የተሟላ ኑሮ

52/201

የቤት መሥሪያ ቦታ መምረጥ

ብዙ ሰዎች ቤት ለመሥራት በሚዘጋጁበት ጊዜ ለአትክልትና ለአበባ መትከያ ያዘጋጃሉ፡፡ ያትክልቱ ቦታ ወይም መሰኮቱ የፀሐይ ብርሃን የሚያገኝ መሆን አለበት፤ ምንያቱም ያለሙቀት፣ ያለአየርና ያለ ፀሐይ ብርሃን ዕፅዋት በሕይወት ሊኖሩና ሊለመልሙ አይችሉም፡፡ ለዕፅዋት ሕይወት እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ከሆኑ ለእኛ፣ ለቤተሰባችንና ለእንግዶቻችን ምን ያህል አስፈላጊ ይሆኑ፡፡ CLAmh 51.3

ቤታችን የጤናና የደስታ ቤት እንዲሆን ከፈለግን ከቆሻሻ ቦታ እርቀን መሥራትና እግዚአብሄር የሰጠን የሕይወት ደጋፊዎች ያላንዳች ችግር የሚገቡበት መሆን አለበት፡፡ ወፍራም መጋረጃ አለማድረግ፣ መስኮትንና መጋረጃዎችን መክፈት፣ መስኮትን እንዳይጋርድና የፀሐይን ብርሃን ከመግባት እንዳያግድ በመስኮት አጠገብ አትክልት ወይም ዛፍ መኖር የለበትም፡፡ የፀሐይ ብርሃን የመጋረጃዎችንና የምንጣፎችን ቀለም ያደበዝዝ ይሆናል፤ ነገር ግን የልጆች ጉንጭ በጤንነት እንዲያንጸባርቅ ያደርጋል፡፡ CLAmh 51.4

ለሽማግሌዎች የሚጠነቀቁ ሁሉ ሙቀት ያለበት ምቹ ክፍል እንደሚያሻቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ዕድሜ እንደገፋ መጠን በሽታን የሚከላከል ኃይል ስለሚቀንስ ብዙ የጸሐይ ብርሃንና ንጹሕ አየር በበለጠ ያስፈልጋል፡፡ CLAmh 51.5

ለአእምሮና ለአካል ጤንነት ንጽህና እጅግ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ቆሻሻ ከሰውነታችን በቆዳ በኩል ዘወትር ይወጣል፡፡ ቀዳ በንጽህና ካልተያዘ በስተቀር በሚሊዮን የሚቆጠሩት ቀዳዶች ቶሎ ስለሚዘጉ በእነዚህ ቀዳዳዎች መውጣት የሚገባው ቆሻሻ ለሌላ የቆሻሻ ማጣሪያ ብልቶች ተጨማሪ ሸክም ይሆናል፡፡ CLAmh 51.6

ብዙ ሰዎች በየቀኑ ጥዋት ወይም ማታ በቀዝቃዛ ወይም ለብ ባለ ውሃ በመታጠብ ይጠቀማሉ፡፡ ገላን መታጠብ ጉንፋን ከማስያዝ ፈንታ ጉንፋንን ይከላከላል፤ ምክንያቱም የደምን መዘዋወር ስለሚያሻሽል ነው፡፤ ደም ወደ ቆዳ ይመጣና ያላንዳች ችግር ይዘዋወራል፡፡ አእምሮና አካል ይነቃቃሉ፡፡ ሥጋችን በቀላሉ ለመኮማተርና ለመዘርጋት ይችላል፤ አእምሮም ይነቃል፡፡ መታጠብ የስሜት ስሮችን (ነርቮችን) ያረጋጋል፡፡ ገላን መታጠብ አንጀትን፣ ጨጓራንና ጉበትን ጤናና ኃይል እንዲያገኙ ይረዳል፤ ምግብም በቀላሉ እንዲፈጭ ያደርጋል፡፡ CLAmh 52.1

ልብስ በንጽሕና መያዝ አለበት፡፡ በቆዳ ቀዳዳዎች የሚወጣው እድፍ በልብስ ላይ ይጣበቃል፤ ልብስ በየጊዜው ካልተለወጠና ካልታጠበ ቆሻሻው እንደገና በሰውነት ይመጠጣል፡፡ CLAmh 52.2

ማንኛውም ዓይነት የንጽሕና ጉድለት ሕመምን ያስከትላል፡፡ የሕይወት ጠላት የሆኑት ጀርሞች የሚኖሩት በጨለማ ቦታ በበሰበሰ ቆሻሻና እርጥበት ባለበት ቦታ ነው፡፡ ቆሻሻ አትክልት ወይም ቅጠል በቤት አጠገብ እንዳይበሰብስና አየሩን እንዳይመርዘው ማድረግ ነው፡፡ በቤት ውስጥ ምንም ዓይነት ቆሻሻ መኖር የለበትም፡፡ ፍጹም ጤንነት ይገኝባቸዋል በሚባሉት ከተማዎች ውስጥ የሚነሳ ወረርሽኝ መነሻው በአንዳንድ ግድ የለሽ ሰዎች ቤት አጠገብ ከሚገኝ የበሰበሰ ቆሻሻ መሆኑ ታውቋል፡፡ CLAmh 52.3

ከሕመም ነፃ ለመሆን፣ ተደሳችና ኃይል ለማግኘት የአካል ንጽሕና፤ ብዙ የፀሐይ ብርሃንና የቤት ንጽሕና አስፈላጊ ናቸው፡፡ CLAmh 52.4