የተሟላ ኑሮ

97/201

ውሃን በሚገባ መጠቀም

በጤናም ጊዜ ሆነ ሲታመሙ ውኃ አምላክ ከሰጠን በረከቶች ታላቁ ነው፡፡ በሚገባ ከተገለገሉበት ለጤና መድኅን ነው፡፡ የሰዎችንና የእንስሳትን ጥማት (ጥም) ለማርካት ከአምላክ ዘንድ የተሰጠ መጠጥ ነው፡፡ CLAmh 99.5

በነፃ ተጠጥቶ ለአካል ተፈላጊ የሆነውን ነገር ለማቅረብ፤ አካል በሽታን እንዲቋቋም ይረዳል፡፡ ውኃን ለንጽህና ማዋል (መታጠብ) የደምን መዘዋወር ከሚረዱት ነገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ በቀዝቃዛ ውሃ ገላን መታጠብ ለጡንቻዎች መፍታታት ዋና ነገር ነው፡፡ በሙቅ ውኃ መታጠብ ደግሞ የቆዳን ቀዳዳዎች ከፍቶ ከአካል ውስጥ ቆሻሻው እንዲጣራ ይረዳል፡፤ በሞቀ ወይም በቀዝቃዛ ውኃ መታጠብ ነርቮችን አነቃቅቶ የደምን መዘዋወር ያስተካክላል፡፡ CLAmh 99.6

ውኃ በሚገባ ሲሠራበት የሚሰጠውን ጥቅም በደንብ ስለማያውቁ ብዙዎች እንደ ጠላት ይፈሩታል፡፡ የውኃ ሕክምና የሚገባውን ያህል ተወዳጅነት አላገኘም፤ ከአገልግሎት ላይ ለማዋልም ብዙዎች ሊያሳዩት የማይፈልጉትን ትልቅ ጥረትና ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ግን ማንም ቢሆን ያን የሕክምና ዘዴ ባለማወቅ ወይም በቸልተኛነት አሳቦ ለመተው ምክንያት የለውም፡፡ በቤት ውስጥ በውኃ አማካይነት የሚሰጠውን ሕክምና ማንም ሊያውቀው ይገባል፤ በተለይ እናቶች ለጤነኛና ለበሽተኛ የቤተሰብ አባሎች እንዴት መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ሊያውቁ ይገባል፡፡ CLAmh 99.7