የአድቬንቲስት ቤት

39/88

ክፍል ፲—እናት-የቤት ልዕልት

ምዕራፍ ሠላሳ ስምንት—የእናት ደረጃና ኃላፊነቶች

የባልዋ እኩያ፦ ሚስት እግዚአብሔር በመጀመሪያ እንዳቀደው ከባል እኩል የሆነውን ደረጃዋን መያዝ አለባት። ለስሙ እናት የሚባሉትን ሳይሆን እናት የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም ሁሉ የሚሆኑ ሴቶች ዓለም ያስፈልጋታል። ልዩ የሆኑት የሴት ኃላፊነቶች፣ ከወንድ ይልቅ የተከበሩና የተቀደሱ ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም። የሥራዋን ቅዱስነት በውል ተገንዝባ፣ በእግዚአብሔር ፍርሃትና ብርታት የሕይወትዋን ተልእኮ ለመፈጸም መነሣት ይገባታል። ለዚህ ዓለም ጥቅምና ለሚመጣው የተሻለ ቤታቸውም ጭምር ልጆችዋን ታሠልጥናቸው። 1 AHAmh 160.1

ጉልበትዋን በመቆጠብ ኃይልዋን ሳትጠቀምበት ሚስትና እናት ሙሉ በሙሉ በባልዋ መደገፍ የለባትም። ማንነትዋ ከባልዋ ጋር ሊዋሃድ አይችልም። ከባልዋ እኩል እንደሆነች ይሰማት፤ ከጎኑ ቆማ እርሱም ማድረግ እንዳለበት ሁሉ ሥራዋን በታማኝነት ትፈጽም። ባልዋ በምንም ዓይነት ኃላፊነት ቢቀመጥ - የሀገሪቱ ዋና የሕግ ሹም ቢሆን - እንኳን እናት ልጆችዋን እንድታሠለጥን የተሰጣት ሹመት በከፍታው፣ በክብሩና በማዕረጉ ከእርሱ ቢበልጥ እንጅ አያንስም። 2 AHAmh 160.2

የቤት ንግሥት፦ በዙፋን የተቀመጠው ንጉሥ ከእናት የበለጠ ሥራ የለበትም። እናት የቤት ንግሥት ናት። ልጆችዋ ለከፍተኛውና ዘለዓለማዊው ሕይወት እንዲበቁ የመቅረጽ ኃይል በውስጧ አለ። ከዚህ የበለጠ ተልዕኮ መልአክ እንኳን ሊኖረው አይችልም፤ ይህ ሥራዋ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ አገልግሎት ነውና። ኃላፊነትዋ ምን ያህል ክቡር እንደሆነ ብቻ ታስተውል፤ እርሱ በብርታት ሞልቶ ይቀሰቅሳታል። የሥራዋ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ በመረዳት የእግዚአብሔርን ሙሉ እቃ ጦር በመልበስ ከዓለም ሥነ-ሥርዓት ጋር እንድትስማማ የሚገፋፏትን ፈተናዎች ትቋቋም፤ የእርስዋ ሥራ ከዘመን እስከ ዘመን ለዘለዓለምም ነውና። 3 AHAmh 160.3

እናት የቤት ልዕልት ተገዢዎችዋ ደግሞ ልጆችዋ ናቸው። በእናትነት ክብርና በጥበብ ቤትዋን ማስተዳደር ይጠበቅባታል። ተጽዕኖዋ በቤት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ፣ ንግግሮችዋ ደግሞ ሕግ ሊሆኑ ይገባል። በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ያለች ክርስቲያን ከሆነች፣ ልጆችዋ ክብር እንዲሰጧት ማድረግ ትችላለች። 4 AHAmh 160.4

ልጆች እናታቸው የሚፈልጉትን ልታሟላ የቆመች አገልጋይ ሳትሆን ቃል በቃል፣ መስመር በመስመር፣ መመሪያ በመመሪያ፣ ልታስተምራቸው፣ ልታስተዳድራቸውና ልትመራቸው የተቀመጠች ንግሥት እንደሆነች ሊያውቁ ይገባቸዋል። 5 AHAmh 160.5

