ታላቁ ተጋድሎ

26/45

ምዕራፍ ፳፫—መቅደሱ ምንድን ነው?

ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በላይ ለአድቬንት (ለዳግም ምፅዓት) እምነት መሰረትና ማዕከላዊ ምሰሶ ሆኖ የቆየው ጥቅስ “እስከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ መቅደሱ ይነፃል” [ዳን 8÷14] የሚለው አዋጅ ነበር። የጌታን በቅርብ መምጣት በሚጠባበቁ ሁሉ መካከል እነዚህ የተለመዱ ቃላት ነበሩ። የእምነታቸው ገላጭ ቃል ሆኖ ይህ ትንቢት በሺዎች በሚቆጠሩ አማኞች ከናፍር ይደጋገም ነበር። የሚጠብቋቸው እጅግ የፈኩና እጅግ ተወዳጅ የሆኑት ተስፋዎቻቸው በእነዚህ ወደፊት በተነገሩት ትንቢቶች በሚፈፀሙ ክስተቶች የተደገፉ እንደሆኑ ሁሉም ይሰማቸው ነበር። እነዚህ ትንቢታዊ ቀናት ደግሞ በ1844 ዓ.ም የመከር ወቅት እንደሚያበቁ ተመልክቷል። የክርስቲያኑ ዓለም እንደሚያምነው ሁሉ አድቬንቲስቶችም በዚያን ጊዜ ምድር ወይም የምድር የተወሰነው ክፍል መቅደሱ ነው ብለው ያምኑ ነበር። የመቅደሱ መንፃት ማለት በታላቁ የመጨረሻ ቀን ምድር በእሳት የምትፀዳበት መሆኑን፣ ይህም የሚፈፀመው በዳግም ምፅዓቱ ጊዜ እንደሆነ አድርገው አስተውለው ነበር። ክርስቶስ በ1844 ዓ.ም ወደ ምድር ይመለሳል የሚለው ድምዳሜ የተደረሰውም በዚህ ምክንያት ነበር። GCAmh 297.1

ነገር ግን የተባለው ጊዜ አልፎአል፤ ጌታም አልተገለጠም፤ የእግዚአብሔር ቃል እንደማይሳሳት አማኞች ያውቃሉ፤ የትንቢቱ አተረጓጎማቸው ስህተት መሆን አለበት፤ ግን ስህተቱ የት ላይ ነበር? ብዙዎች 2300 ቀናቱ የሚያበቁት በ1844 ዓ.ም አይደለም በማለት የችግሩን ቋጠሮ በጥድፊያ በጠሱ። በጠበቁት ሰዓት ክርስቶስ ካለመምጣቱ በስተቀር ለዚህ ውሳኔያቸው የሚሰጡት ምክንያት አልነበረም። ትንቢታዊ ቀናቱ ያበቁት በ1844 ዓ.ም ቢሆን ኖሮ ምድርን በእሳት አጽድቶ መቅደሱን ለማንፃት ክርስቶስ ይመለስ ነበር፤ ክርስቶስ በዚያን ጊዜ ስላልመጣ [የመመለሻ]ቀናቱ አላለቁም በማለት ተከራከሩ። GCAmh 297.2

ይህንን መደምደሚያ መቀበል ማለት ከዚህ በፊት [ስለ ትንቢት ዘመናቱ] የተደረሰውን ውጤት መካድ ማለት ነው። 2300 ቀናቱ የሚጀምሩት ከክ.ል.በፊት በ457 ዓ.ዓ መከር ወቅት የየሩሳሌም መታደስና መልሶ መገንባት ትዕዛዝ በአርጤክስስ ሲወጣ እንደነበረ ተደርሶበታል። ይህንን ጊዜ እንደመነሻ በመውሰድ በዳንኤል 9÷25-27 የተብራራው፣ ሁሉም የተተነበዩት ክስተቶች ተግባራዊ የሚሆኑበት ሰዓት ፍፁም መስማማት ያለው ነበር። ስድሳ ዘጠኝ ሳምንታቱ፣ የ2300 ቀናቱ የመጀመሪያዎቹ 483 ቀናት ወደ መሲሁ፣ ወደ ተቀባው የሚያደርሱ ነበሩ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ27 ዓ.ም የክርስቶስ ጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ መቀባት የተነገረውን በትክክል የፈፀመ ነበር። በሰባኛው ሳምንት መሃል መሲሁ ይቆረጥ ዘንድ ነበረው። ከተጠመቀ በሶስት አመት ተኩል በኋላ በፀደይ ወቅት፣ በ31 ዓ.ም ክርስቶስ ተሰቀለ። ሰባዎቹ ሳምንታት ወይም 490 ዓመታቱ በተለይ ከአይሁድ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ነበሩ። በዚህ ዘመን ማብቂያ ላይ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በማሳደድ እሥራኤል ጌታን አልቀበልም ያለችበትን ማህተም አተመች፤ ሐዋርያትም በ34 ዓ.ም ወደ አሕዛብ ፊታቸውን አዞሩ። ከ2300 ውስጥ 490 አመታቱ በዚህ ሁኔታ ሲያበቁ 1810 ዓመታት ይቀራሉ። 1810 ዓመታት ከ34 ዓ.ም ሲቀጥሉ እስከ 1844 ዓ.ም ይደርሳሉ። “ከዚያም” አለ መልአኩ “መቅደሱ ይነፃል።” እስካሁን ድረስ በትንቢቱ የተነገሩት ሁሉ ምንም አይነት ጥርጣሬ በማያስነሳ ሁኔታ፣ በተመደበላቸው በዚያው ጊዜ ተፈጽመዋል። በዚህ ስሌት መሰረት፣ በ1844 ዓ.ም የመቅደሱን መንፃት ጥያቄ የሚመልስ ክስተት ተፈጽሞ ካለመታየቱ በስተቀር፣ ሁሉም ግልጽና ስምሙ ነበር። ቀናቱ የሚያልቁት በዚያን ጊዜ (በ1844) አይደለም ብሎ መካድ ደግሞ፣ ጥያቄውን ሁሉ ማምታታት፣ ሊሳሳት በማይችል ሁኔታ ፍፃሜ ያገኙትን ትንቢታት ተመርኩዞ የተደረሰበትን ማጠቃለያ በገሃድ መካድ ይሆናል። GCAmh 297.3

