ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፴፫—የመጀመሪያው ታላቅ ማጭበርበሪያ
ሰብአዊ ዘራችንን ያሳስት ዘንድ ሰይጣን ጥረቶቹን የጀመረው ከጥንታዊው የሰው ልጅ ታሪክ አንስቶ ነው። በሰማይ አመጽን ያነሳሳው እርሱ፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ ባወጀው ጦርነት በምድር ያሉ ነዋሪዎችም ከእርሱ ጋር እንዲያብሩ ፈለገ። አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ ሕይወት ውስጥ ፍጹም የሆነ ደስታ ነበራቸው፤ ይህ እውነት ደግሞ በሰማይ የእግዚአብሔር ሕግ ጨቋኝና የፍጥረታቱን ደህንነት(ጥቅም) የሚፃረር እንደሆነ አድርጎ ሰይጣን ላቀረበው ነጥብ በቋሚነት አፍራሽ ምስክርነት የሚሰጥ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን ለእነዚህ ኃጢአት-የለሽ ጥንዶች የተዘጋጀውን ውብ መጠለያ ሲመለከት ሳለ የቅናት ስሜቱ ተነሳሳ። ከእግዚአብሔር ነጥሎአቸው በራሱ ቁጥጥር ስር ካደረጋቸው በኋላ ምድርን የራሱ ንብረት በማድረግ ልዑሉን የሚጻረር መንግሥቱን እዚሁ ምድር ላይ ለመመስረት ይቻለው ዘንድ ውድቀታቸውን እውን ሊያደርግ ቆረጠ። GCAmh 385.1
ሰይጣን በእውነተኛ ማንነቱ ራሱን ገልጦ ቢሆን ኖሮ፤ አዳምና ሔዋን ይህንን አደገኛ ጠላት አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው ነበርና፣ ወዲያውኑ ይገፈተር (ተቃውሞ ይገጥመው) ነበር ። ነገር ግን አላማውን በበለጠ ብቃት ማጠናቀቅ ይችል ዘንድ እቅዱን ደብቆ በፅልመት ውስጥ ይሰራ ነበር። በዚያን ጊዜ እጅግ አስደናቂ ተፈጥሮአዊ ገጽታ የነበረውን እባብን እንደ መሳሪያው አድርጎ በመጠቀም፣ ሔዋንን እንዲህ አላት፦ “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?።” [ዘፍ 3÷1]። ሔዋን ከፈታኙ ጋር ክርክር ከማድረግ ተቆጥባ ቢሆን ኖሮ፣ ከአደጋ በተጠበቀች ነበር፤ ነገር ግን እርግጠኛ ባልሆነችበት ጉዳይ ላይ ከጠላት ጋር ድርድር ስታደርግ የጮሌ ማታለያው ሰለባ ሆነች። ዛሬም ብዙዎች የሚሸነፉት እንዲሁ ነው። የእግዚአብሔርን መጠይቅ በተመለከተ ይጠራጠራሉ፤ ይከራከራሉም፤ መለኮታዊ ትእዛዛትን ከመጠበቅ ይልቅ፣ የሰይጣን መሳሪያዎች በውስጣቸው የደበቁትን የሰብአዊ ፅንሰ-ሐሳቦችን ይቀበላሉ። GCAmh 385.2
‘’ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፣ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።’’ [ዘፍ 3÷2-5]። እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ አወጀ፤ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው የበለጠ ጥበብ ባለቤት እንደሚሆኑና ላቅ ያለ የሕያውነት ደረጃ እንዲኖራቸው እንደሚያስችላቸው ነገራቸው። ሔዋን ለፈተና እጅ ሰጠች፤ በእርሷም ተጽእኖ አዳም ኃጢአት ይሰራ ዘንድ ተመራ። እግዚአብሔር የተናገረው ከምሩ(ከልቡ) እንዳልሆነ ሲነግራቸው የእባቡን ቃላት ተቀበሉ፤ ፈጣሪያቸውን አላመኑም፤ ነጻነታቸውን እየገደበባቸው እንደሆነ ተሰማቸው፤ ሕጉን በመጣስም ታላቅ ጥበብና ክብር እንደሚያገኙ አሰቡ። GCAmh 385.3
ነገር ግን አዳም፣ ኃጢአት ከሰራ በኋላ፣ “ከዚህ ፍሬ በበላህ ጊዜ በእርግጥ ትሞታለህ” የሚሉት ቃላት ትርጉም ምን ሆነው አገኛቸው? ሰይጣን እንዳሳመነው ከፍ ወዳለ የሕያውነት ደረጃ የሚያደርሱት ሆነው GCAmh 385.4
አገኛቸው? ሕግን በመተላለፍ በእርግጥ ታላቅ መልካም ነገር እንደሚገኝ፣ ሰይጣንም የሰብዓዊ ዘር ረዳት መሆኑ እንደሚረጋገጥ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን መለኮት በሰጠው ብይን ትርጉም ውስጥ አዳም ይህንን [የጠበቀውን ትርጉም] አላገኘም። የኃጢአቱ መቀጮ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ወደ ተገኘበት ወደ አፈር እንዲመለስ አወጀ፣ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” [ዘፍ 3÷19] አለ። “ዓይናችሁ ይከፈታል” በማለት ሰይጣን የተናገረው እውነት የተረጋገጠው በዚህ አተረጓጎም ብቻ ነበር፦ አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ካመጹ በኋላ ሞኝነታቸውን ያስተውሉ ዘንድ ዓይናቸው ተከፈተ፤ ክፋትን አወቁ፤ የመተላለፍንም መራራ ፍሬ ቀመሱ። GCAmh 385.5
በኤደን መካከል የሕይወት ዛፍ ነበረች፤ ፍሬዋም ሕይወት ዘላለማዊ ሆና እንድትቀጥል የማድረግ ኃይል ነበራት። አዳም ለእግዚአብሔር ታዛዥ እንደሆነ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ፣ ወደዚች ዛፍ በነጻነት የመድረስና ለዘላለም የመኖር ዕድል ይኖረው ነበር። ኃጢአት በሰራ ጊዜ ግን የሕይወትን ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ተከለከለ፤ የሞት ሰለባም ሆነ። “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለው መለኮታዊ ብይን ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ የሚያመለክት ነው። GCAmh 386.1
መታዘዝን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጦ የተገባው የዘላለማዊነት (immortality) ተስፋ፣ ሕግን በመተላለፍ ቅጣት ምክንያት ተወሰደ። አዳም እርሱ ለራሱ የሌለውን ለዘሮቹ ማስተላለፍ አልቻለም። እናም እግዚአብሔር በልጁ መስዋዕትነት ዘላለማዊነትን ይደርሱበት ዘንድ በሚችሉበት ሁኔታ ባያቀርብላቸው ኖሮ በኃጢአት ለወደቀው ሰብአዊ ዘር አንዳች ተስፋ ባልኖረ ነበር። “እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ”፤ ነገር ግን ክርስቶስ “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሐን አውጥቶአል።” [ሮሜ 5÷12፤ 2 ጢሞ 1÷10]። እናም ዘላለማዊነትን ማግኘት የሚቻለው በክርስቶስ ብቻ ነው። የሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” [ዮሐ 3÷36]። ቅድመ ሁኔታዎቹን እሺ ካለ እያንዳንዱ ሰው የዚህ ተመን የሌለው በረከት ባለቤት ይሆናል። “በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት የሚፈልጉ” ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይቀበላሉ [ሮሜ 2÷7]። GCAmh 386.2
