የአድቬንቲስት ቤት

64/88

ምዕራፍ ስድሳ ሦስት—ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉና ስለአጠቃቀሙ ልጆችን ማስተማር

ቀላል የዕለት ተዕለት ኑሮ ልምዶችን አስተምሩ፦ ወላጆች ልጆቻቸውን ራስን ስለ መግዛትና ከሚያምራቸው ነገር የመታቀብን ልማድ እያስተማሩና እያሠለጠኑ ሊያሳድጓቸው ይገባል። የእግዚአብሔርን ቃል የመታዘዝ ኃላፊነታቸውንና የሱስን ለማገልገል የመኖራቸውን ዓላማ ሁልጊዜ በፊታቸው ሊያቀርቡት ይገባቸዋል። ቀለል ባለ የአኗኗር ዘዴ የመኖርን አስፈላጊነት ልጆቻቸውን በማስተማር ውድ ልብስ፣ ውድ መብል፣ ውድ ቤቶችና ውድ የቤት ዕቃዎች መግዛት እንደማያስፈልጋቸው ይምከሯቸው። 1 AHAmh 281.1

ገና ሕፃን እያሉ ማንበብ፣ መጻፍ፣ ቁጥሮችን መረዳትና የራሳቸው መዝገብ እንዲኖራቸው መማር አለባቸው። ደረጃ በደረጃ በዚህ ሥራ እየጎለመሱ ወደ ፊት ይሄዳሉ። ከሁሉም ነገር በፊት ግን እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ እንደሆነ መማር ይኖርባቸዋል። 2 AHAmh 281.2

ወጣቱ ስለቤተሰብ ገንዘብ ተቆርቋሪ መሆን አለበት፦ ስለ ገንዘብ አጠቃቀም በተሳሳተ ማስተዋል ምክንያት ወጣቶች ለብዙ አደጋዎች ተጋልጠው ይገኛሉ። ወደ ሐሳባቸው የሚመጣውን እያንዳንዱን ፍላጎት ማሟላት የሚችል ምንጩ የማይደርቅ ገንዘብ ያለን ይመስል ልንሸከማቸውና እንደፈለጉ ገንዘብ ልንመዝላቸው አይገባንም። ገንዘብ የእርሱን ሥራ እንሠራበት ዘንድ፣ መንግሥቱን እንገነባለት ዘንድ በአደራ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ሥጦታ እንደሆነ ማሰብ አለብን። ወጣቶች ፍላጎቶቻቸውን መገደብ መማር አለባቸው። 3 AHAmh 281.3

ፍላጎቶቻችሁን አታበራክቷቸው፤ በተለይም ለቤት ወጪዎች ያለው ገንዘብ ውስን ከሆነ ፍላጎቶቻችሁ የወላጆቻችሁን አቅም ያገናዘቡ ይሁኑ። ራስ-ወዳድ ላልሆነው ጥረታችሁ እግዚአብሔር እውቅና ይሰጣል፤ ያመሠግናችሁማል…. እጅግ ትንሽ በሆነው ነገር ሁሉ ታማኞች ሁኑ። ከዚያም ታላላቅ ኃላፊነቶችን ቸል የማለት አደጋ አይገጥማችሁም። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው።” 4 AHAmh 281.4

የገንዘብን ዋጋ አስተምሩ፦ ምንም ሳይለፉበት ወደ ወጣቶች የሚደርሰው ገንዘብ ዋጋ አይሰጠውም። ብዙዎች ገንዘብን በችግርና በብዙ ድካም ያገኙታል። የሚያጠፉት ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ የሚገባቸው፤ ልብሳቸውና ምግባቸው ምን ያህል እንደሚያወጣ፣ ቤት ለመግዛት ስንት እንደሚያስፈልግ የሚያውቁ ወጣቶች ምን ያህል ከአደጋ የተጠበቁ ናቸው! AHAmh 281.5

ልጆች ለራሳቸው ገንዘብ ማግኘት የሚችሉባቸውና የራሱን ሕይወት አሳልፎ ለሰጣቸው የሱስ የምሥጋና ሥጦታ ማምጣት የሚያስችሏቸው ብዙ መንገዶች አሉ….ልምድ በሌለው አዕምሮአቸው እንደፈለጉ ከማጥፋት ይታቀቡ ዘንድ፣ ያገኙት ገንዘብ የእነርሱ እንዳልሆነ በማሳየት በብልሃት እንዲጠቀሙበትና ለአገልግሎት ሥራም እንዲያውሉት ሊማሩ ይገባቸዋል። ከእናታቸው ወይም ከአባታቸው ገንዘብ በመውሰድ የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ በሥጦታነት ወደ ጌታ ጎተራ ማስገባት እርካታ ሊሰጣቸው አይገባም። ለራሳቸው እንዲህ ይበሉ “ምንም ዋጋ ያልከፈልሁበትን በስጦታነት ልስጥ?” AHAmh 282.1

