ታላቁ ተጋድሎ

22/45

ምዕራፍ ፲፱—ብርሐን በጨለማ ውስጥ ሲወጣ

በእያንዳንዱ ታላቅ ተሐድሶ ወይም ሐይማኖታዊ እንቅስቃሴ፣ ከዘመን ዘመን እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚሰራው ሥራ አስደናቂ ተመሳሳይነት እንዳለው ያሳየናል። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ግንኙነት የሚያካሂድባቸው መርሆዎች ሁል ጊዜም አንድ አይነት ናቸው። የዚህ ዘመን አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች በፊት ከነበሩት ጋር የሚነፃፀሩ ናቸው፤ እናም በጥንት ዘመናት ቤተ ክርስቲያን የነበራት ተሞክሮ ለዚህ ለእኛ ዘመን ታላቅ ዋጋ የያዘ ትምህርት አለው። GCAmh 251.1

እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት፣ ለድነት ሥራ ወደፊት መቀጠል፣ በታላላቅ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን በተለየ ሁኔታ እንደሚመራቸው ያለ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የሚያስተምረው እውነት የለም። ሰዎች፣ የፀጋና የምሕረት አላማዎቹን ለማስፈፀም የተቀጠሩ፣ በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ያሉ መሳሪያዎች ናቸው። እያንዳንዱ ለራሱ የተሰጠው፣ መሥራት ያለበት ኃላፊነት አለው፤ እያንዳንዱ እግዚአብሔር የሰጠውን ሥራ መፈፀም ይችል ዘንድ እርሱ ለሚኖርበት ዘመን አስፈላጊ ሁኔታዎች እንዲስማማ ተደርጎ ለሥራው የሚበቃ ብርሐን ተመጥኖ ተሰጥቶታል። ሆኖም ምኑንም ያህል ሰማይ ያከበረው ቢሆን የታላቁ የማዳን እቅድ ሙሉ በሙሉ የገባው ቀርቶ፣ በእርሱ የሕይወት ዘመን ሊሰራ ላለው ሥራ የመለኮት ዓላማ ምን እንደሆነ እንኳ ፍፁም በሆነ መልኩ ወደ መረዳት ደረጃ የደረሰ ማንም ሰው ኖሮ አያውቅም። ይሰሩ ዘንድ በሚሰጣቸው ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር ምን እንደሚያከናውን ሰዎች ሙሉ በሙሉ አይገባቸውም፤ በስሙ የሚናገሩትን መልእክት በሙሉ ይዘቱ አይረዱትም። GCAmh 251.2

“የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?”፤ “ሃሳቤ እንደ ሃሳባችሁ መንገዳችሁም እንደመንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።”፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም፤ በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ።” [እዮብ 11÷7፤ ኢሳ 55÷8፣9፤ 46÷9፣10]። GCAmh 251.3

በመንፈሱ የተለየ ብርሐን ሞገስ ያገኙት ነብያት እንኳ የተሰጣቸውን መገለጥ ሙሉ ለሙሉ አልተረዱትም ነበር። በውስጡ የታመቀው መልእክት የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሚፈልጉት መጠን፣ ከዘመን ዘመን ትርጉሙ ይገለጥ ዘንድ ነበረው። GCAmh 251.4

ጴጥሮስ፣ በወንጌሉ አማካኝነት ስለተገለጠው መዳን ሲጽፍ፣ “ስለዚህ መዳን ለእናንተም ስለሚሰጠው ፀጋ ትንቢት የተናገሩት ነብያት ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፣ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩት ነበር። እናንተን [እኛን/…not unto themselves but unto us they did minister…] እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው’” [1ኛ ጴጥ 1÷10-12]። GCAmh 251.5

የተገለጠላቸውን ነገር ሙሉ በሙሉ እንዲረዱት የተሰጣቸው ባይሆንም ነብያቱ ግን እግዚአብሔር ይገልጽ ዘንድ የወደደውን ብርሐን ሁሉ ያገኙ ዘንድ ከልባቸው ጥረዋል። እነርሱ “ተግተው እየፈለጉ መረመሩት”፤ “በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።” በዚህ ክርስትና ዘመን ላሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጥቅም ይሆኑ ዘንድ ለባሪያዎቹ የተሰጡት እነዚህ ትንቢታት እንዴት አይነት ትምህርት ይለግሷቸዋል! “እናንተን [እኛን] እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው”፤ እነዚያ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሰዎች ገና ላልተወለዱ ትውልዶች የሚሆኑ ስለተሰጧቸው መገለጦች “ተግተው እየፈለጉ” እንደመረመሩት መሰከሩ። ይህንን ቅዱስ ቅንዓታቸውን፣ የተሰጣቸውን ሰማያዊ ስጦታ በግድ-የለሽነትና በልፍስፍስነት ከሚመለከቱት የኋለኛው ዘመን የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር አነፃፀሩት። ምቾት አፍቃሪ፣ ዓለም አፍቃሪ ለሆነው፣ ትንቢታትን መረዳት አይቻልም ብሎ ለመናገር ላስቻለው ደንታ-ቢስነት ይህ ከባድ ወቀሳ ነው። GCAmh 252.1

