የተሟላ ኑሮ

105/201

የሰላም ሁሉ ምንጭ

በእውነት መንፈስ አማካይነት የሚገኝ ቀዋሚ ሰላም ምንጩ አንድ ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ ስለዚያ ሰላም ሲናገር እንዲህ አለ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፡28) ፡፡ በተጨማሪ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” የሚል ተስፋ ሰጥቶናል፡፤ (ዮሐንስ 14፡27) ፡፡ CLAmh 110.1

ይህን ሰላም ከእርሱ ተለይተን አንቀበልም፡፡ ሰላሙ በክርስቶስ ውስጥ ስለሚገኝ የምንታደለውም እርሱን ስንቀበል ነው፡፡ ክርስቶስ የሕይወት ምንጭ ነው፡፡ ብዙዎች የሚያስፈልጋቸው ስለእርሱ በሚገባ ማወቅ ነው፡፡ ሰውነታቸውን በሙሉ ለሰማያዊ አዳኝ እንዲያስረክቡ በትዕግሥት፤ በደግነት፤ በጥብቅ መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ መጨነቅ፣ መቅበዝበዝ፣ መታከት የሚወገደው በሕይወት ጨለማ ጓዳ ውስጥ የክርስቶስ የፍቅር ጮራ ሲያበራ ብቻ ነው፡፡ ያን ጊዜ ጤና፣ ብርታት የመንፈስ እረፍትና የአእምሮ ሰላም ይገኛል፡፡ CLAmh 110.2

በሥቃይ ዓለም ውስጥ እንኖራለን፡፡ ወደ ሰማይ ቤት እስክንደርስ በመንገዳችን ላይ መከራ፤ እንቅፋት፤ ፈተናና ችግር ተደቅኖብናል፡፡ ግን ችግርን በማሰላሰል የኑሮን ትግል ሁለት ዕጽፍ የሚያከብዱ አሉ፡፡ ችግር ወይም እንቅፋት ሲያጋጥማቸው ለዘለዓለም የጠፉ፤ የእነርሱ ችግር ከሰው የሌለ፤ ከማይወጡበት ረግረግ የገቡ ይመስላቸዋል፡፡ CLAmh 110.3

ስለዚህ ራሳቸውን አጎሳቁለው በዙሪያቸው ለሚገኙ ሁሉ እንደ ጥላ ይከብዳሉ፡፡ ኑሮ ሸክም ይሆንባቸዋል፡፡ ግን እንዲህ መሆን የለበትም፡፡ ያደረሰባቸውን አስተሳሰብ ለመለወጥ ቆራጥ ጥረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይክበድ እንጂ ለውጥ መገኘቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ዓለም ሆነ በሚመጣው ዓለም ሊደሰቱ የሚችሉ መልካም መልካሙን ያሰቡ እንደሆን ብቻ ነው፡፡ በአሳባቸው ከፈጠሩት ጨለማ ዓይናቸውን አንስተው እግዚአብሔር ከፊታቸው በዘረጋላቸው ብርሃን አማካይነት ፍጻሜ የሌለውን የዘለዓለም ሕይወት ይመልከቱ፡፡ CLAmh 110.4

እግዚአብሔር ለማንኛውም ችግር መፍትሄ አዘጋጅቶአል፡፡ እሥራኤሎች በበረሃ ሲጓዙ መራ ከተባለቸው መራራ ውሃ ሲደርሱ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ምህላና ጸሎት አደረሰ፡፡ እግዚአብሔር አዲስ መፍትሄ አልፈጠረም፡፡ CLAmh 110.5

አስቀድሞ የነበረውን እንዲያስተውሉ አደረገ፡፡ እግዚአብሔር የፈጠራት ቅጠል በውኃው ውስጥ ብትጨመር መራራው ውኃ ለመጠጥ ተስማሚ ሆነ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የተጠሙት ሰዎች ከውኃው ጠጥተው ረኩ፡፡ ከልባችን ከፈለግነው ክርስቶስ ከማንኛውም ችግር ይገላግለናል፡፡ በቃሉ የተመዘገቡትን ተስፋዎች ለማስተዋል ዓይናችን ይገለጣል፡፡ ለሐዘን መጽናኛ የሆነው በረከት ሁሉ እንዴት ከሥራ ላይ እንደምናውል መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ CLAmh 111.1

በመላሳችን የምንቀምሰው መራራ ነገር ሁሉ ማጣፈጫ እንዳለው ይገባናል፡፡ CLAmh 111.2