የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ስድሳ ሰባት—የሚያማልሉ ትዕይንቶችና ድምፆች
የርኩሰት ትዕይንቶችና ድምፆች በዙሪያችን፦ በእያንዳንዱ እርምጃቸው ፈተና ለሚገጥማቸው ልጆቻችሁ ጥልቅ ጭንቀት ቢኖራችሁ ይገባችኋል። ከክፉ ጓደኞቻቸው ጋር እንዳይነካኩ ማድረግ የሚቻል አይደለም.… ትዕይንቶችን ያያሉ፤ ድምፆችን ይሰማሉ፤ ምግባረ-ሰናይነትን ዝቅ ለሚያደርጉ ተጽዕኖዎች መጋለጣቸው አይቀሬ ነው። እነዚህ ተጽዕኖዎች ያለማወላወል ካልተከለከሉ በስተቀር በግልጽ ባይታዩም እንኳን ልብን ማበላሸታቸውና ባህርይ ማንሻፈፋቸው በእርግጥ የማይቀር ነው። 1 AHAmh 296.1
ፈተናን ለመቃወም ሁሉም የመከላከያ ቅጥር ያስፈልጋቸዋል፦ ፈተናዎችን ለመቋቋም በክርስቲያን ቤቶች ዙሪያ ቅጥር መገንባት አለበት። የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ የሚያኮስሱትን ባህርያትና ወንጀሎች ሰይጣን ተወዳጅ እያደረጋቸው ነው። ግልጽ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶችን በሆነ ልብ-ወለድ ጽሑፍ ወይም በትያትር ቤቶች ሳናይ የከተማዎችን መንገዶች አናልፍም፤ አዕምሮ ከኃጢአት ጋር እንዲለማመድ ይማራል። የረከሰውና የጎደፈው አካሄድ በየዕለቱ በሚታተሙ ጽሁፎች አማካይነት ለሰዎች ይደርሳል፤ ፍላጎታቸውን የሚያነሣሱ ነገሮች ሁሉ በሚማርኩ ታሪኮች ይቀርቡላቸዋል። 2 AHAmh 296.2
አንዳንድ እናቶችና አባቶች እጅግ ዋዘኞችና ግድ-የለሾች ከመሆናቸው የተነሣ፣ ልጆቻቸው የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ቤት ወይም የሕዝብ ትምህርት ቤት ውስጥ የመማራቸው ልዩነት አይታያቸውም። “ያለነው በዓለም ነው” ይላሉ፤ “ከእርሱ ልንወጣ አንችልም።” ነገር ግን ወላጆች ሆይ ልናደርገው ከፈለግን ከዓለም የምንወጣበት መልካም መንገድ ማግኘት እንችላለን። በዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናት በፍጥነት እየተባዙ ያሉትን ርኩሰቶች እንዳናይ ልንሆን እንችላለን። በየጊዜው ስለሚፈጸመው ስለ አብዛኛው ኃጢአትና ወንጀል እንዳንሰማ መሆን እንችላለን። AHAmh 296.3
ሕገ-አልበኝነትን ዝሩ፤ የወንጀል መከር ታጭዳላችሁ፦ ብዙዎቹ ተወዳጅ የዕለቱ ሕትመቶች ርጉምነትን በሚያስተምሩ ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ታሪኮች የተሞሉ ወደ ሲኦል መንገድም የሚመሩ ናቸው። ልጆች በዕድሜ ሕፃን በወንጀል እውቀት ግን የጎለመሱ ሆነዋል። በሚያነቧቸው ታሪኮች ለክፋት ይነሳሳሉ። ያነበቡትን በሐሳባቸው ይስሉትና በምናባዊ ድርጊት ያስመስሉታል፤ ከዚያም ፍላጎታቸው ይነሣሳና ቅጣቱን አምልጠው ወንጀልን በመፈጸም ምን ማድረግ እንደሚችሉ መሞከር ይፈልጋሉ። AHAmh 296.4