ባለመታዘዝ ሕይወት እንደሚሆንለት ለአዳም ቃል የገባለት ታላቁ አታላይ ብቻ ነበር። በኤደን ገነት ለሔዋን “ሞትን አትሞቱም” ተብሎ በእባቡ የተነገረው አዋጅ ስለ ነፍስ አለመሞት (immortality) የተሰበከ የመጀመሪያው ሰብከት ነበር። ይሁን እንጂ በሰይጣን ስልጣን ላይ ብቻ የተመረኮዘው ይህ አዋጅ በክርስትናው ዓለም መድረኮች እያተስተጋባ፣ ልክ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በተቀበሉበት ፍጥነትና ቅለት፣ በአብዛኛው የሰው ዘር ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ ነው። “ኃጢአትን የምትሰራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” [ሕዝ 18÷20] የሚለው መለኮታዊ ብይን ተለውጦ ኃጢአት የሰራች ነፍስ አትሞትም፤ ለዘላለም ትኖራለች እንጂ” የሚል ትርጉም እንዲኖረው ተደርጓል። ሰዎች የሰይጣንን ቃላት በተመለከተ በቀላሉ ለመቀበል እንዲያሰፈስፉ ያደረጋቸውን እንግዳ መነሁለል (መንፈዝ)፤ የእግዚአብሔርን ቃላት በተመለከተ ደግሞ እጅግ እምነት የለሽ መሆናቸውን ስናይ ከመደነቅ ውጪ ሌላ ማለት አይቻለንም። GCAmh 386.3
የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ወደ ሕይወት ዛፍ ይደርስ ዘንድ ነፃ ቢሆን ኖሮ፣ ለዘላለም በኖረ፤ ኃጢአትም ዘላለማዊ በተደረገ ነበር። ነገር ግን ኪሩቤልና የሚንበለበለው ሰይፍ “ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ” ዘጋው [ዘፍ. 3÷24]፤ ማንም የአዳም ዘር የሆነ ያንን አጥር አልፎ ሕይወት ሰጭውን ፍሬ እንዲበላ የተፈቀደለት የለም፤ ስለዚህ ዘላለም የሚኖር ኃጢአተኛ የለም። GCAmh 386.4
ነገር ግን ከውድቀት በኋላ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው የማይሞት ነው የሚለውን እምነት በድግግሞሽ ያስተምሩ ዘንድ ልዩ ጥረት እንዲያደርጉ ሰይጣን ለመላእክቱ ትዕዛዝ ሰጠ። ሰዎች ይህንን ስህተት እንዲቀበሉ ካደረጓቸው በኋላም፣ ኃጢአተኞች በዘላለማዊ ስቃይ ውስጥ ይኖራሉ ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ ይመሯቸው ዘንድ ነበራቸው። አሁን የጨለማው ንጉሥ፣ በወኪሎቹ በኩል እየሰራ፣ እግዚአብሔር ማለት የማያስደስቱትን ሁሉ ወደ ገሃነም በማጥለቅ ለዘላለም የቁጣው ገፈት ቀማሾች የሚያደርግ፣ ተበቃይ አምባገነን እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ሊነገር በማይችል ሰቆቃ እየተሰቃዩ፣ በነበልባል ውስጥ ሲንፈራፈሩ፣ ፈጣሪያቸው ከላይ ሆኖ ቁልቁል ሲመለከታቸው የሚረካ አስመስሎ ያቀርበዋል። GCAmh 387.1
በእንዲህ ሁኔታ ሊቀ-ክፋት የራሱን የባህርይ መለዮዎች [ካባ] ወስዶ ፈጣሪና የሰው ልጅ ረዳት የሆነውን እግዚአብሔርን ያለብሰዋል። ጨካኝነት ሰይጣናዊ ነው። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ኃጢአት በመጀመሪያው ታላቅ አማጺ በኩል እስኪገባ ድረስ እርሱ የፈጠረው ሁሉ ንጹሕ፣ ቅዱስና ውብ ነበር። ኃጢአትን ያደርግ ዘንድ ሰውን የሚፈትን ጠላት ሰይጣን ራሱ ነው፣ የሚቻለው ከሆነም ያጠፋዋል፤ ተጠቂውን በቁጥጥሩ ስር እንዳደረገ እርግጠኛ ሲሆን፣ ባደረሰበት ጥፋት ይፈነድቃል። ቢፈቀድለትስ መላውን ሰብአዊ ዘር ጠራርጎ ወጥመዱ ውስጥ ባስገባውና፣ የመለኮት ኃይል ጣልቃ ባይገባ አንድም የአዳም ወንድ ወይም ሴት ልጅ ማምለጥ ባልቻለ/ች ነበር። GCAmh 387.2
በፈጣሪ ላይ ያላቸውን መተማመን አናውጦ የአስተዳደሩን ጥበብና የሕጉን ፍትሐዊነት እንዲጠራጠሩ በማድረግ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችን እንዳሸነፋቸው ሁሉ፣ ሰይጣን ዛሬም ሰዎችን በተመሳሳይ መንገድ ለማሸነፍ እየጣረ ነው። የራሳቸው ተንኮልና ዓመጽ ተገቢ እንደሆነ ማሳመን ይቻላቸው ዘንድ ሰይጣንና ልዑኮቹ እግዚአብሔር ከእነርሱ እጅግ የከፋ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። ፍትሃዊ ላልሆነ አስተዳዳሪ አልገዛም በማለቱ ምክንያት ከሰማይ እንዲባረር በመደረጉ ታላቅ ግፍ እንደተፈጸመበት አድርጎ በማስመሰል፣ ታላቁ አታላይ የራሱን ዘግኛኝ የሆነ የባህርይ ጭካኔ በሰማዩ አባታችን ላይ ለማላከክ ይጥራል። በያህዌ ጥብቅ ድንጋጌዎች አማካኝነት ከወደቀባቸው የባርነት ቀንበር ይልቅ፣ ለስለስ ባለው አገዛዙ ሥር ቢሆኑ ሊያጣጥሙ የሚችሉትን ነፃነት በዓለም ፊት ያቀርባል። እንዲህም በማድረግ ነፍሳት ለእግዚአብሔር ካላቸው ታማኝነት እንዲርቁ በማታለል ይሳካለታል። GCAmh 387.3
በአጭር የምድራዊ ሕይወት ቆይታ ለተሰራ ኃጢአት፣ እግዚአብሔር እስከኖረ ድረስ [ለዘላለም] ሊሰቃዩ እንዳላቸው፤ ኃጥዕ ሙታን በሚቃጠል ገሃነም ውስጥ በእሳትና በዲን ለዘላለም በከፍተኛ ስቃይ የሚኖሩ እንደሆነ የሚያስተምረው አስተምህሮ ለእያንዳንዱ የፍቅርና የምሕረት ስሜት፣ እኛ ባለን የፍትሕ መረዳት እንኳ እንዴት የሚቀፍ ነው! ። ይሁን እንጂ ይህ አስተምህሮ አሁንም በሰፊው የሚስተማርና በብዙ የክርስትና መሰረተ-እምነቶች ውስጥ አሁንም ሰፍኖ ያለ ነው። አንድ ስነ-መለኮት የተማረ ዶክተር እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “የገሃነም እሳትን ስቃይ መመልከት የቅዱሳንን ደስታ ለዘላለም እየጨመረው ይሄዳል። በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ የተወለዱ፣ ተመሳሳይ ተፈጥሮ ያላቸው ሌሎች ሰዎች በእንደዚያ አይነት ስቃይ ውስጥ ሆነው፣ በአንጻሩ ደግሞ እነርሱ ተለይተው ሲመለከቱ ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ እንዲገባቸው ያደርጋቸዋል።” ሌላው ደግሞ እነዚህን ቃላት ነበር የተጠቀመው፦ “በቁጣ እቃዎች ላይ የኩነኔው አዋጅ ለዘላለም ሲፈጸም፣ ጢሳቸው ወደ ሰማይ ሲወጣ የምሕረት እቃዎች እያዩት ሲሆን፤ ቅዱሳንም ከእነዚህ አሳዛኝ ፍጥረቶች ጎን ከመሰለፍ ይልቅ፣ አሜን፣ ሃሌሉያ! ጌታ ይመስገን!” ይላሉ።” GCAmh 387.4
ለመሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንዲህ ያለው ትምህርት የሚገኘው የት ላይ ነው? በሰማይ ያሉት የዳኑ ቅዱሳን የኃዘኔታና የርኅራኄ ስሜቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ይጠፋልን? ሌላው ቢቀር የተለመደው ሰብአዊነት እንኳ ከእነርሱ ይወሰዳልን? እነዚህ ስሜቶች ለሁኔታዎች ስሜታዊ አጸፋ ወደማይሰጥ ደንታ ቢስነት ወይም አረመኔአዊ ጨካኝነት ይለወጣሉን? በፍጹም፤ በፍጹም! እንዲህ አይደለም!። የእግዚአብሔር መጽሐፍ አስተምህሮ እንዲህ አይደለም። ከላይ በትህርት ጥቅስ ውስጥ የቀረቡትን ሃሳቦች ያቀረቡዋቸው የተማሩ፣ እንዲያውም ሃቀኛ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በሰይጣን ማደናገሪያዎች የተሞኙ ናቸው። ፈጣሪያችንን ሳይሆን እርሱን የሚገልጡትን የመራራነትና የክፋት ቀለም ቋንቋውን በመቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጠንካራ አገላለጾችን በተሳሳተ መልኩ እንዲያስተውሉ ያደርጋቸዋል። “እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእሥራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?” [ሕዝ. 33÷11]። GCAmh 388.1
