የተሟላ ኑሮ

193/201

የንፁህ አሳብ ኃይል

የንፁህ አሳብን ጠቃሚነት መገንዘብ ያሻናል፡፡ ማንንም ሰው የሚያዋጣው ትክክለኛ አስተሳሰቡ ነው፡፡ “በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፡፡” (ምሳሌ 23፡7) ራስን መቆጣጠር የሚበረታው በልምድ ነው፡፡ መጀመሪያ ከባድ የመሰለው ሲደጋገም እየቀለለ ይሄድና ትክክለኛ አስተሳሰብና የቀና ሥራ እንደ ልምድ ይሆናል፡፡ CLAmh 205.5

ከፈቀድን መናኛውንና ርካሽን ትተን ክቡር የሆነውን ነገር ልንጨብጥ እንችላለን፡፡ በሰዎች ዘንድ የተከበርን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድን ልንሆን እንችላለን፡፡ CLAmh 205.6

ስለሌሎች መልካም የመናገር ልምድ ይኑራችሁ፡፡ አብራችሁ የምትኖሯቸውን ሰዎች መልካሙን ሥራቸውን በበለጠ ተገንዘቡ፡፡ ጉድለታቸውን አታጋንኑባቸው፡፡ CLAmh 205.7

አንድ ሰው የሠራውን መጥፎ ሥራ ለመንቀፍ ሲቃጣህ ያደረገውን ሌላ መልካም ነገር አመስግንለት፡፡ የአመስጋኝነት መንፈስ ይደርብህ፡፡ እግዚአብሔር ልጁን በመስጠት የገለጠልንን ፍቅሩን በመገንዘብ አመስግን፡፡ ተበድለን እያሉ መተከዙ አይበጅም፡፡ ለማመስገን እንድንችል እግዚአብሔር ፍቅሩንና ወደር የሌለውን ምህረቱን እንድንገነዘብ ይፈልጋል፡፡ CLAmh 206.1

እውነተኛ የእግዚአብሔር ሠራተኞች ነገር ለማንሳትና ለመጣል ጊዜ የላቸውም፡፡ የሌሎችን ስህተት በማውጣትና በማውረድ ጊዜአችንን ማባከን አይገባንም፡፡ CLAmh 206.2

ክፉ ንግግር በሁለት በኩል የሚጎዳ መርገም ነው፡፡ የበለጠ የሚጎዳው ግን ተናጋሪውን ነው፡፡ የጥልና የክርክር ዘር የሚዘራ የሞት ምርት ያፈሳል፡፡ የሌሎችን ስህተት መከታተል በተከታታዩ ጠባይ ክፋትን ያሳድርበታል፡፡ የሌሎችን ክፋት ስንከታተል ወይም ስንመለከት እኛም እንደ እነርሱ እንሆናለን፡፡ የክርስቶስን መልካም ህይወት ስንመለከት ደግሞ እርሱን እንመስላለን፡፡ ያሳየንን ከፍተኛ አርአያነት በመከተል ወደ አምላክ ፊት እስከምንቀርብ ድረስ ከፍ ከፍ እንላለን፡፡ ከክርስቶስ ጋር ግንኙነት ሲኖረን የሚመለከቱንን የሚመራ ብርሃን ከእርሱ ይሰጠናል፡፡ CLAmh 206.3