የአድቬንቲስት ቤት
ክፍል ፩—የሚያምረው ትዳር(ቤት)
ምዕራፍ አንድ—የቤተሰብ ድባብ
ቤተሰብ የሁሉም እንቅስቃሴ ማዕከል ነው፦ ሕብረተሰብ የቤተሰብ ስብስብና ውህደት ሲሆን የቤተሰብ መሪዎች የሚገነቡት ነው። “የሕይወት ጉዳዮች” የሚወጡት ከልብ ነው፤ ቤተሰብ ደግሞ የህብረተሰብ (የሕዝብ)፣ የቤተ-ክርስቲያን እንዲሁም የአገር ልብ ነው። የማህበረሰቡ ደህንነት፣ የቤተ-ክርስቲያን ውጤታማነትና የሀገር ብልፅግና ቤት ውስጥ በሚመነጨው ተጽዕኖ ይወሰናል።1 AHAmh 2.1
የማህበረሰቡ የወደፊት ውድቀት ወይም ምጥቀት በዙሪያችን በሚያድጉ ወጣቶች ጠባይና ግብረ-ገብነት የሚወሰን ነው። ወጣቶች በሚማሩበት ጊዜ በልጅነት ዘመናቸው ባህርያቸው በጨዋ ልማድ፣ ራስን በመግዛትና በቁጥብነት ሲቀረጽ ተጽዕኖአቸው በማህበረሰቡ ላይ ይንፀባረቃል። ያለ ትምህርትና ከቁጥጥር ውጪ ከተተዉ ውጤቱም በራስ ፍላጎት ብቻ የተመሠረተ፤ በፍላጎትና በስሜት ገደብ-የለሽነት የሚመራ ሆኖ ማህበረሰቡን በመቅረጽ ረገድ ያላቸው የወደፊት ተጽዕኖም እንዲሁ ይሆናል። ወጣቶች አሁን የሚመሠርቱት ጓደኝነት፤ የሚያጎለብቱት ልማድ፤ የሚቀበሏቸው መሠረተ-ሐሳቦች መጭውን ዘመን ከወዲሁ የሚያሳዩ፤ ለዓመታት የሚሆነውን የሕብረተሰቡን ገጽታ የሚጠቁሙ መለኪያዎች ናቸው።2 AHAmh 2.2
የሰማይ ጣፋጭ ምሣሌ (የሰማይ ቅምሻ)፦ “ቤት” - ቃሉ የሚያመላክተውን ሁሉ ሆኖ መገኘት አለበት። በምድር ያለ ትንሹ ሰማይ መሆን አለበት። “ቤት” - ፍቅር ዘወትር የሚቆረቁዝበት ሳይሆን የሚኮተኮትበት ቦታ መሆን ይገባዋል። ደስታችን በዚህ የፍቅር ጉልማ፣ ርኅራኄና እውነተኛ የእርስ በእርስ መረዳዳት የሚወሰን ነው።3 AHAmh 2.3
እጅግ ጣፋጭና የሰማይ ተምሳሌት የሆነው ትዳር የጌታ መንፈስ በሊቀ-መንበርነት የሚመራው ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ተፈጻሚ ከሆነ ባልና ሚስት የሚከባበሩ፣ ፍቅር ያላቸውና የሚተማመኑ ይሆናሉ።4 AHAmh 2.4
የቤት ድባብ አስፈላጊነት፦ የአባቶችንና የእናቶችን ነፍስ የከበበው ስሜት ቤቱን ሁሉ ይሞላዋል። በእያንዳንዱ የቤተሰብ ክፍልም ይታያል።5 AHAmh 2.5
በቤተሰብ ዙሪያ ለሚፈጠረው ስሜት ምክንያቶቹ በአብዛኛው ወላጆች ናቸው። በእናትና በአባት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ልጆች የዚህ መንፈስ ተካፋይ ይሆናሉ። ስለሆነም ቤታችሁ ፍቅር በተሞላበት የደግነት መዓዛ የታወደ ይሁን። ከባለቤታችሁ ጋር ተፋትታችሁ ወይም ተቀያይማችሁ ከሆነና የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስቲያኖች መሆን አቅቶአችሁ ከሆነ ተለወጡ። ክርስቶስ ሲመጣ የሚኖራችሁ ባህርይ በሙከራ ጊዜያችሁ[በምድር] የተለማመዳችሁት፤ ያው ራሱ ጠባያችሁ ሳይለወጥ ነው። በሰማይ ቅዱስ ለመሆን መጀመሪያ በምድር ቅዱስ መሆን ይጠበቅባችኋል። በሕይወት ሳላችሁ የምታንፀባርቁት ባህርያችሁ በሞት ወይም በትንሳኤ ጊዜ አይለወጥም። በቤታችሁና በማህበረሰቡ ውስጥ እያላችሁ ያሳያችሁትን ጠባይ እራሱን ይዛችሁ ከመቃብር ትነሣላችሁ። በዳግም ምፅአቱ ክርስቶስ ባህርያችሁን አይቀይረውም። የመለወጥ ሥራ መሠራት ያለበት አሁን ነው። የዕለት ተዕለት ኑሮአችን መዳረሻችንን ይወስናል።6 AHAmh 2.6