ውስን የሆነው የሰዎች አዕምሮ ወደ ዘላለማዊው እግዚአብሔር ምክር ለመግባት ወይም የአላማውን ውጤት ሙሉ በሙሉ መረዳት ባይችልም፣ የሰማይን መልእክቶች እጅግ በደበዘዘ ሁኔታ የሚረዱት ግን በራሳቸው ስህተት ወይም ግድየለሽነት ምክንያት ነው። በፍጡር አመለካከቶች፣ በሰዎች ባህልና የሃሰት ትምህርቶች ምክንያት፣ እግዚአብሔር በቃሉ የገለጣቸውን ታላላቅ ነገሮች ሰዎች በከፊል ብቻ እንዲረዱት የሚያደርጋቸው፣ የእግዚአብሔርን ባርያዎች ጨምሮ፣ የሰዎች አእምሮ የሚታወርበት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ነው የሚባል አይደለም። አዳኙ በአካል አብሯቸው እያለ እንኳ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሁኔታ እንዲሁ ነበር። መሲሁ እሥራኤል የዓለም ገዢነት ዙፋንን እንድትቆናጠጥ የሚያደርግ ምድራዊ ልዑል ነው በሚለው ተወዳጅ ሃሳብ ህሊናቸው ተሞልቶ፣ ስለወደፊቱ መሰቃየቱና ሞቱ የሚናገሩትን የቃላቱን ትርጉም መረዳት ተሳናቸው። GCAmh 252.2

“ዘመኑ ተፈፀመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌሉም እመኑ” [ማር 1÷15] የሚለውን መልእክት ሰጥቶ የላካቸው ክርስቶስ ራሱ ነበር። የዚያ መልእክት መሰረቱ (መነሻው) ዳንኤል 9 ነበር። በመልአኩ የታወጁት ስድሳ ዘጠኝ ሳምንታት እስከ አለቃው እስከ መሲህ ዘመን ድረስ የሚዘልቁ ናቸውና ደቀ መዛሙርቱ በከፍተኛ ተስፋና ደስታ ዓለምን ሁሉ ይገዛ ዘንድ የመሲሁን መንግሥት በየሩሳሌም መመስረት ወደፊት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። GCAmh 252.3

ትርጉሙን ራሳቸው በትክክል ባይረዱትም፣ ክርስቶስ የሰጣቸውን ይህንኑ መልእክት ይሰብኩ ነበር። የሚናገሩት መልእክት በዳንኤል 9÷25 ላይ የተመሠረተ ቢሆንም መሲሁ እንደሚገደል የሚናገረውን በዚያው ምዕራፍ የሚቀጥለውን ጥቅስ ግን አላዩትም። ከመወለዳቸው ጀምሮ ልባቸው ያረፈው ሊመጣ ባለው ምድራዊ መንግሥት ክብር ላይ ነበር። ይህም፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ለትንቢቱ ዝርዝር መግለጫም ሆነ ለክርስቶስ ቃላት ዓይናቸው እንዲታወር አደረጋቸው። GCAmh 252.4

የምሕረትን ግብዣ ለአይሁድ ሕዝብ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን ተወጡ፤ ከዚያም ጌታ ወደ ዳዊት ዙፋን ሲወጣ ማየት በጠበቁበት በዚያው ጊዜ እንደ ወንጀለኛ ተይዞ ሲሰቃይ፣ ሲዘበትበት፣ ሲወገዝና በቀራንዮ መስቀል ላይ ሲንጠለጠል ተመለከቱ። ጌታቸው በመቃብር ተኝቶ ሳለ ምን አይነት ተስፋ መቁረጥና መሪር ሃዘን የነዚያን ደቀ መዛሙርት ልቦች ይጨምቀው ነበር! GCAmh 252.5

ትንቢቱ በተነገረበት በእቅጩ ጊዜና አኳኋን ክርስቶስ መጣ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት በእያንዳንዱ የአገልግሎቱ ክንዋኔ ክስተት ተፈጽሟል። የመዳንን መልእክት ሰበከ፤ “ቃሉ በስልጣን ነበር” [ሉቃስ 4÷32]። ሰማያዊ እንደሆነ የሰሚዎቹ ልቦች መስክረው ነበር። ቃሉና የእግዚአብሔር መንፈስ የልጁን መለኮታዊ ተልዕኮ መስክረዋል። GCAmh 253.1

