ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ
ምዕራፍ 12 - ጥርጣሬን ማሸነፍ
ብዙዎች በተለይም በክርስትናቸው ገና ለጋ የሆኑ ሰዎች ከተጠራጣሪዎች በሚሰነዘሩ አስተያየቶች ይደነግጣሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊያብራሩዋቸው ይቅርና ሊያስተውሉዋቸው የማይችሉ ብዙ ነገሮች ያሉ ሲሆን ሰይጣን ደግሞ እነዚህን በመጠቀም ቅዱሳት መጻሕፍት ከእግዚአብሔር የተሰጡ መገለጦች እንደሆኑ ያላቸውን እምነት ሊናውጠው ይፈልጋል፡፡ እንዲህም በማለት ይጠይቃሉ፡- «ትክክለኛውን መንገድ የማውቀው እንዴት ነው; መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ ከእነዚህ ጥርጣሬዎች መላቀቅ የምችለው እንዴት ነው;» ክየመ 101.1
እግዚአብሔር እምነታችንን ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ሳይሰጠን እንድናምን ፈጽሞ አይጠይቀንም፡፡ ህልውናው፣ ባህሪይው፣ የቃሉ እውነተኛነት ለአእምሮአችን አጥጋቢ በሆኑ ምስክሮች ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የጥርጣሬ በሮችን ሁሉ አልዘጋም፡፡ እምነታችን በማስረጃዎች ላይ እንጂ በተገለጡ ነገሮች ላይ መመስረት የለበትም፡፡ መጠራጠር የሚፈልጉ ሰዎች አጋጣሚውን ያገኛሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እውነትን ለማወቅ ከልባቸው የሚመኙ ሰዎችም እምነታቸውን ለመመስረት በቂ ማስረጃ ያገኛሉ፡፡ ክየመ 101.2
ወሰን የለሽ የሆነውን ጌታ ባህሪይና ስራ ውስን በሆነው አእምሮአችን በሙላት ለማስተዋል መሞከር ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ የተማረና የረቀቀ እውቀት ካለው ሰብአዊ ፍጥረት እንኳን ሳይቀር እግዚአብሔር በምስጢር ካባ ተሸፍኖአል፡፡ «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክን ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?» ኢዮብ 11፡7-8፡፡ ክየመ 101.3
ጳውሎስ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- «የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።» ሮሜ 11፡33፡፡ «ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።» መዝ. 97፡2፡፡ ከእኛ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት፣ እንዲሁም ከድርጊቶቹ በስተጀርባ በሚገኘው መነሻ ምክንያት ውስጥ ፍቅርና ምህረት ወሰን ከሌለው ኃይል ጋር ተቆራኝተው እናያለን፡፡ ለእኛ ለማወቅ የሚጠቅመንን ያህል የእርሱን ዓላማዎች ለማስተዋል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ከዚያ ውጪ ስለሆነው ነገር ሁሉን ቻይ በሆኑት በጌታ ክንዶችና በፍቅር በተሞላው ልቡ ላይ ልንደገፍ ይገባናል፡፡ ክየመ 102.1
የእግዚአብሔር ቃል ልክ እንደ መለኮታዊ ደራሲው ውስን በሆኑት ፍጥረታት በሙላት ሊስተዋሉ የማይችሉ ሚስጢሮችን ይዞአል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የኃጢአት ወደ ዓለም መግባት፣ የክርስቶስ ስጋ መልበስ፣ ዳግም መወለድ፣ ትንሳኤ፣ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ርእሶች ለሰብአዊ ፍጡር አእምሮ ለማስረዳትም ሆነ በሙላት ለመረዳት የሚያዳግቱ ምስጢራት ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የአሰራሩን ምስጢር ማስተዋል ስላልቻልን፣ የእግዚአብሔርን ቃል የምንጠራጠርበት ምክንያት ሊሆነን አይችልም፡፡ በምድራዊው ህይወታችን በብዙ ምስጢራዊ ነገሮች ተከበናል፡፡ በጣም ትንሽ የምትመስለዋን ሕይወት፣ እጅግ ጠቢብ የተባለው ፈላስፋ እንኳን በሙላት ሊያብራራት አይችልም፡፡ በየቦታው ከማስተዋላችን በላይ የሆኑ አስደናቂ ነገሮች አሉ፡፡ ታዲያ በመንፈሳዊውስ ዓለም ከማስተዋላችን በላይ የሆኑ ነገሮችን በማግኘታችን ልንደነቅ ይገባልን; ችግሩ ያለው ደካማና ጠባብ ከሆነው ከሰው አእምሮ ነው፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ አማካኝነት ስለ መለኮታዊ ባሕርይው በቂ ማስረጃ ሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም የአሰራሩን ምስጢር በሙላት ስላልተረዳን ቃሉን ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ክየመ 102.2