እግዚአብሔር ግን በታላቁ የአድቬንት ንቅናቄ ሕዝቦቹን መርቷቸዋል፤ ሃይሉና ክብሩ ከሥራው ጋር ነበርና ሐሰትና የአክራሪነት የጋለ ስሜታዊነት ነው ተብሎ ይነቀፍ ዘንድ፣ በጽልመትና በቅሬታ እንዲያበቃ አይፈቅድም። ቃሉ በጥርጣሬና በውዝግብ ውስጥ ሆኖ ይቀር ዘንድ አይቻለውም። ብዙዎች የቀድሞ ትንቢታዊ ዘመናትን ስሌት ትተው፣ በዚያም ላይ የተመሠረተውን እንቅስቃሴ ቢክዱም፣ ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስና በእግዚአብሔር መንፈስ ምስክርነት የፀኑትን የእምነታቸውንና የተሞክሯቸውን ነጥቦች ይክዱ ዘንድ ፈቃደኛ አልነበሩም። ትክክለኛ የሆኑ የመተርጎሚያ መርሆዎችን ተከትለው ትንቢታትን እንዳጠኑ በማመን የተገኙትን እውነቶች በጽናት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውና ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምርመራቸውን መቀጠል እንደሚገባቸው ተረዱ። በልባዊ ፀሎት ውስጥ ሆነው አቋማቸውን ፈተሹ፤ ስህተታቸውንም ይደርሱበት ዘንድ መጽሐፍ ቅዱሱን አጠኑ። የትንቢት ዘመናቱን ያሰሉበት መንገድ ላይ ምንም ስህተት ማየት ስላልቻሉ የቤተ መቅደሱን ጉዳይ በበለጠ ትኩረት ይመረምሩ ዘንድ ተመሩ። [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 6ን ይመልከቱ]። GCAmh 298.1

በምርመራቸው ውስጥ ምድር ቤተ መቅደስ ናት የሚለውን ሕዝባዊ እይታ የሚያፀና የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ እንደሌለ አስተዋሉ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መቅደሱ፣ ስለ ተፈጥሮው (ባህርይው)፣ መቀመጫውና አገልግሎቱ ዝርዝር ማብራሪያ አገኙ፤ ጉዳዩ ምንም ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ ግልጽና በቂ የሆነ የቅዱሳን ፀሃፊዎችን ምስክርነት አገኙ። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን በፃፈው መልእክቱ እንዲህ ይላል፦ “ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። የመጀመሪያይቱ ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፤ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው የመስዋዕቱም ህብስት ነበረባት፤ ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፤ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበረ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች ኪዳን ታቦት፤ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ፤ በላይዋም ማስተሰሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ።” [ዕብ 9÷1-5]። GCAmh 298.2

ጳውሎስ ስለ እርሱ እየተናገረለት ያለው ይህ ቤተ መቅደስ የታላቁ አምላክ ምድራዊ መኖሪያ ስፍራ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ በሙሴ የተሰራው ማደሪያው ነው። “በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይስሩልኝ” [ዘፀ 25÷8] የሚለው ትዕዛዝ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በተራራው ላይ በነበረበት ጊዜ የተሰጠ ነበር። የእሥራኤል ልጆች በበረሃ እየተጓዙ ስለነበር ማደሪያው የተሰራው ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ ነበር፤ ሆኖም በታላቅ ግርማ የተሰራ ነበር። ግድግዳው ቀጥ ቀጥ ባሉ በወርቅ በደንብ የተለበጡ ሳንቃዎች የብርም ሻኩራዎች የነበሩበት፣ ጣራው ደግሞ ከተገጣጠሙ መጋረጃዎች ወይም መደረቢያዎች፣ ውጫዊው ክፍል ከቁርበት (ቆዳ)፣ ውስጠኛው ደግሞ የኪሩቤሎች ምስል ያለባቸው በሚያምሩ በፍታዎች የተሰራ ነበር። የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ ከያዘው ከውጨኛው አደባባይ በተጨማሪም ማደሪያው በሚያምር መጋረጃ የተለዩ፣ ቅዱስና ቅድስተ ቅዱሳን የተባሉ ሁለት ክፍሎችን የያዘ ነበር። ወደ መጀመሪያው ክፍል መግቢያውንም መጋረጃ ሸፍኖት ነበር። GCAmh 298.3

ከቅዱስ ስፍራው፣ በደቡብ በኩል ለመቅደሱ በቀንና በሌሊት የሚበሩ ሰባት መብራቶችን የያዘ መቅረዝ ነበረ። በሰሜንም በኩል የገፀ ህብስት ገበታ ነበር፤ ቅዱሱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን በሚለየው መጋረጃ ፊት ለፊትም ከእሥራኤል ፀሎት ጋር ሆኖ በየዕለቱ ወደ እግዚአብሔር ፊት የሚወጣው የመልካም መዓዛ ጭስ የሚጨስበት የወርቅ መሰዊያ ነበረ። GCAmh 299.1

በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እግዚአብሔር አሥርቱን ትዕዛዛት የቀረፀባቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች የሚቀመጡበት ሳጥን፣ በከበሩ እንጨቶች ተሰርቶ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ነበር። ከታቦቱ በላይ የሳጥኑ መክደኛ አካል የሆነ፣ እጅግ ውብ የሆነ የጥበብ ሥራ፣ በሁለት ወገን ኪሩቤሎች በላዩ ያረፉበት፣ ከጥሩ ወርቅ የተሰራ የስርየት መክደኛ ነበረ። በዚህ ክፍል በኪሩቤሎች መካከል በሚታየው የክብር ደመና አማካይነት የመለኮት መገኘት ይታወቅ ነበር። GCAmh 299.2

ዕብራውያኑ በከነዓን ከሰፈሩ በኋላ ማደሪያው በሰለሞን መቅደስ ተተካ፤ ይህ መቅደስ ቋሚና በመጠንም የላቀ ቢሆንም በተመሳሳይ መመጣጠን በአንድ አይነት የተሰራ ነበር። በዳንኤል ዘመን ከመፈራረሱ በስተቀር ቤተ መቅደሱ በዚህ ቅርጽ በሮማዊያን እስከወደመበት እስከ 70 ዓ.ም ቆየ። GCAmh 299.3

ይህ ቤተ መቅደስ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች መረጃ የሰጠበት በምድር ላይ የኖረ ብቸኛው ቤተ መቅደስ ነው። ይህ የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ እንደነበረ ጳውሎስ ተናግሯል። ነገር ግን አዲሱ ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ የሌለው ይሆን? GCAmh 299.4

ወደ ዕብራውያን መጽሐፍ እንደገና በመመለስ በጳውሎስ ቃላት በተዘዋዋሪ የተጠቀሰ ሁለተኛ ወይም የአዲስ ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ እንዳለ የእውነት ፈላጊዎች አስተዋሉ፦ “ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት” [ዕብ 9÷1]….ደግሞ የሚለው ቃል ጥቅም ላይ መዋሉ ጳውሎስ ስለዚህ ቤተ መቅደስ ቀደም ብሎ እንደጠቀሰ የሚያመላክት ነው። ከዚህ በፊት ወዳለው ምዕራፍ የመጀመሪያ ክፍል ገልጠው ሲያነቡ፦ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” [ዕብ 8÷1፣2]። GCAmh 299.5

የአዲሱ ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ እዚህ ላይ ተገልጧል። የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ በሰው የተተከለ፣ በሙሴ የተሰራ ነበር፤ ይሄኛው ደግሞ በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለ ነው። በዚያ ቤተ መቅደስ ምድራዊ ካህናት አገልግሎታቸውን ያካሂዱበት ነበር፤ በዚህኛው ደግሞ ታላቁ ሊቀ ካህናችን ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ የሚያገለግልበት ነው። አንደኛው ቤተ መቅደስ በምድር ላይ ነበረ፤ ሌላኛው ደግሞ በሰማይ ነው። GCAmh 299.6

በተጨማሪም በሙሴ የተሰራው ማደሪያ በምሳሌ የተሰራ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን ሲያዘው “እኔ እንደማሳይህ ሁሉ እንደማደሪያው ምሳሌ እንደ እቃውም ሁሉ ምሳሌ እንዲሁ ስሩት” [ዘፀ 25÷9፣40] አለው። ትዕዛዙ እንደገና እንዲህ ሲል ተሰጠ፦ “በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሰራ ተጠንቀቅ” [ዘፀ 25÷9፣40]። ጳውሎስ ሲናገር የመጀመሪያው ድንኳን “ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ”፤ ቅዱስ ስፍራዎቹ “በሰማያት ያሉትን የሚመስለው” ናቸው፤ እንደ ሕጉም መባን የሚያቀርቡት ካህናትም “ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን” ያገለግሉ ነበር፤ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” [ዕብ 9÷9፣23፤ 8÷5፤ 9÷24]። GCAmh 300.1

