የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ አርባ ሦስት—ቅድመ-ወሊድ ተጽዕኖዎች
እናቶች ለመሆን ሴቶች መብሰል ይጠበቅባቸዋል፦ ለእናትነት ብቁ ከመሆናቸው በፊት ሴቶች ትልቅ የትዕግሥት ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። ለዚህ ሥራ ገጣሚ እንዲሆኑ እግዚአብሔር ለይቷቸዋል። ከክርስቶስ ጋር ባላት ቁርኝት የእናት ተግባር ዘለዓለማዊ ይሆናል፤ ከምንረዳው በላይ ነው። የሴቶች ቢሮ ቅዱስ ነው። የእናትየዋ አገልግሎት ቤትዋን ወደ ቤቴል ይቀይረው ዘንድ ክርስቶስ በቤቱ መገኘትያስፈልገዋል። ባልና ሚስት መተባበር አለባቸው። እናቶች በእግዚአብሔር መሠውያ ላይ እራሳቸውን ቢቀድሱ፣ እንዲሁም ከመወለዳቸው በፊትና በኋላ ልጆቻቸውን ለእግዚአብሔር ቢቀድሱ እንዴት ዓይነት ዓለም ይኖረን ነበር! 1 AHAmh 178.1
የቅድመ-ወሊድ ተጽዕኖ አስፈላጊነት፦ የቅድመ-ወሊድ ተጽዕኖ የሚያስከትለው ውጤት በብዙ ወላጆች ዘንድ ብዙም ቦታ የማይሰጠው ነው። ሰማይ ግን እንደዚያ አያየውም። በእግዚአብሔር መልአክ የተላከው መልእክት ሁለት ጊዜም በከበረ መልኩ መሰጠቱ፣ ከሁሉም በላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አስተሳሰባችን የሚያሻው እንደሆነ የሚያመላክት ነው። AHAmh 178.2
ለእብራዊትዋ እናት [የማኑሄ ሚስት] የተነገረው ቃል እግዚአብሔር በሁሉም ዘመን ለሚኖሩ እናቶች የሚናገረው ነው። “ትጠንቀቅ” መልአኩ አለ “ያዘዝኳትን ሁሉ ታድርግ።” የልጁ ደህንነት በእናቱ ልማዶች ተጽዕኖ ይደርስበታል። የምግብ ፍላጎትዋንና ምኞቶችዋን መርህ ሊቆጣጠራቸው ይገባል። እግዚአብሔር ልጅ ስለሰጣት ለእርስዋ ያለውን ዓላማ ለማሳካት ክፉውን ነገር መቃወም ግድ ይላታል። 2 AHAmh 178.3
ለለጋዎቹ የህፃኑ እግሮች ዓለም በአሽከላ የተሞላ ነው። እጅግ ብዙዎች በራስ-ወዳድና ስሜትን በሚያረካ ሕይወት ተከበዋል። የደስታ ጎዳና የሚመስላቸው መንገድ የያዘውን አደጋ እንዲሁም መጨረሻው ምን እንደሆነ አያውቁም። ለጥማታቸውና ለፍላጎታቸው እርካታ ሲባዝኑ ኃይላቸውን ያባክናሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ ዓለምም ሆነ ለሚመጣው ጠፍተዋል። ልጆቻቸው እነዚህ ፈተናዎች ሊገጥሟቸው ግድ እንደሆነ ወላጆች ማስታወስ ይጠበቅባቸዋል። ልጁ ከመወለዱ በፊት ጀምሮ ክፋትን በተሳካ ሁኔታ መቃወም የሚችልበት ዝግጅት ሊደረግለት ይገባል። 3 AHAmh 178.4
ልጅ ከመወለዱ በፊት እናትየዋ የራስዋን ፍላጎት ለማርካት የምትሮጥ ራስ-ወዳድ፣ ትዕግሥት-የለሽና በቃኝን የማታውቅ ከሆነች፣ እነዚህ ባህርያት በልጁ ጠባይም የሚታዩ ይሆናሉ። በመሆኑም ሊያሸንፏቸው እጅግ የሚከብዷቸውን የክፋት ዝንባሌዎች ብዙ ልጆች እንደ ብኩርና ከእናቶቻቸው ወርሰዋል። እናትየዋ ግን ሳትዋዥቅ ለትክክለኛ መርህ ከቆመች፤ ታጋሽና ራስዋን የምትክድ ከሆነች፤ ቸር የዋህና እራስዋን ከሌሎች አስበልጣ የማታይ ከሆነች እነዚህን ወርቃማ ባህርያት ለልጅዋ ልታወርስ ትችላለች። 4 AHAmh 178.5
