ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፴—በሰውና በዲያብሎስ መካከል ያለው ጠላትነት
“በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነት አደርጋለሁ። እርሱም ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” [ዘፍ 3÷15]። ከሰው ውድቀት በኋላ በሰይጣን ላይ የታወጀው መለኮታዊ ፍርድ እስከ ፍፃሜ ድረስ ያለውን ዘመናት ሁሉ የሚያቅፍ፣ በምድርም የሚኖሩት የሰው ዘሮች የሚያልፉበትን ታላቁን ጦርነት የጠቆመ ትንቢት ነበረ። GCAmh 365.1
እግዚአብሔር “ጠላትነትን አደርጋለሁ” ይላል። ይህ ጠላትነት በተፈጥሮ የሚታሰብ (በራሱ ጊዜ የሚከሰት) አይደለም። ሰው መለኮታዊ ሕጉን ሲጥስ ተፈጥሮውም ክፉ ሆነ፤ እናም ከሰይጣን ጋር ስምሙ ሆነ እንጂ አልተቃረነም። በእርግጥም በኃጢአተኛው ሰውና በኃጢአት ጀማሪ መካከል ጠላትነት የለም። ሁለቱም በክህደት ክፉ ሆነዋል። የእርሱን ፈለግ ይከተሉ ዘንድ ሌሎችን በማነሳሳት፣ የሌሎችን ኃዘኔታና ድጋፍ ካላገኘ በስተቀር ከሃዲው ፈጽሞ አያርፍም። በዚህም ምክንያት የወደቁ መላእክትና ክፉ ሰዎች በጠንካራ ጓደኝነት ያብራሉ። እግዚአብሔር ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ሰይጣንና ሰው ሰማይን የሚቃወም ህብረት (ስምምነት) ያደርጉ ነበር፤ መላው ሰብአዊ ቤተሰብም ከሰይጣን ጋር ያለውን ጠላትነት በማወደስ ፈንታ እግዚአብሔርን በመቃወም በአንድነት ይሰለፍ ነበር። GCAmh 365.2
ሰይጣን በሰማይ ላይ በሚያደርገው ጦርነት ትብብር ያገኝ ዘንድ መላዕክት እንዲያምፁ እንዳደረገ ሁሉ፣ ሰውንም ኃጢአት ይሰራ ዘንድ ገፋፋው። ለክርስቶስ ያላቸውን ጥላቻ በተመለከተ በወደቁት መላዕክትና በራሱ መካከል የልዩነት ኃሳብ አልነበረም። በሌሎች ነጥቦች ሁሉ ላይ አለመግባባት የነበረ ቢሆንም የዩኒቨርስን መሪ ስልጣን በመቃወም ግን ጠንካራ ህብረት ነበራቸው። ነገር ግን በራሱና በሴቲቱ፣ በዘሩና በዘርዋ መካከል ጠላትነት እንደሚኖር መግለጫውን ሲሰማ፣ የሰውን ተፈጥሮ የማበላሸት ጥረቶቹ እንደሚስተጓጎሉ አወቀ፤ በሆነ መንገድ ሰው [የሰይጣንን] ኃይል መቋቋም እንዲችል ይደረግ ዘንድ እንዳለው ተረዳ። GCAmh 365.3
በክርስቶስ አማካኝነት ሰዎች የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት ኢላማ ስለሆኑ፣ ሰይጣን በሰው ዘር ላይ ያለው ቁጣ ይነድዳል። የእጁን ሥራ መልክ በማጥፋትና በመበከል፣ መለኮት ለሰው ልጅ መዳን ያለውን እቅድ ማስቆም (ማሰናከል)፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ውርደትን ማምጣት ይሻል። ሰማይን በሃዘን፣ ምድርን በሰቆቃና በውድመት ይሞላ ዘንድ ይወድዳል። ወደ እነዚህ ሁሉ ክፋት እየጠቆመ፣ እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ ምክንያት የመጣ ውጤት መሆኑን ይናገራል። GCAmh 365.4
