የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ስድሳ አምስት—የወደፊት ስንቅ
የቤት ባለቤት መሆንና ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ ከአባካኝነት ልማድ ጋር ሲነጻጸር፡- ወንድምና እህት ቢ(B) የቆጣቢነትን ትምህርት አልተማሩም…. [የሚያገኙት ገንዘብ] ምንም ያህል ብዙ ቢሆን ሁሉንም ይጠቀሙበታል። እስከሚያልቅ ድረስ ደስ ይሰኙበታል፤ ችግር በላያቸው ሲወድቅ ግን የተዘጋጁ አይደሉም…. ወንድምና እህት ቢ ቆጣቢ ሥራ አስኪያጆች ቢሆኑና እራሳቸውን ቢቆጣጠሩ ኖሮ የራሳቸውን ቤት በገነቡ፣ በተጨማሪም በመከራ ጊዜ ሊያወጡትና ሊጠቀሙበት የሚችሉት ተቀማጭ ገንዘብ በኖራቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ እራሳቸው ይደግፏቸው የነበሩትን ሰዎች ያህል እንኳ አይቆጥቡም። እነዚህን ትምህርቶች ለመማር ቸል ካሉ በእግዚአብሔር ቀን ባህርያቸው ፍጹም ሆኖ ሊገኝ አይችልም። 1 AHAmh 288.1
ይህ ምክር ሊጠቅማችሁ ይችላል፡- አልፎ አልፎ በአንድ ጊዜ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝላችሁ የንግድ ሥራ ላይ ቆይታችኋል። ትርፍ በቀላሉ ላይገኝባቸው የሚችሉትን ጊዜያት በማሰብ፣ ልትቆጥቡ ሲገባችሁ የምታስቧቸውን ፍላጎቶቻችሁን ሁሉ ለማርካት ተንቀሳቀሳችሁ። ምርጫችሁንና ፍላጎቶቻችሁን ትገቱ ዘንድ፤ ለወደፊቱ ስንቅ መቋጠር ትችሉ ዘንድ እግዚአብሔር የጣለባችሁን ኃላፊነት አንተና ሚስትህ ብታስተውሉት ኖሮ፣ አሁን ብቃት ባዳበራችሁ፣ ቤተሰባችሁም የኑሮ ምቾትን ባጣጣመ ነበር። መማር ያለባችሁ ትምህርት አለ…. ይህም ትንሿ ነገር ለብዙ ጊዜ እንድትቆይ (እንድትበረክት) ማድረግ ነው። AHAmh 288.2
በዘዴ መቆጠብ ለሚያስፈልገው ቤተሰብ፡- መቆጠብ እንደሚገባችሁ ብትቆጥቡ ኖሮ ለአስቸኳይ ሁኔታ የሚሆንና የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያግዝ የተቀመጠ ገንዘብ ይኖራችሁ ነበር። AHAmh 288.3
በየሣምንቱ የደሞዛችሁ ክፋይ መቀመጥ አለበት። በጣም ለሚያስፈልጋችሁ ወይም ለእግዚአብሔር በስጦታነት የሚመለስ ካልሆነ በቀር መነካት የለበትም።2 AHAmh 288.4
የምታገኙትን ገንዘብ በጥበብና በቁጠባ እየተጠቀማችሁበት ስላልሆነ ብትታመሙ ወይም ቤተሰባችሁን የሚደግፈው ገቢአችሁ ቢቆም፣ የቆጠባችሁት ስለሌለ ችግር ይገጥማችኋል። አጣብቂኝ ሁኔታዎች የምትወድቁበት አጋጣሚ ቢፈጠር ልትደገፉበት የምትችሉበት ነገር ሊኖራችሁ ይገባል። 3 AHAmh 288.5