ደቀ መዛሙርቱ በማይሞት ፍቅር ከተወዳጁት ጌታቸው ጋራ አሁንም ተጣብቀው ነበር። ሆኖም ህሊናቸው በጥርጥርና በማወላወል ተሸፍኖ ነበር። በስቃይ ውስጥ በነበሩበት በዚያን ጊዜ ወደ ስቃዩና ወደ ሞቱ ያመላከተበትን የክርስቶስ ቃላት ማስታወስ አልቻሉም ነበር። የናዝሬቱ የሱስ፣ በእርግጥ እውነተኛው መሲህ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ በሐዘንና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይዘፈቁ ነበርን? በሞቱና በትንሳኤው መካከል በነበሩት በነዚያ ተስፋ ቢስ የሰንበት ሰዓታት፣ አዳኙ በመቃብሩ ተኝቶ በነበረበት ጊዜ፣ ነፍሳቸውን ይገርፈው የነበረ ጥያቄ ይህ ነበር። GCAmh 253.2

የሃዘን ሌሊቱ በእነዚህ የየሱስ ተከታዮች ዙሪያ ቢጠቁርም የተተዉ ግን አልነበሩም። ነብዩ እንዲህ ይላል፦ “በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሐን ይሆንልኛል…. ወደ ብርሐን ያወጣኛል ጽድቁንም አያለሁ።” “ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና ሌሊትም እንደቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሐንዋ ነው።” እግዚአብሔር ተናግሯል፦ “ለቅኖች ብርሐን በጨለማ ወጣ።” “እውሮችንም በማያውቁት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሐን አደርጋለሁ ጠማማውንም አቃናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም።” [ሚክ 7÷8፣9፤ መዝ 139÷12፤ 112÷4፤ ኢሳ 42÷16]። GCAmh 253.3

በጌታ ስም የተደረገው የደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዱ አዋጅ ትክክል ነበር፤ የሚጠቁማቸው ክስተቶችም በዚያው በተመሳሳይ ጊዜ እየተፈፀሙ ነበር። መልዕክታቸው፣ “ዘመኑ ተፈፀመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች” ነበር። በ”ዘመኑ” ማብቂያ እስከ መሲሁ፣ “የተቀባው”፣ ድረስ በሚዘልቁት የዳንኤል 9 ስድሳ ዘጠኙ ሳምንታት ማለቂያ ላይ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ክርስቶስ በመንፈስ መቀባትን አግኝቶ ነበር። ቀርባለች ብለው ያወጁላት “የእግዚአብሔር መንግሥት”ም በክርስቶስ ሞት ተመሠረተች። እንዲያምኑ ሆነው እንደተማሩት ይህ መንግሥት ምድራዊ አልነበረም። “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም በታች ሁሉ ያሉ መንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ” በሚሰጥበት ጊዜ የሚቋቋመው የወደፊት ዘላለማዊ መንግሥትም አልነበረም፤ ስለዚያ “የዘላለም መንግሥት፤ ግዛቶችም ሁሉ” ስለሚገዙለት መንግሥት አልነበረም [ዳን 7÷27]። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ እንደዋለው “የእግዚአብሔር መንግሥት” የሚለው አነጋገር የፀጋን መንግሥትና የክብርን መንግሥት ሁለቱንም እንዲወክል ተደርጎ ነው። የፀጋን መንግሥት ጳውሎስ በዕብራውያን በፃፈው መልእክቱ ወደ እይታ አምጥቶታል። ወደ ክርስቶስ ከጠቆመ በኋላ “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ሩህሩህ አማላጅ እንዳለን በማውሳት “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳን ፀጋ እንድናገኝ ወደ ፀጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” ይላል። [ዕብ 4÷16]። የፀጋ ዙፋን የሚወክለው የፀጋ መንግሥትን ነው፤ የዙፋን መኖር የሚያመለክተው የመንግሥትን መኖር ነውና። በብዙ ምሳሌዎቹ ክርስቶስ “የሰማይን መንግሥት” በማለት የሚገልጸው የመለኮታዊ ፀጋ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ በመወከል ነው። GCAmh 253.4

ስለዚህ የክብር ዙፋን የክብር መንግሥትን ይወክላል፤ ይህ መንግሥት በአዳኙ ቃላት ሲገለጽ ፦ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላዕክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ” [ማቴ 25÷31፣32]። ይህ መንግሥት ገና የወደፊት ነው። እስከ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ድረስ የሚመሰረት አይደለም። GCAmh 254.1