ሥዕላዊ የዋጋ ንፅፅር፦ እናት ብዙ ጊዜ የራስዋን ሥራ አታደንቀውም፤ ለጥረትዋ እጅግ ዝቅተኛ ግምት በመስጠት፣ ተራ የቤት ውስጥ መማሰን አድርጋ ትቆጥረዋለች። ምንም የተለየ ውጤት ሳታይ ቀን ቀንን፣ ሳምንት ሳምንትን እየወለደ ሁሌም ተመሳሳይ ሥራ ትሠራለች። ቀኑ ሲያልቅ ምን ያህል ጥቃቅን ነገሮች እንዳከናወነች እንኳ መናገር አትችልም። ባልዋ በውጭ ካስመዘገበው ስኬት ጋር ሲነጻጻር ሊጠቀስ የሚችል፣ ከቁጥር የሚገባ ምንም ነገር እንዳላደረገች ይሰማታል። AHAmh 161.1

ብዙ ጊዜ አባት የግል እርካታ ስሜቱን አንግቦ፣ በቀኑ ውስጥ ምን ያህል ታላቅ ሥራ እንዳከናወነ በኩራት እየቆጠረ ይገባል። አባባሉ የሚያሳየው ልጆቹን ከመንከባከብ፣ ከማብሰልና ቤቱን በሥርዓት ከማድረግ በቀር ብዙም እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እንዳልሠራችና ተዘጋጅታ ልትጠብቀው እንደሚገባት ነው። የንግድ ሥራ አልሠራችም፤ አልገዛችም፤ አልሸጠችም፤ ግብርናም አልሞከረችም፤ መሬትም አልቆፈረችም፤ መካኒክም አይደለችም፤ ስለዚህ የሚያደክም ሥራ አልሠራችም ይላል። የፍጥረት ሁሉ አለቃ ይመስል ያወግዛታል፤ ይገስጻታል፤ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋል። ቀን ስትደክምና ስትባዝን ለዋለች ለዚያች እናትና ሚስት ይህ በጣም ፈታኝ ነገር ነው። ይባስ ብሎ ስትደክምበት የዋለችው እንዲያ ያዝለፈለፋት ሥራ ምን እንደነበረ እንኳ ማየትም ሆነ መናገር ስለማትችል ልብዋ እጅግ ይቆስላል። AHAmh 161.2

መጋረጃው ቢገለጥና ባልና ሚስት እግዚአብሔር እንደሚያየው የቀኑን ሥራ ማየት ቢችሉ፤ ዘለዓለማዊ ዐይኑ የሁለቱን ሥራ ሲያወዳድር ቢመለከቱ፤ ሰማይ በሚገልጥላቸው እውነት እጅግ በተደነቁ ነበር። አባት ጥረቱ መጠነኛ እንደሆነ ሲረዳ እናት ደግሞ አዲስ ብርታትና ኃይል ተጨምሮላት ሥራዋን በበለጠ በብልሃትና በትዕግስት ሳትሰለች መፈጸም ትችል ነበር። አሁን ዋጋውን አወቀች። አባት በሚሞትና በሚጠፋ ነገር ላይ ሲደክም ሳለ እናት ግን ጊዜያዊ ሳይሆን ዘለዓለማዊ ለሚሆን ተግባር አዕምሮንና ባህርይን እያሳደገች ነው። 6 AHAmh 161.3

ሥራዋን የወሰነው እግዚአብሔር ነው፦ እያንዳንዷ እናት ያሉባት ግዴታዎችና ኃላፊነቶች ምን ያህል ታላቅ እንደሆኑ፣ የታማኝነትዋ ሽልማት ምን ያህል የከበረ እንደሆነ ብታውቅ ኖሮ እንዴት መልካም ነበር። 7 AHAmh 161.4

በመንገዷ የተቀመጡትን ኃላፊነቶች ሁሉ በደስታ የምትሠራ ሴት ሕይወት የከበረ እንደሆነ፣ ደግሞም እግዚአብሔር እራሱ እንድትተገብረው የሰጣት እንደሆነ ትረዳለች። ይህ ሥራ ግን አዕምሮዋን ሊያደኩረው ወይም ንቃተ-ህሌናውን ሊያዳክመው አይገባም። 8 AHAmh 161.5

