የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሰባ ሁለት—እንግዳ ተቀባይነትና መስተንግዶ
ዛሬም በእንግድነት የሚመጡት መላእክት ሊሆኑ ይችላሉ፡- ስለ መስተንግዶ መጽሐፍ ቅዱስ በአንክሮ ብዙ የሚለው ነገር አለው። እንግዳ ተቀባይነትን እንደ ኃላፊነት ከማስቀመጡም በተጨማሪ የዚህን ፀጋ በሥራ ላይ የማዋል ውብ ገጽታዎችና የሚያመጣውንም በረከቶች ይገልፃል። ከእነዚህ ሁሉ ቀዳሚው የአብርሃም ገጠመኝ ነበር…. AHAmh 326.1
እነዚህን የደግነት አድራጎቶች እግዚአብሔር በቃሉ ይመዘግባቸው ዘንድ ጠቀሜታ ያላቸው ሆነው አገኛቸው። ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላም በሐዋርያው እንደገና ተጠቀሱ፡- “እንግዶችን መውደድ አትርሱ በዚህ ሰዎች ተገብቶአቸዋልና መላእክትን ይቀበሉ ዘንድ ሳያውቁ።” ለአብርሃምና ለሎጥ ተሰጥቶት የነበረው ዕድል ለእኛም አልተነፈገንም። እኛም በበኩላችን የእግዚአብሔርን ልጆች በእንግድነት በመቀበል የእርሱን መላእክት ወደ ቤታችን እንጋብዛለን። በዚህ በእኛ ዘመንም መላእክት የሰውን አምሳል በመልበስ ወደ ሰዎች ቤቶች ገብተው ይስተናገዳሉ። በእግዚአብሔር ብርሃን የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም የማይታዩ መላእክት አብረዋቸው ናቸው፤ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት ሲሄዱም በቤታችን በረከትን ትተውልን ይሄዳሉ።1 AHAmh 326.2
ቸል የተባሉ እድሎች፣ አጋጣሚዎችና ልዩ መብቶች፡- የቤተ-ክርስቲያንን ኃላፊነት ሊሸከም የሚችለውን አገልጋይ መንፈስ ቅዱስ ሲመርጥ ያስቀመጠው አንዱ መስፈርት “እንግዶችንም የሚወድ” የሚለው ነው። ለመላው ቤተ-ክርስቲያንም ይህ ቃል ተሰጠ፡- “እንግዶችን የምትወዱ ሁኑ እርስ በእርሳችሁም ያለማንጎራጎር። ሁሉም እያንዳንዱ በተቀበለው ፀጋ መጠን ባልንጀራውን ያገልግለው። እንደ እግዚአብሔር ልዩ ልዩ ፀጋው ደህና መጋቦች።” AHAmh 326.3
እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በሚገርም ሁኔታ ቸል ተብለዋል። ክርስቲያኖች ነን በሚሉት ሰዎች እንኳ እንግዳ ተቀባይነት አይተገበርም። እንግዳ ተቀባይነትን የማሳየቱ አጋጣሚ በራሳችን ሰዎች መካከል እንኳ እንደ ልዩ እድልና በረከት አይታይም። በአጠቃላይ ያለው ማህበራዊነት በጣም ውስን ነው፤ አጀብ ወይም ድንግርግር ሳይፈጠር ካለን ቤተሰብ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ሰው የመጨመር ፈቃደኝነቱም የለም።2 AHAmh 326.4
በቂ ያልሆነ ማስተባበያ፡- የእግዚአብሔርን ቅዱሳት ወደ ቤታቸውና ወደ ልባቸው ላለመጋበዝ ብዙዎች የሚሰጡትን ምክንያት ሰምቻለሁ፡- “ለምን ብትሉ ምንም የተዘጋጀ ነገር የለኝም። የበሰለ ምንም ምግብ የለኝም። ወደ ሌላ ቦታ ይሂዱ።” በዛኛውም ቦታ መስተንግዶ የሚሹትን ሰዎች ላለመቀበል ሆን ተብሎ የተፈጠረ ማስተባበያ ይኖራል። የጎብኝዎቹም ልብ ክፉኛ ያዝናል፤ በዚህ ዓይነቱ መስተንግዶአቸው ምክንያት የእነዚህ ክርስቲያኖች ነን ባዮች ወንድሞችና እህቶች መልካም ያልሆነ ገጽታ ተቀርጾባቸው ይሄዳሉ። እህት ሆይ እንጀራ ከሌለሽ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተደረገው አድርጊ። ወደ ጎረቤትሽ ሂጅና “ባልንጀራዬ ሆይ ሦስት እንጀራ አበድሪኝ፤ ከመንገድ የመጣ ጓደኛዬ ወደ እኔ መጥቷል፤ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝም።” በይ። AHAmh 326.5
