የተሟላ ኑሮ

177/201

በሌሎች ላይ ያለን ተሰሚነት

በሌሎች ዘንድ ያለንን ተሰሚነት የሚወስነው የራሳችን ጠባይና ሥራ ነው፡፡ የክርስቶስን የጸጋ ኃይል ለሌሎች ለማስረዳት ራሳችን መጀመሪያ በደንብ መረዳት አለብን፡፡ ሌሎችን ይድኑበት ዘንድ የምናስተምረው ወንጌል መጀመሪያ ራሳችን የዳንበት መሆን አለበት፡፡ CLAmh 189.3

በተጠራጣሪው ዓለም ዘንድ ተሰሚነት ሊኖረን የሚችለው ክርስቶስ የግል መድኃኒታችን መሆኑን ስናምን ብቻ ነው፡፡ CLAmh 189.4

ኃጥአንን ከደራሽ ጎርፍ ለማውጣት ካሰብን እግራችንን በሕንጻው በክርስቶስ ላይ አጽንተን ማቆም አለብን፡፡ የክርስትና አርማ በውጭ የሚታይ አይደለም፤ ግን አርማው የሰውን ኀብረት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገልጥ መሆን አለበት፡፡ CLAmh 189.5

በተለወጠው ጠባይ አማካኝነት በተገለጠው ጸጋ አማካኝነት አብ ወልድን ለዓለም አዳኝ አድርጎ መላኩን ዓለም ሁሉ መገንዘብ አለበት፡፡ ለራሴ ብቻ በማይል ኑሮ በኩል የሚገኘውን ተሰሚነት ያህል ማንም ሰው በሌሎች ላይ ተሰሚነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ CLAmh 189.6

ለወንጌል መልካምነት መረጃ ሊሆን የሚችል ከሁሉ የበለጠው ምስክር የሚወድና የሚወደድ ክርስቲያን ነው፡፡ CLAmh 189.7

የዚህ ዓይነት ኑሮ ለመኖር፤ ያን መሣይ ተሰሚነት ለማግኘት ጥረትን ፤ መሥዋዕትነትና በሥርዓት መመራትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ስለማይረዱ ብዙ ሰዎች በክርስትና ሕይወት ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን ለክርስቶስ ቀድሰው የሰጡ ሰዎች ከመቼውም ይልቅ እንቅፋት ሲያጋጥማቸው ሲደናገራቸው ሲያዩ ይደንቃቸዋል ያዝናሉም፡፡ CLAmh 190.1

ጠባያቸው የክርስቶስን ጠባይ እንዲመስል፤ ለጌታ ስራም ገጣሚ ሆነው እንዲገኙ ይጸልያሉ ፤ በተፈጥሮአቸው ያለውን ክፋት ሁሉ በሚገልጥ አጋጣሚ ላይ ያሉ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ በፊት ያልተገነዘቡት ስህተታቸው ቁልጭ ብሎ ይታያቸዋል፡፡ እንደ ጥንት እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከመራን እንዴት ይህ ሁሉ ነገር ይደርስብናል? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ CLAmh 190.2