ሐዋሪያው ጴጥሮስ ሲጽፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፡- «ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።» በማለት ይናገራል፡፡ 2 ጴጥ. 3፡16፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ለማስተዋል የሚቸግሩ ጥቅሶች ቃሉን የማያምኑት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም ነገር ግን የበለጠ በቃሉ ላይ መታመንን የሚጨምሩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር በቀላሉ የሚስተዋሉ ነገሮችን ብቻ ይዞ ቢሆን ኖሮ፣ የእግዚአብሔር ታላቅነት ግርማ ውስን በሆነው አእምሮአችን በቀላሉ ቢስተዋል ኖሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ ባልኖረው ነበር፡፡ የምስጢራት መኖር በራሱ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እምነትን ሊጭርልን ይገባል፡፡ ቀለል ባለና ለሰብአዊ ፍጡር ፍላጎት ፍጹም ገጣሚ በሆነ መልኩ እውነትን የሚገልጠው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የጠቢባንን አእምሮ ሲያስደንቅ፣ በምድራዊ እውቀት ብዙ ያልገፉትን ደግሞ የድነትን መንገድ ማስተዋል እንዲችሉ ያግዛቸዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ቀለል ተደርገው የተገለጹት እውነታዎች ከፍ ያሉና በሰው አእምሮ ሊስተዋሉ ከማይችሉ ርእሶች ጋር የተያያዙ ስለሆኑ የምንቀበላቸው እግዚአብሔር ራሱ ስለተናገራቸው ብቻ ነው፡፡ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስና በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ማመን እንዲደርስ በዚህም በእግዚአብሔር መንገድ ይድን ዘንድ ለእያንዳንዱ ነፍስ የድነት እቅድ በግልጽ ተቀምጦአል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ በቀላሉ ሊስተዋሉ ከሚችሉ እውነቶች ባሻገር የእግዚአብሔርን ክብር መሰወሪያ የሆኑና ለሰው አእምሮ ለማስተዋል የሚከብዱ ምስጢራት አሉ፡፡ እውነትን ፈላጊ ሰው ጠለቅ አድርጎ ቃሉን ሲያጠና እነዚህ ምስጢራት በህያው አምላክ ቃል ላይ ያለውን መታመን ይጨምሩለታል፡፡ እንደዚሁም ሰብአዊ አስተሳሰብ ሁሉ ለመለኮታዊው መረዳት እንዲንበረከክ ያደርጋሉ፡፡ ክየመ 103.1
የመጽሐፍ ቅዱስን ታላላቅ እውነቶች በሙላት ማስተዋል እንደማንችል መቀበል ማለት ውስን የሆነው አእምሮአችን ወሰን የለሹን በሙላት ሊይዘው እንዳልቻለ፣ ሰው ውስን በሆነው እውቀቱ ሁሉን አዋቂ የሆነውን ጌታ ዓላማ በሙላት መረዳት አለመቻሉን መቀበል ማለት ነው፡፡ ክየመ 104.1
የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት ሁሉ ማስተዋል ስላልቻሉ፣ ኃይማኖትን የሚክዱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንም አይቀበሉትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እናምናለን የሚሉ ሰዎች ሁሉም ከዚህ ችግር አያመልጡም፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- «ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤» ዕብ. 3፡ 12፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስተከተገለጡ ድረስ የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ መመርመርና «ወደ ጠለቀው የእግዚአብሔር ነገር» መግባት መልካም ነው፡፡ 1 ቆሮ. 2፡ 10፡፡ «ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።» ዘዳ. 29፡29፡፡ የመመርመርን ኃይል ማዳከም የሰይጣን ስራ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲያጠኑ በሰዎች ልብ ውስጥ ትእቢትን በመዝራት እያንዳንዱን ጥቅስ እነርሱን በሚያረካቸው ደረጃ ማብራራት ካልቻሉ ሽንፈት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል እንደማያስተውሉት አምኖ መቀበል ያሳፍራቸዋል፡፡ ያን እውነት እግዚአብሔር ለእነርሱ የሚገልጽበትን ጊዜ ለመጠበቅ ትእግስት የላቸውም፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍትን ለማስተዋል ሰብአዊ ጥበባቸው ብቻውን በቂ ይመስላቸዋል፡፡ ይህንንም ማድረግ ሲያቅታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ስልጣን ይክዳሉ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ የሚመስሉ ብዙ አስተምህሮዎችና መላምቶች ምንም አይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የላቸውም፤ እንዲያውም የቃሉን ጭብጥ የሚቃወሙ ናቸው፡፡ እነዚህም ነገሮች ለብዙ አእምሮዎች የጥርጣሬ ምንጭ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ምንጫቸው እግዚአብሔር ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር የተነገረውን ነገር ያጣመሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ስራዎቹ ሙሉ ማስተዋል በፍጡራን ዘንድ ማግኘት የሚቻል ቢሆን ኖሮ፣ ሌላ ተጨማሪ እውነት መረዳት፣ በእውቀት ማደግ እንዲሁም የአእምሮ መዳበር ባልኖሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ከሁሉ በላይ ባልሆነ ነበር፡፡ ሰውም የእውቀት ጣሪያ ላይ ደርሶ ከዚያ በላይ ማደግ ባልቻለ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን እግዚአብሔርን እናመስግነው! እግዚአብሔር ወሰን የሌለው አምላክ ነው፤ «የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና።» ቆላ. 2፡3፡፡ እናም ሰዎች ስለ እርሱ ጥበብ፣ መልካምነትና ኃይል ለዘላለም ይመረምራሉ፤ ይማራሉ፤ ነገር ግን አውቀው ሊጨርሱት አይችሉም፡፡ ክየመ 104.2
የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት ሁሉ ማስተዋል ስላልቻሉ ተጠራጣሪዎችና ኃይማኖትን የሚክዱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንም አይቀበሉትም፡፡
በዚህ ምድር ህይወታችንም ጭምር እግዚአብሔር የእውነቱን ብርሃን እየገለጠልን እንድንÕዝ ይፈልጋል፡፡ ይህ አይነቱ እውቀት የሚገኝበት መንገድ ደግሞ አንድ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተዋል የምንችለው ቃሉ በመጀመሪያ በተሰጠበት በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ነው፡፡ «በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።» «መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው።» 1 ቆሮ. 2፡11፣10፡፡ አዳኙ ለተከታዮቹ የሰጠው ተስፋ ደግሞ እንዲህ የሚል ነበር፡- «ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል … ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።» ዮሐ. 16፡ 13-14 ክየመ 106.1
