የአድቬንቲስት ቤት

8/88

ምዕራፍ ሰባት—እውነተኛ ፍቅር ወይስ የሚያነሆልል ስሜት

ፍቅር ከየሱስ የተበረከተ ክቡር ሥጦታ ነው፦ ፍቅር ከየሱስ የምንቀበለው የከበረ ሥጦታ ነው። ንጹህና ቅዱስ ፍቅር መርህ እንጂ ስሜት አይደለም። በእውነተኛ ፍቅር የተያዙ ሰዎች ምክንያት-አልባና ጭፍን አይደሉም።1 AHAmh 27.1

እውነተኛና ከልብ የመነጨ፤ ታማኝና ንጹህ ፍቅር ቢኖርም የለም ማለት ግን ይቀልላል። ይህ የከበረ ነገር ብርቅ (ከስንት አንድ) ነው። ብዙ ጊዜ የጋለ ስሜት በስህተት ፍቅር ነው ተብሎ ይታሰባል።2 AHAmh 27.2

እውነተኛ ፍቅር ታላቅና ቅዱስ መመሪያ ነው፤ በጭንቀት ሲፈተን ከሚሞተውና በስሜት ከሚነሳሳው ዓይነት ፍቅር ፈጽሞ የተለየ ባህርይ ያለው ነው።3 AHAmh 27.3

ፍቅር እየተንከባከብን ልናሳድገው የሚገባ ሰማያዊ ቡቃያ ነው። ከአፍቃሪ ልቦች የሚወጡ እውነተኛ የፍቅር ቃላት ደስተኛ ቤተሰብን ይፈጥራሉ፤ በተጽዕኖአቸው ሥር ለሚገኙ ሁሉ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ምሳሌነትን ማሳየት የሚችሉ ናቸው።4 AHAmh 27.4

ፍቅር ወይስ የጋለ ስሜት፦ ፍቅር…. ምክንያት-አልባ ደግሞም የታወረ አይደለም፤ ንጹህና ቅዱስ ነው። የተፈጥሮአዊው ልብ ስሜት ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። ንጹህ ፍቅር በሁሉም እቅዶቹ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያካትትና ከአምላክ መንፈስ ጋር የተስማማ ሲሆን ስሜታዊው ብርቱ ፍላጎት ግን ሐሳበ-ግትር፣ ችኩል፣ ምክንያት-አልባ፣ ለቁጥጥር አሻፈረኝ ባይና ምርጫውም ሁሉ ለጣኦት የተሰጠ ነው። እውነተኛ ፍቅር በያዘው ሰው ባህርይ ላይ የእግዚአብሔር ፀጋ በግልጽ ይታያል። ትህትና፣ ቀናነት፣ እውነተኛነት፣ ግብረ-ገባዊነትና ኃይማኖተኛነት ወደ ጋብቻ ጥምረት የሚወስደውን እርምጃ የሚያሳዩ ባህርያት ናቸው። በእውነተኛ ፍቅር ቁጥጥር ሥር ያሉ ሁሉ አብረው ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ የፀሎት ስብሰባ ሰዓታቸውን አያባክኑም፤ የቤተ-ክርስቲያን የአገልግሎት ፍላጎታቸውም አይወሰድባቸውም። እግዚአብሔር በለጋስነት የሰጣቸው የማደግ እድልና ክብር ለዕውነት ያላቸውን አድናቆት አይገድበውም።5 AHAmh 27.5

ጠንካራ መሠረት የሌለው ፍቅር ስሜትን ብቻ አርኪና ሐሰበ-ግትር፤ ጭፍንና ከቁጥጥር ውጭ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ክብር፣ እውነት፣ የበለፀገና የላቀ የአዕምሮ ጉልበት ሁሉ በፍላጎት ባርነት ሥር ይወድቃሉ። በዚህ የስሜታዊ ፍቅር ሰንሰለት የታሰረ ሰው ለምክንያታዊነትና ህሌናው ለሚነግረው ነገር ሁሉ ጆሮውን ይደፍናል። ድርድርም ሆነ ተማጽኖ እየተከተለው ያለው መንገድ የሚያመጣውን መዘዝ ሊያሳዩት አይችሉም። እውነተኛ ፍቅር ኃይለኛ፣ የሚፋጅና ችኩል ፍላጎት አይደለም፤ በተቃራኒው የፍቅር ባህርይ የተረጋጋና ጥልቅ ነው። የውጫዊውን ነገር አልፎ ይመለከታል። በባህርይ ብቻ ይማረካል። ጠቢብና ልዩ ነው፤ ታማኝነቱም ገሃድና የማያልቅ ነው።7 AHAmh 27.6

