የአድቬንቲስት ቤት

34/88

ምዕራፍ ሠላሳ ሦስት—የመለኮታዊ ምሪት ተስፋዎች

የመለኮታዊው ጓደኛ አስተዋይነት እንዴት ጣፋጭ ነው፦የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ሊለግሳችሁ፣ ፀሎታችሁን ሊሰማ አዛኙ አዳኛችሁ በርኅራኄና በፍቅር እየተመለከታችሁ ነው። የእያንዳንዷን እናት የልብ ሸክም ይረዳል፤ በአደጋ ጊዜም ከእርሱ የሚቀርብ ጓደኛ ከቶ አታገኝም፤ የማይታጠፈው ክንዱ እግዚአብሔርን የምትፈራ ታማኝ የሆነችን እናት ይደግፋታል። በምድር ሳለ በድህነት የምትኖር፣ ብዙ የሚያስጨንቋት ችግሮችና ግራ የሚያጋቡ ውጣ ውረዶች ሲታገልዋት የነበረች እናት ያሳደገችው እርሱ የእያንዳንዷን ክርስቲያን እናት ጭንቀትና ችግር በሚገባ ይረዳል፤ ያዝንላትማል። ልጅዋን በርኩስ መንፈስ የተያዘባትን፣ ልብዋ እጅግ ተጨንቃ የነበረችን እናት፣ ስጋትዋን ሊያስታግስላት ረዥም መንገድ በእግሩ የተጓዘ ያ አዳኝ የእናትን ፀሎት በመስማት ልጆችዋን ይባርካል። AHAmh 140.1

ሊቀበር በመንገድ ላይ ሳለ ለመበለትዋ ሴት ብቸኛ ልጅዋን መልሶ የሰጠ፣ ዛሬም በሐዘንተኛዋ እናት ልቡ ይነካል። በአልዓዛር መቃብር የርኅራኄ እንባ ያፈሰሰ፣ ተቀብሮ የነበረውን በድን ሕይወት ዘርቶ ለማርታና ለማርያም የሰጠ፤ መግደላዊት ማርያምን የማረ፤ በመስቀል ተንጠልጥሎ በስቃይ ላይ እያለ እንኳ እናቱን ያስታወሰ፤ ለሚያለቅሱት ሴቶች በመገለጥ ከሞት የመነሣቱን የመጀመሪያ ብሥራት እንዲነግዱ መልክተኞች ያደረገ አዳኝ፣ እርሱ ሴትን በሁሉም የሕይወት ጎዳናዎች ሊረዳት ዛሬ አቻ የሌለው ጓደኛዋ ነው። 1 AHAmh 140.2

የክርስቲያን እናትን ሥራ የሚስተካከል ተግባር የለም። በጌታ ተግሳጽና ተጽዕኖ ሥር ልጆችን ማሳደግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የምትረዳ ናት። ሸክምዋ ከምትችለው በላይ እንደከበዳት ስንት ጊዜ ተሰምቷት ይሆን! ሁሉንም ሸክም በሩኅሩኅ አዳኝዋ ፊት በፀሎት ማቅረብ መቻልዋ እንዴት ዓይነት ግሩም እድል ነው! ሸክምዋን በእግሩ ሥር ጥላ በነዚያ ፈታኝ ሰዓታት ጥበብ በሚሰጣት፣ ደስታ፣ ተስፋና ብርታት በሚያጎናጽፋት በእርሱ ሥር ሆና መገኘት ኃይልዋን ታድሳለች። ጭንቀቶችዋ ሁሉ የሚገባው ንቁ ጓደኛ ማግኘት፣ በስቃይ ለደከመች እናት እንዴት ጣፋጭ ነው! እናቶች በተደጋጋሚ ወደ ክርስቶስ ቢሄዱ በሙሉ ልብም ቢያምኑት ሸክማቸው በቀለለ፣ ለነፍሳቸውም ዕረፍት ባገኙ ነበር። 2 AHAmh 140.3

የሰማይ አምላክ ፀሎታችሁን ይሰማል፦ ያለ መለኮታዊ እርዳታ ልጆቻችሁን በተገቢው መንገድ ልታሳድጉ አትችሉም፤ የአዳም የውድቀት ተፈጥሮ ሁልጊዜም ሊነግስ ይጥራልና። የእውነት መርሆዎች በሕይወት ውስጥ ምግብ እንዲያገኙ በነፍስ ሥር እንዲሰድዱ ልብ መዘጋጀት አለበት። 3 AHAmh 140.4