የእግዚአብሔርን ቃል ማስተዋል የምንችለው ቃሉ በመጀመሪያ በተሰጠበት በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሰው የማገናዘብ ችሎታውን እንዲለማመድ ይፈልጋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ደግሞ ከሌላ የትኛውም ጥናት በላይ የአዕምሮን ችሎታ ያጠነክራል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማስተዋል ከፈለግን ለመማር በተዘጋጀ መንፈስ፣ ሕፃናት በወላጆቻቸው ላይ ባላቸው አይነት እምነት፣ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እየጠየቅን መቅረብ ያስፈልገናል፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል እንዲሁም ከእኛ ማስተዋል በላይ የሆነው ታላቅነቱ ራሳችንን እንድናዋርድና ቃሉንም በምንከፍትበት ጊዜ ልክ ወደ እርሱ መገኘት ውስጥ እንደምንገባ በመቁጠር በታላቅ አክብሮት እንድናጠናው ያነሳሳናል፡፡ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ስንቀርብ አእምሮአችን ከእርሱ በላይ ስልጣን ላለው አምላክ እውቅና መስጠት እንዲሁም ልባችን ለታላቁ አምላክ መስገድ አለበት፡፡ ክየመ 106.2
በአርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስተዋል የሚቸግሩ ብዙ የተሰወሩ ነገሮች ቢኖሩም ማስተዋልን ለማግኘት ከእግዚአብሔር ጥበብን ለሚጠይቁ ሁሉ እርሱ የሰጣቸው ዝግጁ ነው፡፡ ነገር ግን ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ቅዱሳት መጻሕፍትን በስህተት ለማስተዋል ወይም ደግሞ ለማጣመም ሁልጊዜ የተጋለጥን እንሆናለን፡፡ ምንም ትርፍ የሌላው እንዲያውም ጉዳት የሚያመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ አነባብ አይነት አለ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ያለ አክብሮትና ያለ ጸሎት ሲከፈት፣ አስተሳሰባችን በእግዚአብሔር ላይ ሳያነጣጥር ሴቀርና ከፈቃዱም ጋር ያልተስማማ ከሆነ፣ አእምሮአችን በጥርጣሬ ደመና ይከሰባል፡፡ በመሆኑም የዚህ አይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በውስጣችን ያለውን ጥርጣሬ የሰለጠ ያጠናክራል፡፡ ጠላት አስተሳሰባችንን ሰመቆጣጠር የተሳሳቱ ትርጉሞችን (መረዳትን) . ያቀርብልናል፡፡ ሰዎች ሰቃልና በተግባር ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ለመፍጠር በማይፈልጉበት ጊዜ ሁሉ፤ ምንም ያህል አንኳን ጥሩ የትምህርት ደረጃ ቢኖራቸውም ስላ ቃሉ ባላቸው ግንዛቤ የሳቱ ይሆናሉ፡፡ በእንደዚህ አይነት ሰዎች አስተምሮ ላይ መደገፍ አስተማማኝ አይሆንም፡፡ ስህተትን ፍለጋ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነሱ ሰዎች ምንም አይነት መንፈሳዊ መረዳት አያገኙም፡፡ በተዛባ አይታቸውም ብዙ የጥርጣሬ እና የአላማመን ምክንያቶችን ይደረድራሉ፡፡ ቀላልና ግልጽ የሆኑትን እውነቶች አንኳን ሳይቀር ማመን ይሳናቸዋል፡፡ ክየመ 107.1
ምንም እንካ ብንተሰውረውም ሆነ በአብዛኛው ያለማመንና የጥርጣሬ እውነተኛ ምንጭ የኃጢአት ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮዎችና መመሪያዎች በትእቢት በተወጠረውና በኃጢአት ፍቅር በተነደፈው ልብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ትእዛዛቱንም ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ስልጣን ለመጠራጠር ዝግጁዎች ናቸው፡፡ ወደ እውነት ለመድረስ፣ እውነትን ለማወቅ እውነተኛ መሻትና ለመታዘዝም ፈቃደኛ የሆነ ልብ ያስፈልገናል፡፡ በዚህ መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚቀርቡ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በቂ መረጃ ያገኛሉ፡፡ ለመዳን የሚያበቃቸውንም የቃሉን እውነት መረዳት ይችላሉ፡፡ ክየመ 107.2