ልክ ሰው እንደወደቀ፣ ለኃጢአተኛው ዘር መዳን ይሆን ዘንድ እቅድ በተነደፈበት ጊዜ፣ የፀጋ መንግሥት ተጀመረ። ይህም መንግሥት በእግዚአብሔር እቅድና በተስፋው ሕያው ነበረ፤ በእምነትም አማካይነት ሰዎች ተገዥዎቹ መሆን ይችሉ ነበር። ሆኖም እስከ ክርስቶስ ሞት ድረስ ገና አልተቋቋመም ነበር። አዳኙ የምድራዊ ተልዕኮውን ከጀመረ በኋላ እንኳ በሰዎች ግትርነትና ምስጋና-ቢስነት ዝሎ ከቀራንዮ መስዋዕትነት ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ ይችል ነበር። በጌቴሰማኒ፣ የስቃይ ጽዋው በመዳፉ ውስጥ ተርበተበተች፤ በዚያን ጊዜም የደም ላቡን ከግንባሩ ጠርጎ ውግዙ ዘር በኃጢአታቸው እንዲሞቱ ትቷቸው መሄድ ይችል ነበር። ይህንን ቢያደርግ ኖሮ ለወደቁ ፍጡራን መፍትሔ አይኖርም ነበር። ሆኖም አዳኙ ሕይወቱን አሳልፎ ሲሰጥና እየተሟጠጠ በነበረው እስትንፋሱ “ተፈፀመ” ብሎ ሲጮህ፣ ያኔ፣ የድነት እቅድ መፈጸሙ ተረጋገጠ። በኤደን ለነበሩት ኃጢአተኛ ጥንዶች የተገባው የማዳን ተስፋ ፀደቀ። በእግዚአብሔር ተስፋ አማካኝነት ቀድሞ የነበረው የፀጋ መንግሥት በዚያን ጊዜ ተመሠረተ። GCAmh 254.2

ደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻው የተስፋቸው መፈራረስ አድርገው ያዩት የክርስቶስ ሞት፣ ተስፋቸው ለዘላለም እንዲረጋገጥ ያደረገ ነበር። ወደ ከባድ ሃዘን ቢያስገባቸውም እምነታቸው ትክክል እንደነበረ የሚያሳይ፣ ከሁሉም የሚበልጠው ማስረጃ ነበር። በእንጉርጉሮና በተስፋ መቁረጥ የሞላቸው ያ ክስተት ለእያንዳንዱ የአዳም ልጅ የተስፋ በር የከፈተ፣ በዘመናት ሁሉ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ ዘላለማዊ ደስታቸውና የወደፊት ሕይወታቸው ማዕከል የሆነ ነበር። GCAmh 254.3

በደቀ መዛሙርቱ ተስፋ መቁረጥ የተነሳ በመጣው ሃዘን ውስጥ እንኳን የወሰን የለሽ የምሕረት እቅዶች ፍፃሜ እያገኙ ነበር። “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” [ዮሐ 7÷46] በተባለለት መለኮታዊ ፀጋና በትምህርቱ ስልጣን ልባቸው ተማርኮ የነበረ ቢሆንም ቅሉ ለክርስቶስ ከነበራቸው የፍቅር ንፁህ ወርቅ ጋር የዓለማዊ ኩራትና የራስ ወዳድነት ምኞት ተራ ብረት ተቀላቅለው ነበሩበት። ጌታቸው የጌቴሰማኒ ጥላ ወደሚያርፍበት ወደዚያ አስጨናቂ ሰዓት በገባበት በዚያ ጊዜ የፋሲካው በዓል በተከበረበት ክፍል እንኳ “ደግሞም ማናቸው ታላቅ ሆኖ እንዲቆጠር በመካከላቸው ክርክር ነበር” [ሉቃ 22÷24]። የአትክልት ስፍራው ውርደትና ውጋት፣ የፍርድ ወንበሩና የቀራንዮ መስቀል በፊታቸው ቀርቦ እያለ፣ የእነርሱ ራዕይ በዙፋኑ፣ በዘውዱና በክብሩ የተሞላ ነበር። በጊዜያቸው የነበረውን የሐሰት ትምህርት የሙጥኝ እንዲሉ፣ የመንግሥቱን ትክክለኛ ባህርይ የሚያሳዩትን፣ ወደ ስቃዩና ወደ ሞቱ የሚጠቁሙትን የአዳኙን ቃላት ሳያስተውሉ እንዲያልፏቸው ያደረገው የልባቸው በእብሪት መወጠርና ለዓለማዊ ክብር የነበራቸው ጥማት ነበር። እነዚህም ክስተቶች ከባድ፣ ግን ደግሞ ይታረሙ ዘንድ በላያቸው እንዲመጣ የተፈቀደውን አስፈላጊ ፈተና አስከተለ። ደቀ መዛሙርቱ የመልዕክታቸውን ትርጉም በተሳሳተ መንገድ ተረድተው፣ የሚጠብቁት ምን እንደሆነ ማወቅ ቢሳናቸውም፣ በእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ሰብከዋልና ጌታ ለዚያ እምነታቸው ዋጋ ይከፍላቸዋል፤ መታዘዛቸውንም ከፍተኛ ክብር ይሰጠዋል። የጌታቸውን ከመቃብር የመነሳት የከበረ ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ በማዳረስ የፋና ወጊነቱ ኃላፊነት በአደራ ይሰጣቸው ዘንድ ነበራቸው። ለእነርሱ እጅግ መራራ የመሰለው ተሞክሮ እንዲገጥማቸው የተፈቀደበት ምክንያትም ለዚህ ሥራ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነበር። GCAmh 254.4

