የአድቬንቲስት ቤት

32/88

ምዕራፍ ሠላሳ አንድ—በፍቅር ውስጥ ያለ ዋስትና

የፍቅር አገልግሎት ኃይል፦ የፍቅር መሣሪያዎች ግሩም ኃይል አላቸው፤ መለኮታዊ ናቸውና። “የለዘበች አነጋገር ቁጣን ታበርዳለች” “ፍቅር ታጋሽ ናት በጎም ናት” እንዲሁም “ኃጢአትን ሁሉ የሚሸፍን” የበጎ ሥጦታ ትምህርቱ ቢገባን፣ ሕይወታችን በእንዴት ዓይነት የፈውስ ኃይል ፀጋ ይባረክ ነበር! ሕይወት እንዴት በተለወጠ ነበር! ምድር የሰማይ ቅምሻ በሆነች ነበር! AHAmh 133.1

እነዚህ ድንቅ ትምህርቶች በቀላሉ ሊነገሩ ትናንሽ ልጆችም እንኳ ሊያስተውሏቸው የሚችሉ ናቸው። የልጅ ልብ ለስላሳና በትንሽ ነገር የሚማረክ ነው፤ እኛ ታላላቆችም“እንደ ህጻናት” ስንሆን ያልተወሳሰበ፣ ደግና ለስለስ ያለውን የአዳኙን ፍቅር ስንማር የታናናሾችን ልብ ለመንካትና የፍቅርን የፈውስ አገልግሎት ለማስተማር ከባድ ሆኖ አናገኘውም።1 AHAmh 133.2

በዓለም መነጽር ስናየው ገንዘብ ኃይል ነው፤ በክርስቲያን አመለካከት ግን ፍቅር ኃይል ነው። በዚህ መርህ ውስጥ አዕምሮአዊና መንፈሳዊ ኃይላት ተካትተዋል። ንጹህ ፍቅር መልካም ለማድረግ ልዩ ብቃት አለው፤ ከመልካም ነገር ውጪ ሌላ መሥራት አይችልም። ጠብና ሥቃይን አስወግዶ ወደር የማይገኝለትን እውነተኛ ደስታን ያመጣል። አብዛኛውን ጊዜ ሀብት የማበላሸትና የማጥፋት ተጽዕኖ አለው፤ ኃይልም ጉዳት ያደርሳል። እውነትና መልካምነት ግን የንጹህ ፍቅር መገለጫ ባህርያት ናቸው።2 AHAmh 133.3

ፍቅር የሚንከባከቡት ተክል ነው፦ ቤት ፍጹም ንጹህ የሆነውና እጅግ የከበረው ፍቅር እምብርት መሆን አለበት። ሠላም፣ መስማማት፣ ፍቅርና ደስታ… እነዚህ የከበሩ ነገሮች በቤተሰቡ አባላት ልብ ውስጥ እስኪዋሐዱ ድረስ ዘወትር በጽናት ልንንከባከባቸው ይገባል። የፍቅር ተክል በጥንቃቄ መኮትኮትና ውኃ መጠጣት አለበት፤ ያለዚያ ይሞታል። ነፍሳችን እንዲፋፋ ከፈለግን ለእያንዳንዱ መልካም ነገር ከፍተኛ ዋጋ መስጠት አለብን። ሰይጣን በልባችን የሚተክለው ክፉ ምኞት፣ ቅናት፣ ርኩስ ሐሳብ፣ ባለጌ አነጋገር፣ ትዕግስት-የለሽነት፣ ጥላቻ፣ ራስ-ወዳድነት፣ ምቀኝነትና እብሪት ሁሉ ተመንግሎ መጣል አለበት። እነዚህ ክፉ ነገሮች በሕይወታችን አቆጥቁጠው እንዲቀሩ ከፈቀድንላቸው ብዙ የሚያረክሱ ፍሬዎችን ያፈራሉ። ኦ! ወርቃማዎቹን የፍቅር ፍሬዎች የሚገድሉ፣ ነፍስን የሚበክሉ መርዛማ እፅዋትን ስንቶች ኮትኩተው አሳድገዋል!3 AHAmh 133.4

የልጅነታችሁንም ጊዜ አስታውሱ፦ ገና ሕፃናት እንደሆኑ ረስታችሁ፣ የራሳችሁን የልጅነት ጊዜ ዘንግታችሁ ግትርነት ብቻ አታንፀባርቁባቸው። ፍጹም እንዲሆኑ አትጠብቁ፤ በአንድ ጊዜ ጎልማሳ ሴቶችና ወንዶች ልታደርጓቸው አትሞክሩ። እንዲህ በማድረጋችሁ ለእናንተ የከፈቱትን በር ታዘጋላችሁ። ለእናንተም የከረቸሙትን በር ጉዳት ለሚያመጡ ተጽዕኖዎች እንዲከፍቱት ትመሯቸዋላችሁ። ለአደጋ ሲጋለጡ ከመንቃታችሁ በፊት፣ ለጋ አዕምሮአቸውን ሌሎች እንዲበርዙት መንገድ ትከፍታላችሁ…. AHAmh 133.5

