ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ

22/27

ምዕራፍ 11 - የጸሎት በረከት

እግዚአብሔር በፈጠረው ተፈጥሮ፣ በቃሉ፣ እንዲሁም በፍቅር እንክብካቤውና በመንፈሱ አማካይነት በሚያሳድረው ተጽእኖ ይናገረናል፡፡ እነዚህ ግን በቂ አይደሉም፡፡ እኛ ደግሞ ልባችንን በፊቱ ማፍሰስ ያስፈልገናል፡፡ መንፈሳዊ ህይወትና ብርታት እንዲኖረን ከፈለግን፣ ከሰማያዊ አባታችን ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል፡፡ አሳባችን ወደ እርሱ ሊሳብ ይችል ይሆናል፤ ስለ እጁ ስራዎች፣ ስለ ምህረቱ፣ ስለባርኮቱ እናሰላስል ይሆናል፤ በዚህ ብቻ ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሙላት ተገናኝተናል ለማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ስለ አለንበት ትክክለኛ ሁኔታ ለእርሱ የምንናገረው ነገር ሊኖረን ይገባል፡፡ ክየመ 87.1

ለወዳጅ የልብን እንደሚያጫውቱ ጸሎትም ለእግዚአብሔር የልብን ማጫወት ነው፡፡ የምንጸልየው ስለ እኛ ሁኔታ ለእግዚአብሔር የሚያውቀውን መረጃ ለመስጠት ሳይሆን፣ እርሱን በልባችን ለመቀበል እንዲያግዘን ነው፡፡ ጸሎት እግዚአብሔርን ወደ እኛ አያወርደውም፤ ነገር ግን እኛን ወደ እርሱ ከፍ ያደርገናል፡፡ ክየመ 87.2

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው አስተማራቸው፡፡ እለታዊ ፍላጎታቸውን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዲያቀርቡና የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲጥሉት መራቸው፡፡ ልመናቸው እንደሚሰማ የሰጣቸው ዋስትና ለእኛም ጭምር ነው፡፡ ክየመ 87.3

ኢየሱስ ራሱ በሰዎች መካከል በኖረ ጊዜ ጸሎትን አዘውትሮ ተለማምዶአል፡፡ አዳኛችን ፍላጎቶቻችንንና ድካማችንን ተጋርቶ ስለነበር፣ ስራውን ለመስራትና ፈተናን ለመጋፈጥ እንዲችል አባቱ ጥንካሬ እንዲሰጠው ይለምን ነበር፡፡ እርሱ በሁሉ ነገር ምሳሌያችን ነው፡፡ «በሁሉ እንደእኛ የተፈተነ» ወንድማችን ሲሆን ምንም ኃጢአት የሌለበትና ስብዕናውም ለኃጢአት ጀርባውን የሰጠ ነበር፡፡ በኀጢአት በተሞላች ዓለም ውስጥ ያለውን ትግልና የነፍስ ስቃይ በትእግስት አልፎታል፡፡ ከለበሰው ሰብአዊ ተፈጥሮ የተነሳ ጸሎት ለእርሱ አስፈላጊና ደግሞም የበረከት ምንጭ ነበር፡፡ ከአባቱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ደስታና መጽናናትን ያገኝ ነበር፡፡ ታዲያ የሰው ልጆች አዳኝ ለሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ጸሎት እንዲህ ካስፈለገው፣ ደካማና ሟች ለሆኑት ኀጢአተኛ ፍጡራን ምን ያህል በበለጠ ብርቱና sሚ ጸሎት ያስፈልጋቸው ይሆን! ክየመ 88.1