የእግዚአብሔርን አቅጣጫ በመከተል ልጆቻቸውን የሚያሠለጥኑ ወላጆች፣ ከሰማይ እርዳታ እንደሚያገኙ ያውቃሉ። ሲያስተምሩ ስለሚማሩ ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። የእግዚአብሔርን መንገድ በመጠበቅ በሰበሰቡት እውቀት ልጆቻቸው ድሎችን ይቀዳጃሉ። ተፈጥሮአዊውንም ሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የክፋት ዝንባሌ ለማሸነፍ ብቁ ይሆናሉ። 4 AHAmh 141.1

ወላጆች ሆይ በማይታክት ጥረት ለልጆቻችሁ እየሠራችሁ ነው? ያላሰለሰ ጥንቃቄአችሁን፣ ልባዊ ሥራችሁንና ጭንቀታችሁን እግዚአብሔር ልብ ይለዋል፤ ፀሎታችሁን ይሰማል። በደግነትና በትዕግሥት ልጆቻችሁን ለጌታ አሠልጥኑ። ሰማይ ሁሉ በሥራችሁ ፍላጎት ያድርበታል…. እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያብራል፤ ልፋታችሁን በስኬት ዘውድ ይሸልማል። 5 AHAmh 141.2

የመዳንን እውነት ግልጽ ለማድረግ ስትሞክሩ፤ ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው እንዲቀበሉ ለልጆቻችሁ ስታመላክቷቸው መላእክት ከጎናችሁ ይቆማሉ። በእርግጥም የዓለም ተስፋ ስለሆነው የቤተልሔሙ ሕፃን የከበረ ታሪክ ፍላጎት ማሳደር ይችሉ ዘንድ እግዚአብሔር ለአባቶችና ለእናቶች ፀጋን ያጎናጽፋል። 6 AHAmh 141.3

ጠይቁና ተቀበሉ፦ በዚህ ጠቃሚ ሥራቸው ወላጆች መለኮታዊ እርዳታ መጠየቅና መቀበል አለባቸው። ወላጆች [ራሳቸው ልጆች ሳሉ] ባህርያቸው፣ ልማዳቸውና ተሞክሯቸው በዝቅተኛ ጥራት የተቀረጸ፤ በሕፃንነትና በወጣትነት ጊዜያቸው የተሰጣቸው ትምህርት መልካም ወዳልሆነ ባህርይ የመራቸው ቢሆንም እንኳ ተስፋ እንዳይቆርጡ። የየሱስ ኃይማኖት ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነውና መለወጥ የሚችለው የእግዚአብሔር ኃይል ከተወረሰውና ከተንሰራፋው ዝንባሌአቸው ሊያድሳቸው ይቻለዋል። “እንደገና መወለድ” ማለት መለወጥ፣ በየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን ማለት ነው። 7 AHAmh 141.4

ልጆቻችንን ቃሉ እንደሚለው እናስተምራቸው። ከጠራችሁት እግዚአብሔር ይመልስላችኋል። እነሆኝ ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ? ይላችኋል። እያንዳንዷ ነፍስ ግቧን ለመምታት ትችል ዘንድ ሰማይ ከምድር ጋር የተቆራኘ ነው። ጌታ እነዚህን ልጆች ይወድዳቸዋል። ለታላቁ ጥሪያቸው ማስተዋልን ይዘው ያድጉ ዘንድ ይፈልግባቸዋል። 8 AHAmh 141.5

መንፈስ ቅዱስ ይመራል፦ እናት ለእግዚአብሔር መንገድና ፈቃድ እራስዋን በማስረከብ እውነተኛ ልምድ እንድታዳብር፣ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደሚያስፈልጋት ልታውቅ ይገባታል። ከዚያም በክርስቶስ ፀጋ ብልህ፣ ደግና አፍቃሪ መምህርት ትሆናለች። 9 AHAmh 141.6

እያንዳንዱ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ያለ ወላጅ በቤት ውስጥ መምህር ይሆን ዘንድ የሚያስችለውን ብርታትና ፀጋ ክርስቶስ ሊሰጠው ተዘጋጅቷል። ይህ የቤት ትምህርት ሥነ-ሥርዓት የመቅረፅና የመሥራት ተጽዕኖ አለው። 10 AHAmh 142.1

መለኮታዊ ኃይል ከሰው ጥረት ጋር ይተባበራል፦ ያለ ሰው ጥረት መለኮታዊ መምራት አይገኝም። እግዚአብሔር በኃይል መሥራት የሚችለው ወላጆች በእምነት በእርሱ ተደግፈው፣ ለወደቀባቸው የተቀደሰ ኃላፊነት ሲነቁና ልጆቻቸውን በመልካሙ መንገድ ለማሠልጠን ሲነሡ ነው። ለራሳቸውና ለልጆቻቸው መዳን ሲሉ በጸሎትና በጥንቃቄ ልጆቻቸውን ከሚያስተምሩ ወላጆች ጋር እግዚአብሔር ይተባበራል። የራሱ የሆነውን መልካም ደስታ ለመፈለግና ለመተግበር እንዲችሉ አምላክ በውስጣቸው ይሠራል። 11 AHAmh 142.2