በእግዚአብሔር ተግሳጽና እንክብካቤ ልጆችዋን ታሳድግ ዘንድ የእናት ኃላፊነት በእግዚአብሔር በራሱ የተሰጣት ሥራ ነው። እግዚአብሔርን መውደድና መፍራት ሁልጊዜ በልጆችዋ ጨቅላ አዕምሮ ሊቀመጥ ይገባዋል። ሲታረሙም እግዚአብሔር በማታለል፣ በውሸትና ጥፋት በመሥራት ስለማይደሰት፣ የገሰጻቸው እርሱ ራሱ እንደሆነ ሊሰማቸው ይገባል። እንዲህም ሲሆን የእነዚህ ታናናሾች አዕምሮ ከእግዚአብሔር ጋር በመቆራኘት የሚያደርጉትና የሚናገሩት ሁሉ ከእርሱ ክብር ጋር በተያያዘ መልኩ ይሆናል። ሲያድጉም ንፋስ እንደሚያወዛውዘው መቃ በፍላጎታቸውና ሊፈጽሟቸው በሚገባቸው ኃላፊነቶቻቸው መሀል ወዲያ ወዲህ ሲርመሰመሱ አይኖሩም። 9 AHAmh 161.6

የሚፈለገው ነገር እነርሱን ወደ የሱስ መምራት ብቻ አይደለም…. እነዚህ ልጆች የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት ይሆኑ ዘንድ ሊማሩና ሊሠለጥኑ ይገባቸዋል። “ወንዶች ልጆች በጎልማሳነታቸው እንዳታክልት አደጉ። ሴቶች ልጆቻችንም በግንብ ሥራ እንዳለ እንደተወቀረ የማዕዘን አምድ ይሆኑ ዘንድ።” ይህ የመቅረጽ፣ የማንጠርና የማለስለስ ሥራ የእናት ነው። የህጻኑ ባህርይ ሊጎለብት ይገባዋል። እናት ለዘለዓለም የሚፀኑ ትምህርቶችን በልብ ጽላት ላይ መጻፍ አለባት፤ ምንም ዓይነት ነገር ጣልቃ እንዲገባ ብትፈቅድ ወይም ይህን የተቀደሰ ሥራዋን ቸል ብትል፣ የእግዚአብሔር ቅሬታ እንደሚገጥማት እርግጠኛ ትሁን…. ክርስቲያን እናት እግዚአብሔር የቀጠራት ሥራ አለባት፤ ከእግዚአብሔር ጋር ከተቆራኘችና በመንፈሱ ከተሞላች ለዚህ ሥራዋ ዋዘኛ አትሆንም። 10 AHAmh 162.1

ታላቁና የከበረው ተልዕኮዋ፦ ለእያንዳንዷ እናት የተሰጠ በዋጋ ሊገመት የማይችል ለዘለዓለም የከበረ ጥቅም የሚያስገኝ እድል አለ። ተደጋጋሚና ተራ የሆነው ሥራ፣ ሴቶች ድካም-ትርፉ እንደሆነ የሚቆጥሩት የቤት ውስጥ ልፋት፣ ታላቅና የከበረ ተግባር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል። ዓለምን በተጽዕኖዋ ትባርክ ዘንድ የተሰጣት የማይገኝ እድል ነው፤ ይህ ልብዋን በደስታ ሊያስፈነድቀው ይገባዋል። በብርሃን ጊዜም ሆነ በጽልመት ልጆችዋን በቀጥተኛ መንገድ ወደ ላይኛው ክብር ልታራምዳቸው ይቻላታል። በመለኮታዊ ምሣሌ የልጆችዋን ባህርይ ለመቅረጽ ተስፋ ማድረግ የምትችለው ግን መጀመሪያ ክርስቶስ ያስተማረውን በራስዋ ሕይወት ለመተግበር ያልተገደበ ጥረት ስታደርግ ነው። 11 AHAmh 162.2

ከሕይወትዋ ተግባራት መካከል የከበረው ኃላፊነትዋ ለልጆችዋ ነው። ነገር ግን ራስ-ወዳድ ፍላጎትን ለማርካት ስንት ጊዜ ነው ይህ ኃላፊነት ወደ ጎን የሚገፋው! የልጆች የአሁንና የዘለዓለማዊ ጥቅማቸው ለወላጆች በአደራነት ተሰጥቷል። የማስተዳደሩን ሥልጣን ሊቆናጠጡና ቤተሰቦቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ክብር ሊመሩ ይገባቸዋል። የእግዚአብሔር ሕግ ሊደርሱበት የሚፈልጉት ከፍ ያለ ደረጃ ይሁን፤ ፍቅር ሁሉንም ነገር ይግዛ። 12 AHAmh 162.3