ለወዳጅ የልብን እንደሚያጫውቱ፣ ጸሎትም ለእግዚአብሔር የልብን ማጫወት ነው፡፡

በሰማይ ያለው አባታችን የበረከቱን ሙላት በእኛ ላይ ሊያወርድ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ወሰን ከሌለው የፍቅር ምንጭ የፈለግነውን ያህል የመጠጣት መብት ተሰጥቶናል፡፡ ታዲያ ከዚህ የከበረ ዕድል አንጻር ሲታይ፣ በትንሹ መጸለያችን እንዴት የሚገርም ነው! እግዚአብሔር ከልጆቹ መካከል በጣም የደካማውን ሰው ልባዊ ጸሎት እንካDን ለመስማት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፍላጎቶቻችንን በእግዚአብሔር ዘንድ ለማቅረብ ብዙ ስንፍና ተጠናውቶናል፡፡ ወሰን በሌለው ፍቅር የተሞላው የእግዚአብሔር ልብ ከጠየቁት ወይም ከሚያስቡት ሁሉ በላይ ሊባርካቸው እጅግ Õጉቶ ሳለ፣ በትንሹ ብቻ ስለሚጸልዩትና እምነታቸውም ደካማ ስለሆነው ለፈተና ስለተጋለጡት፣ ምስኪንና ረዳተቢስ የሰው ልጆች መላእክት ምን ያስቡ ይሆን; መላእክት በእግዚአብሔር ፊት መስገድ ይወዳሉ፤ ወደ እርሱም መጠጋት ደስታቸው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግን እንደ ትልቅ ባርኮት ነው የሚቆጥሩት፤ እግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠው እርዳታ በጣም የሚያስፈልጋቸው ምድራዊ ልጆች ግን ያለ የእግዚአብሔር መንፈስ ብርሃንና፣ ያለ ጌታ አጀብ መንገዳቸውን በማድረግ የረኩ ይመስላሉ፡፡ ክየመ 88.2

መጸለይን ቸል የሚሉ ሁሉ የክፉው ጨለማ ይከብባቸዋል፡፡ የጠላት የፈተና ሹክሹክታ ወደ ኃጢአት ይመራቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ እግዚአብሔር በጸሎት ውስጥ ያስቀመጠውን በረከት ስላልተጠቀሙበት ነው፡፡ ጸሎት የሁሉን ቻይ አምላክ ወሰን የለሽ ሀብት የተከማቸበትን የሰማይ ግምጃ ቤት ለመክፈት የሚያስችል በእምነት እጅ ውስጥ የሚገኝ ቁልፍ ሆኖ ሳለ፣ ለምድን ነው የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለመጸለይ የሚሰንፉት; ያለ ጽኑ ጸሎትና በትጋት የተሞላ ንቃት በይበልጥ ግዴለሽ እየሆንንና ከትክክለኛው መስመር እየወጣን ለመሄድ እንዳረጋለን፡፡ ከሳሻችን ወደ ጸጋው ዙፋን ቀርበን ፈተናውን ለመssም የሚያስችለንን ጸጋና ኃይል እንዳናገኝ መንገዳችንን ሁልጊዜ ሊያጥርብን ይፈልጋል፡፡ ክየመ 89.1

እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንዲሰማና እንዲመልስ ስንጠባበቅ በቅድሚያ ልናሟላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛው ከእርሱ ዘንድ እርዳታ እንደሚያስፈልገን መረዳት ነው፡፡ #በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና$ (ኢሳ. 44፡3) በማለት አምላካችን ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚናፍቁ ሁሉ እንደሚረኩ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ አሰራር ልብ ክፍት ሊሆን ይገባል፤ አልያ የእግዚአብሔርን ባርኮት መለማመድ አይቻልም፡፡ ክየመ 89.2

በውስጣችን ያለው የጎዶሎነት ስሜት ራሱ እኛን በመወከል ከአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ጥሪውን በግልጽ መንገድ ያስተጋባል፡፡ እንደዚያም ቢሆን፤ እነዚህን የጎደሉንን ነገሮች ያሟላልን ዘንድ እግዚአብሔርን ልንፈልገው ይገባል፡፡ #ለምኑ ይሰጣችኋል$ #ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም;$ ማቴ. 7፡7፤ ሮሜ. 8፡32፡፡ ክየመ 90.1