የሱስ ስለ እኛ የሚያገለግልበት ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ዋናው ኦሪጅናል (እውነተኛው) መቅደስ ሲሆን በሙሴ የተሰራው ደግሞ የእርሱ ቅጅ ነበር። እግዚአብሔር መንፈሱን በምድራዊው ቤተ መቅደስ ሰሪዎች ላይ አደረገ፤ በግንባታው የታየው የጥበብ ሥራ ችሎታ የመለኮትን ጠቢብነት ያንፀባርቅ ነበር። ግድግዳዎቹ የግዙፍ ወርቅ መልክ ነበራቸው፤ ከወርቅ የተሰራው መቅረዝ ሰባት መብራቶች የሚወጣውን ብርሐን በሁሉም አቅጣጫ ያንፀባርቁት ነበር። የገፀ ህብስቱ ገበታና የዕጣን መሰዊያው እንደተለሰለሰ ወርቅ ያንፀባርቁ ነበር። ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተነደፉ የመላእክት ስዕል ያለበት እጅግ የሚያምረው የገበር ጣራ መጋረጃ ለሚማርከው ትዕይንት ውበት የሚጨምር ነበር። ከሁለተኛው መጋረጃ ወዲያ የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት፣ ገብቶ በሕይወት መኖር የሚችለው ታላቁ ካህን ብቻ የሆነበት ቅዱስ ማደሪያ (Shekinah) ነበር። አቻ የማይገኝለት የምድራዊው ቤተ መቅደስ ውበት፣ ክርስቶስ በኩራችን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ስለእኛ የሚያገለግልበት ሰማያዊ መቅደስ ክብር ግርማ ምን ሊመስል እንደሚችል ለፍጡር ያሳየ ነበር። ሺህ ጊዜ ሺህ የሚያገለግሉት፣ እልፍ አዕላፋትም በፊቱ የሚቆሙለት [ዳን 7÷10]፣ የሚያንፀባርቁ ጠባቂ ሱራፌሎች ስለ ክብሩ ፊታቸውን ሸፍነው በሚጠብቁት ዘላለማዊ ዙፋን ግርማ የተሞላው የነገሥታት ንጉሥ መኖሪያ ስፍራ የሆነውን የዚያን [የሰማያዊ] ቤተ መቅደስ አውላላነትና ክብር፣ በሰው እጅ ከተሰሩ ግንባታዎች ሁሉ በውበቱ ተወዳዳሪ የሌለው [ምድራዊው መቅደስ] ለአመል ታህል መግለጽ ቢችል ነው። ሆኖም የሰማያዊውን መቅደስና ለሰው ልጅ መዳን ሲባል የቀጠለውን ሥራ በተመለከተ ያሉትን እውነቶች ምድራዊው ቤተ መቅደስና አገልግሎቶቹ ማስተማር ችለዋል። GCAmh 300.2

በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራዎች በምድር ባለው ቤተ መቅደስ ሁለት ክፍሎች የሚወከሉ ናቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያይ በተደረገ ጊዜ “በዙፋኑ ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ” እንደነበር አመልክቷል [ራዕይ 4÷5]። “የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ በቅዱሳን ሁሉ ፀሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን” [ራዕይ 8÷3] የተሰጠው መልአክ አይቷል። እዚህ ላይ በሰማይ ያለውን ቤተ መቅደስ የመጀመሪያው ክፍል ያይ ዘንድ ነቢዩ ተፈቅዶለት ነበረ፤ በዚያም ስፍራ “ሰባት የእሳት መብራቶች” እና “የወርቅ መሰዊያ” አይቷል፤ እነዚህም በምድር ባለው ቤተ መቅደስ በወርቅ መቅረዝና በዕጣኑ መሰዊያ የሚወከሉ ናቸው። እንደገናም “በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ” [ራዕይ 11÷19] በውስጠኛውም መጋረጃ በኩል ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ተመለከተ፤ በዚህም ስፍራ የእግዚአብሔር ሕግ መቀመጫ ይሆን ዘንድ ሙሴ የሰራው የተቀደሰ ሳጥን የሚወክለውን “የኪዳኑን ታቦት” ተመለከተ። GCAmh 300.3

ይህንን ጉዳይ ሲያጠኑ የነበሩ እነርሱ በሰማይ ቤተ መቅደስ መኖሩን መጠራጠር በማይቻልበት ሁኔታ ማረጋገጫ አገኙ። ሙሴ ምድራዊውን ቤተ መቅደስ የሰራው ባየው ምሳሌ መሰረት ነበር። ያ ምሳሌ ደግሞ በሰማይ ያለው እውነተኛው ቤተ መቅደስ እንደሆነ ጳውሎስ ይናገራል። ዮሐንስም በሰማይ እንዳየው ይመሰክራል። GCAmh 301.1

የእግዚአብሔር መኖሪያ ስፍራ በሆነው በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ዙፋኑ በጽድቅና በፍርድ ተመስርቷል። በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሰው ልጆች ሁሉ የሚፈተኑበት፣ ታላቁ የእውነት መርህ፣ ሕጉ ተቀምጧል። የሕጉን ጽላቶች የያዘው ታቦት፣ ክርስቶስ ፊት ለፊት ሆኖ በደሙ ስለ ኃጢአተኛው በሚለምንበት በስርየት መክደኛ ተሸፍኖአል። በሰው ልጅ ድነት እቅድ ፍርድና ምሕረት የተዋሃዱት እንዲህ ባለ ሁኔታ ነበር። ይህንን ጥምረት ዘላለማዊ ጥበብ ብቻ የሚፈጥረው፣ ዘላለማዊ ኃይል ብቻ የሚያከናውነው ነው። ሰማይን ሁሉ በአድናቆትና በአክብሮት የሚሞላ ጥምረት ነው። የስርየት መክደኛውን በአክብሮት አዘቅዝቀው የሚያዩት በምድራዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያሉት ኪሩቤሎች የሚወክሉት የሰማይ ሰራዊት የድነትን ሥራ በእንዴት አይነት ፍላጎት እንደሚያንሰላስሉት ነው። ንስሐ የሚገባውን ኃጢአተኛ ከበደል ነፃ በማድረግ ከወደቀው ዘር ጋር ያለውን ግንኙነት ሲያድስ ሳለ እግዚአብሔር ፃድቅ መሆን መቻሉ፤ ካልወደቁ መላእክት ጋር አንድ መሆን ይችሉ ዘንድ፣ በእግዚአብሔር መገኘት ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ፣ ክርስቶስ ጎንበስ ብሎ፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን አእላፋት ከጥፋት ጉድጓድ አውጥቶ ነቁጣ በሌለባቸው በራሱ የጽድቅ አልባሳት የሚያለብሳቸው መሆኑ፣ መላእክት ሊመለከቱት የሚሹት የምሕረት ምስጢር ነው። GCAmh 301.2

