተቱ ፈጽሞ የሚረሳ አይሆንም። የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ፣ የመዳረሻዎች ሁሉ ዳኛ ክብሩን ወደ ጎን ብሎ ለሰው ካለው ፍቅር የተነሳ ራሱን ማዋረዱ መቼም ቢሆን የዩኒቨርስን አድናቆትና ፍቅር የሚያተርፍ ነው። የዳኑት ሕዝቦች አዳኛቸውን ሲመለከቱ፣ ፊቱ እያበራ የአብን ዘላለማዊ ክብር ሲመለከቱ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሆነውን ዙፋኑን ሲያዩ፣ መንግሥቱም መጨረሻ እንደሌለው ሲያውቁ፣ በደስታ ሲቃ ይዘምራሉ፦ “ይገባዋል፣ ይገባዋል የታረደው በግ፣ እጅግ በከበረው በራሱ ደም ለእግዚአብሔር ያዳነን።” GCAmh 468.2
የመስቀሉ ምስጢር ሌሎች ምስጢራትን ሁሉ ይፈታል። በፍርሃትና በግርምት የሚሞሉን የእግዚአብሔር መለያ ባህርያት ከቀራንዮ በሚመነጨው ብርሐን ውብና ማራኪ ይሆናሉ። ምሕረት፣ ቸርነትና ወላጃዊ ፍቅር ከቅድስና፣ ከፍርድና ከኃይል ጋር ተዋህደው ይታያሉ። ርቆ፣ ከፍ ከፍ ብሎ፣ የዙፋኑን ግርማ ስንመለከት፣ በደግ መገለጦቹ ባህርይውን እናያለን፤ ከአሁን በፊት ባልሆነ ሁኔታም አባታችን የሚለውን የተወዳጁን መጠሪያ ስያሜ አስፈላጊነት እንገነዘባለን። GCAmh 469.1
በጥበብ መጠን የለሽ የሆነው እርሱ ለድነታችን፣ ልጁን ከመሰዋት በስተቀር ሌላ መንገድ መንደፍ እንዳልተቻለው የሚታይ ይሆናል። ለዚህ መስዋዕትነት ካሳው ደግሞ በዋጋ በተገዙ፣ በቅዱስ፣ በደስተኛና በዘላለማዊ ፍጡራን ምድርን የመሙላቱ ደስታ ነው። ከጨለማ ኃይላት ጋር ያደረገው የአዳኙ ጦርነት ውጤት ለዳኑት የዘላለም ደስታ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚጨምር ነው። አባት በተከፈለው ዋጋ የረካበት የነፍስ ዋጋ ግምት ይህንን ያህል ነው፤ የታላቁን መስዋዕትነቱን ፍሬዎች በማየት ክርስቶስ ራሱ ይረካል። GCAmh 469.2