ክፋትን በልባችን ከሰወርን፣ የሙጢኝ ያልነው የታወቀ ኀጢአት ካለ፣ እግዚአብሔር አይሰማንም፡፡ ስለ ኃጢአቱ የሚናዘዘውንና ራሱን የሚያዋርደውን ነፍስ ጸሎት ግን ጌታ ሁልጊዜ ይቀበላል፡፡ የምናውቃቸውን የተበላሹ ነገሮቻችንን ስናስተካክል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ልመናችንን እንደሚሰማ ልናምን እንችላለን፡፡ የእኛ መልካም ሥራ መቼም ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ እንድናገኝ አያደርገንም፡፡ የሚያድነን የክርስቶስ ብቃት ነው፤ የሚያነጻንም ደሙ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች የራሳችን አድርገን በመቀበል ረገድ ልንሰራው የሚገባን ስራ አለ፡፡ ክየመ 90.2

የብርቱ ጸሎት ሌላው ባሕርይ ደግሞ በእምነት የሚጸለይ መሆኑ ነው፡፡ #ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።$ (ዕብ. 11፡6)፡፡ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- #የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።$ (ማር. 11፡24)፡፡ እኛስ ጌታን እንደቃሉ እንቀበለዋለን; ክየመ 90.3

ቃል ኪዳኑ ሰፊና ወሰን የለሽ ነው፤ ቃል የገባውም የታመነ ነው፡፡ የጠየቅነውን ነገር፣ በጠየቅነው ጊዜ ማግኘት ሳንችል ብንቀር እንካD፣ ጌታ ጸሎታችንን እንደሰማና ደግሞም እንደሚመልሰው ማመናችንን መቀጠል አለብን፡፡ አርቀን የማናይና በቀላሉም የምንስት ከመሆናችን የተነሳ፣ አንዳንዴ ሊባርኩን የማይችሉ ነገሮችን እንጠይቃለን፡፡ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችን ለጸሎታችን መልስ አድርጎ በፍቅሩ የሚሰጠን፣ የነገሮችን ትክክለኛ ምንነት ማየት የምንችልበትን መለኮታዊ ማስተዋል ቢሰጠን ኖሮ የምንመርጠውን፣ እጅግ የሚጠቅመንን ነገር ብቻ ነው፡፡ ጸሎታችን ያልተመለሰ ሲመስለን፣ የሚመለስበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣልና፣ የተስፋውን ቃል ልንጠማጠም ይገባል፡፡ በጣም የሚያስፈልገንን ባርኮትም እንቀበላለን፡፡ በጸሎት እኛ የምንፈልገው ነገር ሁሉ በምንፈልገው መንገድ መልስ ያገኛል ብሎ ማሰብ አጉል ምኞት ነው፡፡ እግዚአብሔር ጥበቡ ጥልቅ ነውና አይሳሳትም፤ መልካምነቱም ታላቅ ነውና በቅንነት ለሚመላለሱት ምንም መልካም ነገር አያጎልባቸውም፡፡ እንግዲያውስ ለጸሎታችሁ አፋጣኝ ምላሽ ባታዩም እንካDን በእርሱ ለመታመን አትፍሩ፡፡ «ጠይቁ ይሰጣችኀDል» በሚለው የታመነው የተስፋ ቃሉ ተደገፉ፡፡ ከጥርጣሬያችንና ከፍርሃታችን ጋር ብንማከር፣ ወይም ያለእምነት በትክክል ልናያቸው የማንችላቸውን ነገሮች ሁሉ ለመፍታት ብንታገል፣ ጭንቀታችን እየጨመረና እየጠነከረ ከመሄድ ውጪ ሌላ የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡ ነገር ግን ረዳተቢስ እንደሆንንና ድጋፍ እንደሚያስፈልገን በመረዳት ራሳችንን በማዋረድ፣ እውቀቱ ወሰን ለሌለው፣ በፍጥረተ ዓለም ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ለሚያየው፣ በፈቃዱና በቃሉ ሁሉን ለሚያስተዳድረው ለእግዚአብሔር በእምነት የሚያስፈልገንን ነገር ብናቀርበው ጩኸታችንን ሊሰማ ይችላል፤ ደግሞም ይሰማል፤ በልባችንም ላይ ብርሃን ያበራል፡፡ ልባዊ በሆነ ጸሎት ወሰን የለሽ ከሆነው መለኮታዊ አእምሮ ጋር እንገናኛለን፡፡ የአዳኛችን ፊት በርህራሄና በፍቅር ወደ እኛ የዞረ ላይመስለን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ፊቱ ወደ እኛ ዞሮአል፡፡ የእጆቹ መዳሰስ ላይሰማን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በሃዘኔታና በፍቅር እጆቹን በእኛ ላይ ጣል አድርጎአል፡፡ ክየመ 90.4