ከትንሳኤው በኋላ በኤማሁስ መንገድ ላይ የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ፣ “ከሙሴና ከነብያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመፃሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጎመላቸው” [ሉቃስ 24÷27]። የደቀ መዛሙርቱ ልብ ተነሳሳ፤ እምነት ተቀጣጠለ። የሱስ ገና ራሱን ሳይገልጥላቸው “ለሕያው ተስፋ” [1ኛ ጴጥ 1÷3] እንደገና ተወለዱ። መረዳታቸውን ቦግ ሊያደርገው፣ “እጅግ [በ]ፀና የትንቢት ቃል” [2ኛ ጴጥ 1÷10] ላይም እምነታቸውን ሊያፀናው አላማው ነበር። እውነት በአዕምሯቸው ጠንካራ ሥር እንዲሰድ የተመኘው በራሱ ግላዊ ምስክርነት በመደገፋቸው ምክንያት ብቻ ሳይሆን እርግጥ በሆኑት፣ ወደፊት ሊሆን ላለው ጠቋሚ በነበረው የሕጉ ተምሳሌቶችና ጥላዎች፣ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ትንቢታት ጭምር ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች በእውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም ለግላቸው ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን እውቀት ወደ ዓለም እንዲያሰራጩት ነው። ይህንንም እውቀት ለማካፈል እንደመንደርደሪያ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ “ሙሴና ነብያት” አመላከታቸው። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አስፈላጊነትና ዋጋ፣ በእንዲህ መልኩ በተነሳው አዳኝ ምስክርነት ምን ያህል እንደሆነ ታይቷል። GCAmh 255.1

ተወዳጅ የሆነውን የጌታቸውን የፊት ገጽታ እንደገና ሲመለከቱ በደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ነበር የመጣው! [ሉቃ 24÷27] ከአሁን በፊት ይሰጥ ከነበረው ትርጉም ለየት ባለ፣ ሙሉና ፍፁም በሆነ ሁኔታ “ሙሴ በሕግ ነብያትም ስለ እርሱ የፃፉትን” [ዮሐ 1÷46] አገኙት። ጥርጣሬው፣ ጭንቀቱ፣ ተስፋ መቁረጡ፣ ለፍፁም ዋስትናና ላልደበዘዘ እምነት ቦታ ለቀቀ። ከእርገቱ በኋላ “ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ” [ሉቃ 24÷53] መኖራቸው የሚያስደንቅ ተዓምር ነበር። የውርደት ሞቱን ብቻ ያወቁ ሰዎች በደቀ መዛሙርቱ ፊት ላይ ለማየት የጠበቁት የሀዘንን፣ የግራ መጋባትንና የመሸነፍን ገጽታ ቢሆንም፤ ደስታንና ድልን ተመለከቱ። ወደ ፊት ለሚጠብቃቸው ሥራ እንዴት አይነት ዝግጅት ሆነላቸው! መለማመድ እስከሚችሉት መጠን እጅግ ከባድ በሚባል ፈተና አልፈው፣ በፍጡር እይታ ሁሉም ነገር የታጣ ቢመስልም፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን በእንዴት ያለ ድል ፍፃሜ እንዳገኘ አይተዋል። ከአሁን በኋላ እምነታቸውን የሚሸረሽር ወይስ የፍቅራቸውን ግለት የሚያቀዘቅዝ ምን ሊኖር ይችላል? ከባድ ሃዘናቸው ውስጥ “ብርቱ መጽናናት” “እንደ ነፍስ መልህቅ እርግጥና ጽኑ” ተስፋ ሆነላቸው [ዕብ 6÷18፣19]። የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ምስክሮች ነበሩና “ሞት ቢሆን ሕይወትም ቢሆን መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን ኃይላትም ቢሆኑ” “በክርስቶስ የሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር”፣ “ሊለያቸው አይችልም።” “በዚህ ሁሉ ግን” አሉ፣ “በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” [ሮሜ 8÷38፣39፣37]። “የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል” [1ኛ ጴጥ 1÷25]። “የሚኮንንስ ማነው? የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ የሱስ ነው።” [ሮሜ 8÷34]። GCAmh 255.2

