የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሃምሳ—ለወላጆች የሚገባቸው ክብር
የልጅ ባለዕዳነት ለወላጆች፦ በጨቅላነታቸው የተንከባከቧቸው፣ በሕመማቸው ያስታመሟቸው ናቸውና ልጆች፣ ወላጆቻቸው ባለውለታቸው እንደሆኑ ሊሰማቸው ይገባል። በእነርሱ ምክንያት ወላጆቻቸው በጭንቀት እንደተሰቃዩ ያስታውሱ። በተለይም ሁልጊዜ ንቁና እግዚአብሔርን የሚመስሉ እንደ ጌታ ፈቃድ የሚራመዱ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ትክክለኛውን መንገድ እንዲከተሉ ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። በልጆቻቸው ላይ የክፋት ሥራ ሲያዩ ልባቸው እንዴት ይከብድባቸው ይሆን! ለዚህ የልብ መጋኛ ምክንያት የሆኑ ልጆች ያካሄዳቸውን መዘዝ ቢያዩ ኖሮ በእርግጥ ይለሰልሱ ነበር። እናታቸው ስታነባ ቢያዩ፣ ስለእነርሱ ወደ እግዚአብሔር የምታደርሰውን ፀሎት ቢሰሙ፣ የተጨነቀውንና የተቆራረጠውን አተነፋፈስዋን ቢያዳምጡ ልባቸው ራርቶ ጥፋታቸውን በፍጥነት ተናዝዘው ይቅርታ በጠየቁ ነበር። 1 AHAmh 206.1
ልጆች ሲጎለምሱ ለመጥፎ ስሜትና ለርኩስ ልማድ ቦታ እንዳይሰጡ፣ በታማኝነት ለእነርሱ የለፋውን ወላጅ ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡታል። 2 AHAmh 206.2
ሁሉም ሊያከብሩት የተገባ ትዕዛዝ፦ “አባትኽንና እናትኽን አክብር። ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ በሚሰጥህ ምድር።” ይህ፣ ቃል የተገባለትን ተስፋ ያዘለ የመጀመሪያው ትዕዛዝ ነው። በሕፃንነት፣ በወጣትነት፣ በጎልማሳነትና በእርጅናም የሚተገበር ነው። በልጆች የሕይወት ዘመን ውስጥ፣ ወላጆቻቸውን ከማክበር ፈቀቅ ይሉ ዘንድ የተፈቀደላቸው ጊዜ የለም። ይህ ከባድ ግዴታ በወንዶችና በሴቶች ልጆች ላይ ጽኑ ነው፤ እግዚአብሔር ለታማኞች በሚሰጠው ምድር ላይ ዕድሜአቸው ይረዝም ዘንድ ማሟላት ካለባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ በቀላሉ የሚታይ ትኩረት የማያሻው ሳይሆን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ጉዳይ ነው። ተስፋው በመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ነው። ብትታዘዙ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝማል። አንታዘዝም ብትሉ በዚያች ምድር ላይ ዕድሜአችሁን ልታራዝሙ አትችሉም። 3 AHAmh 206.3
ለሌላ ለማንም ሰው የማይገባው የፍቅርና የአክብሮት ደረጃ ለወላጆች ይገባቸዋል። በአደራ የተሰጧቸውን ነፍሳት ይንከባከቡ ዘንድ ኃላፊነት የጣለባቸው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው። በሕፃንነት ዕድሜአቸው [ወላጆች] እርሱን ተክተውበእግዚአብሔር ቦታ ለልጆቻቸው እንዲቆሙ አዟቸዋል። የወላጆችን ትክክለኛ ሥልጣን የሚቃወም፣ የእግዚአብሔርን ሥልጣን እምቢ የሚል ነው። አምስተኛው ትዕዛዝ የሚጠይቀው ልጆች ለወላጆቻቸው ክብር እንዲሰጡ፣ እንዲሸነፉና እንዲታዘዙ ብቻ ሳይሆን ፍቅር እንዲሰጧቸውና ርኅራኄ እንዲለግሷቸው ነው። ጭንቀታቸውን እንዲያቃልሉላቸውና ክብራቸውን እንዲጠብቁላቸው፣ በሽምግልናቸው ዘመን እንዲረዷቸውና እንዲያጽናኗቸውም ጭምር ነው። 4 AHAmh 206.4