ስለቁጠባ ሂሳቡ የተመከረ ሌላ ቤተሰብ፡- በህመም ጊዜ ካልሆነ በስተቀር የማትጠቀሙበት በሣምንት አምስት እስከ አስር የሚሆን ብር አጠራቅሙ። እያብቃቃችሁ ከምታገኙት ገቢ የተወሰነውን አስቀምጡ። በብልህ አስተዳደር ዕዳችሁን [ወጫችሁን] ከከፈላችሁ በኋላ ትንሽ ማስቀመጥ ትችላላችሁ። 4 AHAmh 288.6
በሣምንት ሃያ ብር የሚያገኝና ሁሉንም የሚጠቀምበት ቤተሰብ፤ በአንጻሩ ደግሞ ተመሳሳይ የቤተሰብ መጠን ያለው አሥራ ሁለት ብር በሣምንት የሚያገኝ ከዚያ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ብር የሚያጠራቅም ቤተሰብ አውቃለሁ። ይህ ሊሆን የቻለው አስፈላጊ የሚመስሉትን ሆኖም ሊተዉ የሚችሉትን ነገሮች ባለመግዛት ነው። 5 AHAmh 289.1
አግባብ ባለው ኑዛዜ ንብረታችሁን ከአደጋ ጠብቁ፡- የጌታ ንብረት ታማኝ አስተዳዳሪ የሆኑ እነርሱ የሥራቸውን ሁኔታ ያውቃሉ። ለድንገተኛ ጊዜም የተዘጋጁ ይሆናሉ። የዚህ ምድር ዘመናቸው በድንገት ቢያልቅ፣ ርስትና ንብረታቸውን እንዲረከቡ ለተጠሩት የተወሳሰበና ግራ የሚያጋባ ነገር ትተው አያልፉም። AHAmh 289.2
በጥሩ ጤና እያሉ ኑዛዜያቸውን ማሳወቅ ብዙዎች የተለማመዱት ጉዳይ አይደለም። ሆኖም ይህ ማስጠንቀቂያ በወንድሞቻችን ዘንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ሥራቸው በምን ሁኔታ እንዳለ ማወቅ አለባቸው፤ እንዲወሳሰብም መፍቀድ የለባቸውም። በማንኛውም ጊዜ ሊያልፉ እንደሚችሉ አስበው ሥራቸውን ማደራጀት አለባቸው። AHAmh 289.3
ኑዛዜዎች በህግ ፊት ሊቆሙና ሊያሸንፉ እንዲችሉ ተደርገው መፈጸም አለባቸው። ለጌታ ጉዳይ እንደ አስፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እርዳታ መለገስ እስከተቻለ ድረስ፣ ኑዛዜዎች ቢፈጸሙና ለረዥም ዓመታት ቢቀመጡም ጉዳት የለውም። ወንድሞች ሆይ ኑዛዜያችሁን ስላደረጋችሁ ሞት በአንድ ቀን ቀድሞ አይመጣም። በኑዛዜ ሀብታችሁን ለዘመዶቻችሁ ስታከፋፍሉ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዳትረሱ። የእርሱን ንብረት የያዛችሁ የእርሱ ወኪሎች ናችሁ። የእርሱን መጠይቅ ቅድሚያ ልትሰጡት ይገባል። ሚስትህና ልጆችህም ምስኪን እንደሆኑ ሊተዉ አይገባም። የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ለእነርሱም የወደፊት እቅድ ሊበጅላቸው ይገባል። ነገር ግን ልማድ ስለሆነ ብቻ የማያስፈልጋቸውን ዘመዶቻችሁን ሁሉ ሰብስባችሁ ረጅም ዝርዝር ይዛችሁ አትቅረቡ። 6 AHAmh 289.4