ክርስቶስ እንዲህ በማለት ተናግሮአል፡- «በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ዮሐ. 17፡17፡፡ ስለማታስተውሉት ነገር ጥያቄ ከማብዛት ይልቅ፣ የበራላችሁን እውነት በደንብ አጢኑት፤ ያን ጊዜ የበለጠ ብርሃን ትቀበላላችሁ፡፡ በክርስቶስ ጸጋ በግልጽ ለተረዳችሁት እውነት ታዘዙ፤ ይህንን ስታደርጉ አሁን የምትጠራጠሩባቸውን ነገሮች የበለጠ ለማስተዋልና ለመታዘዝ ኃይል ታገኛላችሁ፡፡ ክየመ 108.1
በጣም ለተማረውም ሆነ ምንም ላልተማረው በእኩል የተሰጠ ማስረጃ አለ፡፡ ይሄውም የግል ተሞክሮ መረጃ ነው፡፡ እግዚአብሔር የቃሉን እውነታነት የተስፋውንም እርግጠኝነት ለራሳችን ሞክረን እንድናየው ያድመናል፡፡ እንዲህ ይለናል፡- «እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤» መዝ. 34፡8፡፡ በሌላ ሰው ቃል ላይ ከምንደገፍ ለራሳችን ቀምሰን ማየት አለብን፡፡ «ጠይቁ ይሰጣችኋል» ዮሐ. 16፡24 በማለት ያውጃል፡፡ የተስፋው ቃሎች ይፈጸማሉ፡፡ ሳይፈጸሙ የቀሩበት ጊዜ የለም፤ ለወደፊትም አይኖርም፡፡ ወደ ኢየሱስ ስንቀርብና በፍቅሩ ሙላት ስንደሰት ጥርጣሬያችንና ጨለማችን ሁሉ በመገኘቱ ብርሃን ይገፈፋሉ፡፡ ክየመ 108.2
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- «እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ … ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። …» ቆላ. 1፡ 13፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ሁሉ ደግሞ «እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ…» ዮሐ. 3፡33፡፡ እንዲህም ብሎ መመስከር ይችላል፡- «እርዳታ ፈልጌ ሳለ ኢየሱስን አገኘሁት፡፡ ፍላጎቶቼን ሁሉ አማDላልኝ፡፡ የነፍሴ ረሐብ በጥጋብ ተተካ፡፡ አሁን ለእኔ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ መገለጥ ነው፡፡ ለምን በክርስቶስ ታምናለህ; ብትሉኝ እርሱ ለእኔ መለኮታዊ አዳኜ ስለሆነ ነው፡፡ ለምን በመጽሐፍ ቅዱስን ታምናለህ; ብትሉኝ ለነፍሴ የእግዚአብሔር ድምጽ ሆኖ ስላገኘሁበት ነው፡፡» መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነና ክርስቶስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለራሳችን ምስክርነቱን ልናገኝ እንችላለን፡፡ በጥበብ የተቀነባበረ ውሸት እንደማናምን እናውቃለን፡፡ ጰጥሮስ ወንድሞቹን እንዲህ ይላቸዋል፡- «ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ።» 2 ጴጥ. 3፡ 18፡፡ የእግዚአብሔር ህዝቦች በጸጋ እያደጉ ሲሄዱ ስለ ቃሉ ተጨማሪ መረዳቶችን ማግኘታቸው በsሚነት የሚቀጥል ጉዳይ ይሆናል፡፡ አዲስ ብርሃንን እየተቀበሉ ይሄዳሉ፤ የተቀደሱትን እውነቶች ውበትም የበለጠ ያጤናሉ፡፡ ይህ በዘመናት መካከል በቤተክርስቲያን ታሪክ የታየ እውነት ሲሆን በዚህ ሁኔታም ይቀጥላል፡፡ «የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።» ምሳ. 4፡ 18፡፡ ክየመ 108.3
እግዚአብሔር የቃሉን እውነታነት የተስፋውንም እርግጠኝነት ለራሳችን ሞክረን እንድናየው ያድመናል፡፡
ወደፊት የምንወርሳትን ምድር በእምነት አሻገርን በማየት ከእውነት ምንጭ ጋር በመቆራኘት ልናገኝ የምችለውን የማስተዋል እድገት ከእግዚአብሔር እንጠይቅ፡፡ ዛሬ ግራ ያጋባን ነገር ሁሉ ያን ጊዜ በእግዚአብሔር እርዳታ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ አሁን ለመረዳት ላስቸገሩን ነገሮች ያን ጊዜ መግለጫ እናገኝላቸዋል፡፡ «ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።» 1 ቆሮ. 13፡12፡፡ ክየመ 109.1