የእንጀራ አለመኖር እንደ ምክንያት ቀርቦ ወደ ቤታችን እንዲገባ ለጠየቀን እምቢ የሚያስብል ምሣሌ ተሰጥቶን አያውቅም። ኤልያስ ወደ ሰራፕታዋ መበለት ሲመጣ ቁራሹዋን ከእግዚአብሔር ነብይ ጋር ተጋራች፤ በቤትዋ ውስጥ ይሆን ዘንድ ስለወደደችና ቁራሽዋንም ስላካፈለችው ለብዙ ጊዜ ያቆያትን የእርስዋንና የወንድ ልጅዋን ሕይወት ያተረፈው ተዓምር እንዲፈፀም ምክንያት ሆነች። ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ ይህንን በጎነት በደስታ ለሚያደርጉ ሁሉ AHAmh 327.1
እንዲሁ ይሆንላቸዋል። አንዳንዶች ጤና ማጣታቸውን በማማረር እንደ ምክንያት ያቀርባሉ - አቅም ቢኖረን ኖሮ ባደረግነው ነበር ይላሉ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እራሳቸውን በራሳቸው ለጉመው ስለ እራሳቸው ደካማ ስሜት ስለ ስቃያቸው ስለ ፈተናቸውና መከራቸው ማውራት የዕለት ተዕለት እውነታቸው ሆኗል። ስለ እራሳቸው እንጂ ስለ ሌሎች ማሰብ አይችሉም፤ ሆኖም ርኅራኄና ዕርዳታ የሚሹ ሌሎች ብዙኃን ይኖራሉ። በጤና ማጣት ለምትሰቃዩ ለእናንተ መፍትሄ አለ። እራቁቱን የሆነውን ሰው ብታይ ታለብሰው ዘንድ ድኆችንና ስደተኞችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ እንጀራህንም ለተራበ ትቆርስ ዘንድ [ብትወድ] “በዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይወጣል። ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል።” መልካም ማድረግ ግሩም የበሽታ መድኃኒት ነው። በዚህ ሥራ የሚሳተፉ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዲጠሩ ተጋብዘዋል፤ ይመልስላቸውም ዘንድ ለራሱ ቃል ገብቷል። ነፍሳቸው ከጥማት ይረካል፤ ውኃ እንደሚጠጣም ገነት ይሆናሉ እንደማይቋረጥም ምንጭ።3 AHAmh 327.2
ከራስ-ወዳድነት በሚመነጭ ሌሎችን በማያካትት ሕይወት የሚቀረው በረከት፡- “እኔና ቤተሰቤ” የሚለው የራስ-ወዳድ ነፀብራቅ እግዚአብሔርን ያስከፋዋል። ይህንን መንፈስ የሚያንፀባርቅ እያንዳንዱ ቤተሰብ በክርስቶስ ሕይወት በታየው ንጹህ መርህ መለወጥ አለበት። እራሳቸውን በራሳቸው ዓለም ውስጥ ዘግተው እንግዶችን ለማስተናገድ ፈቃዳቸው ያልሆነ እነርሱ ብዙ በረከት ይቀርባቸዋል።4 AHAmh 327.3
መልካም ለማድረግ በፊታችን የሚያልፉትን አጋጣሚዎች የምንጠቀምባቸው እንደሆነ ለማየት መላእክት እየተከታተሉን ነው - እነርሱም መልሰው ይባርኩን ዘንድ ሌሎችን የምንባርክ እንደሆነ ለማየት እየተጠባበቁን ነው። ሁሉም ባህርይ የማጎልበት ዕድል ያገኙ ዘንድ አንዳንዶች ድኆች፣ አንዳንዶች ሀብታሞች፣ ሌሎች ደግሞ ስቃይተኞች ይሆኑ ዘንድ እራሱ እግዚአብሔር በመካከላቸው ልዩነት አደረገ። ሊፈትነን [ታማኝ] ሆነን መገኘታችንንም ሊያረጋግጥ በልባችን ያለው ይጎለምስ ዘንድ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ለዓላማው ድኆች ይኖሩ ዘንድ ፈቀደ።5 AHAmh 327.4
የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ሲሞት ልብ በራስ-ወዳድነት በድኖና ሽባ ሆኖ ይንዘፈዘፋል።6 AHAmh 328.1
የመስተንግዶ ቸርነት ለማን ይለገስ?፡- ማህበራዊ መስተንግዶአችን በክርስቶስ መንፈስና ቃሉ በሚያስተምረው እንጂ በዓለማዊ ልማድ ሊመራ አይገባውም። እስራኤላውያን በሁሉም በዓሎቻቸው ድኃውን፣ እንግዳውን እንዲሁም የኃይማኖት አስተማሪውንና አገልጋዩን የካህኑም ረዳት የሆነውን ሌዋዊ ሁሉ ይደበልቁ ነበር። እነዚህ የማህበረሰቡ አባላት የሕዝብ እንግዶች እንደሆኑ በማህበራዊና በሃይማኖታዊ ደስታቸው ሁሉ ተካፋይ ሊሆኑ፤ በችግራቸውና በህመማቸው ጊዜ ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ሊያገኙ የተገባቸው እንደሆኑ ይታመን ነበር። እንደዚህ ዓይነቱን ነው ወደ ቤታችን መጋበዝ ያለብን። እንደዚህ ዓይነቱን እንኳን ደህና መጣችሁ በሚሲዮናዊ ሥራ ላይ ለተጠመደችው ነርስ፤ ለአስተማሪው፤ ችግር ላጎበጣትና ድካም ላናወዛት እናት፤ ለደከሙና ላረጁ፤ በአብዛኛው ቤት አልባ ለሆኑ፤ በብዙ ችግርና ተስፋ መቁረጥ ለተንገላቱ ምን ያህል ደስታና ማበረታቻ ነው! AHAmh 328.2
“ምሣ ባደረግህ ጊዜ ወይም እራት” ክርስቶስም አለ “ወዳጆችህን አትጽራ ወንድሞችህንም ዘመዶችህንም ባለጸጎችንም ጎረቤቶችህንም ምን አልባት ይጸሩሃል ደግሞ ብድራት ይሆንልሃል። ነገር ግን ምሣ ባደረግህ ጊዜ ድኆችን ጥራ፣ ጉንድሾችንም፣ አንካሶችን፣ እውሮችንም ምሥጋናም ይገባሃል። የሚከፍሉህ የላቸውምና ዋጋህም ይሆናል በጻድቃን ትንሣኤ።” AHAmh 328.3
እነዚህን እንግዶች ብትቀበሉ ብዙም ሸክም የማይሆኑባችሁ ናቸው። ውድና የተሽቆጠቆጠ መስተንግዶ ማድረግ አያስፈልጋችሁም፤ ለታይታም ጉልበት አታወጡም። የወዳጅነት አቀባበላችሁ ሙቀት፤ ቦታ በምድጃችሁ ዙሪያ፤ መቀመጫ በቤታችሁ ጠረጴዛና የጸሎት ሰዓት በረከትን የመጋራት ዕድል ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች እንደ ሰማይ ጨረፍታ ነው። AHAmh 328.4
ርኅራኄዎቻችን የራስን ወሰንና የቤተሰብን የአጥር ክልል ጥሰው መፍሰስ አለባቸው። ቤቶቻቸው ለሌሎች በረከት ይሆኑ ዘንድ ለሚፈቅዱ ለእነርሱ ወርቃማ አጋጣሚዎች አሉ። ማህበራዊ ተጽዕኖ ግሩም ኃይል ነው፤ ብንወድስ በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን።7 AHAmh 328.5
መጠለያ ምሽግ ለሚፈተኑ ወጣቶች፡- ቤታችን ለተፈተኑ ወጣቶች ቅጥር ሊሆን ይገባዋል። በመንታ መንገድ ላይ የቆሙ ብዙዎች ናቸው። እያንዳንዱ ተጽዕኖ እያንዳንዱ አሻራ በዚህም ሆነ በዚያኛው ዓለም መዳረሻቸውን የሚወስን ምርጫቸውን ቅርጽ የሚያስይዝ ነው። ክፋትና ርኩሰት ይጋብዛቸዋል፤ መዝናኛ ቦታዎች አንፀባራቂና ማራኪ ሆነው የተሠሩ ናቸው፤ ለሚመጣው ሁሉ ማረፊያ አላቸው። በዙሪያችን ብዙ ቤት የሌላቸው ወጣቶች አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ቤት ቢኖራቸውም የሚያግዝና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ኃይል የሌለው መጠለያ በመሆኑ ወደ ክፋት የሚያዘቅጥ ነው። በበራችን አጠገብም ወደ ጥፋትና ውድመት እየወረዱ ናቸው። AHAmh 328.6