በቃሉ የተቀመጠውን ግልጽ ኃላፊነት የሚቃወሙትን፣ ለወላጆቻቸው ያለባቸውን ግዴታ የሚፃረሩትን እግዚአብሔር አያበለጽጋቸውም…. ምድራዊ ወላጆቻቸውን የማያከብሩና የሚያዋርዱ ከሆኑ፣ ፈጣሪያቸውን የሚወዱትና የሚያከብሩት ይሆኑ ዘንድ አይቻላቸውም። 5 AHAmh 207.1
ልጆች የማያምኑ ወላጆች በሚኖሯቸው ጊዜ፣ ትዕዛዞቻቸው ከክርስቶስ መጠይቆች ጋር የሚፃረሩ ከሆኑ፣ ምንም እንኳ የሚያቆስል ቢሆንም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ለሚመጣው ጣጣ እርሱን መታመን ይኖርባቸዋል። 6 AHAmh 207.2
ብዙዎች አምስተኛውን ትዕዛዝ አይጠብቁትም፦ በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት፣ ልጆች በአመፀኛነታቸውና ክብር ባለመስጠታቸው የታወቁ ሆነዋል። እግዚአብሔርም በተለየ ዕይታ አስተውሎታል፤ መጨረሻው እንደቀረበ የሚያመላክት ነው። ሰይጣን የወጣቱን አዕምሮ ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠረው ምንም እንዳልቀረው የሚያሳይ ነው። በብዙዎች ዘንድ የዕድሜ ባለፀጋነት ዋጋ የሚሰጠው አይደለም [በዕድሜ የሚበልጡንን አናከብርም]። 7 AHAmh 207.3
እውነቱን እንደሚያውቁ የሚመሠክሩ ግን የተገባቸውን ክብርና ፍቅር ለወላጆቻቸው የማይሰጡና ምንም ፍላጎት የማያሳዩ፤ የወላጆቻቸውን ፈቃድ ባለመከተል የሚያዋርዷቸውና ከጭንቀቶቻቸው እንዲገላገሉ የማድረግ ፍላጎት የሌላቸው ብዙዎች ናቸው። በርካታ ክርስቲያን ነን ባዮች “አባትኽንና እናትኽን አክብር” የተባለው ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፤ በመሆኑም “ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እግዚአብሔር አምላክኽ በሚሰጥኽ ምድር” የሚለውን የተስፋ ቃል በተመሳሳይ ሁኔታ ፍጹም አይረዱትም። 8 AHAmh 207.4
በዚህ አመፀኛ በሆነ ዘመን፣ በትክክለኛ መመሪያና ሥነ-ሥርዓት ያላደጉ ልጆች ለወላጆቻቸው ያለባቸውን ግዴታ የማያስተውሉ ናቸው። እንዲያውም ወላጆቻቸው የበለጠ ባደረጉላቸው ቁጥር፣ የባሰ ምሥጋና-ቢስና ወላጆቻቸውን የሚያዋርዱ ይሆናሉ። የሚፈልጉት ሁሉ የሚደረግላቸውና የሚሞላቀቁ ልጆች ያ ነገር ሁልጊዜ እንዲደረግላቸው ይጠብቃሉ። የሚፈልጉትም ካልሆነላቸው ተስፋ መቁረጥና ቅሬታ ይሰማቸዋል። ይህ ጠባያቸው ዕድሜ-ልካቸውን የሚያሳዩት ባህርይ ይሆናል። እራሳቸውን መርዳት የማይችሉ፤ ለእርዳታ በሌሎች ላይ የተደገፉ፤ ሌሎች ውለታ እንዲውሉላቸውና እንዲያጎበድዱላቸው የሚጠብቁ ይሆናሉ። ጎልማሳ ወንዶችና ሴቶች ሆነው እንኳ ተቃውሞ ከገጠማቸው የተጎሳቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው መስሎ ይሰማቸዋል። በመሆኑም የራሳቸውን ክብደት መሸከም ተስኗቸው በምሬትና በጭንቀት በምድር ይርመሰመሳሉ፤ ሁሉም ነገር ስለማይጥማቸው ሁልጊዜም የሚነጫነጩና የሚያጉረመርሙ ናቸው። 9 AHAmh 207.5