የማያቋርጠውን የኃጢአተኞች ስቃይ እየተመለከተ ሐሴት ያደርጋል፤ በሲኦል ነበልባል ውስጥ የያዛቸው ፍጡሮቹ እየተሰቃዩ ሲያቃስቱ፣ በስቃይ ሲቃ ሲጮሁና በቁጣ ሲራገሙ እየተዝናና ይደሰታል የሚለውን ሃሳብ ብንቀበል፤ እግዚአብሔር የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነዚህ የሰቆቃ ድምጾች ተመን የሌለው ፍቅር ባለቤት ለሆነው አምላክ ጆሮ እንደ ሙዚቃ ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? በኃጢአተኞች ላይ ማብቂያ የሌለው ስቃይ መድረሱ በዓለማት ሰላምና ሥርአት ላይ ጥፋት ባመጣው በኃጢአት ላይ እግዚአብሔር ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ እንደሆነ ይነገራል። ኦህ ምን አይነት አስከፊ ስድብ ነው! ኃጢአትን የሚያስቀጥልበት ምክንያት [እሳቱ እንዳይጠፋ የሚያደርገው] እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ለማሳየት ነው እንደማለት ነው። በእነዚህ የስነ-መለኮት ሊቃውንቶች አስተምህሮ መሰረት፣ ምሕረት ይገኛል ተብሎ ተስፋ የማይደረግበት የማያባራ የማሰቃየት ሥራ፣ ጎስቋላ ኃጢአተኞችን ያሳብዳቸውና ቁጣቸውን በመራገምና እግዚአብሔርን በመሳደብ ሲገልጹ የኩነኔአቸውን ሸክም ለዘላለም በላይ በላዩ እየጨመሩበት ይሄዳሉ። ዲካ በሌላቸው ዘመናት ኃጢአት እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ የእግዚአብሔር ክብር አይጨምርም። GCAmh 388.2
የዘላለማዊ ስቃይ (eternal torment) ኑፋቄ ያስከተለውን ክፋት ለመገመት ከፍጡር አእምሮ አቅም በላይ ነው። በፍቅርና በመልካምነት የተሞላው፣ በርህራኄ የተትረፈረፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይማኖት በብዙ መላምቶች ደብዝዟል፤ በስህተት ተሸፍኖአል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ባህርይ በምን አይነት የውሸት ቀለሞች እንደቀባ ስናሰላስል፣ መሐሪው ፈጣሪያችን መፈራቱ፣ በታላቅ ስጋት መታየቱ እንዲያውም መጠላቱ ያስገርመናልን? ከመድረክ ላይ በሚሰጡ ትምህርቶች ወደ ዓለም የሚሰራጩት አስደንጋጭ የእግዚአብሔር ገፅታዎች በሺዎች፣ አዎ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተጠራጣሪዎችና ከሃዲዎች እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። GCAmh 388.3
የዘላለማዊ ሥቃይ ጽንሰ-ሃሳብ ባቢሎን የዝሙትዋን ቁጣ ወይን ጠጅ አሕዛብን ሁሉ ካጠጣችበት የስህተት አስተምህሮዎች ውስጥ አንዱ ነው [ራእይ 14÷8፤ 17÷2)። የክርስቶስ አገልጋዮች ይህን ኑፋቄ ተቀብለው ከተቀደሰው መድረክ ላይ መስበካቸው በእርግጥ ምሥጢር ነው። ሐሰተኛውን ሰንበት እንደተቀበሉ ሁሉ ይህንንም የተቀበሉት ከሮም ነው። እውነት ነው፣ ይህንን [ኑፋቄ] ታላላቅና መልካም ሰዎች አስተምረውታል። ሆኖም በዚህ ርዕስ ላይ ያለው ብርሐን ለእኛ የመጣውን ያህል ለእነርሱ አልደረሳቸውም። እነርሱ ኃላፊነት የነበረባቸው በዘመናቸው ስለተገለጠላቸው ብርሐን ብቻ ነበር፤ በዘመናችን ስለሚንፀባርቀው ብርሐን ደግሞ እኛ ተጠያቂዎች ነን። ከእግዚአብሔር ቃል ምስክር ፊታችንን አዙረን አባቶቻችን ያስተማሩአቸው በመሆናቸው ምክንያት የተሳሳቱ አስተምህሮዎችን የምንቀበል ከሆነ በባቢሎን ላይ የታወጀው ፍርድ ተካፋዮች እንሆናለን፤ የዝሙቷን ወይን ጠጅም እየጠጣን ነን። GCAmh 389.1
የዘላለማዊ ስቃይ አስተምህሮ የማይዋጥላቸው አያሌ ወገኖች ወደ ተቃራኒ ስህተት ተመርተዋል። ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር የፍቅርና የርኅራኄ ተፈጥሮ ያለው እንደሆነ አድርገው ሲያቀርቡት ያስተውላሉ። እናም ጌታ ፍጡራኑን ለዘላለም ለሚነድ የሲኦል እሳት አሳልፎ ይሰጣቸዋል ብለው ማመን ይሳናቸዋል። ሆኖም ነፍስ በተፈጥሮዋ የማትሞት ናት የሚለውን መረዳት በመያዝ፣ በመጨረሻ የሰው ዘር በሙሉ ይድናል ወደሚለው መደምደሚያ ከመድረስ ውጪ ሌላ አማራጭ አይታያቸውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ማስፈራሪያዎች እንዲሁ ሰዎችን በማስደንገጥ ወደ መታዘዝ እንዲመጡ ለማድረግ እንጂ በተግባር የሚፈፀሙ እንዳልሆነ አድርገው ብዙዎች ያስባሉ። በዚህ አኳኋንም ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር የሚፈለግበትን መስፈርቶች ከቁም ነገር ሳይቆጥር፤ በራስ ወዳድ ፍላጎት ውስጥ መኖር የሚችል ሆኖ በመጨረሻ ግን እግዚአብሔር በቸርነት እንደሚቀበለው ይጠብቃል ማለት ነው። ይህ በእግዚአብሔር ምሕረት ያለቅጥ የሚደገፍ፣ ሆኖም ፍርዱን ቸል የሚል አስተምህሮ ሥጋዊ ልብን ደስ በማሰኘት ክፉዎች በኃጢአታቸው የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደርጋል። GCAmh 389.2
ሁሉም ሰው ይድናል (universal salvation) የሚለው [አስተምህሮ] አማኞች ነፍስ አውዳሚ የሆነውን ትምህርታቸውን ለማፅናት ሲሉ መጽሐፍ ቅዱሳትን እንዴት አጣመው እንደሚተረጉሟቸው ለማሳየት የራሳቸውን ንግግር መጥቀሱ ብቻ አስፈላጊ ይሆናል። በድንገተኛ አደጋ ሳቢያ ወዲያውኑ የሞተ የአንድ ኃይማኖት የለሽ ወጣት ሥርዓተ ቀብር በተከናወነበት ወቅት አንድ ሁሉ ሰው ይድናል በማለት የሚያምን አገልጋይ (ፓስተር) ለማንበብ የመረጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ዳዊትን በተመለከተ የተጻፈውን ነበር፤ “.…ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ[አልና]” (“He was comforted concerning Amnon, seeing he was dead.”) ይላል [2ኛ ሳሙ 13÷39)። GCAmh 389.3
ተናጋሪው በመቀጠል፦ “በኃጢአት እንዳሉ ዓለምን ትተዋት የሚሄዱ፣ ምናልባት በሰካራምነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የሚሞቱ፣ የወንጀል ቀይ ቀለም ከመጎናጸፊያቸው ሳይታጠብ የሚሞቱ፣ ወይም ደግሞ እንደዚህ ወጣት ንስሐ ሳይገቡ ወይም የኃይማኖትን ልምምድ ሳያጣጥሙ የሚሞቱ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በተደጋጋሚ እጠየቃለሁ። ለእኛ መጽሐፍ ቅዱሳት የሚሉት በቂያችን ነው፤ መልሶቻቸው ለአሰቃቂው ችግር መፍትሄ ይሰጣል። አምኖን ሲበዛ ኃጢአተኛ ነበር፤ የማይፀፀት ነበር፣ እንዲሰክር ተደረገ፣ እንደሰከረም ተገደለ። ዳዊት የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ በሚመጣው ዓለም ለአምኖን መልካም ይሁንለት ክፉ አውቆ የነበረ መሆን አለበት። የልቡ ስሜት መግለጫዎቹ ምን ነበሩ? ‘ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።’ GCAmh 389.4