በሕይወት ሳላችሁ የእግዚአብሔርን ጉዳይ አስታውሱ፡- በሕይወት እያለ ገንዘቡን ሲያከማች ኖሮ ሲሞት ለሆነ በጎ አድራጎት ዓላማ የተወሰነ ገንዘብ ስለለገሰ(ስለተናዘዘ) ብቻ ማንም የክርስቶስን ሐሳብ ያሟላ እንዳይመስለው። 7 AHAmh 289.5
አንዳንዶች በሕይወት ዘመናቸው በስስት ገንዘባቸውን ቋጥረው ከኖሩ በኋላ ቸል ያሉትን ጉዳይ በማስታወስ በኑዛዜያቸው ሊያካክሱት ይሞክራሉ። ነገር ግን ትተውት የኖሩትን ዓላማ ለማሳካት ጥለውት ከሚሄዱት ሀብት ግማሹን ቢሰጡ እንኳን አይበቃም። AHAmh 289.6
ወንድሞችና እህቶች ሆይ ገንዘባችሁን ለራሳችሁ በሰማይ ባንክ ውስጥ አጠራቅሙ እንጂ የተሰጣችሁን የአስተዳዳሪነት ዕድል ለሌላ ትታችሁት አትለፉ። 8 AHAmh 289.7
የመጋቢነትን ሥራ ወደ ልጆች ማስተላለፍ ጥበብ የጎደለው ነው፦ ልጆቻቸው ለእግዚአብሔር ሥራ ከእነርሱ የተሻለ ፍላጎት ፍቅርና መሰጠት እንዳላቸው እርግጠኛ ማስረጃ ከሌላቸው በስተቀር፤ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሥራ ወደ ፊት ለመቀጠል ልባዊ ፍላጎትና ቅናት ያላቸው እርዳታ የሚያሰባስቡ ድርጅቶችም ወደ ፊት ይራመዱ ዘንድ በልግስና የሚሰጡ ካልሆኑ በስተቀር፤ እግዚአብሔር በእጃቸው ያስቀመጠውን ሀብትና ንብረት ለልጃቸው በማስተላለፍ አደራ የማለትን ጉዳይ ወላጆች በከፍተኛ ፍርሃት ሊመለከቱት ይገባል። ነገር ግን ብዙዎች ሀብታቸውን በልጆቻቸው እጅ ይተዋሉ፤ ሰይጣን እንዲያደርጉት ስለሚገፋፋቸው የራሳቸውን የመጋቢነት ኃላፊነት በልጆቻቸው ላይ በመጣል ትተውት ያልፋሉ። እንዲህም በማድረጋቸው የነበራቸው ንብረት በሰይጣን ጎራ እንዲሰለፍ ያደርጉታል። ለእግዚአብሔር ሥራ ዳር መድረስ የሚያስፈልገውን፤ እቅዱ በሙላት እንዲቀጥል የሚያደርገውን ንብረት በመውሰድ ሰይጣን ለራሱ ዓላማ እንዲስማማ አድርጎ ይጠቀምበታል። 9 AHAmh 289.8
የተከማቸ ሀብት መርገም፦ ገንዘብን ለማከማቸት አስበው ሀብት የሚሰበስቡ እነርሱ ለልጆቻቸው መርገም ተትው ያልፋሉ። ይህ የአባቶችና የእናቶች ድርጊት - እጅግ ከባድ ኃጢአት - ነፍስን የሚያጠፋ ኃጢአት ነው፤ ይህም መርገም ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ቂልነት በተሞላበት አባካኝነትና ልቅ በሆነ አኗኗር የወረሱትን ሀብት ጨርሰው ለማኞች ይሆናሉ። ያበላሹት የውርስ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ እንኳ በውል አያውቁትም። እናቶቻቸውና አባቶቻቸው የማከማቸት ሳይሆን የማካፈል መልካም ምሣሌ ቢሆኑላቸው ኖሮ መዝገብ በሰማይ ባስቀመጡ፣ በዚህ ዓለምም ሠላምና ደስታ፣ በወደፊቱም ሕይወት ዘለዓለማዊ ሀብት በወረሱ ነበር። 10 AHAmh 290.1