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም” [ኢዮኤ 2÷26]። “ለቅሶ ማታ ይመጣል ጠዋት ግን ደስታ ይሆናል” [መዝ 30÷5]። ከሞት በተነሳበት ቀን እነዚህ ደቀ መዛሙርት ከአዳኙ ጋር ሲገናኙ ከሚናገራቸው ቃላት የተነሳ ልባቸው ሲቀልጥ ሳለ፣ ለእነርሱ የቆሰሉትን እጆቹን፣ ራሱንና እግሮቹን ሲመለከቱ ሳለ፣ ከማረጉ በፊት ራቅ ብሎ ወደ ቢታንያ ሲመራቸውና እጁን አንስቶ እየባረካቸው “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ስበኩ” “እነሆም ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” [ማር 16÷15፤ ማቴ 28÷20] ብሎ ሲነግራቸው ሳለ፣ በጴንጤቆስጤ ቀን አጽናኙ ሲወርድ፣ ከላይ የመጣው ኃይል ሲሰጥ፣ አማኞቹ የአረገው ጌታቸው በእርግጥ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ተሰምቷቸው ነፍሳቸው ስትፈነድቅ ሳለ፣ እንደ ጌታ ሁሉ የእነርሱም መንገድ በመስዋዕትነትና በሰማዕትነት ጎዳና የሚመራቸው ቢሆንም ከጸጋው ወንጌል አገልግሎት ጋር የሚመጣውን፣ እንደገና ሲመጣ ሊቀበሉት ያላቸውን “የጽድቅ አክሊል”፣ [2ኛ ጢሞ 4÷8] ቀድሞ በነበረው የደቀ መዛሙርትነት ማንነታቸው ሲመኙ በነበረው የምድራዊ ዙፋን ክብር ይለውጡት ኖሮ ይሆን? “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ የሚቻለው” [ኤፌ 3÷25] እርሱ የመሰቃየቱን አብሮነት፣ የደስታው ተካፋይ የመሆንን፣ “ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ” [ዕብ 2÷10] ያለውን ደስታ፣ ሊገለጽ የማይችል ደስታ፣ “የክብርን የዘላለም ብዛት” በማለት ጳውሎስ የሚናገርለት “ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን” “ቢመዛዘን…ምንም እንዳይደለ [ለንጽጽር የማይበቃ/not worthy to be compared]” ያለለት ሁሉ ተካፋይ አደረጋቸው። GCAmh 256.1

በመጀመሪያው የክርስቶስ ምፅዓት ጊዜ “የመንግሥቱን ወንጌል” የሰበኩበት የደቀ መዛሙርት ተሞክሮ የዳግም ምፅዓት መልእክቱን ከሰበኩት ተሞክሮ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። “ዘመኑ ተፈፀመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች” [ማር 1÷15] በማለት ወደ ማስተዋል የመጣው ረጅሙና የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሊያበቃ እንደሆነ፣ ፍርዱ በደጅ እንደሆነና የዘላለም መንግሥት ሊጀምር እንደሆነ ሚለርና ጓደኞቹ አወጁ። ዘመንን በተመለከተ የደቀ መዛሙርቱ ስብከት ዳንኤል 9ን መሰረት ያደረገ ነበር። የሚለርና የግብረ-አበሮቹ መልእክት፣ የዳን 8÷14፣ ሰባዎቹ ሳምንታት አካል የሆኑበትን የ2300 ቀናት ማብቂያ የሚናገር ነበር። የእያንዳንዳቸው ትምህርት አንድ ታላቅ ትንቢታዊ ክፍለ ዘመን የተለያዩ ክፍሎች ፍጻሜ በማግኘታቸው ላይ የተመሠረተ ነው። GCAmh 256.2

እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ዊሊያም ሚለርና ግብረ አበሮቹም ራሳቸው የተሸከሙትን መልእክት ቁም ነገር ሙሉ በሙሉ አልተረዱትም ነበር። በቤተ ክርስቲያን ሥር ሰደው የነበሩት ስህተቶች በትንቢት ውስጥ አስፈላጊ ነጥብ ወደሆነው ትክክለኛ ፍቺ ላይ እንዳይደርሱ አገዷቸው። ስለሆነም ለዓለም ያደርሱ ዘንድ እግዚአብሔር በአደራ የሰጣቸውን መልእክት ማወጅ ቢችሉም፣ ትርጉሙን በትክክል አለመረዳታቸው ቅሬታ እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆነ። GCAmh 256.3