ከዚህ የሚበልጥ የተቀደሰ ሥራ የለም፦ ያገቡ ወንዶች ሚስቶቻቸው ልጆችን እንዲንከባከቡ ቤት ውስጥ ትተው የሚሄዱ ከሆነ እናቶች የሚያከናውኑት ተግባር እንደ አባቶች ሁሉ ታላቅና አስፈላጊ ነው። አንዱ የመስክ ሠራተኛ ቢሆንም ሌላኛዋ ደግሞ ከሸክምዋ፣ ከጭንቀትዋና ከችግርዋ አንፃር የባልንና የአባትን ኃላፊነት በእጅጉ የሚበልጠውን የምታከናውን የቤት ውስጥ አገልጋይ(ሚሲዮናዊት) ናት። ሥራዋ የከበረና ጠቃሚ ነው…. የቤት ውስጥ ድካሟ ምንም ምድራዊ ምሥጋና አይቸረው፣ በማይታየው የሥራ መስክ የሰዎችን አድናቆት አያተርፍ ይሆናል፤ ሆኖም በመለኮታዊ ተምሣሌት ባህርያቸውን ትቀርጽ ዘንድ የቤተሰቧን ፍላጎት ተቀዳሚ በማድረግ የምትጥር ከሆነ የሚመዘግቡት መላእክት በዓለም ካሉ ከታላላቆቹ አገልጋዮች አንዷ እንደሆነች አድርገው ስሟን ይፅፋሉ። የእግዚአብሔር ዐይን የቅርቡን ብቻ ማየት እንደሚችለው እንደተጋረደው የሰው ዐይን አያይም። 13 AHAmh 162.4

እናት ቤተሰቧን ክርስቲያን ለማድረግ የተሾመች የእግዚአብሔር ወኪል ናት። የእግዚአብሔር ስጦታ በሆነው በእምነት በሚቀበሉት በፀጋው ብቻ እንደሚድኑ ልጆችዋን በማስተማር የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ኃይማኖት ተምሣሌት በመሆን ተጽዕኖው በዕለት ተዕለት ግዴታዎቻችንና ደስታችን ሁሉ እንዴት ሊቆጣጠረን እንደሚገባ ማሳየት ይገባታል። ክርስቶስ ለእኛና ለእነርሱ ምን እንደሆነ የሚያስተምረው የማያቋርጠው ትምህርትዋ፣ በታላቁ የማዳን እቅዱ የተገለጸው ፍቅሩ፣ መልካምነቱና ምህረቱ በተባረከና በተቀደሰ ግርምት ልባቸውን ይነካል። 14 AHAmh 163.1

ልጆችን የማሠልጠን ሥራ የክርስትናን ኃይል በተግባር ለማሳየት እግዚአብሔር የያዘው እቅድ አካል ነው። ልጆች ወደ ዓለም ሲበተኑ ለሚጎዳኟቸው ሁሉ መልካም እንጂ ክፋትን የማያደርጉ ይሆኑ ዘንድ እንዲያስተምሯቸው ከባድ ኃላፊነት በወላጆች ላይ ተጥሏል። 15 AHAmh 163.2

የአገልጋዩ የሥራ ጓደኛ፦ አገልጋዩ የራሱ የሥራ ክፍል አለው፤ እናትየዋም እንደዚያው። ክርስቶስ እንዲባርካቸው ልጆችዋን ወደርሱ ታምጣ። የክርስቶስን ቃል ከፍ ከፍ ልታደርግና ለልጆችም ልታስተምር ይገባታል። ከህፃንነታቸው ጀምሮ ቁጥብነትንና እራስን መካድን፣ የሥርዓትና የንጽህና ልማዶችን ልታስጨብጣቸው ይገባታል። ልጆች የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ቃል በተከፈተና በተሰበረ ልብ እንዲሰሙ አድርጋ ልታሳድጋቸው ትችላለች። በተሰጣቸው የቤት ውስጥ የሥራ መስክ ሁሉ ችሎታቸውን በማሻሻል ልጆቻቸው የሰማያዊ ቤተሰብ ገጣሚ ይሆኑ ዘንድ የሚጥሩ እናቶችን እግዚአብሔር ይፈልጋቸዋል። AHAmh 163.3

አዎን ቃሉን ከሚያስተምር እኩል እንዲያውም የሚበልጥ ሥራ በቤት ውስጥ በታማኝነት በመሥራት እግዚአብሔርን ማገልገል ይቻላል። የትምህርት ቤት መምህራን እንደሚሰማቸውና እንደሚያደርጉት ሁሉ እናቶችና አባቶችም እንዲሁ የልጆቻቸው መምህራን ናቸው። 16 AHAmh 163.4

