የአድቬንቲስት ቤት

37/88

ምዕራፍ ሠላሳ ስድስት—የልጆች ጓደኛ

ከልጆች ጋር ጊዜ አሳልፉ፦ እንደ ልማድ ሆኖ አባት ልጆቹን ለመሳብና ወደርሱ ለማስጠጋት የሚያስችሉትን ብዙ ወርቃማ ዕድሎች ሳይጠቀምባቸው ይቀራል። ከሥራ ሲመለስ ከልጆቹ ጋር የተወሰነ ጊዜ በማሳለፍ ከቀኑ ውስብስብነት እፎይ የሚያሰኝ አስደሳች ለውጥ ሊያገኝ ይገባዋል። 1 AHAmh 152.1

አባቶች ሰው ከፈጠረው የተኮፈሰ ክብራቸው ፈታ ብለው፣ ራሳቸውን ለማስደሰትና ለማዝናናት ከሚጠቀሙበት ጊዜ ትንሽ ቆጠብ አድርገው ከልጆቻቸው ጋር በመጫወት፤ ለጥቃቅን ችግሮቻቸው ሐዘኔታ በማሳየት፤ በጠንካራ የፍቅር ሰንሰለት ከልባቸው ጋር ማቆራኘት አለባቸው። ምክራቸው የተቀደሰ ሆኖ እንዲኖርም በሚጎለብተው የልጆቻቸው አዕምሮ ውስጥ ጠንካራ ተጽዕኖ መፍጠር ይኖርባቸዋል። 2 AHAmh 152.2

በወንዶች ልጆች ላይ የተለየ ፍላጎት ይኑራችሁ፦ የወንዶች ልጆች አባት ለልጆቹ ቅርብ በመሆን ሰፋ ያለውን ተሞክሮውን በማካፈል ቀላልና ደግ በሆነ አነጋገር ከልቡ ጋር ሊያቆራኛቸው ይገባል። ፍላጎቶቻቸውና ደስታቸው ሁልጊዜም በእይታው ውስጥ እንዳሉ ሊያሳውቃቸው ይገባል። 3 AHAmh 152.3

የወንድ ልጆች ቤተሰብ ያለው አባት ሊረዳው የሚገባ ነገር ቢኖር ምንም ዓይነት ኃላፊነት ይኑርበት፣ በእቅፉ ውስጥ የተተዉትን ነፍሳት ቸል ማለት እንደማይችል ነው። እነዚህን ልጆች ወደ ዓለም በማምጣት እራሱን ለእግዚአብሔር ተጠያቂ አድርጓል፤ ኃይሉን ሁሉ በመጠቀም ካልተቀደሱ ጉድኝቶችና ከክፉ አጋሮች ሊጠብቃቸው ግዴታ አለበት። ቁንጥንጥ የሆኑትን ልጆቹን ሙሉ በሙሉ ለእናታቸው መተው የለበትም። ይህ እርስዋ ብቻዋን ልትሸከመው የማትችለው ጭነት ነው። የባለቤቱንና የልጆቹን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ነገሮችን ማስተካከል አለበት። ራስዋን መግዛትና ልጆችዋን በጥበብ ማስተዳደር ለእናት ከባድ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ይህን የሚመስል ከሆነ አባት የበለጠውን ሸክም መውሰድ አለበት። ልጆቹን ለማትረፍ በቆራጥ ውሳኔ መጣር ይኖርበታል። 4 AHAmh 152.4

ልጆች ጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ ይሠልጥኑ፦ አባት እንደ ቤተሰብ መሪነቱ ለጠቀሜታና ለኃላፊነት እንዴት እንደሚያዘጋጃቸው ማወቅ አለበት። ከሁሉም ነገር በላይ ይህ የተለየ ሥራ ነው። በሕፃኑ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ግብሩን በመቅረፅ ረገድ እናት ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባት፤ ሆኖም በሥራዋ ሁሉ የባልዋ ትብብር እንዳለበት ሊሰማት ይገባል። ባል ለቤተሰቡ ያለውን ጠቀሜታ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ዓይነት ሥራ ውስጥ ተሰማርቶ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ለልጆች መስጠት የሚያስችለው ሌላ ሥራ መፈለግ አለበት። ቸል የሚላቸው ከሆነ እግዚአብሔር ለጣለበት አደራ ታማኝ አይደለም ማለት ነው። AHAmh 152.5

ከዓለም ማታለል የበለጠ ተጽዕኖ አባት በልጆቹ ላይ ማሳደር ይችላል። መጥፎውን በማረም መልካሙን ደግሞ በማበረታታት ረገድ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ ፍላጎታቸውን መረዳትና የተጋረጠባቸውንም አደጋ ማወቅ ይችል ዘንድ፣ የትንሿን የቤተሰቡን ክበብ ዝንባሌና ባህርያት ማጥናት ይኖርበታል። 5 AHAmh 153.1

የሥራው ጠባይ ምንም ዓይነት ይሁን፣ ከልጆቹ የበለጠ አስፈላጊ ባለመሆኑ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ይጠበቅ ዘንድ ልጆቹን ከማስተማርና ከማሠልጠን ቸል እንዲል ምክንያት ሊሆነው አይችልም። 6 AHAmh 153.2