ዳንኤል 8÷14ን ፦ “እስከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነፃል” የሚለውን ሲያብራራ፣ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው፣ ሚለር፣ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን እይታ፣ ማለትም ቤተ መቅደሱ ምድር ናት የሚለውን ሐሳብ በመቀበል የመቅደሱ መንፃት የሚወክለው ጌታ ሲመጣ ምድር በእሳት የምትፀዳበትን ክስተት ነው ብሎ አመነ። በመሆኑም የ2300 ቀናቱ መጨረሻ በትክክል እንደተነገረ ሲያውቅ፣ ይህ ጊዜ የሚያመለክተው ዳግም ምፅዓቱን መሆን አለበት ብሎ ደመደመ። ስህተቱ የመነጨው ቤተ-መቅደሱ ምንን ይወክላል የሚለውን በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት ያገኘውን እይታ መቀበሉ ነበር። GCAmh 256.4

በምሳሌያዊው (በብሉይ ኪዳኑ) ሥርዓት - የክርስቶስን መስዋዕትነትና ካህንነት የሚወክለው ጥላ - በሊቀ ካህኑ ከሚከናወኑ አመታዊ አገልግሎቶች ውስጥ የመቅደሱ መንፃት አገልግሎት የመጨረሻው ክፍል ነበር። የመጨረሻ የሆነው የመንፃት ሥራ የሚከናወንበት፣ ኃጢአት ከእሥራኤል ዘንድ የሚወገድበት ወይም የሚጣልበት የስርዓቱ መደምደሚያ ነበር። ይህም አስቀድሞ የገለጸው በሰማያዊ መዛግብት ሰፍረው ያሉትን የሕዝቦቹን መተላለፎች ያስወግድ ወይም ይፍቅ ዘንድ በሰማይ ያለው ሊቀ ካህናችን የሚያከናውነው የመጨረሻ አገልግሎቱን ነበር። ይህ አገልግሎት የምርመራን ሥራ፣ የፍርድን ሥራ የሚያካትት ሲሆን ክርስቶስ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማያዊ ደመና ከመገለጡ በፊት የሚያከናወን ነው፤ ምክንያቱም እርሱ የሚገለጠው እያንዳንዱ መዝገብ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ነውና። የሱስ ሲናገር፦ “ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ” [ራእይ 22÷12] አለ። ክርስቶስ ልክ ሊመጣ ሲል የሚከናወነው ይህ አገልግሎት ነው በመጀመሪያው መልአክ መልእክት በራዕይ 14÷7 ላይ የተነገረው፦ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት።” GCAmh 257.1

ይህንን ማስጠንቀቂያ ያወጁ እነርሱ ትክክለኛውን መልእክት በትክክለኛው ጊዜ ተናገሩ። ነገር ግን “ዘመኑ ተፈፀመ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” ብለው በዳንኤል 9 ትንቢት ተመርኩዘው ቢናገሩም በዚያው ጥቅስ ውስጥ ያለውን የመሲሁን ሞት መገንዘብ እንደተሳናቸው ሁሉ ሚለርና ግብረ አበሮቹም መልዕክቱን በዳንኤል 8÷14 እና በራእይ 14÷7 መሰረት ሰብከው፣ ከጌታ ምፅዓት በፊት መታወጅ ያለባቸው በዛው በራእይ 14 ያሉ ሌሎች መልእክቶች መኖራቸውን ማየት ተሳናቸው። በሰባዎቹ ሳምንታት መጨረሻ ስለሚቋቋመው መንግሥት ደቀ መዛሙርቱ እንደተሳሳቱ ሁሉ አድቬንቲስቶችም በ2300 ቀናት መጨረሻ የሚከናወኑትን ክስተቶች በተመለከተ ስህተት ሰሩ። በሁለቱም አዕምሮ እውነትን እንዳያገኝ ያወሩትን፣ በስፋት ተቀባይነት ያላቸውን ስህተቶች የመቀበል፣ እንዲያውም በጽኑ የመደገፍ ሁኔታ ነበር። ሁለቱም መደቦች እርሱ እንዲሰጥ የፈለገውን መልእክት በማድረስ፣ ሁለቱም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽመዋል፤ ሁለቱም መልእክቱን በራሳቸው የተሳሳተተ መንገድ በመረዳታቸው ቅር ተሰኝተዋል (አዝነዋል)። GCAmh 257.2

