የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ አርባ አንድ—ጉድለት ያለበት እናትነት
የሐሳብ ሰማዕት፦ አስፈላጊ የሆኑትን ጥቃቅን የቤት ውስጥ ሥራዎች በመጥላት በከንቱ በምታማርር የቤት እመቤት ምክንያት ብዙ ቤቶች ደስታ-አልባ ሆነዋል። በቅን መንፈስ ብትፈጽማቸው አስደሳችና አስደናቂ ብቻ ሳይሆኑ ትርፋማ የሚሆኑት ተግባራት ተራ፣ አድካሚና አሰልቺ ይሆኑባታል። የሕይወትዋን ባርነት በጥላቻ በመመልከት ሰማዕት እንደሆነች አድርጋ ታስባለች። AHAmh 173.1
የኑሮአችን ኩሽኔታ(ጎማ) ያለችግር ሁልጊዜ ሊሽከረከር አይችልም። ትዕግሥትን የሚፈትንና ጉልበት የሚጨርስ ነው። እናቶች ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ሊቆጣጠሯቸው በማይችሉት ነገሮች ባይኮነኑም እነዚህ ሁኔታዎች በሥራ ሕይወታቸው ላይ ለውጥ አያመጡም ብሎ መካድ ግን ጥቅም የለውም። ውግዘታቸው የሚጀምረው ግን ሁኔታዎች እንዲገዟቸው ሲፈቅዱና መርሆዎቻቸውን ሲያዛቡባቸው፤ ለተጣለባቸው አደራ ታማኝ መሆን ሲያቅታቸው፤ ድካም ሲበዛባቸውና ግዴታቸውን ችላ ሲሉ ነው። ሌሎች ወደ ኋላ ላለማለት ትዕግሥትና ጽናት አጥተው ሲሰጥሙ ሳለ ችግሮችዋን በብቃት የምታሸንፍ ሚስትና እናት ለራስዋ ሥራ ጥንካሬ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ፈተናዎችንና መሰናክሎችን የማለፍ ልምዷ ሌሎችን በቃልና በምሣሌነት ለመርዳት ብቁ ያደርጋታል። በተስማሚ ሁኔታዎች ውስጥ እያሉ ክንውን የሚሆንላቸው ሁሉ በፈተናና በችግር ውስጥ ሲያልፉ የባህርይ ለውጥ ይታይባቸዋል። ከፈተናዎቻቸው አንፃር ሲታይ የተሽመደመዱ ይሆናሉ። ሁኔታዎች እንዲጫወቱብን የእግዚአብሔር እቅድ አይደለም። 1 AHAmh 173.2
ኃጢአት የሚሆን ቅሬታን ማጎልበት፦ ምንም የሚያስደስት ነገር በቤታቸው የማያገኙ ብዙ ባሎችና ልጆች፤ ቤታቸው የወቀሳና የማጉረምረም ቦታ የሆነባቸው ሁሉ፣ ምቾትና ደስታ ከቤት ውጪ ለመፈለግ ወደ አልኮሆል መሸጫዎች ወይም ወደ ተከለከሉ ትዕይንት ቤቶች ይሄዳሉ። ሚስትና እናት በቤተሰብ ተግባራት ተውጣ ስለችግሮችዋ መብከንከንዋና ብስጭትዋን ባልዋና ልጆችዋ ባሉበት መግለጽ ብታቆምም፣ ቤትን ለባልዋና ለልጆችዋ ደስተኛ የሚያደርጉትን ጥቃቅን በጎ አድራጎቶች ሐሳብዋ ውስጥ አታስገባቸውም። የሚበሉት ወይም የሚለብሱት ነገር ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ስትል ባልዋና ወንዶች ልጆችዋ እንደ እንግዳ ገብተው ይወጣሉ። AHAmh 173.3