ንፁህ ከባቢ አየርን መፍጠር፦ የእያንዳንዱ የክርስቲያን ቤተሰብ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል። ወላጆችም በንግግራቸውና ለእርስ በእርስ በሚያሳዩት ጠባይ ልጆቻቸው እንዲሆኑላቸው የሚፈልጉትን ባህርይ ዓይነት በኑሮአቸው በመተግበር ሕያው ምሣሌነትን ሊለግሷቸው ያስፈልጋል። የንግግር ሥርዓትና ንጽህና እንዲሁም እውነተኛ ክርስቲያናዊ ደግነት ሁልጊዜም መለማመድ አለብን። ለራሳቸው ክብር እንዲሰጡ፤ ለእግዚአብሔር ታማኝ፣ ለመመሪያቸውም ሐቀኛ እንዲሆኑ ልጆችንና ወጣቶችን አስተምሯቸው። የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩና እንዲታዘዙ አሠልጥኗቸው። እነዚህ መመሪያዎች ሕይወታቸውን በመቆጣጠር ከሌሎች ጋር በሚያደርጉት ጓደኝነትም ተግባራዊ ይሆናሉ። ነውር የሌለበት ሁኔታንም በመፍጠር፣ ለደከሙ ነፍሳት የሚያበረታታ ተጽዕኖ በመሆን፣ ወደ ቅድስናና ወደ ሰማይ የሚያደርሰውን ቀና መንገድ ለመያዝ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። እያንዳንዱ ትምህርት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስና ስብዕናን የሚገነባ ይዘት ይኑረው፤ ይህም ሲሆን በፍርድ ቀን በሰማይ መጽሐፍ የሰፈረውን መዝገባችሁን ለማየት የማያሳፍራችሁ ይሆናል። AHAmh 3.1
እንደዚህ ዓይነቱን ትዕዛዝ የተቀበሉ ልጆች ኃላፊነት ያለበትን ቦታ ለመያዝ (ለመሙላት) የተዘጋጁ፤ በመመሪያነትና በምሣሌነት ሌሎች መልካም የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ሁልጊዜ የሚያግዙ ይሆናሉ። የግብረ-ገብነት አስተዋይነታቸው ያልዶለዶመባቸው ትክክለኛ መርሆዎችን የሚያውቁና ለተፈጥሮአዊ ሥጦታቸው ትክክለኛ ግምት በመስጠት የአካላዊ፣ አዕምሮአዊና ግብረ-ገባዊ ኃይላቸውን በእጅጉ የሚጠቀሙበት ይሆናሉ። እነዚህ ነፍሳት በጠንካራ ምሽግ ከፈተና የተጠበቁ፤ በቀላሉ ሊደረመስ በማይችል ግንብ የተከበቡ ናቸው።7 AHAmh 3.2
የሰማያዊ ቤተሰብ ምሣሌ የሚሆን ቤተሰብ እግዚአብሔር በምድር እንዲኖረው ይፈልጋል። ወላጆችና ልጆች በእያንዳንዱ ቀን ይህንን በአዕምሮአቸው ያሰላስሉ፤ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል እንደሆኑ አድርገው እርስ በእርስ ይነጋገሩ። ይህም ሲሆን ለዓለም በሚለግሱት ተግባራዊ ትምህርት እግዚአብሔርን የሚወዱና ትዕዛዛቱንም የሚጠብቁ ቤተሰቦች ባህርይ ምን እንደሚመስል ያሳያሉ። ክርስቶስ ይከብራል፤ ሰላሙ፣ ፀጋውና ፍቅሩ እንደከበረ ሽቶ መዓዛ ቤቱን በሙሉ ያውደዋል።8 AHAmh 4.1