ጸሎታችን ያልተመለሰ ሲመስለን፣ የሚመለስበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣልና፣ የተስፋውን ቃል ልንጠማጠም ይገባል፡፡

ከእግዚአብሔር ምህረትንና ባርኮትን ለመጠየቅ ስንቀርብ፣ በልባችን የፍቅርና የይቅርባይነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል፡፡ «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» በማለት እየጸለይን፣ ይቅር የማይል መንፈስ እንዴት ሊኖረን ይችላል; የእኛ ጸሎት እንዲሰማ የምንፈልግ ከሆነ እኛ ይቅር ለመባል በምንፈልገው መንገድና በዚያው መጠን ይቅር ልንል ይገባል፡፡ ክየመ 92.1

በትእግስት መጽናት በጸሎት ጠይቆ ለመቀበል ሌላው በቅድሚያ ልናሟላው የሚገባ ነገር ነው፡፡ በእምነትና በተሞክሮ ለማደግ ሁልጊዜ መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ «በጸሎት ጽኑ» (ሮሜ. 12፡ 12)፤ «በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ።» (ቆላ. 4፡2) ጴጥሮስ ደግሞ አማኞችን «በጸሎት ንቁ…» ይላል፡፡ (1ጴጥ. 4፡7) «በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።» (ፊል. 4፡6) በማለት ጳውሎስ ያዛል፡፡ ይሁዳ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- «እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።» ይሁዳ 20፣21፡፡ ሳያsርጡ መጸለይ ማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ ህይወት ወደ ህይወታችን እንዲፈስና ከእኛም ህይወት ደግሞ ንጽሕናና ቅድስና ወደ እርሱ መልሶ እንዲፈስ ከአምላክ ጋር ነፍስን ማቆራኘት ማለት ነው፡፡ ክየመ 92.2

በጸሎት መትጋት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ከማድረግ ምንም ነገር አያደናቅፋችሁ፡፡ በነፍሳችሁና በኢየሱስ መካከል ክፍት የሆነ የግንኙነት መስመር ዘወትር እንዲኖር በማድረግ የሚገባችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡ ጸሎት ወደ ሚደረግበት ስፍራ ለመሄድ እያንዳንዱን ዕድል ተጠቀሙበት፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ተግባራቸውን በታማኝት ለመፈጸምና ሊያገኙ የሚችሉትን ባርኮቶች በትጋትና በጉጉት ለመሰብሰብ ዝግጁዎች ሆነው በጸሎት ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ የሰማይ ብርሃን ጨረር ሊያገኙ ወደሚችሉበት ስፍራ ራሳቸውን ለማስቀመጥ የሚረዳቸውን ዕድል ይጠቀሙበታል፡፡ ክየመ 93.1

በነፍሳችሁና በኢየሱስ መካከል የማያቋርጥ የግንኙነት መስመር እንዲኖር በማድረግ የሚገባችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡

በቤተሰብ የጸሎት ጊዜ ሊኖረን ይገባል፤ ከሁሉም በላይ ግን በግል በስውር የምንጸልየውን ጸሎት ቸል ልንለው አይገባም፤ የነፍስ ህይወት ያለው በዚያ ነውና፡፡ ጸሎት ቸል ተብሎ ነፍሳችን ፈጽሞ ሊያብብ አይችልም፡፡ የቤተሰብ ወይም የጉባዔ ጸሎት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ለብቻችን በመሆን ሁሉን ለሚመረምሩት የእግዚአብሔር ዓይኖች ህይወታችንን መገላለጥ ያስፈልጋል፡፡ የምስጢር ጸሎታችን የሚሰማው ጸሎት ሰሚ በሆነው አምላክ ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ ያለውን የልብ ሸክም የትኛውም ለማወቅ የሚÕÕ ጆሮ ሊሰማው አይችልም፡፡ በስውር ጸሎት ነፍስ በዙሪያዋ ከከበባት ተጽእኖና ከስሜታዊነት ነጻ ትወጣለች፡፡ በእርጋታ፣ ግን በግለት እግዚአብሔርን መቅረብ ይቻላል፡፡ በስውር ያለውን ከሚያየውና ጆሮውም ከልብ የሚጸለየውን ጸሎት ለመስማት ልቡ ከተከፈተው አምላክ ጣፋጭና ለዘለቄታው ከእኛ ጋር የሚቆይ እርዳታ እናገኛለን፡፡ በዚህም ነፍስ ከሰይጣን ጋር ለምታደርገው ተጋድሎ የሚያጠነክራትና የሚያዘልቃትን ሰማያዊ የብርሃን ጨረር በእምነት ትሰበስባለች፡፡ እግዚአብሔር የጥንካሬያችን ምንጭ ነው፡፡ ክየመ 93.2

በÕዳችሁ ጸልዩ፤ ወደ ዕለት ተግባራችሁ ስትሰማሩም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ያለማsረጥ የሚያቀና ይሁን፡፡ ሔኖክ ከእግዚአብሔር ጋር የተራመደው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡ በስውር የምንጸልያቸው ጸሎቶች በእግዚአብሔር የጸጋ ዙፋን ፊት እንዳለው የከበረ እጣን ናቸው፡፡ ልቡ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘን ሰው ሰይጣን ሊያሸንፈው አይችልም፡፡ ክየመ 94.1

ለእግዚአብሔር ልመናችንን ለማቅረብ የማንችልበት ጊዜ ወይም ቦታ የለም፡፡ በእውነተኛ ጸሎት ልባችንን እንዳናፈስ የሚከለክለን ምንም ነገር የለም፡፡ በመንገድ ላይ ከተሰበሰበ ህዝብ መሃል ሆነን፣ ወይም በስራ ተጠምደን ባለንበት ሁኔታም ቢሆን ነህምያ በንጉስ አርጤክሰስ ፊት መጠይቁን ሲያቀርብ እንዳደረገው፣ እኛም እግዚአብሔር መለኮታዊ ምሪት እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን፡፡ በየትኛውም ቦታ ብንሆን በስውር የምንጸልይበትን ዕድል ልናገኝ እንችላለን፡፡ የልባችን በር ዘወትር የተከፈተና ኢየሱስም እንደ ሰማያዊ እንግዳ ሆኖ በነፍሳችን እንዲኖር ያለማsረጥ ልናድመው ይገባል፡፡ ክየመ 94.2

ምንም እንካDን ኃጢአት በበከለው ከባቢ አየር ውስጥ የምንኖር ብንሆንም ቆሻሻውን መተንፈስ ግን አያስፈልገንም፡፡ በሰማያዊው ከባቢ አየር ውስጥ መኖር እንችላለን፡፡ ልባዊ በሆነ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት (መገኘት) ራሳችንን ከፍ በማድረግ ወደ ምናባችን የሚመጡትን ርኩስ ነገሮችና በኃጢአት የተበከሉ አስተሳሰቦችን እንዳይገቡ በር መዝጋት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔርን እገዛና በረከት ለመቀበል የሚፈቅዱ ሁሉ፣ በቅድስና ከባቢ አየር ውስጥ ይመላለሳሉ፤ ከሰማይም ጋር sሚ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ክየመ 94.3