የቤት እመቤትዋ ሥራዋን በጥንቃቄ እያከናወነች ቢሆንም የተፈረደባትን ባርነት በመቃወም ሁልጊዜ በመጮኽ ዕጣ ፈንታዋን ለሴት ከተሰጣት የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ሕይወት ጋር በማወዳደር፣ ያሉባትን ኃላፊነቶችና ቁጥጥሮች በማጋነን ስሞታ ልታቀርብ ትችላለች…. ፍሬ-ቢስ የሆነ የተለየ ሕይወት ስትናፍቅ ኃጢአት የሚሆንባትን የቅሬታ መንፈስ በማጎልበት ቤትዋን ለባልዋና ለልጆችዋ ደስታ-አልባ ልታደርገው ትችላለች። 2 AHAmh 173.4
በዓለም ከንቱነት መያዝ፦ ሰይጣን ወላጆችንና ልጆችን የሚስቡ አስደሳች ነገሮችን አዘጋጅቷል። አታላዩ ኃይሉን እናቶች ላይ መጫን ከቻለ ብዙ እንደሚያተርፍ ጠንቅቆ ያውቃል። ዓለም በአታላይነት፣ በማጭበርበርና በመከራ የተሞላ ሆኖ ሳለ የሚያጓጓ እንዲመስል ሆኖ ቀርቧል። ልጆችና ወጣቶች በጥንቃቄ ካልሠለጠኑና ስነሥርዓት ካልተማሩ አፈንግጠው መውጣታቸው አይቀሬ ነው። ያለ ቋሚ መመሪያ ፈተናን መቋቋም ከባድ ይሆንባቸዋል። 3 AHAmh 174.1
አላስፈላጊ ሸክምን መሸከም፦ ብዙ እናቶች አስፈላጊ ባልሆኑ ከንቱ ነገሮች ላይ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ። ለጊዜያዊና ስሜታዊ ነገሮች ሙሉ ትኩረታቸውን በመስጠት ዘለዓለማዊ ስለሆኑ ነገሮች ቆም ብለው አያስቡም። ስንቶች ልጆቻቸውን ይተዋሉ! በዚህ ምክንያት ስንት ህፃናት ግርድፍ ሆነው፣ ሻክረውና ቀጭጨው ይቀራሉ። 4 AHAmh 174.2
ወላጆች በተለይም እናቶች እግዚአብሔር እንዲሠሩት የተወላቸውን የተለየ ኃላፊነት የሚጠይቅ ሥራ በትክክል በሚረዱበት ጊዜ እነርሱን ሊያሳስቧቸው በማይገቡ ሆኖም ጎረቤቶቻቸውን በሚያስጨንቁ ጉዳዮች ላይ አይጠመዱም። ቤት ለቤት እየዞሩ የወሬ ቋት በመሆን በጎረቤቶቻቸው ግድፈቶች፣ ጥፋቶችና ተለዋዋጭነት ላይ አይወሸክቱም። ለልጆቻቸው ከባድ የመንከባከብ ኃላፊነት ስለሚሰማቸው በጎረቤቶቻቸው ላይ ወቀሳ ለመሰንዘር ጊዜ የላቸውም። 5 AHAmh 174.3
ሴት ለብርታትና ለመጽናናት ወደ እግዚአብሔር ብትመለከት በእርሱ ፍርሃትም የዕለት ተግባርዋን ብታከናውን በባልዋ ከበሬታና አመኔታ ታተርፋለች። መልካም ለማድረግ የግብረ-ገብነት ጥንካሬ ያላቸው የተከበሩ ወንዶችና ሴቶች ለአቅመአዳም/ሔዋን ታደርሳለች። እድላቸውን ቸል የሚሉ ኃላፊነታቸውና ሸክማቸው በሌሎች ላይ እንዲጫን የሚፈቅዱ እናቶች ግን ግዴታቸው ሳይቀየር በራሳቸው ላይ ተጭኖ ያገኙታል፤ በቸልተኝነትና በግድ-የለሽነት የዘሩትንም ዘር በመሪር ሐዘን ያጭዱታል። አጋጣሚ የሚባል ነገር በዚህ ምድር ሕይወት ላይ የለም፤ ምርቱ በሚዘራው ዘር የሚወሰን ነው። 6 AHAmh 174.4