ብዙ ነገር የሚወሰነው በእናቶችና በአባቶች ነው። በሥርዓታቸው ጠንካራና ቆራጥ ሆኖም ደግ መሆን ይኖርባቸዋል። በበዛ ቅንነት በመሥራትም የሰማይ መላእክት ሠላምንና ግሩም ምሣሌነትን ለማካፈል የሚሳቡበት፣ ሥርዓት ያለውና ትክክለኛ ቤተሰብ ለመመሥረት መጣር ይኖርባቸዋል።9 AHAmh 4.2
ቤታችሁን ብሩህና ደስተኛ አድርጉት፦ መድኃኒታችን ለአንጸባረቃቸው ባህርያት ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት ቤታችሁን ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ብሩህና ደስታ የሞላበት ማድረግን አትርሱ። ክርስቶስን ወደ ቤታችሁ ከጋበዛችሁት መልካሙን ከመጥፎው መለየት ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ የጽድቅ ዛፎች ሆነው የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ እንዲያፈሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።10 AHAmh 4.3
መከራ ሊወራችሁ ይችላል፤ ይህ ግን የሰው ዕጣ ፈንታ ነው። ቀኑ ሁሌም ደመናማ ሊሆን ቢችል እንኳ ትዕግሥት፣ ም ሥጋናና ፍቅር በል ባችሁ ብር ሃን ያኑሩ። 11 AHAmh 4.4
ቤታችሁ በቁሳዊ ነገር ያላሸበረቀ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የደስታ ቃላት የሚነገሩበትና መልካም ተግባራት የሚከናወኑበት፣ ርኅራኄና ፍቅር ሁልጊዜ የሚስተናገዱበት ይሁን።12 AHAmh 4.5
ቤታችሁን በብረት በትር ሳይሆን በጥበብና በፍቅር አስተዳድሩ። ልጆች ለፍቅር ሕግ ለመገዛት ፈቃደኞች ናቸው። በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ ልጆቻችሁን አሞግሱ። በምትችሉት ሁሉ ሕይወታቸው በደስታ የተሞላ እንዲሆን አድርጉ። መውደድንና ፍቅርን በመግለጽ የልብን አፈር አለስልሳችሁ ለእውነት ዘር አዘጋጁት። አስታውሱ፣ ጌታ ለመሬት ደመናና ዝናብን ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ለመብቀልና ለማበብ የሚያስችለው ያማረ ፈገግታ ያለውን የጸሐይ ጮራንም ጭምር ነው። አሁንም አስታውሱ፤ ልጆች ወቀሳና ተግሳጽ ብቻ አይደለም የሚያስፈልጋቸው፤ መበረታታትንና መመስገንን እንዲሁም ደስታን የሚፈነጥቁ መልካም ቃላትን ጭምር ነው።13 AHAmh 4.6
በቤተሰባችሁ መካከል ጠብ አይኑር “ከሰማይ ግን የወረደች ጥበብ ታራቂ አስቀድሞ ንጹህ ናት ደግሞም የእርቅ ወዳጅ ገርም እሺ ባይም ምህረትና መልካም ፍሬ የመላባት ያለ ማድላትና ያለ ግብዝነት። የጽድቅ ፍሬ ግን በሠላም ትዘራለች ሠላም ለሚያደርጉ።” በቤት ውስጥ የሚያስፈልጉን ሠላምና ደግነት ናቸው።14 AHAmh 4.7
የሚያቆራኝ የለዘበ ትስስር፦ የቤተሰብ ትስስር በምድር ላይ ካሉ ግንኙነቶች ሁሉ እጅግ የጠበቀው ነው፤ ፈጽሞ ልዝብና ቅዱስ ነው። ለሰው ዘር ሁሉ በረከት እንዲሆን የታቀደ ነው። በረከት የሚሆነውም የጋብቻ ቃል ኪዳን በብልሃትና እግዚአብሔርን በመፍራት ሲፈጸም፣ ይዞትም ለሚመጣው ኃላፊነት ተገቢውን እሳቤ መስጠት ሲቻል ነው።15 AHAmh 5.1