ስለ ኢየሱስ ልዩ የሆነ መረዳትና ስለ ዘላለማዊ እውነታዎች ዋጋ ሙሉ መረዳት ያስፈልገናል፡፡ የቅድስና ውበት የእግዚአብሔር ልጅን ልብ ሊሞላው ይገባል፡፡ ይህም ተግባራዊ እንዲሆን የሰማያዊ ነገሮች መለኮታዊ መገለጥ እንዲኖረን መጸለይ አለብን፡፡ ክየመ 95.1

ሰማያዊውን ከባቢ አየር መተንፈስ የሚያስችለውን መለኮታዊ ኃይል ከጌታ ለመቀበል እያንዳንዱ ነፍስ ወደ እርሱ መጠጋት አለበት፡፡ ወደ እግዚአብሔር በጣም ተጠግተን ስንኖርና ያልጠበቅነው መከራና አሳብ ሁሉ ሲመጣ፣ ልክ የሱፍ አበባ ወደ ጸሐይ ፊቱን እንደሚያዞር እኛም ወደ ሚረዳን ጌታ እንሮጣለን፡፡ ክየመ 95.2

ፍላጎታችሁን፣ ደስታችሁን፣ ሃዘናችሁን፣ ጭንቀታችሁን ወይም ፍርሃታችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡት፡፡ የማይችለውን ሸክም በእርሱ ላይ ልትጭኑበት አትችሉም፤ ልታደክሙትም አትችሉም፡፡ የራስ ጠጉራችሁን የቆጠረው እርሱ ስለ ልጆቹ ጉዳይ ፈጽሞ ግዴለሽ አይሆንም፡፡ «ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።» ያዕ. 5፡11፡፡ የፍቅር ልቡ በሰቆቃችንና ስለ ኀዘናችን በምንናገረው ነገር ይነካል፡፡ አእምሮአችሁን የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ፊት አቅርቡት፡፡ ለእርሱ ለመሸከም የሚከብደው ምንም ነገር የለም፤ ምክንያቱም ዓለማትን ሁሉ በእጁ ይዞአልና፤ በዩንቨርስ ውስጥ ያለውንም ሁሉ የሚያስተዳድረው እርሱ ነው፡፡ ለእኛ ሰላም የሚጠቅመውን ማንኛውንም ነገር ቸል ብሎ አያልፍም፡፡ ለእርሱ ለማንበብ የሚያስቸግረው የጨለመ የህይወት ምዕራፍ የለንም፤ እርሱ ሊያስወግደው የሚከብደው ጭንቀትም የለንም፡፡ የሰማይ አባታችን የማያየው ወይም የእርሱን ትኩረት የማይስብ ምንም አይነት መከራ ከልጆች መካከል ታናሽ በሆነው ላይ እንካD አይመጣም፤ ምንም አይነት ጭንቀት ነፍስን አያሰቃይም፤ እንዲሁም እርሱ የማያዳምጠውና ትኩረት የማይሰጠው አንድም እውነተኛ ጸሎት ከከንፈር አይወጣም፡፡ «ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል።» መዝ. 147፡3፡፡ በእግዚአብሔርና በእያንዳንዳD ነፍስ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የግል እና የጠበቀ ከመሆኑም ባሻገር ይህ ግንኙነት በምድር ላይ የእርሱ ጥበቃ የሚያስፈልጋት ነፍስ አንድ ብቻ እንኳን ብትሆን ጥበቃውን ለእርሷ ለመለገስና የሚወደውን አንድያ ልጁን ለእርሷ ደህንነት ሲል ለመስጠት የሚያስችል አይነት ነው፡፡ ክየመ 95.3