“እናም ከዚህ ንግግር የምንገነዘበው ምክንያታዊ ድምዳሜ ምንድን ነው? ማብቂያ የሌለው ሥቃይ የዳዊት እምነት(religious belief) አካል ያልነበረ መሆኑን አይደለምን? በአእምሮአችን የፀነስነው ሀሳብ ይህ ነው (የተረዳነው ይህ ነው)፤ ብሎም የበለጠ ደስ የሚያሰኝ፣ በተሻለ እውቀት ላይ የተመሠረተና የበለጠ በጎ አድራጊ የሆነውን ወደር የማይገኝለትን ለሁሉ የሚሆን ንጽህናና ሰላም ጽንሰ ሀሳብ የሚደግፍ ድል አድራጊ መከራከሪያ እዚህ እናገኛለን። ልጁ መሞቱን ሲያይ ተፅናና። ለምን? ምክንያቱም ዳዊት በትንቢት አይን አሻግሮ ሲያይ ግርማ ሞገስ የተላበሰውን የወደፊት መመልከት ችሎ ነበር፤ እናም ያ ልጅ ከሁሉም ፈታኝ ነገር ነጻ ሆኖ፣ ከባርነት ተፈትቶና ከኃጢአት ብልሹነቶች ፀድቶ፤ በበቂ ሁኔታ ቅዱስና አዋቂ ከተደረገ በኋላ ወደ ላይ ከወጡና ሀሴት ከሚያደርጉ መናፍስት ህብረት እንዲቀላቀል ሲደረግ አየ። የእርሱ ብቸኛ መፅናናት ተወዳጅ ልጁ ካለበት የኃጢአትና የሥቃይ ኑሮ ተገላግሎ እጅግ ከፍታ ያለው የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በፅልመት በተጋረደው ነፍሱ ላይ ወደሚያርፍበት፣ አእምሮውም የመንግሥተ ሰማያትን ጥበብና የማይሞት ፍቅርን ጣፋጭ ደስታ ይቀበል ዘንድ ወደሚከፈትበት፣ ሰማያዊውን ውርስ እረፍትና ህብረት ከቀሩት ጋር ለማጣጣም በተቀደሰ ተፈጥሮ በመዘጋጀቱ ነው።” GCAmh 390.1
“የሰማይ ጽድቅ በዚህ [ምድር] ሕይወታችን ልንሠራው በምንችለው ምንም ነገር ላይ፣ አሁን በሚሆነው የልብ ለውጥ፣ አሁን በምናምነው እምነትም ሆነ በምንመሰክረው ሐይማኖት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ፣ እንድናምን ያደርገናል።” GCAmh 390.2
እንዲህም በማለት ታማኝ [ነኝ ባዩ] የክርስቶስ አገልጋይ በኤደን በነበረው እባብ የተነገረውን ሐሰት እንደገና ይደግመዋል፦“ሞትን አትሞቱም።” “…ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይናችሁ እንድትከፈት። እንደ አምላክም ትሆናላችሁ።” እንዲህም በማለት ያውጃል፣ እጅግ የከፉቱ ኃጢአተኞች - ነፍሰ ገዳዩ፣ ሌባው እንዲሁም አመንዝራው - ከሞት በኋላ ወደ ዘላለማዊ ተድላ ይገቡ ዘንድ እንደሚዘጋጁ ይናገራል። GCAmh 390.3
ቅዱሳት መጻሕፍትን አጣማሚው ከምን ተነስቶ ነው ከእንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ የደረሰው? ለመለኮታዊ አቅርቦት ፈቃድ ዳዊት እንደታዘዘ ከሚገልጸው አንድ አረፍተ ነገር ላይ ብቻ በመነሳት ነው። “ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።” ። ጥልቅ ኃዘኑ በጊዜ ብዛት ቀንሶለት ሃሳቡ ከሞተው [አምኖን] ሃሳቡ ተመልሶ፣ ከሰራው ወንጀል ቅጣት የተነሳ ፈርቶ በራሱ ወደሸሸው፣ በሕይወት ወዳለው ልጁ [አቤሴሎም] ዞረ። ከቅርብ ዘመዱ ጋር ዝሙት ፈጻሚው፣ ሰካራሙ አምኖን እንደሞተ፣ ኃጢአት ከሌለባቸው መላዕክት ጋር ይቀላቀል ዘንድ ወደሚነጻበትና ወደሚዘጋጅበት የተድላ ሥፍራ ወዲያውኑ እንደተጓጓዘ የሚያስረዳው መረጃ እንግዲህ ይህ ነው! በእርግጥም የሥጋዊውን ልብ በደንብ እንዲያረካ ሆኖ የተዘጋጀ ደስ የሚያሰኝ ተረት! ይህ የሰይጣን የራሱ አስተምህሮ ነው፤ ሥራውንም በብቃት ያከናውንለታል። በእንደዚህ አይነት ትምህርት አማካኝነት ርጉምነት ቢበዛ ልንደነቅ ይገባናልን? GCAmh 390.4
ይህ ሐሰተኛ መምህር የተከተለው መንገድ የሌሎች የብዙዎችን ሁኔታ የሚገልጽ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ቃላት ከተዛማች ትርጉማቸው ይነጠላሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እንዲገልጹት ከሚፈለግባቸው ማብራሪያ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ትርጉም ያላቸው ሆነው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ የተነጠሉ ምንባቦች ተጣመው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ መሰረት የሌላቸው አስተምህሮዎች ማስረጃ ሆነው ጥቅም ላይ ይውላሉ። የሰከረው አምኖን ሰማይ ቤት እንዳለ እንደማስረጃ ሆኖ የቀረበው ምስክር፣ አንድም ሰካራም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርስ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽና በማያጠራጥር ሁኔታ የሠፈረውን ቃል በቀጥታ የሚቃረን፣ ኢምንት መደምደሚያ ነው [1ኛ ቆሮ 6÷10)። ተጠራጣሪዎች፣ እምነት የለሾችና በሁሉም ነገር ላይ ጥያቄ የሚያነሱ እነርሱ እውነትን ወደ ሐሰት የሚለውጡት በእንዲህ አይነት መንገድ ነው። እልፍ አእላፋትም ትክክል በሚመስል ማደናጋሪያቸው ተታለው በሥጋዊ የደህንነት አልጋ ላይ እየተወዛወዙ እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ተደርገዋል። GCAmh 391.1
የሁሉም ሰው ነፍስ በሕልፈት ሰዓት በቀጥታ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምትሄድ መሆኑ እውነት ቢሆን ኖሮ በሕይወት ከመኖር ይልቅ ሞትን አብልጠን እንመኝ ነበር። በዚህ እምነት ምክንያት ብዙዎች ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ ተመርተዋል። መከራ፣ ግራ መጋባትና ኃዘን እጅግ በሚበረታበት ጊዜ በቀላሉ የሚበጠሰውን የሕይወት ገመድ ቆርጦ መጨረሻ ወደሌለው ዓለም ተድላ መምጠቅ ቀላል ነገር ይመስላል። GCAmh 391.2
ሕጉን የሚተላለፉትን እንደሚቀጣ እግዚአብሔር በቃሉ የማያወላውል ማስረጃ ሰጥቷል። እግዚአብሔር እጅግ ሲበዛ መሐሪ ከመሆኑ የተነሳ በኃጢአተኛ ላይ ፍርዱን ተግባራዊ አያደርግም ብለው ራሳቸውን የሚሸነግሉ እነርሱ የቀራንዮን መስቀል መመልከት ብቻ ይበቃቸዋል። አንዳች ነቁጥ የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ሞት “የኃጢአት ዋጋ ሞት” መሆኑን፣ እያንዳንዱም የሕገ-እግዚአብሔር መተላለፍ ተገቢውን ቅጣት እንደሚቀበል ይመሰክራል። ልቡ እስኪሰነጠቅ፣ ሕይወቱም እስክትደቅ ድረስ የመተላለፍን ኩነኔና የአባቱን ፊት መሰወር ተሸከመ ። ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው ኃጢአተኞች እንዲድኑ ነበር። የሰው ልጅ በሌላ በምንም አይነት መንገድ ከኃጢአት ቅጣት ነፃ ሊሆን አልቻለም። በዚህ ከባድ ዋጋ (cost) የተበረከተው ስርየት ተካፋይ ለመሆን የማይፈልግ እያንዳንዱ ነፍስ የመተላለፍን ኩነኔና ቅጣት ራሱ በግሉ መሸከም ግድ ይሆንበታል። GCAmh 391.3
ሁሉም ሰው ይድናል የሚለውን አስተምህሮ የሚደግፈው ሰው፣ ቅዱስ፣ ደስተኛ መላእክት ሆነው በሰማይ እንዳሉ ስለሚነግረን እግዚአብሔርን ስለማይመስሉና ንስሐ ስለማይገቡ፣ ስለ እነርሱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ የሚስተምረውን እናጢን። GCAmh 391.4
