የአድቬንቲስት ቤት

24/88

ክፍል 7—የጌታ ርስት

ምዕራፍ ሃያ ሦስት—ልጆች - በረከቶች

ቤተሰብ እግዚአብሔር ያቀደው ነው፦ ረዳት ትሆነው ዘንድ ሔዋንን ለአዳም የሰጠ እርሱ…. ወንዶችና ሴቶች በተቀደሰው ጋብቻ ተጣምረው የክብር ዘውድ የደፉ የሰማይ ቤተሰብ አባል እንደሆኑ እውቅና የሚያገኙ ቤተሰቦች እንዲያፈሩ አዝዟቸዋል።1 AHAmh 106.1

ልጆች የጌታ ቅርሶች ናቸው፤ በመሆኑም የእርሱን ንብረት በማስተዳደራችን ተጠያቂዎች ነን…. ወደ ጌታ ቀርበው:- “እነሆኝ እኔ እግዚአብሔርም የሰጠኝ ልጆች” ማለት እስኪችሉ ድረስ ወላጆች በፍቅር በእምነትና በፀሎት ለቤተሰቦቻቸው ይሥሩ።2 AHAmh 106.2

ልጅ የሌለው ቤት የተራቆተ ሥፍራ ነው። የነዋሪዎቹ ልቦች ራስ-ወዳድ የመሆን አደጋ ያጋጥማቸዋል፤ ለራሳቸው እንደሚቀልላቸው አድርገው የሚወዱ፣ ለራሳቸው ምቾት የሚብከነከኑ ይሆናሉ። ለራሳቸው የእዘኑልኝ ስሜት የሚያንፀባርቁ ሆነው ሳለ ለሌሎች የሚለግሱት ግን አንዳች ነገር የላቸውም።3 AHAmh 106.3

ምክር ልጅ ለሌላቸው ጥንዶች፦ በእያንዳንዱ ሰው ልዩ ተፈጥሮአዊ አደረጃጀትና በተለያዩ ሁኔታዎች የሚገለጸው ራስ-ወዳድነት መሞት አለበት። ልጆች ቢኖሯችሁና አዕምሮአችሁ ስለራሳችሁ ከማሰብ ተላቅቆ ለልጆቻችሁ ደህንነት፣ መሠልጠንና ምሣሌ መሆን ቢኖርበት ለእናንተ መልካም ነበር…. ልክ እንደ እናንተ ሁለት ሰዎች ቤተሰብ ሲመሠርቱ ትዕግስትን፣ ራስን-መግዛትንና እውነተኛ ፍቅርን ተግባራዊ ለማድርግ ግድ የሚያስብሏቸው ልጆች ከሌሉ እራስ-ወዳድነት እንዳይነግሥ ዘወትር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለሌሎች ለማድረግ በምንም ዓይነት ግዴታ ውስጥ እንዳልሆናችሁ እየተሰማችሁ ለራሳችሁ ጥንቃቄ፣ ፍላጎትና ትኩረት የምትሹ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።4 AHAmh 106.4

ልጅ የሌላቸው ጥንዶች ትኩረታቸው (ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል) ለራሳቸው ብቻ ስለሆነ ብዙዎች የአካል፣ የአዕምሮና የግብረ-ገብነት በሽተኞች ሆነዋል። እነዚህን ሰዎች ከመቆርቆዝ የሚያድናቸውና ሕይወት የሚዘራባቸው ዕረፍት የለሽ የሆነው የልጆች ጉልበትና ጤናማ የሆነው የተለያየ ገጽታን የሚፈጥረው የወጣቶች አዕምሮ ሊሆን ይችላል።5 AHAmh 106.5

ለልጆች እንክብካቤ በማድረግ ጨዋ ልማዶች ይዳብራሉ፦ በልጅነቴ ስቃይ ደርሶብኝ ስላደግሁ ለሁሉም ልጆች በጣም የተለየ ፍቅር አለኝ። ብዙ ልጆችን ልንከባከባቸው ወስጃቸዋለሁ፤ ውስብስብነት ከሌለው ልጅነት ጋር አብሮነት መፍጠር ሁሌም ታላቅ በረከት እንደሆነልኝ ይሰማኛል…. AHAmh 106.6

ከልጆች ጋር ለመግባባት የሚያስፈልጉት ባህርያት ርኅራኄ፣ ራስን መግዛትና ፍቅር በማንኛውም ቤተሰብ ባርኮትን የሚያመጡ ናቸው። የበለጠ ደስታ ለሚፈልጉና መስከን ለሚያሻቸው ሁሉ ግትር ባህርይን የሚያለሰልስና የሚያስገዛ ተጽዕኖ አለው። የልጅ በቤት ውስጥ መኖር የማጣፈጥና የማንጠር ሥራ ይሠራል። በፈሪሃእግዚአብሔር ሥር ያደገ ልጅ በረከት ነው።6 AHAmh 107.1

ለተደገፉን ልጆቻችን ፍቅርና እንክብካቤ ስንለግስ ሸካራ የሆነውን ተፈጥሮአችንን ያስወግደዋል፤ ለስላሳና ሩኅሩኅ ያደርገናል፤ መልካም ጎናችን የበለጠ እንዲዳብር ተጽዕኖ ይፈጥራል።7 AHAmh 107.2

በሔኖክ ላይ የነበረው የልጁ ተጽዕኖ፦ የመጀመሪያ ልጁ ከተወለደ በኋላ ሔኖክ የተሻለ ልምምድ ላይ ደረሰ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ወደበለጠ ቅርበት ተመራ። እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ ያሉበትን ግዴታዎችና ኃላፊነቶች በተሻለ ሙሉነት ወደ መረዳት መጣ። ልጁ ለአባቱ ያለውን ፍቅር፣ ለጥበቃው ያለውን ፍጹም እምነት ሲያይ፤ ለዚያ ለመጀመሪያ ልጁ ያለውን ልባዊ ናፍቆትና ርኅራኄ ሲያጤን ግሩም ስለሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር የከበረውን ትምህርት ቀሰመ። አንድያ ልጁን በመስጠት አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅርና የእግዚአብሔር ልጆች በሰማያዊ አባታቸው ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን መተማመን ተማረ።8 AHAmh 107.3

ድንቅ መተማመን፦ ልጆች እግዚአብሔር ለወላጆቻቸው ያበደራቸው እንቁ ስጦታዎች ናቸው፤ አንድ ቀን ከእጃቸው ይፈልጋቸዋል። ሥልጠናቸው የበለጠ ጊዜ፣ የተሻለ ጥንቃቄና ፀሎት ያስፈልገዋል። ትክክለኛውን መመሪያ በተሻለ አቅርቦት ይሻሉ…. AHAmh 107.4

አስታውሱ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ናቸው። እንድትጠነቀቁላቸው አደራ ያላችሁ ለሰማይ እንድታሠለጥኗቸውና እንድታስተምሯቸው የተሰጧችሁ ናቸው። የተቀደሰውን አደራ ስታከናውኑ እንዴት ተግባራዊ እንዳደረጋችሁት መጠየቃችሁ አይቀሬ ነው።9 AHAmh 107.5