የሰብአዊ ዘር አማላጅ የሆነበት “ስሙ ቁጥቋጥ የሚባለው” የክርስቶስ ሥራ በሚያምረው በዘካርያስ ትንቢት ተገልጧል። ነቢዩ እንዲህ አለ፣ “እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሰራል ክብርንም ይሸከማል በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሳል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል።” [ዘካ 6÷13]። GCAmh 301.3

“የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሰራል።” በመስዋዕትነቱና በአስታራቂነቱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰረትና ገንቢዋም ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲያመለክት “የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ነው፤ በእርሱም ህንፃ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል። በእርሱም እናንተ ደግሞ” አለ ሐዋርያው “ለእግዚአብሔር መኖርያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሰራላችሁ።” [ኤፌ 2÷20-22]። GCAmh 301.4

“ክብርንም ይሸከማል።” ለወደቀው ዘር የተደረገው የድነት ክብር የክርስቶስ ነው። ማብቂያ በሌላቸው ዘመናት ሁሉ የዳኑት መዝሙር “ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን….ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን” [ራእይ 1÷5፣6] ይሆናል። GCAmh 301.5

“በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሳል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል።” አሁን ገና “በክብሩ ዙፋን” ላይ [ማቴ 19÷28] አይደለም፤ የክብር መንግሥት ገና አልጀመረችም። የመካከለኛነቱ (የአማላጅነቱ) ሥራ ካላለቀ በስተቀር ጌታ አምላክ “ለመንግሥቱ መጨረሻ የሌለውን” “የአባቱን የዳዊት ዙፋን” አይሰጠውም [ሉቃ 1÷32፣33]። እንደ ካህን አሁን ክርስቶስ ከአባቱ ጋር በዙፋኑ ተቀምጦአል [ራዕይ 3÷21]። “የሚፈተኑትን ሊረዳቸው” ይችል ዘንድ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነው”፤ “ህመማችንንም ተሸክሞአል፤ ደዌያችንንም” የተቀበለው ከዘላለማዊው [ከእግዚአብሔር] ጋር የተቀመጠው በራሱ ሕያው የሆነው [ክርስቶስ] ነው። “ማንም ኃጢአት ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” [ኢሳ 53÷4፤ ዕብ 4÷15፤ 2÷18፤ 1ኛ ዮሐንስ 2÷1]። የእርሱ አማላጅነት፣ የተወጋና የተሰበረ አካል፣ ነቁጣ የሌለበት ሕይወት ነው። የቆሰሉት እጆች፣ የተወጋው ጎን፣ መልኩን ያጣው እግሩ፣ መቤዤቱ ተመን ሊወጣለት በማይችል ዋጋ ለተገዛው ለወደቀው የሰው ልጅ ይቃትታል። GCAmh 302.1

“የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል።” እግዚአብሔር ለጠፋው ዘር ያለው ፍቅር፣ ልጁ ለሰው ካለው ፍቅር የማያንስ፣ የመዳን ምንጭ ነው። የሱስ ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና” [ዮሐ 16÷26፣27]። “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና” [2ኛ ቆሮ 5÷19]። በላይ ባለው ቤተ መቅደስ በሚካሄደው አገልግሎት “የሰላም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል።” “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” [ዮሐ 3÷16]። GCAmh 302.2

መቅደሱ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በመጽሐፍ ቅዱሳቱ በግልጽ ተመልሷል። ቤተ መቅደስ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ እንደዋለው የሚያመለክተው መጀመሪያ፣ የሰማያዊ ነገሮች ምሳሌ ሆኖ በሙሴ ስለተሰራው ማደሪያ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ምድራዊው ቤተ መቅደስ የሚጠቁመው፣ በሰማይ ያለውን “እውነተኛይቱን ድንኳን” ነው። ክርስቶስ ሲሞት ምሳሌና ጥላ የነበረው ሥርዓት አበቃ። በሰማይ ያለው “የእውነተኛይቱ ድንኳን” የአዲሱ ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ ነው። የዳንኤል 8÷14 ትንቢት፣ መለኮት እንደደነገገው (ከክ.ል.በኋላ) ባለው ጊዜ እየጠቀሰ ያለው ቤተ መቅደስ፣ የአዲሱ ቃል ኪዳን ቤተ መቅደስ መሆን አለበት ማለት ነው። 2300 ቀናቱ ባለቁበት ጊዜ፣ በ1844 ዓ.ም ለብዙ መቶ ዓመታት በምድር ላይ ቤተ መቅደስ አልነበረም። ስለዚህም “እስከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም መቅደሱ ይነፃል” [ዳን 8÷14] የሚለው ትንቢት የሚያመለክተው ያለ ምንም ጥርጥር ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ ነው። GCAmh 302.3

ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ ገና መልስ እየጠበቀ ነው፤ የመቅደሱ መንፃት ምንድን ነው? ከምድራዊው ቤተ መቅደስ ጋር ተያይዞ የነበር አገልግሎት እንደነበረ የብሉይ ኪዳን መፃሕፍት ይናገራሉ። ነገር ግን በሰማይ መጽዳት ያለበት ነገር ያለ ይሆን? የምድራዊውና የሰማያዊው የሁለቱም መቅደሶች መንፃት በዕብራውያን 9 ላይ በግልጽ ተብራርቷል። “እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነፃል፤ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።” እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው (በምድር ያለው) በዚህ [በእንስሳት ደም] ይንጻ እንጂ በሰማያት ያሉት ግን ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነፁ የግድ ነበረ [ዕብ 9÷22፣23]፤ እርሱም የክርስቶስ የከበረ ደም ነው። GCAmh 302.4