“እኔ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ በከንቱ እሰጣለሁ” [ራእይ 21÷6፣7]። ይህ የተስፋ ቃል የተሰጠው ለተጠሙ ብቻ ነው። ይህ የሚሰጣቸው የሕይወት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው የሚገነዘቡ፣ ሌላውን ነገር ሁሉ አጥተው እርሱን ያገኙ ዘንድ የሚሹ ብቻ ናቸው። “ድል የነሣ ሁሉን ይወርሳል እኔም አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጄ ይሆናል” [ራዕይ 21÷6፣7]። እዚህ ላይም ቅድመ ሁኔታዎች በግልጽ ተቀምጠዋል። ሁሉን ነገር ለመውረስ ኃጢአትን መቋቋምና ድል መንሳት ይኖርብናል። GCAmh 391.5
ጌታ በነብዩ በኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ሲል ያውጃል፦ “ጻድቅ መልካም እንዲሆንለት በሉት።” “ነገር ግን ወዮ ለዝንጉ [ለበደለኛ]! ክፉም ይደርስበታል። እንደ እጁም ሥራ ፍዳው ይሆንለታል።” (ኢሳ. 3÷10-11)። “ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ” ይላል ጠቢቡ፣ “ዘመኑም ረጅም ቢሆን እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤ ለኀጥእ ግን ደህንነት የለውም” [መክ 8÷12፣13]። “የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን” ኃጢአተኛው ቁጣን ለራሱ እንደሚያከማች ጳውሎስ ይመሰክራል፤ “እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤” “ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል” [ሮሜ 2÷5፣6፣9]። GCAmh 392.1
“ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም” [ኤፌ 5÷5]። “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” [ዕብ 12÷14]። “ትዕዛዙን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው። ስልጣናቸው በሕይዎት ዛፍ ላይ ይሆን ዘንድ። በደጅም ወደ ከተማ ይገባሉ። ውሻዎችና አስማተኞች፣ ሴሰኛዎችም፣ ነፍሰ ገዳዮችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩት፣ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።” [ራእይ 22÷14፣15]። GCAmh 392.2
እግዚአብሔር ስለ ባህርይው፣ ኃጢአትንም ስለሚያስተናግድበት መንገድ ለሰዎች መግለጫ ሰጥቷቸዋል። “እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ” [ዘፀ 34÷6፣7]። “ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።” “በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።” [መዝ 145÷20፤ 37÷38]። የመለኮታዊው መንግሥት ኃይልና ሥልጣን አመፅን ለማጥፋት ሥራ ላይ ይውላል። ሆኖም የአጸፋ ፍርዱ መሐሪ፣ ታጋሽ እና ቸር ከሆነው ከእግዚአብሔር ባህርይ ጋር ፍጹም የተስማማ ይሆናል። GCAmh 392.3
እግዚአብሔር የማንንም ሰው ፈቃድ ወይም አስተያየት በግድ አይቆጣጠርም። የባርነትም መታዘዝ አያስደስተውም። የእጆቹ ሥራዎች የሆኑት ፍጡራን ይወደድ ዘንድ የተገባው ስለሆነ እንዲወዱት እጅግ ይፈልጋል። ለእርሱ እንዲታዘዙ የሚሆኑበት ምክንያት ለጥበቡ፣ ለፍትሁና ለቸርነቱ በእውቀት ላይ የተመሠረተ አድናቆት ስለሚኖራቸው ነው። የነዚህ ባህርያት ትክክለኛ መረዳት ያላቸው ሁሉ ይወዱታል፤ ምክንያቱም በመለያ-ባህርያቱ ከመደነቃቸው የተነሳ ወደ እርሱ ይሳባሉና። GCAmh 392.4
መድኃኒታችን ያስተማራቸውና ምሳሌ ይሆን ዘንድ በተግባር የገለጻቸው የቸርነት፣ የምሕረትና የፍቅር መርሆች የእግዚአብሔር ፈቃድና ባህርይ ቅጂዎች ናቸው። ክርስቶስ ከአባቱ ከተቀበለው በቀር አንዳችም ሌላ ነገር እንዳላስተማረ ተናግሯል። የመለኮታዊ አስተዳደር መርሆች “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ከሚለው ከመድኃኒታችን መመሪያ ጋር ፍጹም ስምሙ ናቸው። ለዓለም ደህንነት ሲል፣ እንዲያውም ፍርዱ የሚጎበኛቸው ጭምር መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፣ እግዚአብሔር በኃጥአን ላይ ፍርዱን ተግባራዊ ያደርጋል። ከመንግሥቱ ሕግጋትና ከባህርይው ፍትሃዊነት ጋር የተስማሙ እንዲሆኑ ያደርጋቸው ዘንድ ከቻለ ደስተኞች ያደርጋቸዋል። በእርሱ፣ የፍቅሩ መገለጫ በሆኑ ነገሮች ይከባቸዋል፤ የሕጉን እውቀት ይለግሳቸዋል፤ በምሕረት ስጦታዎቹም ይከተላቸዋል። እነርሱ ግን ፍቅሩን ይንቃሉ፣ ሕጉን ያፈርሳሉ፣ ምህረቱንም አንቀበልም ይላሉ። ስጦታውን ያለማቋረጥ ሲቀበሉ ሳለ ሰጭውን ግን ያዋርዱታል፤ ኃጢአቶቻቸውን እንደሚጸየፍ ስለሚያውቁ እግዚአብሔርን ይጠሉታል። ጌታ ጠማማነታቸውን ለረጅም ጊዜ ይታገሣል፣ ነገር ግን ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰንበት ወሳኝ ሰዓት በስተመጨረሻ ይደርሳል። ያን ጊዜስ እነዚህን አማፅያን በእርሱ ጎራ አድርጎ በሰንሰለት ያሥራቸዋልን? ፈቃዱንስ ያደርጉ ዘንድ ያስገድዳቸዋልን? GCAmh 392.5
ዲያብሎስ አለቃቸው ይሆን ዘንድ የመረጡ፣ በኃይሉም ቁጥጥር ስር የሆኑ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር መገኘት ይገቡ ዘንድ የተዘጋጁ አይደሉም። ትዕቢት፣ ማጭበርበር፣ ዝሙት፣ ጭካኔ ከባሕርያቸው ጋር ተቆራኝተዋል። ታዲያ ምድር ላይ እያሉ ከናቋቸውና ከጠሏቸው ጋር ለዘላለም ለመኖር ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ይችላሉን? እውነት ለቀጣፊ ፈጽሞ አስደሳች አይሆንም፤ የዋህነት የራስን ክብርና ኩራትን የሚያረካ አይሆንም። ንፅሕና በምግባረ ብልሹዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። የማያዳላ ፍቅር ለራስ ወዳዶች ውብ መስሎ አይታይም። ፍጹም ምድራዊና ራስ ወዳድ በሆኑ ፍላጎቶች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለተዋጡ ለእነርሱ ሰማይ ምን ደስታ ሊለግሳቸው ይችላል? GCAmh 393.1
በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ ሕይወታቸውን የጨረሱ፣ በድንገት ወደ ሰማይ ቢወሰዱና እዚያ ሁሌም የሚኖረውን ከፍ ያለና የተቀደሰ ፍጽምና ሊያዩ - እያንዳንዱን በፍቅር የተሞላ ነፍስ፣ እያንዳንዱን በደስታ ፀዳል የሚፈካውን፣ በመልካም ጥዑመ ዜማ ለእግዚአብሔርና ለበጉ ክብር የሚተመውን በሐሴት ሲቃ የተሞላውን ሙዚቃ፣ በዙፋኑም ከተቀመጠው ፊት እየፈነጠቀ በተዋጁት ላይ የሚያርፈውን የማያቋርጥ የብርሐን ጅረት ሊመለከቱ - በእግዚአብሔር ፊት፣ በእውነትና በቅድስና ጥላቻ ልባቸው የሞላው እነርሱ ከሰማያዊ ሰራዊት ጋር መቀላቀልና የምስጋና መዝሙራቸውን አብረው መዘመር ይችላሉን? የእግዚአብሔርንና የበጉን ክብር መቋቋም ይችላሉን? አይችሉም። ለሰማይ የሚሆን ባህርይ ይገነቡ ዘንድ የምሕረት (የአመክሮ) ዓመታት ተሰጥቷቸው ነበር፤ አዕምሮ ንጽህናን ይወድ ዘንድ ፈጽመው አላሰለጠኑትም፤ የሰማይን ቋንቋም አልተማሩም፤ አሁን ጊዜው አልፏል። በእግዚአብሔር ላይ የነበረው የአመጽ ሕይወት ለሰማይ ገጣሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ንጽህናው፣ ቅድስናውና ሰላሙ ለእነርሱ ስቃይ ይሆንባቸዋል፤ የእግዚአብሔር ክብር የሚባላ እሳት ይሆንባቸዋል። ከዚያ ቅዱስ ስፍራ በርግገው ለመጥፋት ይናፍቃሉ። ያድናቸው ዘንድ የሞተላቸውን ፊት ከማየት ይደበቁ ዘንድ ውድመትን በአዎንታ ይቀበላሉ። የኃጥአን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ምርጫ አስቀድሞ የተወሰነ ነው። ከሰማይ መገለላቸው እነርሱ ወደውና ፈቅደው ያደረጉት ሲሆን በእግዚአብሔር በኩል ደግሞ ተገቢና ርኅራኄ የሞላበት ነው። GCAmh 393.2
እንደ የጥፋት ውኃው ሁሉ የታላቁ ቀን እሳትም ኃጥአን እንደማይድኑ የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ያውጃል። ለመለኮታዊ ስልጣን የሚያስገዙት አንዳች ጠባይ የላቸውም። ፈቃዳቸው አመፃን ተለማምዷል፤ ሞት ሲመጣ የኃሳባቸውን ሞገድ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ለማዞር ጊዜ ያለፈበት ይሆናል — ከመተላለፍ ወደ መታዘዝ ከጥላቻ ወደ ፍቅር ለመዞር ሰዓቱ ያለቀ ይሆናል። GCAmh 393.3
ነፍሰ-ገዳዩን ቃየንን በሕይወት በማትረፍ፣ ኃጢአተኛው በሕይወት እንዲኖር፣ ገደብ የለሽ ኃጢአትንም መሥራት ይቀጥል ዘንድ መፍቀድ ውጤቱ ምን እንደሚመስል እግዚአብሔር ለዓለም ምሳሌ ሰጥቷል። በቃየን ትምህርትና ምሳሌነት ተጽዕኖ ምክንያት “የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እስኪሆን ድረስ ከዘሩ የወጡ እልፍ አዕላፋት ወደ ኃጢአት ተመሩ። ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሽታ ነበረች። ምድርም ግፍ ሞላባት።” [ዘፍ 6÷5-11]። GCAmh 394.1
እግዚአብሔር ለዓለም ካለው ቸርነት የተነሳ በኖህ ዘመን የነበሩትን ክፉ ነዋሪዎችን አጠፋቸው፤ የሰዶምን ብልሹ ነዋሪዎች በምህረቱ አጠፋ። አታላይ በሆነው የሰይጣን ኃይል አማካኝነት እየታገዙ የክፋት ሰራተኞች አዘኔታና አድናቆት ይቸራቸዋል፤ ስለዚህም ሌሎችን በቀጣይነት ወደ አመጽ ይመራሉ። በቃየንና በኖህ ዘመን፣ በአብርሃምና በሎጥ ጊዜ እንዲሁ ነበር፤ በእኛ ዘመንም እንዲሁ ነው። እግዚአብሔር በመጨረሻ ፀጋውን አንቀበልም ያሉትን የሚያጠፋው ለዓለማት ካለው ምሕረት የተነሳ ነው። GCAmh 394.2
“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ የሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” [ሮሜ 6÷23]። ሕይወት የፃድቃን ውርስ ሲሆን፣ ሞት ደግሞ የኃጥአን ድርሻ ነው። ሙሴ ለእሥራኤል እንዲህ አለ፦ “ዛሬ ሕይወትንና መልካምነትን፣ ሞትንና ክፋትን (በፊትህ) አኑሬአለሁ” [ዘዳ 30÷15]። በእነዚህ ጥቅሶች የተወሳው ሞት በአዳም ላይ የታወጀው ሞት አይደለም፤ ምክንያቱም ለመተላለፉ ቅጣት ሁሉም የሰው ዘር ይሰቃያልና። ይህ ከዘላለም ሕይወት ጋር በንጽጽር የቀረበው ሁለተኛው ሞት ነው። GCAmh 394.3
የአዳም ኃጢአት ባስከተለው ውጤት ሞት በሰው ዘር ሁሉ ላይ አለፈ፤ ሁሉም በተመሳሳይ ወደ መቃብር ይወርዳሉ። የድነት እቅድ ባለው አቅርቦት አማካኝነት ደግሞ ሁሉም ከመቃብራቸው ሊነሱ አላቸው። “ፃድቃንም አመፀኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ እንዳላቸው”… [የሐዋ ሥራ 24÷15] “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” [1ኛ ቆሮ 15÷22]። ከመቃብር በሚነሱት ሁለት መደቦች መካከል ግን ልዩነት ተደርጎአል። “በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሳኤ፣ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሳኤ ይወጣሉና” [ዮሐ 5÷28፣29]። “ለሕይወት ትንሳኤ ይነሱ ዘንድ የተገባቸው ሆነው የተቆጠሩ እነርሱ የተባረኩና የተቀደሱ ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ስልጣን የለውም” [ራዕይ 20÷6]። ንስሐ በመግባት በእምነት ይቅርታ ያላገኙ እነርሱ ግን የመተላለፍን ቅጣት — የኃጢአትን ዋጋ መቀበል አለባቸው። በሚፈጀው ጊዜና በጥንካሬው የተለያየ የሆነ እንደሥራቸው መጠን ይቀጣሉ። ነገር ግን በስተመጨረሻ ዕጣቸው በሁለተኛው ሞት የሚደመደም ይሆናል። ከፍርዱና ከምህረቱ ጋር ስምሙ በሆነ መልኩ፣ ኃጢአተኛውን ከነኃጢአቱ ያድነው ዘንድ ለእግዚአብሔር የማይቻለው ስለሆነ፣ የተገባው እንዳልሆነ ራሱ (ኃጢአተኛው) ያረጋገጠውን፣ በመተላለፉ ምክንያት ያጣውን ሕያውነት እንዳይኖረው ያስቀርበታል። በመንፈስ የተመራው ፀኃፊ እንዲህ ይላል፦ “ለኃጢአተኛ ጥቂት ጊዜ ቀረው፣ አይገኝም። ቦታውን ትሻለህ አታገኘውም።” ሌላውም እንዲህ ይናገራል፦ “እንዳልሆኑም [እንዳልነበሩም] ይሆናሉ/they shall be as though they had not been” [መዝ 37÷10፤ አብድ 16]። በክፉ ሥራቸው ተሸፍነው ተስፋ ወደ ሌለው ወደ ዘላለማዊ መረሳት ይዘቅጣሉ። GCAmh 394.4
በእርሱ መዘዝ ከመጣው ኃዘንና ውድመት ሁሉ ጋር በእንዲህ ሁኔታ ኃጢአት መጨረሻው ይበጅለታል። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “ዝንጉዎችንም [ክፉዎችንም] አጠፋህ፣ ስማቸውንም [ከዘላለም እስክ] ዘላለም ደመሰስህ። ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ [ኦ ጠላት ሆይ፣ ውድመቶች ለዘላለም አበቁ/thou hast destroyed the wicked, thou hast put out their name forever and ever. O thou enemy, destructions are come to a perpetual end]” [መዝ 9÷5፣6]። ዮሐንስ፣ በራዕይ መጽሐፍ፣ ስለ ዘላለማዊው መንግሥት ወደፊት በናፍቆት ሲመለከት በአንዲት በጥላቻ ኖታ እንኳ ያልተረበሸ ዓለም አቀፋዊ የምስጋና ዜማ ሰምቷል። በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ፍጡር ለእግዚአብሔር ክብር ሲሰጥ ይሰማ ነበር [ራዕይ 5÷13]። ፈጽሞ በማይቆም ስቃይ እየተንከላወሱ (እየተንፈራፈሩ)፣ እግዚአብሔርን የሚሰድቡ የጠፉ ነፍሳት ከእንግዲህ አይኖሩም፤ በሲኦል ያሉ ጎስቋላ ፍጡራን ማንቋረር ከዳኑት መዝሙሮች ጋር አይሰባጠርም። GCAmh 395.1