ለልጆች የሚለገስ ጥበብ የጎደለው ቸርነት የሚባል ነገር አለ። እየተከፈለላቸው ከተማሩት ይልቅ በኮሌጅ እየሠሩ የተማሩት ያገኙትን ዕድል የበለጠ ያገናዝባሉ፤ የከፈሉትን ዋጋ ያውቃሉና። እራሳቸውን መርዳት የማይችሉ በላያችን ላይ የተቀመጡ ጭነቶች እስኪሆኑብን ድረስ በአጉል የዋህነት ልጆቻችንን መሸከም የለብንም። 6 AHAmh 282.2

አንድ ወጣት አገልጋይ ወይም ሃኪም ለመሆን የሚያስችለውን የትምህርት ቤት ክፍያ ሠርቶ የማግኘት አካላዊ ብቃት እያለው፣ በሚያደክም ሆኖም ጠቃሚ በሆነ ሥራ ልምድ ሳያገኝ ገንዘብ በገፍ በመስጠት ቁጭ ብሎ እንዲማር በማድረግ ወላጆች ያለባቸውን ኃላፊነት በስህተት ይተገብሩታል። 7 AHAmh 282.3

ልጆች ለራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲሠሩ አበረታቷቸው፦ ከከተማ ውጪ የሚኖር ልጅ የአትክልት ሥፍራ አያያዝ የሚማርበት ትንሽ ቁራጭ መሬት ሊኖረው ይችላል። ሴቶችም ወንዶችም በዚህ ሥራ ሊሳተፉ ይችላሉ፤ በትክክል ከተማሩም የገንዘብን ዋጋና ቆጣቢነትን ያስተምራቸዋል። ለሚሲዮናዊ ሥራ ገንዘብ ከማጠራቀማቸው በተጨማሪ፣ ልጆች የራሳቸውን ልብሶች በመግዛት ሊያግዙ ይችላሉ፤ ይህን እንዲያደርጉ ሊበረታቱ ይገባቸዋል። 8 AHAmh 282.4

የገንዘብ ግድ-የለሽ አጠቃቀም እንዲቀንስ አበረታቱ፦ ኦ! ለቤት ውስጥ ሥራ ምንም ለማይጠቅሙ ቁሳቁሶች፣ በልብሳችን ላይ ለሚቀጠሉ ዘርፎችና ጌጣጌጦች፣ ለጣፋጭ ነገሮችና ለማያስፈልጉ ኮተቶች የምናወጣው ገንዘብ! ወላጆች ሆይ እራስን ለማስደሰት የእግዚአብሔርን ገንዘብ መጠቀም ስህተት እንደሆነ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው…. በሚችሉት ሁሉ ሳንቲማቸውን እንዲያጠራቅሙ ለአገልግሎት ሥራም እንዲያውሉት አበረታቷቸው። ራስን በመካድ የዳጎሰ ልምድ ያገኛሉ፤ እንደዚህ ዓይነቱ ትምህርት መጠንን ካለማወቅ ልማድ ይጠብቃቸዋል። 9 AHAmh 282.5

ልጆች የማይረቡና የማይጠቅሙ ጥቃቅን ነገሮችን በመግዛት ገንዘቡ ከእጃቸው እንዲጠፋ ከማድረግ ይልቅ ለሥጋዊ ፍላጎታቸው እምቢ በማለት ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ ሊማሩ ይገባል። ይህ ሥራ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ይተግበር። ብልሃትና ዘዴ ይጠይቃል፤ ሆኖም ልጆች ሊያገኙት ከሚችሉት እውቀት እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ትምህርት ነው። ሁሉም ህፃናት ስጦታቸውን ወደ ጌታ ቢያመጡ፣ ልግስናቸው አንድ ላይ ሲደባለቅና በቀጣይነት ሲፈስ ወደ ትልቅ ወንዝ የሚያድግ ጥቃቅን ጅረቶችን መፍጠር ይችላል። 10 AHAmh 282.6

ልጆች ስጦታቸውን ለእግዚአብሔር የሚያስቀምጡበት ትንሽ የገንዘብ ሳጥን ከምድጃችሁ አናት ላይ ባለ መደርደሪያ ወይም በሚታይ ሥፍራ ላይ አስቀምጡላቸው….ይህ ልምምድ ለእግዚአብሔር ያሠለጥናቸዋል። 11 AHAmh 283.1