የክርስቲያን እናት የጠቃሚነትዋ ወሰን በቤት ውስጥ ኑሮ ብቻ መገደብ የለበትም። በቤተሰቧ ዙሪያ የምታሳርፈው የፈውስ ተጽዕኖ የጠቀሜታዋን ዳርቻ በማስፋት በጎረቤቶችና በእግዚአብሔር ቤተ-ክርስቲያንም ሊደርስ ይገባዋል። ለተሰጠች እናትና ሚስት ቤትዋ የወህኒ ቤት አይደለም። 17 AHAmh 164.1

የሕይወት ተልእኮ አላት፦ የሥራዋን ቅዱስነት በማስተዋል በእግዚአብሔር ፍርሃትና ብርታት የሕይወትዋን ተልእኮ ታንግብ። ለዚህ ዓለም ጠቃሚ፣ ለተሻለው ዓለም ገጣሚ እንዲሆኑ ልጆችዋን ታስተምር። እኛ ለክርስቲያን እናቶች እንናገራለን፡ - ኃላፊነታችሁን በመረዳት እግዚአብሔርን ለማክበር እንጂ የራሳችሁን ፍላጎት ለማርካት እንዳትኖሩ እንለምናችኋልን። የባሪያን መልክ ያዘ እንጂ ክርስቶስ እራሱን ደስ አላሰኘም። 18 AHAmh 164.2

ዓለም ሰውን በሚያበላሽ ተጽዕኖ ተጥለቅልቋል። ፋሽንና ልማድ በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ኃይላቸውን አሳርፈዋል። እናት የማስተማር፣ የመምራትና የመገደብ ኃላፊነትዋን ከዘነጋች ልጆችዋ ያለ ጥርጥር ክፋትን ተቀብለው ከመልካሙ ነገር ፈቀቅ ይላሉ። እያንዳንዷ እናት ሳታሰልስ ወደ አዳኝዋ በመቅረብ እንዲህ ትጸልይ “አስተምረን ጌታ፣ ልጁን እንዴት እናስተካክለው? ምን እናድርግለት?” እግዚአብሔር በቃሉ የሰጠውን ትዕዛዝ በጥንቃቄ ታስተውል፤ እንደ አስፈላጊነቱም ጥበብ ይሰጣታል። 19 AHAmh 164.3

የመለኮትን ምሣሌ ቅርጽ ማውጣት፦ እግዚአብሔር በሰማይ ነው፤ ከዙፋኑ የሚወጣው ብርሃንና ክብር ልጆችዋ ክፉውን ይቋቋሙ ዘንድ ለማስተማር በምትጥረው ታማኝ እናት ላይ ያርፋል። በአስፈላጊነቱና በጠቃሚነቱ የርስዋን ሥራ የሚስተካከል የለም። እንደ አርቲስት ሸራ ላይ የውበት ቅርጽ አትስልም፤ እንደ ሐውልት ሠሪም እብነ-በረድ አትወቅርም፤ እንደ ደራሲ በኃይለ-ቃል አትጽፍም፤ እንደ ሙዚቀኛ መልካም ስሜት የሚፈጥሩ ዜማዎችን አታንጎራጉርም። የርስዋ ሥራ በእግዚአብሔር እርዳታ የመለኮትን ምሳሌ በሰው ነፍስ ውስጥ ማበልጸግ ነው። ይህንን በቸልታ የማታልፍ እናት የተሰጣት እድል ዋጋ እንደማይገኝለት ትረዳለች። በራስዋ ባህርይና በማሠልጠን ዘዴዎችዋ ከፍተኛውን አርዓያነት በልጆችዋ ፊት ለማቅረብ በቅንነት ትጥራለች። ሀያል የሆነውን የአዕምሮዋን ጉልበት ልጆችዋን ለማሠልጠን ትጠቀምበት ዘንድ በቅንነት፣ በትዕግስትና በወኔ እራስዋን ለማሻሻል ትለፋለች። በእያንዳንዱ እርምጃዋም “እግዚአብሔር ምን ተናገረ?” ብላ ትጠይቃለች። ቃሉን በትጋት ታጠናለች። የዕለት ተዕለት ልምዷ፣ የሚደጋገሙትና የተለመዱት ችግሮችዋና ኃላፊነቶችዋ የእውነተኛው ሕይወት ትክክለኛ ነፀብራቅ ይሆኑ ዘንድ ዐይኖችዋን ከክርስቶስ አታነሳም። 20 AHAmh 164.4