ለቅድመ-ወሊድ ጥንቃቄ የሚያስፈልጉ ነገሮች፦ እናት ልጆችዋን ከመውለዷ በፊት የነበራትን ሕይወት ምንም ሳትቀይረው በእርግዝና ወቅትም መቀጠልዋ በተለምዶ የምትሠራው ስህተት ነው። በዚህ አስፈላጊ ወቅት የእናትየዋ ሥራ ሊቀልላት ይገባል። በአካልዋ ከፍተኛ ለውጥ እየተካሄደ ነው። ብዙ ደም ስለሚያስፈልጋት ደም ሊጨምሩ የሚችሉ ምርጥ ምግቦችን መመገብ አለባት። የተሟላ ንጥረ-ነገር የያዙ ምግቦችን በገፍ ካላገኘች፣ አካላዊ ጥንካሬዋን ጠብቃ መቆየት አትችልም። የሚወለደው ልጅም ንቃት የጎደለው ይሆናል።* አልባሳትዋም ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። ሰውነትዋ ከቅዝቃዜ እንዲጠበቅ ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል። የበቂ ልብስ እጥረትን ለማካካስ ኃይልዋን መጠቀም የለባትም። የተመጣጠነ ንጥረነገር ያለው ምግብ ከተነፈገች፣ የደም ጥራትና መጠን ያነሳት ትሆናለች። የደም ዝውውርዋ ደካማ ይሆንና ልጅዋም እነዚህ ጉድለቶች ይኖሩታል። አካሉን ለመመገብ የሚያስፈልገውን በቂ ደም የሚያስገኘውን ተመጣጣኝ ምግብ የመውሰድ ችሎታ የሌለው ይሆናል። የእናቱና የልጁ ጤንነት በአብዛኛው በሞቃት ልብስና በተመጣጠነ ምግብ የሚወሰን ነው። 5 AHAmh 179.1
አካባቢዋ ሁሉ የሚማርክና ደስ የሚል እንዲሆን ጥንቃቄ መደረግ አለበት። የሚችለውን ሁሉ በማድረግ የእናትና የሚስትን ሸክም ያቀል ዘንድ አባትና ባል የተለየ ኃላፊነት ተጥሎበታል። በችሎታው ሁሉ ያለችበትን ሁኔታ በማጤን ሊሸከማት ይገባዋል። ገራም፣ ሩኅሩኅ፣ ቸር፣ ለስላሳና በተለየ ሁኔታ ለፍላጎትዋ ትኩረት የሚሰጥ መሆን አለበት። አንዳንድ ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት በጋጥ ውስጥ የሚያድሩ እንሰሳት የሚደረግላቸውን እንክብካቤ ግማሽ እንኳን አያገኙም። 6 AHAmh 179.2
የምግብ ፍላጎት ብቻ አደጋ የሌለበት ምሪት አይሰጥም፦ ከእውነታው በመነሣት ሳይሆን ከራሳቸው የተለየ ሁኔታና ከባህል አንጻር የእርጉዞች ፍላጎት ቅጥ ያጣና መረን የለቀቀ ሊሆን ይችላል የሚባለው ሃሳብ ልክ አይደለም። የሴቶች ፍላጎት በእርግዝናቸው ወቅት ተለዋዋጭ፣ የሚዋዥቅና ለማርካትም ከባድ ሊሆን ይችላል። የምትወስደው ምግብ ለሰውነትዋ እንዲሁም ለልጅዋ አድገት ጠቃሚ መሆኑ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራት፣ ባህል ስለፈቀደላት ብቻ የምትመኘውን ሁሉ ማግኘት የምትፈልግ ሴት አለች። ምግቡ ንጥረ-ነገር የሞላበት ይሁን እንጂ የሚያስጎመዥ መልክ ያለው መሆን አይጠበቅበትም….ቀለል ያለ ምግብ በመምረጥ ስለምትበላው ምግብ ጥራት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖር ይህ ወቅት ነው። መርህ ያላቸውና በደንብ የተማሩ ሴቶች ከባድ ምግብ ያለመብላት ልምዳቸውን በዚህ ጊዜም አይተዉትም። ሌላ ሕይወት ጥገኛቸው እንደሆነ ግምት ውስጥ በማስገባት በልምዳቸው በተለይም በምግብ ዙሪያ ጥንቁቅ ይሆናሉ። ደስ ስለሚልና ስለሚጣፍጥ ብቻ ጥቅም የሌለው ምግብ መብላት የለባቸውም። ሕሊናቸውን ሲያደምጡት እንዳያደርጉት የሚከለክላቸው፤ ነገር ግን ብዙ የዞረባቸው ምክር ሰጪ (አዋቂ) ነን ባዮች እንዲፈጽሟቸው የሚገፋፏቸው ነገሮች አሉ። በወላጆች ሆዳምነት የተነሣ በሽተኛ ልጆች ይወለዳሉ…. AHAmh 179.3