(እውነተኛ) ፍቅር ከጋለ ስሜትና ፍላጎት ግዛት ወጥቶ ወደ መንፈሳዊነት ይቀየርና በቃልና በተግባር ይገለጻል። አንድ ክርስቲያን ትዕግስት-የለሽነትንና ነጭናጫነትን አስወግዶ የተቀደሰ ቸርነትና ፍቅር ሊኖረው ይገባል። የሚያስከፉና ግትር ባህርያት በክርስቶስ ፀጋ መለስለስ ይገባቸዋል።8 AHAmh 28.1

ስሜታዊነትን እንደ ቁምጥና ልንሸሸው ይገባል፦ ምናባዊነትንና በፍቅር ታማሚ የመሆንን ስሜት ልክ እንደ ሥጋ ደዌ በሽታ ልንርቀው ይገባል። በዚህ ዘመን ያሉ ብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ደግነት ይጎድላቸዋል፤ ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል…. ደግ የሆኑ ሰዎች ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ባህርያት ቢጎድሏቸውም እንኳ ትልቅ የግብረ-ገብነት ዋጋ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።9 AHAmh 28.2

ፍላጎታቸውና ዓላማቸው ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ፣ አዛኝ ህሊና የሌላቸው፣ ነገር ግን ኃይማኖተኝነትን ሙያቸው አድርገው የያዙ ሰዎች አሉ። ከንቱና የማይረቡ ናቸው። ንግግራቸው ርካሽ ነው። ከፍ ከፍ ከሚያደርጉና ከሚያበለጽጉ አስተሳሰቦች ይልቅ የመጠናናት ጊዜና የትዳር ሐሳብ አዕምሮአቸውን ይቆጣጠረዋል።10 AHAmh 28.3

ለትዳር የማግባባትና ለጋብቻ የመቋመጥ ጉዳይ ወጣቱን አፍዝዞታል። የፍቅር ገመምተኛነትና ስሜታዊነት ተንሰራፍቷል። ከእንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ ተጽዕኖ ወጣቱን ለመጠበቅ ብልሐት ያስፈልጋል።11 AHAmh 28.4

ሴቶች ልጆች እራስን-መካድንና እራስን-መግዛትን እየተማሩ አይደሉም። እንደ ብርቅ ይታያሉ፤ ኩራታቸውና ትምክህተኝነታቸው ይበረታል። ሐሳበ-ግትርና የግላቸውን ፍላጎት ብቻ የሚያዩ እስኪሆኑ ድረስ የራሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ ይፈቀድላቸዋል። ከእንደዚህ ዓይነት ጥፋት ልጆቻችሁን ለመመለስ ምን አይነት መንገድ ብትከተሉ እንደሚሻላችሁ ለማወቅ የአዕምሮአችሁን ዲካ መንካት ይኖርባችኋል። በአጉል ድርቅናቸው፤ ቁጥብነት በማጣታቸው፤ የሴትነት ለዛ ስለሌላቸው ሰይጣን ልክ እምነት በሌላቸው ሰዎች ከንፈር እንደሚነገሩ ተረቶች እንዲመስሉ እያደረጋቸው ነው። ወጣት ወንዶችም እንደዚሁ በራሳቸው ፍላጎት አንዲመሩ ተትተዋል። ዕድሜአቸው ገና አሥራዎቹ ከመግባቱ በተመሳሳይ ዕድሜ ከሆኑ ኮረዳዎች ጎን መራመድ ይጀምራሉ፤ ሴቶቹንም ወደ ቤታቸው ይሸኟቸዋል፤ ወሲብም ይፈጽማሉ። ወላጆችም በራሳቸው ፍላጎት ከመዋጣቸው በተጨማሪ ለልጆቻቸው ባላቸው የተሳሳተ ፍቅር ምክንያት የሚሞላቀቅ ጠባያቸውን ቸል በማለት ለውጥ ለማምጣት ቁርጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ስለሚያቅታቸው በዚህ ፈጣን ዘመን የሚከንፉትን ልጆቻቸውን ለማስተካከል አይሞክሩም።12 AHAmh 28.5