ውለታ-ቢስ ለሆኑ ልጆች በሰማይ ቦታ የለም፦ ሰይጣን የወጣቶችን አዕምሮ አሳውሮት የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ማስተዋል እንደተሳናቸው አይቻለሁ። አስተዋይነታቸው ደንዝዞ ለቅዱሱ ሐዋርያ ትዕዛዝ ቁብ አይሰጡም:- “ልጆች ለወላጆቻችሁ ታዘዙ በጌታችን ይህ የቀና ነውና። አባትህንና እናትህን አክብር። ከትዕዛዛቱ ይህች የመጀመሪያይቱ ናትና ከተስፋ ጋር የምትባል። መልካም እነዲሆንልህ ዕድሜህም እንዲረዝም በ[አዲሲቱ] ምድር ላይ።” AHAmh 208.1
“እናንት ልጆች ላባቶቻችሁ ታዘዙ በነገር ሁሉ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።” ወላጆቻቸውን የሚያዋርዱና የማይገዙላቸው፣ ምክራቸውንና ትዕዛዛቸውንም ቸል የሚሉ ልጆች አዲስ በምትሆነው ምድር ዕድል ፈንታ የላቸውም። አመጸኛ አልታዘዝም ባይና ምስጋና-ቢስ ለሆነ/ች ልጅ በነፃችው አዲሲትዋ ምድር ቦታ የላትም። እንደነዚህ ዓይነቶቹ መታዘዝንና መሸነፍን እዚህ ካልተማሩ መቸም አይማሩትም። የተዋጁት መኖሪያ በነዚህ አመፀኞች አልገዛ ባዮችና አፈንጋጮች የሚበላሽ አይሆንም። ማንም ትዕዛዝን የሚጥስ የሰማይን መንግሥት አይወርስም። 10 AHAmh 208.2
ፍቅር ሊታይና ሊገለጽ ይገባዋል፦ ፍቅርን የማያንፀባርቁ፤ የፍቅር መግለጫ ቃላት ድኃ የሆኑ፤ ሊሞገሱ ለተገባቸው ወላጆቻቸው ምንም ፍቅር የሌላቸው የሚመስሉ ልጆች አይቻለሁ። የእነርሱ ምርጫ ለሆኑት ጥቂት ሰዎች ግን የፍቅር ናዳ የሚያወርዱና የሚደባብሱ አሉ። ይህ እግዚአብሔር የሚወድደው ነው? የለም አይደለም። ሁሉንም የፍቅርና የፈገግታ ጮራዎች ወደ ቤት ክበብ አምጡ። ለነዚህ ጥቃቅን አድራጎቶቻችሁ አባታችሁና እናታችሁ አድናቆት ይቸሯችኋል። ቀንበራቸውን ለማቃለል መጣራችሁ፤ ነዝናዛነትንና ምሥጋና-ቢስነትን ለማስወገድ መልፋታችሁ፤ ለሰው የማታስቡ ግድየለሽ ልጆች እንዳልሆናችሁ ያሳያል። በዚያ ተስፋ-ቢስ በነበራችሁበት ጊዜ እራሳችሁን መርዳት በማትችሉበት የሕፃንነትና የልጅነት ዘመናችሁ ለተደረገላችሁ እንክብካቤና ፍቅር ምሥጋና እንደምትሰጡ ያስረዳል ። 11 AHAmh 208.3
ልጆች ሆይ የእናታችሁ መውደድ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ያለዚያ ደስታ-ቢስ ትሆናላችሁ። ልጆች ወላጆቻቸውን ሊወዱ፤ በመልካም ገጽታ ደስ በሚያሰኙ ቃላትና በልባዊ መተባበር ፍቅራቸውን ሊያሳዩ፤ አባታቸውን በውጭ፣ እናታቸውን በቤት ውስጥ ሊረዱ የተገባቸው አይደሉምን? 12 AHAmh 208.4
ሥራዎች ለክርስቶስ እንደተሠሩ ተደርገው መታሰብ አለባቸው፦በእውነት ከተለወጣችሁ፣ የየሱስ ልጆች ከሆናችሁ፣ ወላጆቻችሁን የምታከብሩ ትሆናላችሁ። ሥሩ ያሏችሁን መተግበር ብቻ ሳይሆን ልትረዷቸው የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች ትፈልጋላችሁ። ይህንን በማድረጋችሁ ለየሱስ እየሠራችሁ ነው። እነዚህ እንክብካቤዎችና አሳቢነት የሚታይባቸው አድራጎቶች፣ ለእርሱ ለራሱ እንደተደረጉለት ይቆጥራቸዋል። ይህ ወደር የማይገኝለት እጅግ አስፈላጊ ሚሲዮናዊ ሥራ ነው። እነዚህን ጥቃቅን የዕለት ተዕለት ተግባራት በታማኝነት የሚያከናውኑ የከበረ ልምድ እያካበቱ ናቸው። 13 AHAmh 209.1