የሰዎች ጥረት ብቻውን ለሰማይ የሚያዘጋጃቸውን ፍፁም ባህርይ እንዲያዳብሩ ሊያደርጋቸው አይችልም። በመለኮታዊ እርዳታ ግን ታላቅና ቅዱስ ሥራ ሊከናወን ይችላል። 12 AHAmh 142.3

በእግዚአብሔር ብርታት እንደ ወላጆች ኃላፊነታችሁን ለመሸከም ስትነሡ፣ የኃላፊነት ገበታችሁን ሳትለቅቁ፣ ጥረታችሁን ሳታላሉ፣ በቆራጥ ተነሳሽነት ልጆቻችሁን እግዚአብሔር እንደሚፈልጋቸው ለማድረግ ስትጥሩ፣ ጌታ ቁልቁል እያያችሁ ድጋፉን ይቸራችኋል። የምትችሉትን ሁሉ ለማድረግ እየጣራችሁ እንደሆነ ያውቃል፤ ኃይልም ይጨምርላችኋል። እናት ወይም አባት ሊሠሩት የማይችሉትን የሥራ ድርሻ እርሱ ያከናውነዋል። ብልህ፣ ትዕግሥተኛና በሳል ጥረት ከምታደርግና፣ እግዚአብሔርን ከምትፈራ እናት ጋር እርሱ ይሠራል። ወላጆች ሆይ በቤታችሁ እንድትሠሩት እግዚአብሔር የተወላችሁን ሥራ እርሱ እራሱ ሊሠራው ሐሳብ አያቀርብላችሁም። በዚህ ዓለም ከከበባቸው አደጋ ልጆቻችሁን ትታደጓቸው ዘንድ ከወደዳችሁ፣ ለልግምና እጃችሁን በመስጠት ሰነፍ ሠራተኞች አትሁኑ። 13 AHAmh 142.4

ፈተና ሲመጣ የሱስን ተጠማጠሙበት፦ ወላጆች ሆይ በመንገዳችሁ የሚያበሩትን የመለኮታዊ ብርሃን ጮራዎች ሰብስቡ። ክርስቶስ በብርሃን እንደሆነ እንዲሁ በብርሃን ተራመዱ። ልጆቻችሁን ለማትረፍ በቅድስና ጎዳና ደረጃችሁንብታስጠብቁ እጅግ አስቸጋሪ ፈተናዎች ይመጡባችኋል፤ ከቆማችሁበት ግን ፈቀቅ አትበሉ። የሱስን ተጠማጠሙት፤ እንዲህ ይላል፡- “በጉልበቴ ግን ያጸናኛል ሰላም ያደርግልኛል።” ችግሮች ይበዛሉ፤ መሰናክሎችም ይገጥሟችኋል፤ ሳታቋርጡ ወደ የሱስ ተመልከቱ። ድንገተኛ አደጋ በሚመጣበትም ጊዜ ጌታ ሆይ አሁን ምን ላድርግ? ብላችሁ ጠይቁት። 14 AHAmh 142.5

የጦርነቱ ፅናት በጨመረ መጠን [ወላጆች] የበለጠ እርዳታ ከሰማያዊ አባታቸው ይሻሉ፤ የሚገኘውም ድል በዚያው ልክ አመርቂ ይሆናል። 15 AHAmh 143.1

ስለዚህ በእምነት ሥሩ። እንደ ዘርፈ-ብዙው የክርስቶስ ፀጋ ታማኝ አገልጋዮች፣ ትዕግስተኞችና አፍቃሪዎች በመሆን ወላጆች የተሰጣቸውን ሥራ ሊሠሩ ይገባቸዋል። ታማኝ ሆነው እንዲገኙ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም ነገር በእምነት ይተግበር። እግዚአብሔር ፀጋውን ለልጆቻቸው እንዲሠጥ ሁልጊዜ ይፀልዩ። በሥራቸው የዛሉ፣ ትዕግስት ያጡና የሚጨነቁ ፈጽሞ መሆን የለባቸውም። ከልጆቻቸውና ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ ይኖርባቸዋል። የትህትናና የንጽህና የላቀ ደረጃ ላይ ልጆቻቸውን ለማድረስ በእውነት የሚሠፉ፣ በትዕግሥትና በፍቅር የሚጥሩ ወላጆች በእርግጥ ውጤታማ ይሆናሉ። 16 AHAmh 143.2