ከተለያዩ ዝንባሌዎች ጋር እራሳችሁን አለማምዱ፦ አባት በሥራ ሕይወት ወይም መጻሕፍትን በማንበብ ሐሳብ ተውጦ፣ ለልጆቹ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብና ዝንባሌዎቻቸውን ለማጥናት ጊዜ ማጣት የለበትም። እንደተለያየ ዝንባሌያቸው በጠቃሚ ሥራ ላይ እንዲጠመዱ የሚያደርጉ መንገዶችን ለመቀየስ ማገዝ አለበት። 7 AHAmh 153.3

አባቶች ሆይ በተቻላችሁ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ይኑራችሁ። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በተስማማ ሁኔታ ታሠለጥኗቸው ዘንድ የተለያዩ ዝንባሌዎቻቸውን ተለማመዱ። የሚያጣጥል (የሚያንቋሽሽ) ቃል ፈጽሞ ከከንፈራችሁ እንዳያልፍ። ጨለማን ወደ ቤት አታምጡ። ለልጆቻችሁ አስደሳች፣ ቸርና አፍቃሪ ሁኑ፤ ነገር ግን በጅልነት አታሞላቅቋቸው። ሁሉም ሰው በእነዚህ ሁኔታዎች ማለፍ እንደሚገደደው ሁሉ ጥቃቅን ቅሬታዎቻቸውን እራሳቸው ይሸከሙ። ለእርስ በእርሳቸው ያላቸውን ትንንሽ መወነጃጀል ይዘው ወደ እናንተ እንዲመጡ አታበረታቷቸው። በመካከላቸው አመኔታንና መከባበርን ያዳብሩ ዘንድ እርስ በእርስ መሸካከም እንዲችሉ አስተምሯቸው። 8 AHAmh 153.4

በሥራቸውና በጨዋታቸው ተጎዳኟቸው፦ አባቶች ሆይ…. ፍቅርን ከሥልጣን ጋር፣ ቸርነትንና ርኅራኄን ከጥብቅ ቁጥጥር ጋር አዋህዱ። ከትርፍ ጊዜያችሁ የተወሰነውን ለልጆቻችሁ ስጡ። በደንብ እወቋቸው፤ በሥራቸውና በጨዋታቸው ጓደኛ ሁኑላቸው፤ አመኔታቸውንም ታገኛላችሁ። ጓደኝነታችሁን አሳድጉ፤ በተለይ ከወንድ ልጆቻችሁ ጋር። በዚህ አካሄዳችሁ ለመልካም አስተዳደግ ጠንካራ ተጽዕኖ መሆን ትችላላችሁ። 9 AHAmh 153.5

ከተፈጥሮ ትምህርት አስተምሯቸው፦ አባት የእናትን ሸክም ለማቃለል ይሞክር…. ወደሚያማምሩት አበቦችና ግዙፍ ዛፎች በማመላከት በቅጠሎቻቸው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና ፍቅር እንዲያዩ ይርዳቸው። እነዚህን ሁሉ የፈጠረ አምላክ መልካሙንና ውቡን ሁሉ እንደሚወድ ያስተምራቸው። ክርስቶስ ደቀ-መዛሙርቱን ወደ መስክ አበቦች(lilies)ና የሰማይ ወፎች በማመልከት፣ እግዚአብሔር ለእነዚህ ፍጥረታት እንዴት እንደሚያስብና ከእነርሱ እጅግ ለሚበልጠው ሰው አምላክ እንዴት ሊጠነቀቅ እንደሚችል በማስረጃነት አቅርቧቸዋል። ምኑንም ያህል ብንኳኳል፤ አምረን ለመታየት የተቻለንን ጥረት ሁሉ ብናደርግ፣ በፀጋ፣ በሞገስና በውበት ከዝቅተኛዋ የመስክ አበባ እንኳን ልንተካከል እንደማንችል ንገራቸው። በዚህም አዕምሮአቸው ከሰው ሠራሹ ወደ ተፈጥሮው ይሳባል። እነዚህን ውብ ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ለእነርሱ መደሰቻ ይሆኑ ዘንድ እንደሰጣቸው በማየት አቻ የሌለውን ልባዊና ክቡር ፍቅር ለእርሱ እንዲሰጡ ይማራሉ። 10 AHAmh 153.6

ወደ አትክልት ሥፍራው ወስዶ ሊፈነዱ ያሉትን በተለያየ ቀለማት ያሸበረቁትን እምቡጥ አበባዎች ያሳያቸው። የተፈጥሮን ታላቅ መጽሐፍ በመክፈት የእግዚአብሔር ፍቅር በእያንዳንዱ ዛፍ አበባና ሳር እንደሚገለጽ በማሳየት ስለፈጣሪ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን መስጠት ይችላል። እግዚአብሔር ለእነዚህ ዛፎችና አበቦች እጅግ ጥንቃቄ ማድረጉን በማሳየት እንዲያደንቁ፤ በአምሳሉ የፈጠረውን ሰውማ እንዴት ይሆን ብለው ግርምት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። ልጆች በመልካም ባህርይ ውበት፣ በቸርነትና በፍቅር ፀጋ አጊጠው ያማሩ እንዲሆኑ እንጂ በሰውሠራሽ ቅጭልጭል እንዲንቆጠቆጡ እግዚአብሔር እንደማይፈልግ ገና በሕፃንነታቸው ሊያስተምራቸው ይችላል። 11 AHAmh 154.1