ከተፈጥሯዊ አለመሞት (Natural Immortality) መሰረታዊ ስህተት ላይ የተደገፈ በሞት ጊዜ ንቃተ ህሊና እንደነቃ የሚቆይበት (የማይሞትበት) አስተምህሮ አለ፤ ይህ አስተምህሮ ልክ እንደ ዘላለማዊ ስቃይ አስተምህሮ ሁሉ፣ የመጽሐፍ ቅዱሳትን ትምህርቶች፣ ምክንያት የሚለውን፣ ወይም የሰብዓዊነትን ስሜቶች የሚቃረን ነው። በስፋት ተቀባይነት እንዳለው እምነት ከሆነ፣ በሰማይ ያሉት የተዋጁት በምድር የሚከናወነውን ሁሉ፣ በተለይም ትተዋቸው የሄዱትን ወዳጆቻቸውን ሕይወት በቅርበት እንደሚያውቁ ያትታል። በሕይወት ያሉት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ማወቃቸው፣ በሚወዷቸው የሚፈፀሙትን ኃጢአቶች መመልከታቸው ሐዘንን፣ ቅር መሰኘትን እንዲሁም የሕይወትን ሰቆቃ ሁሉ ሲገዳደሩ ማየታቸው ለሞቱት እንዴት የደስታ ምንጭ ሊሆን ይችላል? ምን ያህል የሰማይ ተድላ ነው በወዳጆቻቸው በላይ በሚያንዣብቡት ዘንድ የሚጣጣመው? እስትንፋስ አካልን እንደለቀቀች፣ ንስሐ ያልገባው ነፍስ ለሲኦል ነበልባል ትገበራለች የሚለውስ እምነት ምን ያህል የሚሰቀጥጥ ነው! ያልተዘጋጁትና ወደ ሞት የሚወርዱት ጓደኞቻቸው ወደ ዘላለማዊ ህመምና ኃጢአት ሲገቡ ያዩ ዘንድ ወደ ምን አይነት የስቃይ ዲካ መጥለቅ ይኖርባቸዋል! በዚህ አስጨናቂ ሐሳብ ምክንያት ብዙዎች ወደ እብደት ተገፍተዋል። GCAmh 395.2
እነዚህን ነገሮች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ሰው በሞተ ጊዜ እንደማያውቅ ዳዊት ይናገራል፦ “መንፈሱ [እስትንፋሱ] ትወጣለች፣ ወደ መሬትም ይመለሳል፣ በዚያን ቀን ትምክህቱ (ሐሳቡ) ሁሉ ይጠፋል [His breath goeth forth, he returneth to his earth; in that very day his thoughts perish]” [መዝ 146÷4]። ሰለሞንም ተመሳሳዩን ምስክርነት ይጋራል፦ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” “ፍቅራቸው፣ ጽላቸውና ቅንዓታቸው ጠፍታለችና ከፀሐይም በታች በሚሰራው ነገር ለዘላለም ፈንታ የላቸውም።” “ሥራና ሀሳብ፣ ጥበብና እውቀትም አንተ ወደ ምትሄድበት በሲኦል (in the grave) አይገኝምና” [መክ 9÷5፣6፣10]። GCAmh 395.3
ስለ ፀሎቱ መልስ የሕዝቅያስ ሕይወት በአሥራ አምስት ዓመት በተራዘመ ጊዜ ውለታ የማይረሳው ንጉሥ ስለ ታላቅ ምህረቱ ለእግዚአብሔር የምስጋና መታሰቢያ ተቀኘ። በዚህ መዝሙር ደስ የተሰኘበትን ምክንያት ይናገራል፦ “ሲኦል አያመሰግንህምና፣ ሞትም ምስጋና አይሰጥህምና፤ ወደ ሲኦል የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። ሕያው፣ ሕያው ያመሰግንሃል እንደ እኔ ዛሬ” [ኢሳ 38÷18፣19]። በብዛት ተቀባይነት ያለው የስነ መለኮት ትምህርት የሞቱት ፃድቃን በሰማይ እንደሆኑ፣ ወደ ተድላ እንደገቡ፣ እንዲሁም በማይሞት አንደበት እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ያትታል፤ ሕዝቅያስ ግን በሞት ውስጥ እንደዚህ ያለ ውብ ተስፋ ያይ ዘንድ አልቻለም። የመዝሙረኛው ምስክርም ከእርሱ ቃላት ጋር ይስማማል፦ “በሞት የሚያስብህ የለምና፤ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማነው?” “ሙታንና ወደ ዝምታ የወረዱት ሁሉ እግዚአብሔርን አያመሰግኑትም” [መዝ 6÷5፤ 115÷17]። GCAmh 395.4
ጴጥሮስ በጴንጤ ቆስጤ ቀን፣ የኃይማኖት አባቱ “ዳዊት እንደሞተም እንደተቀበረም….መቃብሩም እስከዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ ነው”፣ “ዳዊት ወደሰማያት አልወጣምና” ሲል ተናግሮአል [የሐዋ ሥራ 2÷29፣34]። እስከ ትንሳኤ ድረስ ዳዊት በመቃብር የመቆየቱ እውነታ ፃድቃን ሲሞቱ ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ያረጋግጥልናል። በመጨረሻ ዳዊት በእግዚአብሔር ቀኝ መቆም የሚችለው ክርስቶስ ከሞት በመነሳቱ ምክንያት፣ በትንሳኤ አማካኝነት ብቻ ነው። GCAmh 396.1
ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ሙታን ባይነሱ ክርስቶስ ደግሞ አልተነሳምና። ክርስቶስም ካልተነሳ ኃይማኖታችሁ ከንቱ ነው፤ እስከዛሬ ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲህም በክርስቶስ ያንቀላፉ ደግሞ ፈጽመው ጠፉ” [1ኛ ቆሮ 15÷16-18]። ላለፉት አራት ሺህ ዓመታት ፃድቃን ሲሞቱ በቀጥታ ወደ ሰማይ የሄዱ ከሆነ፣ ትንሳኤ ከሌለ በስተቀር “በክርስቶስ የተኙ ደግሞ ፈጽመው ጠፉ” በማለት እንዴት ጳውሎስ ተናገረ? ትንሳኤ አስፈላጊ አይሆንም። GCAmh 396.2
ሰማዕቱ ቲንዳል ሙታን ተኝተው የሚቆዩበትን አስተምህሮ በመደገፍ ለተቃዋሚው ጳጳሳዊ ሲናገር፦ “አንተ እነርሱን [ለቀው የሚሄዱትን ነፍሳት] በሰማይ፣ በሲኦልና በጊዜያዊ ማቆያው ስፍራ (purgatory) እንዳሉ ማድረግህ ክርስቶስና ጳውሎስ ትንሳኤ እንዳለ ያረጋገጡበትን መከራከሪያ የሚያፈርስ ነው።” “ነፍሳት በሰማይ ከሆኑ፣ መላእክት እንደሆኑት ሁሉ በመልካም ሁኔታ የማይሆኑበትን ምክንያት እስኪ ንገረኝ? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ትንሳኤ የመኖሩ አስፈላጊነት(አላማ) ምንድን ነው?” ብሏል።-William Tyndale, Preface to New testament (ed. 1534). Reprinted in British Reformers-Tindale, Frish, Barnes, ገጽ 349። GCAmh 396.3
በሚሞትበት ጊዜ ይገኛል ተብሎ ተስፋ የሚደረግበት ዘላለማዊ ደስታ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሆነው ትንሳኤ በስፋት ቸል እንዲባል እንዳደረገ የማይካድ ሃቅ ነው። ይህ ዝንባሌ በዚህ ምዕተ ዓመት መጀመሪያ በዶክተር አዳም ክላርክ ተወስቷል፦ “የትንሳኤ አስተምህሮ የሚያስከትለው ውጤት ከአሁኑ ጊዜ ይልቅ በጥንታዊ ክርስቲያኖች ዘንድ የተሻለ ነው ተብሎ ይታሰብ የነበረ ይመስላል! ጥንታዊያን የተሻለ ትኩረት ይሰጡት ነበር። ይህ እንዴት ሆነ? ሐዋርያት በቋሚነት ስለዚህ ጉዳይ አጥብቀው ይናገሩ ነበር፤ በእርሱም አማካኝነት የእግዚአብሔር ተከታዮች እንዲተጉ፣ እንዲታዘዙና ደስተኛ እንዲሆኑ ያደፋፍሯቸው ነበር። ከእነርሱ በኋላ የመጡት የአሁኖቹ ደግሞ የሚጠቅሱት አልፎ አልፎ ነው! ሐዋርያት እንደሰበኩት እንዲሁ ጥንታዊ ክርስቲያኖች አመኑ፤ እኛም እንደምንሰብከው እንዲሁ ሰሚዎቻችን ያምናሉ። በወንጌሉ ከዚህ የበለጠ ትኩረት የተሰጠው አስተምህሮ የለም፤ በአሁኑ የአሰባበክ አደረጃጀት ደግሞ እንደዚህ አስተምህሮ ቸል የተባለ የለም!”-Commentary, Remarks on 1 Corinthians 15, paragraph 3። GCAmh 396.4