ወላጆች የልጅነታቸውን ዓመታት መርሳት የለባቸውም፤ የርኅራኄና የፍቅር ጥማታቸውን እንዲሁም ሲኮነኑና በኃይለ-ቃል ሲገሠጹ ምን ያህል ሐዘን ይሰማቸው እንደነበረ መዘንጋት የለባቸውም። በአስተሳሰባቸው እንደገና ወጣት ይሁኑ፤ የአእምሮአቸውን ደረጃ ዝቅ አድርገው የልጆቻቸውን ፍላጎት ለመረዳት ይሞክሩ።4 AHAmh 134.1

ልጆቻችሁ የሚፈልጉት ለስለስ ያሉና የሚያበረታቱ ቃላትን ነው። ችግራቸውን የሚያስረሱ፣ በልባቸው የፀሐይ ጮራ የሚፈነጥቁ፣ የፍቅርና የቸርነት ቃላትን መናገር ለእናቶች እንዴት ቀላል ነው!5 AHAmh 134.2

ወላጆች ሆይ ለልጆቻችሁ ፍቅር ሥጡ፡- ፍቅር በጨቅላነታቸው፣ ፍቅር በልጅነታቸው፣ ፍቅር በወጣትነታቸው ለግሱ። የተኮፋተረ ግንባር ሳይሆን ሁሌም በብርሃን የፈካ ፊት አሳዩአቸው።6 AHAmh 134.3

ልጆቻችሁን አንፀባራቂ ደስታ ውስጥ ጠብቋቸው፦ ታናናሾች በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በጥንቃቄ ልናጽናናቸው ይገባል። በህፃንነትና በወጣትነት መካከል ያሉ ልጆች በተለምዶ ማግኘት ያለባቸውን ትኩረት አያገኙም። የቤተሰቡ አካል መሆናቸውን እንዲረዱ የሚያመላክቱ እናቶች ያስፈልጋሉ። ተስፋዎቻቸውንና ግራ የሚያጋቡ ነገሮቻቸውን እናታቸው ልታዋያቸው ይገባታል። ለእንግዳ ሰዎች ከሚደረገው ቸርነት በተሻለ ሁኔታ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊጠነቀቁላቸው እንደሚገባ ያስታውሱ። በእናታቸው ምሪት ሥር አንፀባራቂ ደስታ ሊ ከብባቸው የተገባ ነው።7 AHAmh 134.4

ድልን ይቀዳጁ ዘንድ ልጆቻችሁን እርዷቸው…. በፍቅር ከባቢ አየር ከልሏቸው፤ ከዚያም ፍንክች የማይለውን ግትርነታቸውን ታለዝቡታላችሁ።8 AHAmh 134.5

ልጆች ከምግብ ይልቅ ፍቅር በሚያስፈልጋቸው ጊዜ፦ በልጆቻቸው ትንንሽ ልብሶች ላይ አላስፈላጊ ማስተካከያ ለማድረግ ወይም ልብሳቸው ላይ ጥልፍ ለመጥለፍ ጊዜ ለማግኘት ሲሉ ብዙ ወላጆች በአሳፋሪ ሁኔታ ልጆቻቸውን ቸል ይላሉ። ልጆቻቸው በድካም እየተዝለፈለፉ እርዳታቸውን ሲፈልጉ በዝምታ ያልፏቸዋል፤ AHAmh 134.6

ወይም ምግብ ይሰጧቸዋል። ምግብ አለመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን ሳይርባቸው መብላታቸው ጉዳት አለው። ፈልገውት የነበረው የእናታቸውን የሚያሳርፍ ጉያ ነበረ። በህፃንነታቸውና በልጅነታቸው እያንዳንዷ እናት እነዚህን ጥቃቅን የፍቅር መግለጫዎች ለልጆችዋ መለገስዋ እጅግ ጠቀሜታ ያለው ነው። በዚህ መልኩ እናት የልጆችዋን ልብና ደስታ ከራስዋ ጋር ማቆራኘት ትችላለች። እናት ለልጆችዋእግዚአብሔር ለእኛ የሆነውን ያህል ናት።9 AHAmh 134.7

ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶች መሟላት አለባቸው፦ በማንኛውም ጊዜ ልጆቻችሁን በእርግጥ እንደምታፈቅሯቸው ልታሳውቋቸው ይገባል፤ ፍላጎታቸውን ለማርካት እንደምትደክሙ፤ ደስታቸውም ለእናንተ ዋጋ ያለው እንደሆነና የምታቅዱት ነገር ሁሉ ለእነርሱ ደህንነት ብቻ ሲባል እንደሆነ ልታስገነዝቧቸው ይገባል። አግባብነት ያለው ከሆነ የሚፈልጉትን ለመስጠት እሺ በሏቸው።10 AHAmh 135.1

ስሜታዊ ሆናችሁ ልጆችን ከማዘዝ ፈጽሞ ተቆጠቡ። ሥልጣንና ፍቅር ይዋሃዱ፤ መልካምና ውብ የሆነውን ባህርይ ሁሉ ተንከባክባችሁ አሳድጉ። ክርስቶስን በመግለጽ ከፍ ላለው መልካምነት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ምሯቸው። የማያስደስቱ እየሆኑ በሄዱ ቁጥር እናንተም ምን ያህል እንደምተወዷቸው ለመግለጽ እየተቸገራችሁ ትሄዳላችሁ። አንድ ልጅ ለእርሱ ደስታ እንደምትጥሩ አመኔታው ካደረበት ፍቅር እያንዳንዱን የልዩነት ግድግዳ ይንደዋል። አዳኙ ለሰዎች የተጠቀመበት መርህ ይህ ነው። ይህ መርህ በቤተ-ክርስቲያንም እውን ሊሆን ይገባዋል።11 AHAmh 135.2

ፍቅር ሊገለጽ ይገባዋል፦ አንዱ ለሌላው ፍቅርን የመግለጽ እጥረት በብዙ ቤተሰቦች አለ። መመጻደቅ አስፈላጊ ባይሆንም ፍቅርም ሆነ ርኅራኄ ብጹዕ፣ ንጹህና ክቡር በሆነ ሁኔታ ሊገለጽ ይገባዋል። ብዙዎች ፍጹም ግትርነትን በልባቸው በማሳደግ በቃልና በተግባር ሰይጣናዊ የሆነውን የባህርያቸውን ጎን ያሳያሉ። ርኅራኄ የተሞላበት ፍቅር በባልና በሚስት፣ በወላጆችና በልጆች፣ በወንድሞችና በእህቶች መካከል ሊበረታታ ይገባዋል። እያንዳንዱ ችኩል አነጋገር ይቁም፤ አንዱ ለሌላው የሚያሳየው ፍቅር የጎደለው አካሄድ መስሎ የሚታየው እንቅስቃሴ እንኳን በፍጹም አይኑር። አስደሳች ሊሆንና በቸርነት ሊናገር የእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ኃላፊነት ነው።12 AHAmh 135.3

በጥቃቅን በጎ አድራጎቶች፣ በንግግርና አሳቢነት በሚታይበት ትኩረት ሁሉ ደግነትን መዋደድንና ፍቅርን ግለጹ።13 AHAmh 135.4

ልጆች ወላጆቻቸውን ያከብሩ ዘንድ የሚያስተምረው ከሁሉም የበለጠውና ውጤታማ የሆነው መንገድ፣ አባት ለሚስቱ የሚሰጠውን ደግነት የተሞላበት ትኩረት እንዲሁም እናት ለባልዋ የምትሰጠውን ክብርና ውዳሴ እንዲያዩ እድሉን መፍጠር ነው፤ በወላጆቻቸው መሃል ፍቅር እንዲያዩ ማድረግ ነው። ልጆች አምስተኛውን ትዕዛዝ ለመጠበቅ የሚበረታቱትና በማስተዋልም ቃሉን የሚታዘዙት፤ “ልጆች ለወላጆች ታዘዙ በጌታችን ይህ የቀና ነውና” የሚለውን ቃል የሚተገብሩት፤ በእናታቸውና በአባታቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ተንተርሰው ነው።14 AHAmh 135.5

የክርስቶስ ፍቅር በወላጆች ይንፀባረቅ፦ እናት የልጆችዋን አመኔታ አግኝታ ልጆችዋ እንዲታዘዟትና እንዲወድዷት ስታስተምራቸው፣ በክርስቲያን ሕይወት የመጀመሪያውን ትምህርት ሰጠቻቸው ማለት ነው። ወላጆቻቸውን እንደሚወድዱ፣ እንደሚያምኑና እንደሚታዘዙ ሁሉ ለአዳኛቸውም እንዲሁ እምነት፣ ፍቅርና መታዘዝን መተግበር ይገባቸዋል። ወላጅ በታማኝ እንክብካቤና ትክክለኛ ሥልጠና ለልጁ የሚያሳየው ፍቅር፣ የሱስ ለታማኝ ሕዝቦቹ ያለው ፍቅር መስታወት ነው።15 AHAmh 135.6