እያንዳንዱ ትዳር የፍቅር ቦታ መሆን አለበት፤ የእግዚአብሔር መላእክት የሚኖሩበት በመገኘታቸውም ገር የሚያደርገውንና እራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በወላጆችና በልጆች የሚያሳድሩበት ቦታ ይሁን።16 AHAmh 5.2
ቤታችን ቤቴል፣ ልባችን ደግሞ ቅዱስ ሥፍራ ሆኖ መዘጋጀት አለበት። የእግዚአብሔር ፍቅር በነፍሳት ዘንድ ዋጋ በሚሰጥበት ቦታ ሁሉ ሠላም ይኖራል፤ ብርሃንና ደስታም ይሆናል። የእግዚአብሔርን ቃል በፍቅር በቤተሰቦቻችሁ ፊት ዘርጉና “እግዚአብሔር ምን ተናገረ?” በሉ።17 AHAmh 5.3
የክርስቶስ መገኘት ቤትን ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፦ በፍቅር፣ በርኅራኄና በለዘብታ የተዋበ ቤት መላእክት ሊጎበኙት የሚናፍቁትና እግዚአብሔርም የሚከብርበት ነው። በጥንቃቄ የተጠበቀ የክርስቲያን ቤት በልጅነትና በወጣትነት ዘመናቸው ላሉ ሁሉ የሚኖረው ተጽዕኖ ከዚህ ዓለም ብልሽትና ብክለት እርግጠኛው መከላከያ ነው። በእንደዚህ ዓይነቱ ቤት ያደጉ ልጆች ምድራዊ ወላጆቻቸውን እንዲሁም ሰማያዊ አባታቸውን መውደድን ይማራሉ።18 AHAmh 5.4
ታዳጊዎችን በካይ የሆነው የዓለም ተጽዕኖ እንዳያገኛቸው፣ ገና በጨቅላነታቸው በእነርሱና በዓለም መካከል የተገነባ ጠንካራ አጥር ሊኖራቸው ይገባል።19 AHAmh 5.5
እያንዳንዱ የክርስቲያን ቤተሰብ የክርስቲያንን ምሣሌነት ኃይልና ችሎታ ለዓለም በተግባር ማሳየት ይኖርበታል…. ቤተሰባቸውን ከግብረ-ገብነት ርኩሰትና ብክለት ነፃ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ወላጆች በአግባቡ ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።20 AHAmh 5.6
ቅድስና ለእግዚአብሔር ቤታችሁን ይሙላ…. ወላጆችና ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ስለመተባበር እራሳቸውን ያስተምሩ። ልማዳቸውንና ምግባራቸውን ከእግዚአብሔር እቅድ ጋር ማስማማት ይኖርባቸዋል።21 AHAmh 5.7
የቤተሰቡ ግንኙነት በምሣሌነቱ ሌሎችን ለቅድስና የሚጋብዝ ተጽዕኖ ማሳደር ይገባዋል። የክርስቲያን ቤተሰቦች በእግዚአብሔር እቅድ ተመሥርተውና ተመርተው ክርስቲያናዊ ጠባይ ለማዳበር ግሩም የሆነ እርዳታ የሚለግሱ ናቸው…. የሰውን የአድቬንቲስት ቤት ፍቅርና ንጽህና ጠብቆና ክቡር አድርጎ ማቆየት ለሚቻለው ለብቸኛው ለእርሱ [ለእግዚአብሔር] ወላጆችና ልጆች በአንድነት የፍቅር አገልግሎት ሊሰጡት መተባበር አለባቸው።22 AHAmh 5.8
እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል መስቀሉን ተሸክሞ የሱስ መንገዱን ሲመራ መከተል ይችል ዘንድ በክርስቲያን ቤት መጀመሪያ መተግበር ያለበት የክርስቶስ መንፈስ በቤት ውስጥ መሙላቱን ማየት ነው።23 AHAmh 6.1