በምሳሌያዊው እና በእውነተኛው አገልግሎት የሚደረግ የማንፃት ሂደት የሚከናወነው በደም መሆን አለበት፤ በፊተኛው በእንስሳት ደም ሲሆን በኋለኛው ደግሞ በክርስቶስ ደም ነው። ይህ የማንፃት ሂደት በደም መከናወን ለምን እንዳለበት ጳውሎስ ምክንያት ሲሰጥ ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም ይላል። መከናወን ያለበት ሥራ ስርየት፣ ወይም ኃጢአትን ማስወገድ ነው። ነገር ግን በሰማይስ ሆነ በምድር ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዘ ሃጢአት እንዴት ሊኖር ይችላል? የምሳሌያዊውን (የብሉይ ኪዳኑን) አገልግሎት በማጣቀስ ይህ ሊስተዋል ይችላል፤ ምክንያቱም በምድር ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት “ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን” [ዕብ 8÷5] አገልግሎት ሲፈጽሙ ነበርና ነው። GCAmh 303.1

የምድራዊው ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሁለት ክፍል ነበረው። ካህናት በቅዱስ ስፍራው በየቀኑ ሲያገለግሉ ሳለ ሊቀ ካህኑ ደግሞ በአመት አንድ ጊዜ በቅድስተ ቅዱሳኑ የተለየ የማስተሰርየት ሥራ፣ መቅደሱን ለማንፃት ያገለግላል። እለት-ተዕለት ንስሐ የሚገባው ኃጢአተኛ መስዋዕቱን ወደ ድንኳኑ ደጃፍ ያመጣና እጁን በሚታረደው እንስሳ ራስ ላይ አድርጎ ኃጢአቱን ይናዘዛል፤ በዚህም ሁኔታ በምሳሌ የራሱን ኃጢአት ወደ በደል አልባው መስዋዕት ያስተላልፋል። ከዚያም እንስሳው ይታረድ ነበር። “ደም ሳይፈስ” ስርየት የለም ይላል ሐዋርያው። “የስጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነው” [ዘለ 17÷11]። የተጣሰው የእግዚአብሔር ሕግ የተላላፊውን ሕይወት ጠየቀ። ኩነኔውን ታራጁ የተሸከመለትን፣ የኃጢአተኛውን የተሰዋ ሕይወት የሚወክለውን ደም ካህኑ ወደ ቅዱስ ስፍራው ይወስደውና ኃጢአተኛው የተላለፈውን ሕግ የያዘውን ታቦት ከጋረደው መጋረጃ ፊት ለፊት ይረጨዋል። በዚህ ሥርዓተ ምሳሌ ኃጢአቱ በደሙ በኩል ወደ መቅደሱ ይገባ ነበር። አንዳንድ ጊዜያት ደሙ ወደ ቅዱስ ስፍራው አይወሰድም ነበር። ሙሴ የአሮንን ልጆች “የሕዝቡንም ኃጢአት እንድትሸከሙ ለእናንተ ሰጥቶታልና” [ዘለዋ 10÷17] ብሎ እንዳዘዛቸው ስጋውን ካህኑ ይበላው ነበር። ሁለቱም ስርዓቶች በምሳሌነት የሚወክሉት ኃጢአት፣ ኩነኔውን ከተናዘዘው ዘንድ ወደ ቤተ መቅደሱ መተላለፉን ነው። GCAmh 303.2

ሥራው በእንደዚህ ሁኔታ እለት እለት አመቱን ሙሉ ይቀጥል ነበር። የእሥራኤላዊያን ኃጢአት ወደ መቅደሱ ይተላለፍ ነበርና ይህንን ሁሉ ኃጢአት ለማስወገድ የተለየ ሥራ አስፈላጊ ነበር። ለእያንዳንዳቸው ቅዱስ ክፍሎች ስርየት እንዲደረግ እግዚአብሔር አዞ ነበር። “ከእሥራኤል ልጆች ርኩሰት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሳ ለመቅደሱ ያስተሰረይለታል፤ እንዲሁም በእርኩሰታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል” [ዘሌዋ 16÷16፣19]። ለመሰዊያውም ስርየት ይደረግለት ነበር “ከእሥራኤል ልጆች ርኩሰት ያነፃዋል ይቀድሰውማል።” [ዘሌዋ 16÷16፣19]። GCAmh 303.3

በታላቁ የስርየት ቀን በአመት አንድ ጊዜ መቅደሱን ያነፃ ዘንድ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባ ነበር። እዚያ የሚከናወነው ሥራ የዓመቱን አገልግሎት የሚቋጭ ነበር። በስርየት ቀን ሁለት የፍየል ጠቦቶች ወደ ድንኳኑ በር ይወሰዱና ዕጣ ይጣልባቸዋል። “አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር አንዱንም ዕጣ ለሚለቀቅ” [ዘሌዋ 16÷8]። የእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ዕጣ የወደቀበት ፍየል ለሕዝቡ ለኃጢአት መስዋዕት ሆኖ ይታረድ ነበር። ካህኑም ደሙን ይዞ መጋረጃውን አልፎ በስርየት መክደኛው ላይና በስርየት መክደኛው ፊት ይረጨው ነበር። ከመጋረጃው በፊት በሚገኘው የዕጣን መሰውያ ላይም ደሙ ይረጭ ነበር። GCAmh 303.4

“አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል በላዩም የእሥራኤልን ልጆች በደል ሁሉ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸከማል [….unto a Land not inhabited]” [ዘለዋ 16÷21፣22]። የተለቀቀው ፍየል ከዚያ ወዲያ ወደ እሥራኤል ሰፈር አይመጣም፤ ወደ በረሃ የወሰደውም ሰው ወደ ሰፈር ከመምጣቱ በፊት ራሱንና ልብሶቹን በውሃ ማጠብ ይጠበቅበት ነበር። GCAmh 304.1

ስነ-ስርዓቱ በጠቅላላ የተነደፈው የእግዚአብሔርን ቅድስና፣ ኃጢአትንም እንዴት እንደሚጠላ በእሥራኤላዊያን አዕምሮ ላይ እንዲቀረጽ ተደርጎ ነበር፤ በተጨማሪም ከኃጢአት ጋር ከተላከኩ ሳይረክሱ እንደማይቀሩ ለማሳየት ነበር። ይህ የስርየት ሥራ በሚደረግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ነፍሱን እንዲያሰቃይ ይጠበቅበት ነበር። ሥራ ሁሉ ይቆማል፣ የእሥራኤል ጉባኤ ሁሉ ቀኑን በታላቅ መዋረድ ሆነው በእግዚአብሔር ፊት በፀሎት በፆምና ልብን በጥልቅ በመመርመር ሊያሳልፉት ይገባ ነበር። GCAmh 304.2

ስርየትን በተመለከተ ምሳሌያዊው አገልግሎት አስፈላጊ እውነቶችን ያስተምራል። በኃጢአተኛው ፈንታ፣ ምትኩ ተቀባይነት ነበረው፤ ነገር ግን በሚታረደው [እንስሳ] ደም ኃጢአቱ አይጠፋም ነበር። ስለዚህም [ኃጢአቱ] ወደ ቤተ መቅደሱ የሚተላለፍበት መንገድ ተዘጋጅቶ ነበር። በደም መስዋዕት ኃጢአተኛው ለሕጉ ስልጣን እውቅና ይሰጣል፤ የተላለፈውንም ኩነኔ ንስሐ ይገባል፤ ሊመጣ ላለውም አዳኝ ባለው እምነት አማካኝነት ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት ያለውን ፍላጎት ይገልጻል፤ ሆኖም ግን ከሕጉ ኩነኔ ገና ሙሉ በሙሉ አይፈታም ነበር። በስርየት ቀን ከማህበሩ የተቀበለውን መስዋዕት ደም ይዞ ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባና መጠይቁን ያሟላ ዘንድ፣ ደሙን በስርየት መክደኛው ላይ፣ በቀጥታ ከሕጉ በላይ፣ ይረጨዋል። ከዚያም በመካከለኛነት ባህርይው ኃጢአቶቹን ሁሉ በራሱ ላይ አድርጎ፣ ከመቅደሱ ላይ ወስዶ ይሸከማቸዋል። በሚለቀቀው ፍየል ላይ እጆቹን በመጫን ኃጢአቱን ሁሉ በእርሱ ላይ ይናዘዛል። በምሳሌውም በእርሱ ላይ የነበረው ኃጢአቱ ሁሉ ወደ ፍየሉ ይተላለፋል። ፍየሉም ተሸክሞአቸው ይሄዳል፤ ኃጢአቶች ሁሉ ለዘላለም ከሕዝቡ እንደተለዩ ይታመን ነበር። GCAmh 304.3

“ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ” የሚሆነው ስርየት በዚህ መልክ ይፈፀም ነበር። በምድራዊው መቅደስ ውስጥ በምሳሌ የተከናወነው አገልግሎት፣ በሰማያዊው መቅደስ አገልግሎት በተግባር ይፈፀማል። አዳኛችን ካረገ በኋላ እንደ ሊቀ ካህን ሥራውን ጀምሮአል። ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስተ አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” [ዕብ 9÷24]። GCAmh 304.4

በመቅደሱ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ፣ እንደ በር ሆኖ በሚያገለግለው፣ ቅዱስ ክፍሉን ከውጨኛው ሥፍራ በሚለየው በ“መጋረጃው ውስጥ”፣ ካህኑ ዓመቱን ሙሉ የሚካሄደው አገልግሎት የሚወክለው ክርስቶስ እንዳረገ ያከናወነውን አገልግሎት ነው። የኃጢአት መስዋዕቱን ደምና ከእሥራኤል ፀሎት ጋር ወደ ላይ የሚወጣውን ዕጣን በእግዚአብሔር ፊት የማቅረብ አገልግሎት የካህኑ የዕለት ተዕለት ተግባር ነበር። እንዲሁም ክርስቶስ ደሙን በእግዚአብሔር ፊት ይዞ ስለ ኃጢአተኞች ይማልዳል፣ በተጨማሪም የራሱን ጽድቅ የከበረ መዓዛ፣ በፀፀት ውስጥ ካሉ አማኞች ፀሎት ጋር አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል። በሰማይ ያለው መቅደስ የመጀመሪያው ክፍል ይደረግ የነበረው አገልግሎት ይህን ይመስል ነበር። GCAmh 304.5