ኢየሱስ እንዲህ ብሎአል፡- #በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና።$ ፤ #እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።$ ዮሐ. 16፡26-27፤ 15፡16፡፡ በኢየሱስ ስም መጸለይ ማለት ግን በጸሎታችን መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ስሙን እየጠሩ ከመጸለይ ያለፈ ትርጉም አለው፡፡ የተስፋውን ቃል በማመን፣ በጸጋው ላይ በመደገፍና ስራውን በመስራት በኢየሱስ አእምሮና መንፈስ መጸለይ ማለት ነው፡፡ ክየመ 96.1

እግዚአብሔር እርሱን እናመልከው ዘንድ ከዓለም ውስጥ ወጥተን እንድንመነኩስ አሳቡ አይደለም፡፡ ሕይወታችን ልክ እንደ ኢየሱስ ሊሆንልን ይገባል፤ እርሱ ለጸሎት ወደ ተራራ ይወጣ ነበር፤ ለማገልገል ደግሞ ከህዝቡ ጋር ይቀላቀል ነበር፡፡ ከመጸለይ ውጪ ሌላ ምንም የማያደርግ ሰው ፈጥኖ መጸለዩን ይተዋል፤ ወይም ጸሎቱ ዘልማዳዊ ብቻ ይሆናል፡፡ ሰዎች ከማህበራዊ ህይወት ሲገለሉ፣ ከክርስትና ተግባርና መስቀልን ከመሸከም ሲሸሹ እንዲሁም ስለ እነርሱ ለተጋው ጌታ መትጋት ሲያቆሙ የጸሎትን ፍሬ ነገርና ለመጸለይ የሚያነቃቃቸውን ነገር ያጣሉ፡፡ ጸሎታቸው በራስወዳድነት የተሞላ ይሆናል፡፡ ስለ ሰብአዊ ፍጥረት ፍላጎት ወይም ስለ ክርስቶስ መንግስት መssም፣ ለመንግስቱም መስራት እንዲችሉ ኃይል ለመቀበል መጸለይ አይችሉም፡፡ ክየመ 96.2

በእግዚአብሔር አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ እርስ በርስ የመደፋፈርንና የመበረታታትን በረከት ቸል ስንል ለውድቀት እንዳረጋለን፡፡ የቃሉ እውነት በአእምሮአችን ውስጥ ግልጽነቱንና አስፈላጊነቱን ያጣል፡፡ ልባችን ቀዳሽ በሆነው ኃይል መነቃቃቱ ያቆማል፤ በመንፈሳዊ ህይወታችን ውድቀት ይገጥመናል፡፡ ከሌሎች ክርስትያኖች ጋር ባለን ግንኙነት ለሌሎች መራራት ባለመቻል ኪሳራ ያጋጥመናል፡፡ ራሱን ከሌሎች የሚያገል ሁሉ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ ባቀደው ዓላማ እየኖረ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ተፈጥሮአችንን በምናጎለብትበት ጊዜ ለሌሎች ሰዎች በመራራት እግዚአብሔርን ስናገለግል ጥንካሬ እንዲኖረን ያደርገናል፡፡ ክየመ 97.1

ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ጥሩ ግንኙነት ቢኖራቸውና የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሁም የመዳንን የከበሩ እውነቶች ቢነጋገሩ፣ የራሳቸው ልብ ይታደሳል፤ እርስ በርስም መተናነጽ ይችላሉ፡፡ በየዕለቱም ስለ ሰማያዊ አባታችን አዳዲስ መረዳቶችን እያገኘን እንሄዳለን፡፡ ስለ ፍቅሩም የመናገር ዝንባሌያችን ይጨምራል፡፡ ይህንንም ስናደርግ የራሳችን ልብ ይሞቃል፤ ደግሞም እንበረታታለን፡፡ ስለ ራሳችን ቀንሰን ስለ ኢየሱስ ብዙ ብናስብና ብናወራ የእርሱን ሀልዎት (መገኘት) አብዝተን እንለማመድ ነበር፡፡ ክየመ 97.2