ምክር በወሲብ ቀስቃሽ ፍቅር ለታመመች ወጣት፦ እህት ሆይ በዚህ ጥፋት በተስፋፋበትና የተበላሸ ዘመን (በተለይ ለሴቶች) ወደ አሳዛኙ ስህተት ወድቀሻል። ወንዶችን ከሚገባቸው በላይ ወደሻቸዋል፤ አብሮነታቸውን አፍቅረሻል፤ ትኩረትሽ የሚሸነግላቸው ሆኗል፤ አንቺም ከሐዋርያው ልባዊ ምክር ጋር መቸም የማይስማማ ትውውቅ ትፈቅጃለሽ፤ እንዲህ ይላልና “ክፉ ከሚመስል ሁሉ ሽሹ።’’ ከወሲብ ቀስቃሽ የፍቅር ውጥንሽ አዕምሮሽን መልሺ። ወሲብ ቀስቃሽና የፍቅር ታማሚነት ስሜትሽን ከኃይማኖትሽ ጋር ብታዳብይው ዝቅ ዝቅ እንጂ ከፍ ከፍ ልትይ አትችይም። የምትጎጅው ደግሞ አንቺ ብቻ አይደለሽም፤ በተጽዕኖሽና በምሣሌነትሽ ሌሎች ይቆስላሉ…. በሐሳብ መባከንሽና መቃዠትሽ፤ የወሲብ ቀስቃሽ ፍቅር ግንብን መገንባትሽ፤ ከአስፈላጊነትሽ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። በምናብ ዓለም ውስጥ ኖረሻል፤ ሐሳብ የወለደው ሰማዕት ሆነሻል፤ ሐሳብ የወለደው የስም ክርስቲያንም ሆነሻል። ከወጣቱ የኃይማኖት ልምድ ጋር ተዋህዶ የሚገኝ የቀዘቀዘ ስሜት በአሁኑ ዘመን እጅግ የተለመደ ነው። እህቴ ሆይ! እግዚአብሔር እንድትለወጪ ይፈልጋል። እለምንሻለሁ የፍቅር ግንዛቤሽ ከዚህ የተሻለ ይሁን። አዕምሮአዊና አካላዊ ኃይልሽን በደሙ ለገዛሽ ለአዳኝሽ አገልግሎት አውዪው። የምትሰሪው ሥራ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ይሆን ዘንድ ሐሳብሽንና ስሜትሽን ቀድሺ።13 AHAmh 29.1

ለወጣት ተማሪ ማስጠንቀቂያ፦ አሁን በተማሪ ሕይወት ውስጥ ነህ/ሽ፤ አእምሮህ/ሽ በመንፈሳዊ ትምህርት ከባቢ አየር ውስጥ ይኑር። ሁሉንም ይሉኝታ ከሕይወትህ/ሽ አስወግድ/ጂ። ጥንቁቅ መመሪያ ለራስህ/ሽ ስጥ/ጪ። አንተነትህ/ አንችነትሽ በራስ-መግዛት ሥር ይኑር። ባህርይህ/ሽ በሚቀረጽበት ጊዜ ውስጥ ነህ/ሽ። እግዚአብሔር ለሰጠህ/ሽ ሥራ የመዘጋጀትን ውጤታማነት ፈጽሞ ቅዱስና የላቀ የሆነውን ፍላጎትህ/ሽን ሊቀንስ የሚችል በመሆኑ በባህርይህ/ሽ ውስጥ ምንም ነገር ዋጋ የሌለውና የማያስፈልግ ሊባል አይገባም።14 AHAmh 29.2

ጥበብ የጎደለው መጠናናትና ትዳር ውጤት፦ በእያንዳንዱ እርምጃችን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮች ይገጥሙናል። በታላላቆችም ሆነ በወጣቶች በሚበረታቱ ስህተቶች ምክንያት ጥበብ የጎደለው መጠናናትና ጋብቻ ውጤቱ በማይረባ ነገር መጣላት፤ በጠብ በመቃቃርና ባልተገደበ ፍላጎት ምክንያት የባልና የሚስት እምነት ማጉደል፤ የራስን ፍላጎት ለመገደብ አለመፈለግና ለከት-የለሽ በሆነ ምኞት ዘለዓለማዊ ለሆኑ ጉዳዮች ፍላጎት ማጣት ከመሆን አይዘልም። የእግዚአብሔርን የትንቢት ቃል ቅድስና የሚወዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታይ ነን የሚሉ ክርስቲያኖች እንኳ ብዙ አይደሉም። ከዚህ የተሻለ ነፃነት ያለው ሁኔታም እንደሚፈልጉ ነፃና መረን የለቀቀ ጠባያቸው ይመሰክራል። ራስ-ወዳድ የሆነ ፍላጎታቸውንም ከማርካት መቆጠብ አይፈልጉም።15 AHAmh 29.3

ፍላጎታችሁን ተቆጣጠሩት፦ “የልቦናችሁን ወገብ ታጠቁ” ይላል ሐዋርያው። ሐሳባችሁን ተቆጣጠሩት እንጂ መረን አትልቀቁት። በራሳችሁ ቆራጥ ጥረት ሐሳባችሁን ልትጠብቁትና ልትቆጣጠሩት ትችላላችሁ። ቀና ሐሳብ አስቡ፤ ቅን ሥራም ትሠራላችሁ። ከዚያም ተገቢ ባልሆኑ ነገሮች ላይ እንዳይጣበቁ ፍላጎቶቻችሁን መቆጣጠር አለባችሁ። ክርስቶስ በሕይወቱ ገዝቷችኋል፤ እናንተ የእርሱ ናችሁ፤ የሐሳባችሁ ኃይልና የልባችሁ ፍላጎት እንዴት ተግባር ላይ እንደሚውል በሁሉም ነገር ልታማክሩት ይገባል።16 AHAmh 30.1