ከእይታቸው ወደ ላይ ሲወጣ ሳለ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እምነት ወደዚያ ቦታ ተከተለው። ተስፋቸው ማዕከል ያደረገው በዚህ ላይ ነበር፤ “ይህም ተስፋ” አለ ጳውሎስ “እንደ ነፍስ መልህቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው። በዚያም የሱስ ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።” “የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጃዎች ደም አይደለም።” [ዕብ 6÷19፣20፤ 9÷12]። GCAmh 305.1

ይህ አገልግሎት ለአሥራ ስምንት ምዕተ ዓመታት በመቅደሱ የመጀመሪያ ክፍል ቀጠለ። የክርስቶስ ደም ለሚፀፀቱ አማኞች ማለደ፤ ከአባቱ ይቅርታንና ተቀባይነትን አረጋገጠላቸው። ነገር ግን ኃጢአታቸው በመጽሐፍ መዝገብ ውስጥ እንደ ሰፈረ ነበር። በምሳሌው አገልግሎት በአመቱ መጨረሻ የስርየት ሥራ እንደነበረ ሁሉ፣ የክርስቶስ ሥራ ለሰው ልጅ ድነት ከመፈፀሙ በፊት፣ ኃጢአትን ከመቅደሱ ለማውጣት መከናወን ያለበት ሥራ ገና ይቀራል። ይህ አገልግሎት 2300 ቀናት ሲያልቁ የጀመረው አገልግሎት ነው። በዚያን ጊዜ በነቢዩ ዳንኤል እንደተነገረው፣ የከበረ ሥራውን የመጨረሻ ክፍል ለማከናወን — መቅደሱን ለማንፃት — ታላቁ ካህናችን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገባ። GCAmh 305.2

በጥንት ጊዜ እንደሚደረገው፣ የሕዝብ ኃጢአት በእምነት የኃጢአት መስዋዕቱ ላይ እንደሚጫን፣ በምሳሌም በደሙ በኩል ወደ ምድራዊው መቅደስ እንደሚተላለፍ፣ የአዲሱ ቃል ኪዳንም፣ ንስሐ የሚገቡ ሁሉ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ ተጭኖ [በምሳሌ ሳይሆን] በትክክል ወደ ሰማያዊው መቅደስ ይተላለፋል። የምድራዊውም ምሳሌያዊ ማንፃት የተበከለበትን ኃጢአት በማስወገድ እንደሚከናወን ሁሉ፣ እውነተኛው የሰማያዊ መንፃትም እዚያ ተመዝግበው ያሉትን ኃጢአቶች በማስወገድ ወይም በመደምሰስ ይከናወናል። ይህ ከመፈፀሙ በፊት ግን ኃጢአትን በመናዘዝ፣ በክርስቶስ እምነት በኩል እነማን የዚህ ስርየት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ለመወሰን የመዝገብ መጻሕፍት መመርመር አለባቸው። ስለዚህ የመቅደሱ መንፃት የምርመራ ሥራ፣ የፍርድ ሥራ ያካተተ ነው። ይህ ሥራ ክርስቶስ ሕዝቦቹን ነጻ ለማውጣት ከመምጣቱ በፊት መከናወን ያለበት ተግባር ነው፤ ምክንያቱም በሚመጣበት ጊዜ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለው ዘንድ ዋጋው ከእርሱ ጋር ይሆናልና። [ራእይ 22÷12]። GCAmh 305.3

ስለዚህም የትንቢቱን ቃል ብርሐን የተከተሉ እነዚያ በ2300 ቀናት ማብቂያ ማለትም በ1844 ዓ.ም፣ ለመምጣቱ የመጨረሻ መዘጋጀት የሚሆነውን የስርየትን የማጠቃለያ ሥራ ያከናውን ዘንድ ክርስቶስ በሰማይ ባለው መቅደስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባበት እንጂ ወደ ምድር የሚመጣበት እንዳልሆነ አስተዋሉ። GCAmh 305.4

በተጨማሪም የኃጢአት መስዋዕቱ፣ መስዋዕት ወደሆነው ክርስቶስ እንደሚጠቁሙ፣ ሊቀ ካህኑ መካከለኛ (አስታራቂ) የሆነውን ክርስቶስን እንደሚወክል፣ የሚለቀቀው ፍየል ደግሞ የኃጢአት ደራሲ የሆነውን፣ በእውነት ንስሐ የሚገባው ሰው ሁሉ ኃጢአት በመጨረሻ የሚጫንበትን፣ ሰይጣንን እንደሚወክል ግልጽ ሆነ። በኃጢአቱ የመስዋዕት ደም አማካኝነት ሊቀ ካህኑ ኃጢአትን ሁሉ ከመቅደሱ አንስቶ በሚለቀቀው ፍየል ላይ ያኖረው ነበር። በአገልግሎቱ መጨረሻ ክርስቶስም በራሱ ደም አማካኝነት የሕዝቦቹን ኃጢአት ሁሉ ከሰማያዊ ቤተ መቅደስ ያነሳና ፍርድ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የመጨረሻውን ቅጣት መሸከም ባለበት በሰይጣን ላይ ይጭነዋል። የሚለቀቀው ፍየል ወደ እሥራኤል ማህበር እንደገና ፈጽሞ ላይመለስ ሰው ኖሮበት ወደማያውቅ ምድር ይሸኛል። እናም ሰይጣን ለዘላለም ከእግዚአብሔርና ከሕዝቦቹ መገኘት ይወገዳል፤ ከዚያም በመጨረሻው የኃጢአትና የኃጢአተኞች ውድመት ጊዜ አብሮ ይጠፋል (ከህልውና ይፋቃል)። GCAmh 305.5