በሰውና በሰይጣን መካከል ጠላትነትን የሚፈጥረው፣ ክርስቶስ በነፍስ ውስጥ የሚተክለው ፀጋ ነው። ያለዚህ የሚለውጥ ፀጋና አዲስ የሚያደርግ ኃይል፣ የሚፈልገውን ለመፈፀም ምንጊዜም የተዘጋጀ አገልጋይ፣ የሰይጣን እስረኛ ሆኖ ይቀጥል ነበር። ነገር ግን በነፍስ ውስጥ ያለው አዲሱ መርህ ሰላም በነበረበት በዚያ ስፍራ ጥልን ይፈጥራል። ክርስቶስ የሚያካፍለው ኃይል፣ ሰው የአምባገነኑንና የነጣቂውን ኃይል ይቋቋም ዘንድ ያስችለዋል። ኃጢአትን ከመውደድ ይልቅ የሚፀየፍ፣ በውስጥ የሚወተውቱትን እነዚያን ፍላጎቶች የሚቋቋምና ድል የሚነሳ ማንኛውም ሰው፣ ሙሉ ለሙሉ ከላይ የሆነን መርህ አሰራር ያንፀባርቃል። GCAmh 365.5
በክርስቶስ መንፈስና በሰይጣን መንፈስ መካከል ያለው ቅራኔ እጅግ ጎልቶ የወጣው ምድር ለክርስቶስ ባደረገችው አቀባበል ነበር። አይሁዳዊያን አንቀበልህም ወደማለት የተመሩበት ዋና ምክንያት ያለ ምድራዊ ሃብት፣ ድምቀትና ግርማ-ሞገስ ስላልተገለጠ አልነበረም። የእነዚህን ውጫዊ ጥቅማጥቅሞች ጎዶሎ ከመካስ የሚያልፍ ኃይል እንደነበረው አይተዋል። ነገር ግን የክርስቶስ ንጽህናና ቅድስና እግዚአብሔርን የማይመስሉ ሰዎችን ጥላቻ ቀሰቀሰ። ራስን የመካድና ኃጢአት አልባ የሆነ የመሰጠት ሕይወቱ ኩሩና ፍትወታዊ ለሆነ ሕዝብ የማያባራ ተግሳጽ ሆነ። በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ጥላቻን ያስከተለው ምክንያት ይህ ነበር። ሰይጣንና ርኩስ መላእክት ከክፉ ሰዎች ጋር አበሩ። የክህደት ኃይላት ሁሉ በእውነት ቀንዲል ላይ ተመሳጠሩ። GCAmh 366.1
በጌታቸው ላይ የተንጸባረቀው ያው ጥላቻ በክርስቶስ ተከታዮች ላይም ይንፀባረቃል። አስቀያሚውን የኃጢአትን ባህርይ የሚያይ፣ ከላይ በሚመጣው ኃይልም ፈተናን የሚቋቋም እርሱ ያለጥርጥር የሰይጣንንና የጋሻ ጃግሬዎቹን (ተገዥዎቹን) ቁጣ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው። ለእውነት ንፁህ መርሆዎች ያለው ጥላቻና [በዚያ እውነት] ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው ነቀፌታና ስደት ኃጢአትና ኃጢአተኞች እስካሉ ድረስ ይቀጥላል። የክርስቶስ ተከታዮችና የሰይጣን አገልጋዮች መኳኋን አይችሉም። የመስቀሉ ንዴት አሁንም አልበረደም። “በእውነትም በክርስቶስ የሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” [2ኛ ጢሞ 3÷12]። GCAmh 366.2
ከእግዚአብሔር መንግሥት በተቃረነ ሁኔታ፣ ስልጣኑን ይመሰርቱ፣ መንግሥቱንም ያቋቁሙ ዘንድ የሰይጣን ወኪሎች በእርሱ እየታዘዙ በማያባራ ሥራ ተጠምደዋል። ለዚህም ግብ ሲሉ የክርስቶስን ተከታዮች ለማታለል፣ ከታማኝነታቸውም ገለል ይሉ ዘንድ ያባብሏቸዋል። አላማቸውን ያሳኩ ዘንድ ልክ እንደመሪያቸው መጽሐፍ ቅዱስን ያዛባሉ፣ ያጣምማሉ። ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ ነቀፋ ያሳርፍ ዘንድ እንደጣረ ሁሉ ልዑኮቹም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በአደባባይ ይዘልፏቸዋል። ክርስቶስን የገደለው መንፈስ ተከታዮቹንም ያጠፉ ዘንድ ኃጢአንን ያንቀሳቅሳል። ይህ ሁሉ በዚያ በመጀመሪያው ትንቢት ተነግሮአል፤ “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ”፤ ይህም እስከ ዘመን ፍፃሜ የሚቀጥል ይሆናል። GCAmh 366.3