ልጆችን አሥራትና ሥጦታ እንዲሰጡ አስተምሯቸው፦ ጌታ አሥራት የራሱ መሆኑን ብቻ ሳይሆን እንዴት መጠበቅ እንዳለበትም ይነግረናል። እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር ከፍሬህም ሁሉ በኩራት።” አሥራታችንን በታማኝነት የምንመልስ ብንሆንም እንኳ ገንዘባችንን ለራሳችን ካዋልነው በኋላ የተረፈውን ወደርሱ እንድናመጣ ይህ ቃል አያስተምረንም። የእግዚአብሔር ድርሻ መጀመሪያ ይለይ። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ስጦታ የተሰጠው ትዕዛዝ መርህ ለአሥራትም ያገለግላል “እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን ከናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደቀናው መጠን በቤቱ ያስቀምጥ።” ወላጆችም ልጆችም እዚህ ላይ ተካትተዋል። 12 AHAmh 283.2

አንዳንድ ጊዜ ሀብታም አባቶች የሚሠሯቸው ጥፋቶች፦ ልጅ የሚያልፍባቸው ሁኔታዎች ከወላጆቹ ምሣሌነት ይልቅ የበለጠ ተጽዕኖ ያሳርፉበታል። እራሳቸው በወጣትነታቸው ጊዜ የነበሩትን ዓይነት ልጆቻቸው እንዲሆኑ የሚፈልጉ፣ ካልተሳካላቸው ደግሞ የጊዜውን ብልሹነት የሚኮንኑ አንዳንድ ሀብታም አባቶች አሉ። እነርሱ ካለፉባቸው ዘመናት ጋር በሚመሳሰሉ ሁኔታዎች ልጆቻቸውም እንዲያልፉ ማድረግ ካልቻሉ በስተቀር፣ ያንን ዓይነት ባህርይ ልጆቻቸው ያንፀባርቁ ዘንድ የመጠበቅ መብት የላቸውም። አባትየው ያለፈበት ሁኔታ አሁን የሆነውን እንዲሆን አድርጎታል። በወጣትነት ዘመኑ በድህነት ተጨቁኖ በትጋትና በጽናት መሥራት ነበረበት። ባህርይው በጥብቅ የድህነት ትምህርት ቤት የተቀረጸ ነበር። ፍላጎቶቹ የተገደቡ፣ በሥራው ንቁና ምርጫዎቹም ቀላል ነበሩ፤ ምግብና አልባሳት ማግኘት ይችል ዘንድ የነበሩትን ክህሎቶቹን ሁሉ መጠቀም ነበረበት። ቆጣቢነትን መተግበር መለማመድ ነበረበት። አባቶች የሚለፉት እነርሱ ከጀመሩበት ልጆቻቸው እንዲጀምሩ ሳይሆን ሀብታም ከመሆን እንዲነሱ ነው። ይህ የተለመደ ስህተት ነው። አባቶቻቸው በተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸው ቢማሩባቸው ኖሮ ልጆቹም እንደ ወላጆቻቸው ጠቃሚ በሆኑ ነበር። አባቶች የልጆቻቸውን ሁኔታ ቀይረውታል። የአባቱ ጌታ ድህነት ነበር፤ አሁን የሀብት መትረፍረፍ ልጅየውን ከብቦታል። የሚፈልገው ነገር ሁሉ ይሟላለታል፤ የአባትየው ባህርይ የተቀረጸው በማያፈናፍን የቆጣቢነት መርህ ነበር፤ እያንዳንዱ ጥቃቅን መልካም ነገር ሁሉ ዋጋ ይሰጠው ነበር። የልጁ ባህርይና ልማድ የሚቀረጸው ያኔ በነበረው ሁኔታ ሳይሆን በአሁኑ ነው - በምቾትና በመሞላቀቅ.… ድሎት በሁሉም አቅጣጫ ሞልቶ ተትረፍርፎ እያለ እርሱ [ልጁ] እንዴት ይነፈገዋል? 13 AHAmh 283.3

የወላጆች ወደር የማይገኝለት ውርስ ለልጆች፡- ወላጆች ለልጆቻቸው ትተውላቸው የሚያልፉት ወደር የሌለው ቅርስ የጠቃሚ ሥራ እውቀትንና አድልኦ የሌለው ልግስናን ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሕይወት የገንዘብን ትክክለኛ ዋጋ ያሳያሉ። የገንዘብ ጠቀሜታው የራሳቸውንና የሌሎችን ሰዎች አስፈላጊ አቅርቦቶች ለማግኘትና የእግዚአብሔርን ዓላማ ወደ ፊት ለማራመድ ብቻ እንደሆነ በሚኖሩት ኑሮ ያረጋግጣሉ። 14 AHAmh 284.1