የታመነች እናት በዘለዓለማዊው የዝና መጽሐፍ ትመዘገባለች፦ የራስ ክህደትና መስቀሉ የእኛ ድርሻዎች ናቸው፤ እንቀበላቸው ይሆን? ታላቁ የመከራ ቀን በላያችን ላይ ሲወድቅብን እራስን በመስዋዕትነት የማቅረብንና የአርበኝነትን መንፈስ ስለፈለግነው ብቻ በቅጽበት ልናጎለብተው የምንችለው ባህርይ እንደሆነ አድርጎ ማንም እንዳይጠብቅ። አይደለም፤ ይህ መንፈስ አሁን ከዕለት ተዕለት ልምምዶቻችን ጋር በመዋሃድ፣ በመመሪያነትና በተምሣሌትነት በልጆቻችን አዕምሮና ልብ ውስጥ ሊጎዘጎዝ ይገባዋል። የእስራኤል እናቶች እራሳቸው አይዋጉ ይሆናል፤ የጦር ዕቃውን በኩራት ታጥቀው በወንድነት ለእግዚአብሔር ሰልፍ የሚዋጉ ጀግኖች ግን ማሳደግ ይችላሉ። 21 AHAmh 165.1

እናቶች ሆይ የልጆቻችሁ ዕጣ ፈንታ በመዳፋችሁ ውስጥ ነው። በዚህ ሥራችሁ ከወደቃችሁ በጠላት ጦር ውስጥ ነፍሳትን የማጥፋት ሥራ አስፈፃሚ ሆነው እንዲያገለግሉ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔርን በሚመስል ተምሣሌትነትና በታማኝ ስነ-ሥርዓት ወደ ክርስቶስ ልትመሯቸው ብዙ ነፍሳትን ለማዳን የሚጠቀምባቸው የእጁ መሣሪያዎች ልታደርጓቸውም ትችላላችሁ። 22 AHAmh 165.2

የክርስቲያን እናት ሥራዋ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ከተተገበረ፣ ለዘለዓለም እንዲታወስ ይደረጋል። የፋሽን ሱሰኛ የሆኑ ሁሉ የማይሞት ውበት ያለውን የዚያችን የክርስቲያን ሴት ሥራ ሊያዩት ወይም ሊያስተውሉት ፈጽሞ አይችሉም፤ ልቅና ያልተጌጠ በሆነው ቀሚስዋና ኋላ ቀር በሆነው አስተሳሰቧ ያሽሟጥጧታል። የሰማይ ግርማዊነት ግን የዚህችን ታማኝ እናት ስም በዘለዓለማዊው የዝና መጽሐፍ (Book of Immortal Fame) ላይ ያሰፍረዋል። 23 AHAmh 165.3

ጊዜያቱ ዋጋ የማይገኝላቸው ናቸው፦ የሙሴ የወደፊት ሕይወትና በእስራኤል መሪነቱ የፈጸመው ታላቅ ተልዕኮ የክርስቲያን እናት ሥራ አስፈላጊነት ምስክር ነው። ይህንን የሚተካከል ሥራ የለም…. እስከ መጨረሻው ታማኝ ክርስቲያኖች ይሆኑ ዘንድ ወላጆች ልጆቻቸው ገና ሕፃን እያሉ ማሠልጠንና ማስተማር ይጀምሩ። የተጠራነው በእንክብካቤአችን ሥር የተቀመጡት ልጆች የእግዚአብሔር ነገሥታት ሆነው ለዘለዓለም እንዲገዙ እንድናሠለጥናቸው እንጂ ዓለማዊ ግዛት እንዲወርሱ አይደለም። AHAmh 165.4

እያንዳንዷ እናት ጊዜዎችዋ ዋጋ የማይገኝላቸው እንደሆኑ ይሰማት፤ ሥራዎችዋም በታላቁ የፍርድ ቀን ይፈተሻሉ። የብዙዎቹ ወንዶችና ሴቶች ውድቀትና ወንጀልም የህፃናትን እግሮች ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመምራት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመዘንጋታቸው ምክንያት የተፈፀመ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ዓለምን በዕውቀት፣ በእምነትና በቅድስና የባረኳት ሁሉ የተጽዕኖአቸውና የስኬታቸው ዋና ምንጭ ለሆነው መርህ ምክንያት በትጋት የምትጸልይ ክርስቲያን እናት እንደሆነችም ይገለጣል። 24 AHAmh 165.5