ሰይጣን ሰራዊቱን ሁሉ ያሰባስብና ጉልበቱን በሙሉ ወደ ጦርነቱ ይማግዳል። [አሁን እየገጠመው ካለው የተሻለ] የሚቋቋመው ኃይል የማያጋጥመው ታዲያ ለምንድን ነው? የክርስቶስ ወታደሮች እንቅልፋሞችና ግድየለሾች የሆኑት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ያላቸው እውነተኛ ቁርኝት እጅግ አናሳና የመንፈሱ ድሃ ስለሆኑ ነው። ለጌታቸው ለየሱስ እንደነበረ ሁሉ፣ ለእነርሱም ኃጢአት የሚያቅለሸልሽና የሚያፀይፍ አይደለም፤ ክርስቶስ እንዳደረገው ኃጢአትን ቆርጠውና ወስነው አይጋፈጡትም። የኃጢአትን ከልክ ያለፈ ክፋትና ተንኮል አይረዱትም፤ ለጨለማው ልዑል ባህርይና ኃይልም ዓይናቸው ታውሯል። ከሰይጣን ጋር ያለው ጠላትነት እጅግ አናሳ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ስለ ኃይሉና ስለክፋቱ፣ በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ስለሚያውጀው ጦርነት መጠን እጅግ ከፍተኛ የሆነ የእውቀት ማጣት ስላለ ነው። እልፍ አዕላፋት እዚህ ላይ ይታለላሉ። ጠላታቸው፣ የክፋት መላእክትን አእምሮ የተቆጣጠረ፣ በደንብ በጎለመሱ እቅዶችና ጥበበኛ እንቅስቃሴዎች የነፍሳትን መዳን ለማስቀረት ከክርስቶስ ጋር የሚፋለም ኃያል የጦር ጀነራል መሆኑን አያውቁም። በታማኝ ክርስቲያኖች፣ የወንጌል አገልጋዮች በሆኑ መካከል እንኳ፣ በመድረክ ላይ የሚደረግ ምንአልባት ያልታሰበ ማውሳት ካልሆነ በስተቀር ስለሰይጣን የሚሰማ ነገር ከስንት አንድ ነው። በቀጣይነት እየተካሄደ ያለውን አድራጎቶቹንና ስኬቱን እንደሌለ ያልፉታል፤ የበርካታ ማታለያዎቹን ምልክቶች ቸል ይሏቸዋል። በሕይወት መኖሩን እንኳ የዘነጉት ይመስላሉ። GCAmh 366.4
ሰዎች የዘዴዎቹ አላዋቂዎች ሆነው ሳለ ንቁው ጠላት ግን በእያንዳንዷ ቅጽበት ዱካቸውን ይከታተላል። በቤተሰብ እያንዳንዱ ጓዳ፣ በከተሞቻችን እያንዳንዱ መንገድ፣ በብሔራዊ መማክርት ውስጥ፣ በፍርድ ቤቶች፣ ራሱን ጣልቃ እያስገባ፣ እያታለለ፣ እያማለለ የወንዶችን፣ የሴቶችንና የልጆችን ነፍስና አካል በሁሉም ስፍራ እያጠፋ፣ ቤተሰቦችን እየለያየ፣ ጥል፣ አስመሳይነት፣ ብጥብጥና ግድያ እየዘራ ነው። የክርስቲያኑ ዓለም ደግሞ እነዚህ ነገሮች ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያቀዳቸው፣ መኖር ያለባቸው፣ አድርጎ የሚያስብ ይመስላል። GCAmh 367.1
ከዓለም ጋር የሚለዩአቸውን ቅጥሮች በማፈራረስ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማሸነፍ ሳያሰልስ እየጣረ ነው። ጥንታዊ እሥራኤላዊያን ወደ ተከለከሉ፣ ከአሕዛብ ጋር ወደሚደረጉ ጉድኝቶች እግራቸውን ሲሰዱ ኃጢአት ወደ መሥራት ተገፋፉ። የዚህ ዘመን እሥራኤሎችም ከትክክለኛው መስመር የሚወጡት በተመሳሳይ ሁኔታ ነው። “እነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሐን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” [2ኛ ቆሮ 4÷4]። የክርስቶስ ቁርጠኛ ተከታዮች ያልሆኑ ሁሉ የሰይጣን ባለሟሎች ናቸው። ባልተለወጠ ልብ ውስጥ የኃጢአት ፍቅር፣ ኃጢአትን የመውደድና