የተሟላ ኑሮ
“ልታነጻኝ ትችላለህ”
ላየው ሁሉ ያስፈራራል፤ በሽታው የሚያስደነግጥ መልክ ስለሰጠው የፈራረሰውን ገላውን ማየት ይዘገንናል፡፡ እርሱን ያዩ ሁሉ በድንጋጤ ወደ ኋላቸው ወደቁ፡፡ ተደናገጡና ከእርሱ ለመሸሽ አንዱ በሌላው ላይ ወደቁ፡፡ አንዳንዶቹ ወደ የሱስ እንዳይቀርብ ሊያደርጉ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ ሊሰማቸው ወይም ሊያያቸው አልቻለም፡፡ የጥላቻ አስተያየታቸው አልተሰማውም፡፡ የሚያየው የእግዚአብሔርን ልጅ ብቻ፤ የሚሰማው ሕይወት ሰጪውን ድምፁን ብቻ ነበር፡፡ ከክርስቶስ እግር ተንበረከከና “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው፡፡ (ማቴዎስ 8፡2) ፡፡ CLAmh 151.1
የሱስም “ፈቃዴ ነው ንጻ” ብሎ እጁን ጫነበት፡፡ (ቁጥር 3) ፡፡ በፍጥነት በለምፃሙ ላይ ለውጥ ታየ፡፡ ደሙ ጤናማ፤ ሕዋሳቱ የነቁ፤ ጡንቻዎቹ ብርቱ ሆኑ፡፡ በለምፁ በሽታ ምክንያት ሊጥ የመሰለው ገላው የጥንቱ መልኩ ተመለሰለት፡፡ CLAmh 151.2
ገላው እንደ ሕጻን ገላ ወላንሳ ሆነለት፡፡ CLAmh 151.3
የለምጻሙን መፈወስ ካህናቱ ቢሰሙ ኖሮ አልተፈወሰም ብለው በሀሰት ይመሰክሩበት ነበር፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ለለምጻሙ ማን እንደፈወሰው እንዳይናገር አስጠንቀቀው፡፡ ግን ወዲያውኑ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ መሥዋዕት በማቅረብ ማንም ሳይሰማ ለካህናቱ ራሱን እንዲያስመረምር አዘዘው፡፡ CLAmh 151.4
ካህናቱ መሥዋዕቱን ከመቀበላቸው በፊት ለምጣሙን መርምረው መዳኑን መመስከር አለባቸው፡፡ CLAmh 151.5
ምርመራው ተከናወነ፡፡ ካህናቱ ከአገር እንዲወጣ ፈርደውበት የነበረውን ለምፃም መዳኑን መሰከሩለት፡፡ CLAmh 151.6
የዳነው ሰው ከዘመድ ከወዳጅ ከኅብረተሰብ ተቀላቀለ፡፡ የጤናን ክቡርነት በበለጠ ተረዳ፡፡ በብርታቱና ከቤተሰቡ ጋር እንደገና በመቀላቀሉ ከፍ ያለ ደስታ ተሰማው፡፡ የሱስ እንዳይናገር ቢያስጠነቅቀውም ማን እንደፈወሰው መሸሸግ አልቻለም፡፡ በደስታ የፈወሰውን ኃይልና ችሎታ እያመሰገነ አወጀ፡፡ CLAmh 151.7
ወደ የሱስ ሲቀርብ “ለምፃም” ነበር፤ የበሽታ ጠንቅ አካሉን በሙሉ አበስብሶት ነበር፡፡ ለምፃም የነካ እንደ ርኩስ ይቈጠር ስለነበር ደቀመዛሙርቱ የሱስ ለምፃሙን እንዳይነካ ለማድረግ ሳይሹ አልቀሩም፡፡ ግን የሱስ እጁን በለምፃሙ ላይ በመጫኑ አልረከሰም፡፡ ለምፁ ተወገደ፡፡ የኃጢአት ለምፅም ቢሆን እንደዚሁ ነው፡፡ ሥር የሰደደ፤ ለሞት የሚያደርስ በመሆኑ ሰብዓዊ ኃይል ሊያነፃው አይችልም፡፡ CLAmh 151.8
“ራስ ሁሉ ለሕመም፤ ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል፡፡ ከእግር ጫማ አንስቶ እስከራስ ድረስ ጤና የለውም፡፡ ቁስልና እበጥ የሚመግልም ነው፡፡ አልፈረጠም፤ አልተጠገነም፡፡ በዘይትም አልለዘበም፡፡” (ኢሳይያስ 1፡5፣6) ፡፡ የሱስ ግን ከሰብዓዊ ጋር ቢኖርም ኃጢአት አይነካውም፤ የእርሱ መገኘት ለኃጥአን ፈውስ ነው፡፡ “ጌታ ሆይ ብትወድ ልታነፃኝ ትችላለህ” ብሎ ከእግሩ ሥር የሚወድቅ ሁሉ “ፈቃዴ ነው ንፃ” የሚል መልስ ያገኛል፡፡ CLAmh 152.1
አንዳንድ ጊዜ የሱስ ሊፈወሱ የፈለጉትን ወዲውኑ አልፈወሳቸውም፡፡ ግን ለምፃሙን ልመናው ከአፉ ከመውጣቱ ፈወሰው፡፡ CLAmh 152.2
ምድራዊ በረከት እንድንቀበል ስንጸልይ መልሱ ይዘገይ ይሆናል፤ ወይም እግዚአብሔር የለመንነውን ትቶ ሌላ ይሰጠን ይሆናል፡፡ ግን ኃጢአታችን እንዲወገድልን ስንጸልይ እንደዚህ አይሆንም፡፡ ከኃጢአታችን ሊያነፃን፤ ልጆቹ ሊያደርገን፤ ቅዱስ ሕይወት እንድንኖር ሊያስችለን ፈቃዱ ነው፡፡ CLAmh 152.3
ክርስቶስ “ከዚህ ክፉ ዓለም ሊያድነን በአባታችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሱን ለወጠልን፡፡” “እንደፈቃዱ ብንለምነው እንደሚሰማን ማመን ያስፈልገናል፡፡ እንደሚሰማን ካመንን ደግሞ የለመንነውን ነገር እንደሚፈጸም እናውቃለን፡፡” (ገላትያ 1፡4፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፡14፣15) ፡፡ CLAmh 152.4
የሱስ ያዘኑትንና ተስፋ የቈረጡትን ተመለከተ፡፡ የልባቸው ተስፋ ጨልሞ፤ ምድራዊ ፍላጎታቸው መንፈሳዊ ብርታታቸውን አድክሞት ስላየ ሁሉንም ወደ እርሱ ቀርበው እንዲያርፉ ጋበዛቸው፡፡ CLAmh 152.5
ታታሪዎቹን ሰዎች “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፤ ሸክሜም ቀሊል ነውና” አላቸው፡፡ (ማቴዎስ 11፡29) ፡፡ CLAmh 152.6