የትንሳኤ ግሩም እውነት ሙሉ በሙሉ ሊጋረድ እስኪቃረብ፣ በክርስቲያኑም ዓለም አልታይ እስከሚል ድረስ ይህ ሁኔታ ቀጥሏል። አንድ ከፍተኛ የኃይማኖታዊ ፀኃፊ በ1ኛ ተሰሎ 4÷13-18 ባለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ አለ፦ “ለተግባራዊ ምቾት ሲባል የፃድቃን ሟች አለመሆን (immortality) አስተምህሮ፣ ስለ ጌታ ዳግም ምፅዓት አስተምህሮ ያለውን ማንኛንውም የጥርጥር ቦታ ተክቶልናል። ስንሞት ጌታ ይመጣልናል። ልንጠነቀቅለትና ልንጠብቀው የሚገባን ያ ነው። ሙታን ከወዲሁ ወደ ክብር አልፈዋል። ለፍርዳቸውና ለደስታቸው መለከቱን አይጠብቁም።” GCAmh 397.1
ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሊለያይ በተቃረበበት ጊዜ ግን የሱስ፣ እነርሱ በቅርቡ ወደ እርሱ እንደሚመጡ አልነገራቸውም። “እሄዳለሁ ቦታ አዘጋጅላችሁ ዘንድ” አለ “በሔድሁም ቦታም ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ ዳግም እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” [ዮሐ 14÷2፣3]። ጳውሎስም በተጨማሪ ይነግረናል፦ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ። ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።” በመጨመርም “ስለዚህም እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ” [1ኛ ተሰ 4÷16-18] ይላል። GCAmh 397.2
በእነዚህ በሚያጽናኑ ቃላትና የዩኒቨርሳሊስቱ አገልጋይ በተናገራቸው መካከል ምን ያህል ሰፊ መቃረን አለ። የኋለኛው [ዩኒቨርሳሊስቱ] ያዘኑትን ጓደኞቹን ሲያጽናና፣ የሞተው ምኑንም ያህል ኃጢአተኛ የነበረ ቢሆንም የመጨረሻ እስትንፋሱን ሲተነፍስ በመላእክት መካከል ተቀባይነት እንደሚያገኝ አረጋገጠላቸው። ጳውሎስ ደግሞ ወንድሞቹን የሚያመላክተው ወደፊት ስለሚሆነው የጌታ መምጣት፣ የመቃብር ሰንሰለት ተሰብሮ በክርስቶስ የሞቱ ለዘላለም ሕይወት እንደሚነሱ ነው። GCAmh 397.3
ማንም ወደ ተባረኩት እልፍኞች ከመግባቱ በፊት፣ ጉዳያቸው መመርመር፣ ባህርያቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ፊት እየታየ ማለፍ አለበት። ሁሉም የሚዳኙት በመጽሐፍ ተጽፎ እንደተገኘው ነው። ዋጋቸውም እንደሥራቸው ነው። ይህ ፍርድ በሞት ጊዜ የሚከናወን አይደለም። የጳውሎስን ቃላት ልብ በሉ፦ “ቀን ቀጥሮአልና በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሳቱ ሁሉን አረጋግጦአል” [የሐዋ ሥራ 17÷31]። እዚህ ላይ ሐዋርያው በግልጽ እንዳስቀመጠው ዓለም የሚፈረድበት፣ ወደፊት የሚሆን፣ የተዘጋጀ የተለየ ጊዜ አለ። GCAmh 397.4
ይሁዳ ስለዚህ ጊዜ ሲናገር፦ “መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እሥራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ድረስ ጠብቆአቸዋል።” እንደገናም የሄኖክን ቃላት በመጥቀስ “እነሆ እግዚአብሔር ይመጣል ከአእላፋት ቅዱሳን ጋራ በሁሉ ይፈርድ ዘንድ [ይሁዳ 6፣14፣15]።” ዮሐንስም “ሙታንንም አየሁ ታናሾችን ታላቆችንም በእግዚአብሔር ፊት ቁመው መፃሕፍትም ተከፈቱ፤ ሙታንም ተፈረዱ በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደሰሩት መጠን” [ራእይ 20÷12]። GCAmh 397.5
ነገር ግን የሞቱት በሰማይ ያለውን ተድላ እያጣጣሙ፣ ወይም በሲኦል ነበልባል ውስጥ እየተንፈራፈሩ ከሆነ ወደፊት የሚመጣ ፍርድ አስፈላጊነቱ ምንድን ነው? በእነዚህ አስፈላጊ ነጥቦች ላይ ያሉ የእግዚአብሔር ትምህርቶች የማይታወቁ ወይም እርስበርሳቸው የሚጣረሱ አይደሉም። በተራ ሰዎች የሚስተዋሉ ናቸው። ምን ዓይነት ሐቀኛ አዕምሮ ነው በአሁኑ ጽንሰ-ሐሳብ ውስጥ ጥበብም ሆነ ፍትህ ሊያይ የሚችለው? ፃድቃን ከእርሱ ጋራ አብረው ምናልባትም ለረጅም ዘመናት ከኖሩ በኋላ፣ በፍርድ ሰዓት ጉዳያቸው ተመርምሮ ፦ “አወን አንተ መልካም ባርያ የታመንህም” “ግባ ወደ ጌታህ ደስታ” [ማቴ 25÷21፣41] የሚለውን ምርቃት (ባርኮት) ይቀበላሉን? ኃጥአን ደግሞ ከመሰቃያ ስፍራቸው ተሰባስበው አለሙን ሁሉ ከሚፈርደው ዘንድ “ከእኔ ሂዱ እላንት እርጉማን ወደ ዘላለማዊ እሳት” የሚለውን ቅጣት [ማቴ 25÷21፣41] ይቀበላሉን? ኦህ ከባድ ቀልድ! በእግዚአብሔር ጥበብና ፍርድ ላይ የሚሰነዘር አሳፋሪ ክስ! GCAmh 397.6
የነፍስ አትሞትም ጽንሰ-ሃሳብ፣ ሮም ከእምነት-የለሽነት (ፓጋኒዝም) በመዋስ ወደ ክርስትናው ዓለም ኃይማኖት ከቀላቀለቻቸው የሐሰት አስተምህሮዎች አንዱ ነው። ሉተር “ቁጥር ስፍር ከሌላቸው አስገራሚ የሮም ጳጳሳዊ አዋጆች ቁልል አዛባ” ጋር መድቦታል።-E. Petavel, The Problem of Immortality, page 255። ሙታን ምንም አያውቁም በሚለው በመክብብ በሚገኘው የሰለሞን ቃል ላይ የተሐድሶ አራማጁ ሃሳብ ሲሰጥ እንዲህ ይላል፦ “ሙታን የማይሰሙ ለመሆናቸው ሌላኛው ማረጋገጫ፤ ስለዚህ ሰለሞን የሚያስበው ሙታን ሙሉ በሙሉ እንደተኙና ምንም ነገር እንደማያስቡ ነው። ቀናትንም ሆነ ዓመታትን ሳያሰሉ ተጋድመዋል፤ በሚነቁበት ጊዜ ግን እንዲያው ለአንድ አፍታ ተኝተው እንደነበረ ይሰማቸዋል”።-Martin Luther, Exposition of Solomon’s Book Called Ecclesiastes, page 152። GCAmh 398.1
በሞት ጊዜ ፃድቃን ወደ ሽልማታቸው ወይም ኃጥአን ወደ ቅጣታቸው እንደሚሄዱ የሚነገረው አረፍተ ነገር በቅዱሳት መፃሕፍቱ ውስጥ የትም አይገኝም። የኃይማኖት አባቶችና ነብያትም እንደዚህ አይነት ማረጋገጫ ትተው አላለፉም። ክርስቶስንና ሐዋርያቱም ምንም ፍንጭ አልሰጡም። የሞቱት ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። እስከ ትንሳኤ ድረስ የሚተኙ እንደሆኑ ነው የተነገረላቸው [1ኛ ተሰሎ 4÷14፤ እዮብ 14÷10-12]። የብሩ ድሪ በሚበጠስበት፣ የወርቁም ኩስኩስት በሚሰበርበት በዚያን ቀን [መክ 12÷6] የሰው ኃሳብ ይጠፋል። ወደ መቃብር የሚወርዱ እነርሱ በዝምታ ናቸው። ከፀሐይ በታች ስለሚከናወነው ከእንግዲህ አንዳች ነገር አያውቁም [እዮብ 14÷21] ለደከሙ ፃድቃን የተባረከ እረፍት! ጊዜ ቢረዝምም ቢያጥርም ለእነርሱ ግን እንደ አፍታ ነው። ይተኛሉ፣ ወደ ክቡር ዘላለማዊነትም ይገቡ ዘንድ በእግዚአብሔር መለከት ይቀሰቀሳሉ። “መከለት ይነፋልና ሙታንም ያለ ጥፋት ይነሳሉ… ይህም የሚጠፋው የማይጠፋውን በለበሰ ጊዜ፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ የዚያን ጊዜ የተፃፈው ነገር ይፈፀማል። ሞት በመሸነፍ ተዋጠ” [1ኛ ቆሮ 15÷52-55]። ከጥልቅ እንቅልፋቸው ሲጠሩ ሳለ ካቆሙበት እንደገና ማሰብ ይጀምራሉ። የመጨረሻው ስሜት፣ ድንገተኛ የሞት ህመም ነበረ፣ በመቃብር ኃይል ስር እየወደቁ እንደሆነ የተሰማቸው የመጨረሻው ሃሳብ። ከመቃብር ሲነሱ፣ የመጀመሪያቸው ሃሳብ የደስታ ሃሳብ “ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?” በሚለው የአሸናፊነት ጩኸት ያስተጋባል [1ኛ ቆሮ 15÷52-55]። GCAmh 398.2