እነዚህ ወጣቶች በርኅራኄ የተዘረጋ እጅ ያስፈልጋቸዋል። እንዲሁ የሚነገሩ ደጋግ ቃላት በነፃ የሚለገሱ ጥቃቅን እንክብካቤዎች በነፍስ ላይ የሚያንዣብቡ የፈተና ደመናዎችን ይገፋሉ። በእውነት የሚገለጽ ሰማይ-ወለድ የሆነ የርኅራኄ ኃይል የክርስቶስ መሰልነትን መዓዛ የሚያመነጩ ቃላት ለሚያስፈልጋቸው፤ ገራሙና ለስላሳው የጌታ የፍቅር መንፈስ ዳበሳ ለሚያሻቸው ሁሉ የልባቸውን በር የመክፈት ጉልበት አለው። ወጣቱን የማወቅና የመረዳት ፍላጎት ብናሳይ ወደ ቤታችን ብንጋብዛቸውና በጠቃሚና በሚያበረታታ ተጽዕኖ ብንከብባቸው እግራቸውን ወደ መልካሙ መንገድ የሚመልሱ ብዙዎች በሆኑ ነበር።8 AHAmh 329.1
ቀላል የሆነውን የቤተሰብ አኗኗር ጠብቁ፡- ሁሌም እንደሚያደርጉት እንግዶች ሲመጡ የእናትን ትኩረትና ጊዜ ሁሉ እንዲወስዱ ሊፈቀድላቸው አይገባም። የልጆችዋ ምድራዊና መንፈሳዊ ደህንነት ቅድሚያ መሰጠት አለበት። ውድ ኬኮችን ሳምቡሳዎችንና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን በማቅረብ ጊዜ መጥፋት የለበትም። እነዚህ ተጨማሪ ወጭዎች ናቸው፤ ብዙዎች እነዚህን ማግኘት አይችሉም። ከሁሉም የሚበልጠው ክፋት ግን ምሣሌነቱ ነው። የተለመደው የቤተሰብ ቀለል ያለ ኑሮ አይለወጥ። ከአቅማችሁ በላይ የሆነ የኑሮ ቄንጥ ጠብቄ ልኖር እችላለሁ የሚለውን እሳቤ ለማንፀባረቅ አትድከሙ። በጠባያችሁም ሆነ በምታቀርቡት ምግብ ያል ሆናችሁትን ሆናችሁ ለመታየት አትሞክሩ። እንግዶችን በቸርነት መንከባከብና ቤታቸው እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ቢጠበቅባችሁም እግዚአብሔር ለሰጣችሁ ታናናሽ ልጆቻችሁ መምህር እንደሆናችሁ ምንጊዜም አስታውሱ። AHAmh 329.2
እየተመለከቷችሁ ነው፤ የትኛውም እርምጃችሁ እግራቸውን ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዳይመራቸው ተጠንቀቁ። በእያንዳንዱ ቀን ለቤተሰቡ እንደምትሆኑት ማለትም አስደሳች አሳቢና ደጎች እንደሆናችሁ እንዲሁ ለእንግዶቻችሁ ሁኑ። እንደዚህ ሲሆን ሁሉም አስተማሪና የመልካም ሥራ ምሣሌ መሆን ይችላል። በሚበሉት በሚጠጡትና በሚለብሱት ነገር ብቻ አዕምሮአቸውን ከመሙላት ይልቅ ከዚያ የበለጠ አስፈላ ጊ ነገር እንዳለ ም ሥክሮች ይሆናሉ። 9 AHAmh 329.3
ዕረፍትና ሠላም ያለበት ከባቢ አየር ይኑር፡- የቤት ኑሮአችንና የማህበራዊ ግንኙነታችን በክርስቶስ ቀናነትና ቸርነት ቁጥጥር ሥር ቢሆን ከአሁኑ እጅግ በተሻለ ሁኔታ ደስተኞች በሆንን ነበር። የእንግዶችን ምኞት ከማርካት ወይም አድናቆታቸውን ለማግኘት ከሚለፋው የታይታ ተግባር ይልቅ በፍቅራችን፣ በፍልቅልቅነታችንና በርኅራኄአችን በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ ለማስደሰት እንትጋ። ከክርስቶስ ፈቃድ ጋር ለመስማማት ስንጥር ሌሎች ይመልከቱን። ጥሪታችን ብዙም ባይሆን ይበቃኛል የማለትና ያመሥጋኝነት መንፈስ በእኛ ውስጥ ይዩ። የእውነተኛው ክርስቲያን ቤት ሁኔታ የሚታወቀው በሠላሙና በዕረፍት ሰጪነቱ ነው። ይህ ምሣሌነት ውጤት ሳያስገኝ በከንቱ አይቀርም።10 AHAmh 330.1