ከመጠን ያለፈ ምግብ ከተበላ፣ ሰውነትን ከሚረብሹ ነገሮች ነፃ ለማድረግና አላስፈላጊውን ምግብ ለማስወገድ፣ የሚፈጩት አካላት መሥራት ከሚገባቸው በላይ ይሠራሉ። እንደዚህ ሲሆን እናት በራስዋ ላይ ግፍ ትሠራለች፤ ለሚወለደውም ልጅዋ የበሽታ የመሠረት ድንጋይ ትጥላለች። የሚያመጣውን መዘዝ ቸል በማለት ደስ እንዲላት ብቻ የተመኘችውን ሁሉ የምትበላ ከሆነ፣ ቅጣቱን ትሸከማለች፤ ብቻዋን ግን አይሆንም፤ በእርስዋ ግድ-የለሽነት ምንም የማያውቀው ሕፃን ይሰቃያል። 7 AHAmh 180.1
እራስን መቆጣጠርና ልክን ማወቅ አስፈላጊዎች ናቸው፦ የእናት አካላዊ ፍላጎቶች በምንም ዓይነት ቸል መባል የለባቸውም። የሁለት ሰው ሕይወት በራስዋ የሚወሰን በመሆኑ ምኞትዋ በርኅራኄ ሊከበርላት የሚያስፈልጓት ነገሮችም በለጋስነት ሊቀርቡላት ይገባል። በምግብም ሆነ በሌላ በማንኛውም ነገር በዚህ ጊዜ አካላዊ ወይም አዕምሮአዊ ጥንካሬዋን የሚቀንሱ ነገሮችን ማስወገድ አለባት። እራስዋን ትቆጣጠር ዘንድ በራሱ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ በከባድ ግዴታ ሥር ናት። 8 AHAmh 180.2
ልጅ ከመውለዷ በፊት እናት፣ በምትወስደው የማያወላውል ልክን የማወቅ ልማድ የወደፊቱን ሰው የትክክለኛ ባህርይ መሠረት ታጠናክራለች…. ይህ ትምህርት በግድየለሽነት መታለፍ የለበትም። 9 AHAmh 180.3
ደስተኛና በቃኝ የሚልን ፀባይ አበረታቱ፦ እናት ለመሆን የተቃረበች እያንዳንዷ ሴት፣ በዙሪያዋ ያለው ነገር ምንም ይሁን ምን ያለ ማቋረጥ ደስተኛ፣ ፍልቅልቅና በቃኝ ባይ ጠባይ ማበረታታት አለባት፤ ምክንያቱም በዚህ አቅጣጫ የምታደርገው ጥረት ሁሉ አሥር እጥፍ ሆኖ በልጅዋ አካላዊና ግብረ-ገባዊ ባህርይ በኩል ይከፈትላታልና። ይህ ብቻ አይደለም፤ ቀና አስተሳሰብን እንደ ልማድ በማዳበር፤ ደስተኛ የአስተሳሰብ ሁኔታን በማበረታታት፤ አስደሳች ስሜትዋን በቤተሰቧና በጓደኞችዋ ላይ ልታሳርፍ ትችላለች። የአካላዊ ጤንነትዋም ደረጃ በእጅጉ ይሻሻላል። የሕይወት ምንጭ ኃይል ያገኛል። ለተስፋ መቁረጥና ትካዜ እጇን ብትሰጥ ኖሮ ይከሰት እንደነበረው የደም ዝውውርዋ ዝግ አይልም። በደስታ በለመለመው መንፈስዋ ምክንያት አዕምሮአዊና ግብረ-ገባዊ ጤናዋ ይበረታታል። የፈቃድ ኃይል የአዕምሮን ዝንባሌ በማሸነፍ ነርቭን የማረጋጋት ብቃቱን ያሳያል። ይህን ከእናታቸው መውረስ የነበረባቸውን ጥንካሬ የተነፈጉ ልጆች፣ የተቻለውን ያህል እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ለህልውናቸው ሕጎች የበለጠ ትኩረት ቢሰጡ የተሻለ ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ። 10 AHAmh 180.4
ሠላማዊና አመኔታን ያዘለ ጠባይ ያዙ፦ እናት ለመሆን የምትጠብቅ ሴት ነፍስዋን በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ማስቀመጥ አለባት። አዕምሮዋ ሠላም ያለው ይሁን፤ የክርስቶስን ቃል በመተግበር በጌታ ፍቅር ትረፍ፤ እግዚአብሔር ጋር ሠራተኛ እንደሆነች ታስታውስ። 11 AHAmh 181.1