ንቁ ለሆነው የልጆችና የወጣቶች አዕምሮ የሚሳሉት የወደፊት ምናባዊ ራዕዮች እንደ እውነት ናቸው። የሕግንና የራስ መግዛትን ቅጥር የሚያፈርሱ ርዕዩተ-ዓለማትን ሲተነበዩና ሁሉም የአሠራር ዘዴዎች ሲገለጹ ብዙዎች እነዚህን ሐሳቦች በውክልና ይወስዳሉ። ቢችሉስ እነዚህ ስሜታዊ ጽሑፎች ከሚገልጹአቸው ወንጀሎች የባሰ ድርጊት ወደመፈፀም ይመራሉ። በእንደዚህ ዓይነት ተጽዕኖዎች የማህበረሰቡ ግብረገብነት የተሰበረ ይሆናል፤ የሕገ-አልበኝነት ዘሮች በስፋት ይበተናሉ፤ መከሩ የወንጀል ምርት መሆኑ ማንንም ሊያስደንቀው አይገባም። AHAmh 297.1
የተወዳጅ ሙዚቃ አታላይነት፦ እውነትን እናምናለን ብለው የሚመሰክሩ የወጣት ሴቶችና ወንዶች አስተሳሰብ ምን ያህል የወረደ እንደሆነ ስመለከት እጅግ ያሳስበኛል። አዕምሮአቸው በትርጉም-የለሽ ነገር የተሞላ ነው። ንግግራቸው ባዶና ከንቱ ወሬ ብቻ ነው። ለሙዚቃ የተዘጋጀ ጆሮ አላቸው። የትኛውን የአካል ክፍል ስሜት መቀስቀስ እንዳለበት፤ በማስመሰል አዕምሮን የመመሰጥና የመማረክ ብሎም ክርስቶስ እንዳይፈለግ የማድረጉን ዘዴ ሰይጣን ያውቀዋል። እንዲህም ሲሆን ነፍስ ለመለኮታዊ እውቀትና ለፀጋ እድገት ያለው መንፈሳዊ ፍላጎት ወደ ተፈለገው ደረጃ ሳይደርስ ይቀራል። AHAmh 297.2
ወጣቶች ከፍ ያለ አቋም መያዝ እንዳለባቸውና ምክር ሰጫቸውና መሪያቸው የእግዚአብሔር ቃል መሆን እንደሚገባው አይቻለሁ። እንደ ቀላል የሚያዩአቸው በወጣቶች ላይ የተጣሉ ከባድ ኃላፊነቶች አሉ። በቤታቸው ውስጥ የዘፈን መደመጥ መጀመር ወደ ቅድስናና መንፈሳዊነት በመገፋፋት ፈንታ አዕምሮአቸው ከእውነት እንዲርቅ የማድረጊያ ዘዴ ሆኗል። ከንቱ ዘፈናቸውና የቀኑ ተወዳጅ የሙዚቃ ዝርዝር ከምርጫቸው ጋር የሚስማማ ይመስላል። ለፀሎት የሚያስፈልገውን ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያዎች ይወስዱታል። ሙዚቃ አላግባብ ሥራ ላይ የማይውል ከሆነ ታላቅ በረከት ነው። በተሳሳተ መንገድ ሲተገበር ደግሞ አስከፊ መርገም ነው። ያነቃቃል፤ ያስደስታል፤ ነገር ግን ክርስቲያን በፀጋ ዙፋን ሥር ብቻ ሲሆን የሚያገኘውን ጉልበትና ብርታት የሚሰጥ አይደለም። እራሱን ዝቅ በማድረግና የሚያሻውን በማሳወቅ በመሪር ዋይታና እንባ ሰማያዊውን ጉልበት በመለመን ክፉው ከሚያመጣበት ኃይለኛ ፈተና የሚሸሽግ ቅጥር አይሠራለትም። ሰይጣን ወጣቱን በእስረኛነት እየመራው ነው። ይህን ያነሆለላቸውን ኃይል ሊሰብሩ የሚችሉበት ምን ልነግራቸው እችላለሁ! እርሱ በሚያግባባ ብልሃቱ ወደ ሲኦል የሚመራቸው አታላይ ጠቢብ ነው።5 AHAmh 297.3