የወጭ መዝገብ በሰማይ አለ፡- ስለ እርሱ ለሚደረገው መስተንግዶ የሚወጣውን እያንዳንዱን ወጭ ክርስቶስ ይመዘግባል። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገውን ሁሉ እርሱ ያቀርባል። ለክርስቶስ ሲሉ ባልንጀሮቻቸውን የሚያስተናግዱ ጉብኝቱ ለራሳቸውም ሆነ ለጎብኝዎቻቸው ትርፋማ ይሆን ዘንድ የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ እነርሱ ለተለየ በረከት በመብቃታቸው በሰማይ የሚመዘገቡ ናቸው…. የራሱን ሕይወት በመስጠት ክርስቶስ መስተንግዶ አስተምሮናል። በውኃው ዳር በተራበ ሕዝብ ተከብቦ ሳለ ሳይስተናገዱና ሳይታደሱ ወደ ቤታቸው ይሄዱ ዘንድ አልተቻለውም። ለደቀ-መዛሙርቱ እንዲህ አለ:-“እላንት ስጧቸው ሊበሉ [እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው]።” ማቴ 14፡16። በፈጠራ ኃይሉ እስኪጠግቡ መገባቸው። ሆኖም የቀረበላቸው ምግብ እንዴት ቀለል ያለ ነበር! ድሎት አልነበረባቸውም። የሰማይ ሀብት ሁሉ በእጁ እያለ በውድ ግብዣ ሊያቀማጥላቸው ይችል ነበር። ነገር ግን የሚስፈልጋቸውን ብቻ ማለትም በባህር ዙሪያ የሚኖሩ የዓሳ አስጋሪዎች የዕለት ምግብ የሆነውን መብል አቀረበላቸው። ወንዶች በዛሬው ዘመን ያልተወሳሰበ የኑሮ ዘይቤ ቢኖራቸው፤ ከተፈጥሮ ሕጎች ጋር በስምምነት ቢኖሩ፤ ለሁሉም የሰው ልጆች ፍላጎት የተትረፈረፈ አቅርቦት በኖረ ነበር። በፈጣሪ መንገድ ላይ ለመሥራት ያለው እድል በሰፋ፤ ሐሳብ የወለዳቸውን ፍላጎቶች የማሳደድ ዝንባሌ በቀነሰ ነበር። AHAmh 330.2
ድህነታችን የእንግዳ ተቀባይነታችን በር ሊዘጋብን አይገባም። ያለንን ልናካፍል ይገባናል። ገቢያቸው አናሳ ሆኖ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ስለማይችል በታላቅ ችግር ውስጥ ተዘፍቀው፤ መኖር አቅቷቸው የሚንገዳገዱ አሉ። ነገር ግን በቅዱሳን አካል ተሸፍኖ የሚያዩትን የሱስን ከልባቸው ስለሚወዱት ጉብኝታቸው ውጤታማ ይሆን ዘንድ በተቻላቸው መጠን በመጣር አማኞችንም ሆነ የማያምኑ ሰዎችን በእንግድነት ይቀበላሉ። እነዚህ እንግዶች በቤተሰቡ አንድነትና በመሠውያው እንኳን ደህና መጣችሁ ይባላሉ። የፀሎት ቅመም መዓዛ በሚስተናገዱት ላይ ተጽዕኖውን ያሳርፋል፤ እንደዚህ ዓይነቱ ጉብኝት አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም እንኳ ቢሆን የምትጠፋን ነፍስ ከሞት ለመታደግ በቂ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ሥራ ጌታ ይከፍላል ፤ “እመልሳለሁ” ይላል።11 AHAmh 330.3
ለሚገኙ ዕድሎች የነቃችሁ ሁኑ፡- ወንድሞችና እህቶች ሆይ ንቁ! መልካም ሥራን ለመሥራት አትፍሩ። “መልካምንም በማድረግ አንታክት የምናጭድበት ጊዜ አለንና ካልደከምነ።” ኃላፊነታችሁ እስኪነገራችሁ አትጠብቁ። ዐይናችሁን ክፈቱና በዙሪያችሁ ያሉትን ተመልከቱ። ረዳት ከሌላቸው ከተቸገሩና ከተጎዱ ጋር ራሳችሁን አስተዋውቁ። እራሳችሁን አትደብቁባቸው፤ ፍላጎታቸውንም አትከልክሏቸው። በያዕቆብ ለቀረቡት መልእክቶች ማረጋገጫ የሚሆን ንጹህ ኃይማኖት በራስ-ወዳድነት ወይም በብልሹነት ያልተበከለ ማንነት ማን ሊያቀርብ ይችላል? በታላቁ የማዳን እቅድ ውስጥ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ የሚጨነቁ እነማን ናቸው?12 AHAmh 331.1