የተሟላ ኑሮ

32/201

በትንንሽ ነገር መደሰት

እናቶች ልጆቻቸው ድጋፍ ፈላጊና ራሳቸውን ብቻ ወዳጆች ብቻ እንዳይሆኑባቸው መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ልጆች ከሁሉ የበለጡ ሆነው እንዳይሰማቸው መጠንቀቅ ያሻል፡፡ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያጫውቱ ሁሉን ነገር ራሳቸው ያደርጉላቸዋል፤ ልጆች የተፈጥሮ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ራሳቸውን ችለው መጫወት አለባቸው፡፡ ይህ የሆነ እንደሆን በትንሽ ነገር መደሰትን ይማራሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ችግር እንዴት በድፍረት መጋፈጥ እንደሚገባቸው መማር አለባቸው፡፡ በሚደርስባቸው ትንንሽ ጉዳት ሁሉ በመደናገጥ ፈንታ እያንዳንዱን ችግር ችላ ለማለት እንዲችሉ ማስተማር ነው፡፡ ልጆች ለሌሎች አሳቢዎች የሚሆኑበትን መንገድ ማሳየት ይገባል፡፡ CLAmh 33.1

ልጆች እንደተናቁ እንዳይሰማቸው፡፡ ሥራ ስለሚበዛባቸው አንዳንድ ጊዜ እናቶች ልጆቻቸውን ለማስተማርና ፍቅርና ርኅራኄያቸውን ለመግለጽ ምንም ጊዜ የላቸውም፡፡ ልጆች አስፈላጊያቸው የሆነውን ርኅራኄና ጓደኝነት ከወላጆቻቸው ወይም ከቤተሰባቸው ካላገኙ ወደ ሌላ ቦታ ፍለጋ መሔዳቸው እደማይቀር ወላጆች መርሳት አይገባቸውም፡፡ ፍቅርና ጓደኝነት ፍለጋ የሚሔዱበትም ቦታ አእምሯቸውንና ጠባያቸውን የሚያበላሽ ሊሆን ይችላል፡፡ CLAmh 33.2

ጊዜ በማጣትም ሆነ ባለማሰብ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን እንደሚገባ አያስደስቱም፡፡ በዚህ ፈንታ ዓይናቸው እስኪፈዝና እጃቸው እስኪዝል ድረስ ለልጆቻቸው የገንዘብ አባካኝነታቸው ምሳሌ የሆነውን ጌጣ-ጌጥ ይሠራሉ፡፡ ልጆቹ ለአቅመ ሔዋና ለአቅመ አዳም ሲደርሱ የዚህ ዓይነት ትምህርት የዕብሪትና የሞራል ውድቀት ፍሬ ያፈራል፡፡ በዚህ ጊዜ እናቲቱ በልጆችዋ መበላሸት ታዝናለች እንጂ ራስዋ የዘራቸው ዘር ፍሬ መሆኑን አትገነዘብም፡፡ CLAmh 33.3

አንዳንድ እናቶች ልጅ አስተዳደጋቸው ሥርዓት የለውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ልጆቻቸው ጉዳት እስኪያገኛቸው ድረስ ስድ ይሰዷቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የሚያስደስታቸውን ነገር እንኳን እንዳያደርጉ ይከለክሏቸዋል፡፡ እንደዚህ በሚያደርጉበት ጊዜ የክርስቶስን ምሳሌነት አይከተሉም፡፡ እርሱ ሕጻናትን ወደደ፤ ስሜታቸው አስተዋለ፤ በደስታቸውም ሆነ በችግራቸው ጊዜ አዘነላቸው፡፡ CLAmh 33.4

አባትዮው ወይም ባልዮው የቤተሰቡ መሪ ነው፡፡ ሚስቱ ፍቅሩንና ርኅራኄውን እንደዚሁም ልጆቹን በማስተማር እንዲረዳት ትመኛለች፤ ይህም ተገቢ ነገር ነው፡፡ ልጆቹ የሱም ጭምር እንደመሆናቸው መጠን የእነርሱ ደህንነት ሊያስደስተው ይገባል፡፡ ልጆቹ የርሱን ርዳታና መሪነት ይፈልጋሉ፤ እርሱም ልጆቹን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት እንዲችል ስለ ሕይወት ትክክለኛ አስተያያት ሊኖረው፤ ለቤተሰቡ ጥሩ ጓደኞች ሊመርጥ፤ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ፍቅርና ፍርሃት በቃም የሚመራ መሆን አለበት፡፡ CLAmh 34.1