ምክንያት የመፈለግ ባህርይ አለ። በተለወጠ ልብ ውስጥ ደግሞ የኃጢአት ጥላቻ፣ የመቋቋምም ቁርጥ ውሳኔ አለ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የማይመስሉና የማያምኑ ሰዎችን ጓደኝነት ሲመርጡ ለፈተና ራሳቸውን ያጋልጣሉ። ሰይጣን ራሱን ከእይታ ውጪ አድርጎ በስውር አሳሳች ግርዶሹን ዓይናቸው ላይ ያኖርባቸዋል። እንደዚህ አይነቱን ጓደኝነት ያመጣባቸው ዘንድ ተጠንቶ የተቀነባበረ እንደሆነ ማየት ይሳናቸዋል። ሁልጊዜ በባህርይ በንግግርና በድርጊት ዓለምን እየመሰሉ ሲሄዱ ሳለ የበለጠ እየታወሩ ይሄዳሉ። GCAmh 367.2
ከዓለማዊ ወግና ባህሎች ጋር መጣጣም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ዓለም ይቀይራታል እንጂ ዓለምን ወደ ክርስቶስ መቸም አይለውጠውም። ከኃጢአት ጋር መለማመድ፣ የክፋትነት ክብደቱ እየቀነሰ የሚሄድ እንዲመስል እንደሚያደርግ እሙን ነው። ከሰይጣን አገልጋዮች ጋር መዋል የመረጠ እርሱ ብዙም ሳይቆይ ጌታውን መፍራት ያቆማል። ዳንኤል በንጉሡ አዳራሽ እንደነበረ ሁሉ እኛም በሥራ ላይ እያለን ስንፈተን እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን እርግጠኛ መሆን እንችላለን፤ ራሳችንን በፈተና ውስጥ ካስቀመጥን ግን ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ መውደቃችን አይቀርም። GCAmh 367.3
ፈታኙ እጅግ በተዋጣለት ሁኔታ የሚሰራው በቁጥጥሩ ስር ናቸው ተብለው በማይጠረጠሩ ሰዎች አማካይነት ነው። የክህሎትና የትምህርት ባለፀጋዎች፣ እነዚህ ባህርያቶቻቸው ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለመኖራቸውን ያስተሰረይላቸው፣ ወይም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝላቸው ይመስል፣ ይደነቃሉ፣ ይከበራሉ። ተሰጥዖና ባህል በራሳቸው ከታዩ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። እነዚህ ግን የቅድስናን ቦታ ሲወስዱ፣ ነፍስን ወደ እግዚአብሔር በማስጠጋት ፈንታ ከእርሱ ሲያርቁአት፣ በዚያን ጊዜ እርግማንና ወጥመድ ይሆናሉ። ደግነትና ንጥረት የሚመስሉ ባህርያት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከክርስቶስ ዘንድ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ የተንሰራፋ ነው። ከዚህ የከፋ ስህተት መቸም አልነበረም። እነዚህ ጠባያት የእያንዳንዱን የክርስቲያን ባህርይ ሊላበሱ ይገባል፤ ምክንያቱም እውነተኛ ኃይማኖትን በመደገፍ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ነው፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር መቀደስ አለባቸው፣ ያለዚያ ለክፋት ጉልበት የሚሆኑ ናቸው። የታረመ የአእምሮ ችሎታና ደስ የሚያሰኝ ጠባያት ያለው፣ በተለምዶ ግብረ ገብነት የሌላቸው የሚባሉ ድርጊቶችን ከመፈፀም የራቀ፣ ብዙ ሰው፣ በሰይጣን እጆች ውስጥ የተሳለ መሳሪያ ነው። ሳይታወቅ ውስጥ ውስጡን የሚሰራው የአታላይ ባህርይው ተጽዕኖና ምሳሌነት፣ አላዋቂና ያልታረሙ ከሆኑት በባሰ ሁኔታ የክርስቶስ ሥራ (አላማ) አደገኛ ጠላት ያደርገዋል። GCAmh 368.1