የጎደፉ አስተሳሰቦች ወደ አልነጹ ድርጊቶች ይመራሉ፦ ይህ ምግባረብልሹነት (corruption) በየትም ቦታ ዓለምን ያጥለቀለቀበት ዘመን ነው። የዐይን ዝሙትና ብልሹ ፍላጎቶች በማንበብና በማየት ይቀሰቀሳሉ። ልብ በጎደፈ አስተሳሰብ የረከሰ ሆኗል፤ ዝቅ ያሉና የተዋረዱ ትዕይንቶች ላይ በመመሰጥ አዕምሮ ይደሰታል። በቆሸሹ አስተሳሰቦች የተሞሉ እነዚህ የረከሱ ምስሎች ግብረ-ገብነትን በማበላሸት የተሞኙትንና በስሜት የቃተቱትን ፍጡራን ርኩስ ስሜታቸው ይቆጣጠራቸው ዘንድ ያዘጋጇቸዋል። ከዚያም ኃጢአትና ወንጀል በእግዚአብሔር አምሣል የተፈጠሩትን ሰዎች ቁልቁል በመጎተት ወደ አራዊት ደረጃ ዝቅ ያደርጓቸውና መጨረሻም የሲኦል እራት ያደርጓቸዋል።6 AHAmh 297.4
ክፉ ነገር አላይም፦ ልጆቻቸው ከእግዚአብሔር የጠፉ እንዳይሆኑ ወላጆች የማያቋርጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመዝሙር 101 የሰፈረው የዳዊት ቃል-ኪዳን የቤት ተጽዕኖዎችን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት ለተጣለበት ሁሉ መሀላ መሆን አለበት። መዝሙረኛው እንዲህ አለ “በዐይኔም ፊት ክፉ ነገር አላኖርም። የሕግ ተላላፊውን ሥራ ጸላሁ፣ አይጣበቅብኝም። ጠማማ ልብም ከእኔ ይራቅ። ክፉውንም ሰው አላውቅም። ባልንጀራውን በስውር የሚያማውንም አጠፋዋለሁ። ዐይኑ የታበየውንና ልቡ የሻከረውን መታገስ አይቻለኝም። አይኖቼ በምድር ምዕመናን ላይ ናቸው። ከእኔ ጋራ ይቀመጡ ዘንድ በቀናው መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል። ተንኮል አድራጊው ግን በቤቴ ውስጥ አይኖርም። ሐሰት የሚናገር በፊቴ አይጸናም።” 7 AHAmh 298.1
በልበ-ሙሉነት እንዲህ በሉ፡- “ምንም ትርፍ ለማያስገኝ ነገር ለሌሎች አገልግሎት እውል ዘንድ ገጣሚ ለማያደርገኝ ንባብ ውድ ጊዜዬን አላጠፋም። ሐሳቤንና ጊዜዬን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ብቁ ለሚያደርገኝ ተግባር አውለዋለሁ። ጆሮዎቼ የጌታ ናቸው፤ የጠላትን በማታለል የማሳመን ጥረት አላዳምጥም። ድምጼ በእግዚአብሔር ተጽዕኖ ሥር ላልሆነ ለማንኛውም ነገር አይገዛም። ሰውነቴ የመንፈስ ቅዱስ መቅደስ ነው፤ ኃይሎቼ ዋጋ ላለው ፍላጎት የተቀደሱ መሆን ይገባቸዋል።” 8 AHAmh 298.2