የፍርድ ማስጠንቀቂያው እንደነበረ እንዲታወጅ በመፍቀዱ ግን እግዚአብሔር መልካም የሆነውን አላማውን አሳክቷል። ታላቁ ቀን ቅርብ ነበር፤ በልባቸው ያለውን ይገልጽላቸው ዘንድ በምሪቱ በግልጽ ወደታወቀ የጊዜ ፈተና እንዲደርሱ አደረገ። መልእክቱ የተነደፈው ለቤተ ክርስቲያን መፈተኛና መንፃት እንዲሆን ነበር። መሻቶቻቸው በዚህ ምድር ላይ ወይስ በክርስቶስና በሰማይ ላይ ያረፉ መሆናቸውን እንዲያዩ መመራት ነበረባቸው። አዳኙን እንደሚወዱት መስክረዋል፤ አሁን ፍቅራቸውን በተግባር ማሳየት ነበረባቸው። ዓለማዊ ተስፋዎቻቸውንና ምኞቶቻቸውን ትተው የጌታቸውን መምጣት በደስታ ይቀበሉት ይሆን? መልእክቱ መንፈሳዊ ደረጃቸው በትክክል ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማስተዋል እንዲችሉ እንዲያደርጋቸው የታሰበ ነበር፤ በንስሐ እና ራስን በማዋረድ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እንዲነቃቁ በምሕረት የተላከ ነበር። GCAmh 257.3

ቅሬታውም ያወጁትን መልእክት በተሳሳተ መንገድ የመተርጎማቸው፣ የራሳቸው ሥራ ውጤት ቢሆንም ለመልካም እንዲሆንላቸው ተለወጠ። ማስጠንቀቂያውን ተቀብለናል ብለው የመሰከሩትን ልብ ይፈትናል። ይህ ቅሬታ ሲጋረጥባቸው ልምምዳቸውን በችኮላ ትተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያላቸውን እምነት ይጥሉታል? ወይስ በፀሎትና ራስን በማዋረድ የትንቢቱን አስፈላጊነት ያልተረዱት የት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ይጥራሉ? ከፍርሃት ወይም ከስሜት ግፊትና ከመቅበጥበጥ ምን ያህሉ እርቀዋል? በግማሽ ልብ የነበሩና የማያምኑስ ምን ያህሉ ነበሩ? የክርስቶስን መገለጥ እንደሚፈልጉ እልፍ አዕላፋት ተናግረዋል። የዓለምን ስድብና ነቀፋ፣ የመዘግየትንና ቅር የመሰኘትን ፈተና እንዲቋቋሙ ሲጠሩ እምነቱን ይክዱ ይሆን? እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያለውን ጉዳይ ወዲያውኑ ባለመረዳታቸው ምክንያት ፈጽመው ግልጽ በሆኑ የቃሉ ምስክርነቶች ፀንተው የቆሙትን እውነቶች ወደ ጎን ገሸሽ ይሏቸው ይሆን? GCAmh 258.1

ይህ ፈተና፣ እውነተኛ እምነት ያላቸው እነርሱ፣ የቃሉ አስተምህሮና የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ብለው ያመኑትን የሚታዘዙ እነርሱ፣ ያላቸው ጥንካሬ ምን ያህል እንደሆነ የሚገልጽ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን የራሱ ተርጓሚ በማድረግ ፈንታ የሰዎችን ጽንሰ-ሐሳብና ማብራሪያ የመቀበልን አደጋ ከዚህ አይነት ልምምድ ውጪ ሌላ ሊያስተምራቸው በማይችል ሁኔታ ያስተምራቸዋል። ለእምነት ልጆች፣ ከስህተታቸው የተነሳ የሚመጣ ግራ መጋባትና ሃዘን የሚፈለገውን ማስተካከያ ለማድረግ ይሠራል። የትንቢታዊ ቃሉን በትኩረት እንዲያጠኑ ይመራቸዋል። የእምነታቸውን መሰረት በጥንቃቄ እንዲመረምሩ ይማራሉ፤ በክርስትናው ዓለም በስፋት ተቀባይነት ያለው ቢሆን እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ያልተመሠረተ ማንኛውንም ነገር እንዲቃወሙ ይማራሉ። GCAmh 258.2

እንደ ጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ፣ ለእነዚህም አማኞች፣ በፈተና ጊዜ ለመረዳት የማይቻለው፣ ደብዛዛ የነበረው፣ ወደፊት ግልጽ ይሆናል። “የጌታን መጨረሻ” ሲመለከቱ ከስህተታቸው የተነሳ ቢፈተኑም ለእነርሱ ያለው የፍቅር እቅድ ሳያቋርጥ እየተፈፀመ እንደሆነ ይገባቸዋል። “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም” እንደሆነ፤ “ቃል ኪዳኑንና ምክሩን ለሚጠብቁ” መንገዶቹ ሁሉ “ቸርነትና እውነት” [ያዕ 5÷11፤ መዝ 25÷10] እንደሆኑ በዚህ የተባረከ ልምምድ ይማራሉ። GCAmh 258.3