በልባዊ ፀሎትና በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ፣ ሰለሞን፣ በዓለም ዘንድ ግርምትንና አድናቆትን ያተረፈለትን ጥበብ አገኘ፤ ነገር ግን ከኃይሉ ምንጭ ፈቀቅ ሲልና በራሱ ሲደገፍ የፈተና ታዳኝ ሆነ። ከዚያም በዚህ ከንጉሦች ሁሉ ጥበበኛ በሆነው ላይ ያረፉት ግሩም ድንቅ ክህሎቶች ያደረጉት ነገር ቢኖር ሰሎሞንን ለነፍሳት ባላጋራ የበለጠ ስኬታማ የሆነ ሥራ አስፈጻሚ ማድረግ ነበር። GCAmh 368.2
ሰይጣን ሁልጊዜም አዕምሮአቸውን ከኃቁ ለመጋረድ ሲጥር ሳለ፣ ክርስቲያኖች፣ “መጋደላቸው ከደምና ከስጋ ጋር ሳይሆን ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር” [ኤፌ 6÷12] መሆኑን ፈጽመው መዘንጋት የለባቸውም። ቅዱስ ማስጠንቀቂያው በምዕተ ዓመታቱ ሁሉ ወደ እኛ ዘመን የማስጠንቀቂያ ደወል እያቃጨለ ነው። “በመጠን ኑሩ፣ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና” [1ኛ ጴጥ 5÷8]። “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” [ኤፌ 6÷11]። GCAmh 368.3
ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከ እኛ ጊዜ ታላቁ ጠላታችን ለመጨቆንና ለማጥፋት ኃይሉን ሲጠቀም ኖሮአል። አሁን በቤተ ክርስቲያን ላይ የመጨረሻውን ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው። የሱስን መከተል የሚፈልጉ ሁሉ ከዚህ ከማይታክት ጠላት ጋር ጥል መግጠማቸው አይቀርም። ክርስቲያን የመለኮትን ምሳሌ የበለጠ እየመሰለ ሲሄድ ለሰይጣን ጥቃቶች ራሱን ኢላማ እያደረገ እንደሚሄድ የማያጠራጥር ጉዳይ ነው። የክፉውን ማታለያዎች ለማጋለጥና ክርስቶስንም በሰዎች ፊት ለማቅረብ በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ ያሉ እነርሱ፣ በብዙ እንባና ፈተናዎች በትህትናም ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ስለማገልገል ከተናገረው የጳውሎስ ምስክርነት ጋር ማበር ይችላሉ። GCAmh 368.4
እጅግ በከረረና ተወዳዳሪ በሌለው ብልጣ ብልጥ ፈተናዎቹ ሰይጣን በክርስቶስ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ ሆኖም በእያንዳንዱ ግጭት ተገፈተረ። እነዚያ ጦርነቶች ስለእኛ የተደረጉ ናቸው፤ እነዚያ ድሎች፣ እኛ ድል እናደርግ ዘንድ የሚቻለን እንዲሆን ያደርጉናል። ለሚሹት ሁሉ ክርስቶስ ብርታትን ይሰጣል። ያለ እራሱ እሽታ በስተቀር ማንም ሰው በሰይጣን አይሸነፍም። ፈታኙ ፈቃድን የመቆጣጠር ወይም ነፍስን አስገድዶ ኃጢአት የማሰራት ኃይል የለውም። ማስጨነቅ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም መበከል አይቻለውም። ሰቆቃን እንጂ መርከስን አያስከትልም። ክርስቶስ ድል የመንሳቱ እውነት ሰይጣንንና ኃጢአትን በቆራጥነት ይዋጉት ዘንድ ተከታዮቹን ሊያበረታታቸው ይገባል። GCAmh 368.5