እርሱ ለእኛ እንደሚጠነቀቀው ያህል እኛ እርሱን ብናስበው፣ ሁል ጊዜ እርሱን ባሰብነውና ከእርሱም ጋር ማውራትና እርሱን ማመስገን ደስታችን በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ትኩረታችንን በእነርሱ ላይ አሳርፈናልና ጊዜያዊ ስለሆኑ ነገሮች ስናወራ እንደመጣለን፡፡ ወዳጆቻችንን ስለምንወዳቸው ስለ እነርሱ መናገር ደስ ይለናል፡፡ ደስታችንንም ሆነ ሀዘናችንን ከእነርሱ ጋር እንካፈላለን፡፡ ነገር ግን ከምድራዊ ወዳጆቻችን አስበልጠን እግዚአብሔርን የምንወድበት ብዙ ምክንያት አለን፡፡ ከዚህም የተነሳ እርሱን ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በላይ መጀመሪያ ማድረግ፣ ስለ እርሱ መልካምነትና ኃይል ማውራት ተፈጥሮአችን ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ብዙ ባርኮቶች አሳባችንንና ፍቅራችንን ሙጥጥ አድርገው በመውሰድ፣ ሰጪውን እንድንረሳ ሊያደርጉን አይገባም፡፡ ይልቁንም ከሰማያዊ ረድኤታችን ጋር በፍቅርና በአመስጋኝ መንፈስ ሊያስተሳስሩን ስለ እርሱም ያለማsረጥ ሊያስታውሱን የተሰጡን ናቸው፡፡ እየኖርን ያለነው በምድር አዘቅት ውስጥ ነው፡፡ ዓይናችንን አንስተን ወደ ተከፈተው ሰማያዊ መቅደስ ደጅ እንመልከት፡፡ በዚያም «በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊድናቸው በሚችለው» ዕብ. 7፡ 25 በኢየሱስ ላይ የእግዚአብሔር ክብር ሲያጸባርቅበት እናያለን፡፡ ክየመ 97.3

እግዚአብሔርን ማምለክና በእርሱም ሥራ ውስጥ ድርሻ ማግኘት እንደ ትልቅ ደስታ ልንቆጥረው የሚገባ ነገር ነው፡፡

እግዚአብሔርን «ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም» (መዝ. 107፡8) ልናመሰግነው ይገባል፡፡ የአምልኮ ህይወታችን በመጠየቅና በመቀበል ላይ ሊወሰን አይገባም፡፡ ሁልጊዜ ስለ ጎደሉን ነገሮች ብቻ በማሰብ የተቀበልናቸውን ባርኮቶች አንርሳ፡፡ በምስጋና አፋችንን ሳንከፍት ብዙ ልንጸይ አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ምህረት ያለማsረጥ እየተቀበልን በምላሹ የምንሰጠው ምስጋና ግን ምን ያህል በጣም ትንሽ ነው! ክየመ 98.1

ጥንት እስራኤላዊያንን ጌታ ለአምልኮ ሲሰበሰቡ እንዲህ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸው፡- «እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ።» ዘዳ. 12፡7፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የምናደርገው ነገር ሁሉ በደስተኛ ስሜት፣ በውዳሴ ዝማሬና በምስጋና እንጂ በኀዘንና በጠቆረ ፊት መሆን የለበትም፡፡ ክየመ 98.2

አምላካችን ሩህሩህና መሐሪ አምላክ ነው፡፡ ለእርሱ የሚደረግ አገልግሎት ልብን በሐዘን የሚሞላ፣ አስጨናቂ ልምምድ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም፡፡ እግዚአብሔርን ማምለክንና በእርሱም ስራ ውስጥ ድርሻ ማግኘትን እንደ ትልቅ ደስታ ልንቆጥረው የሚገባ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር እጅግ ታላቅ መዳን ያዘጋጀላቸው ልጆቹ እርሱን እንደ ጨካኝና አምባገነን ጌታ አድርገው እንዲቆጥሩት አይፈልግም፡፡ እርሱ የቅርብ ወዳጃቸው ነው፡፡ በሚያመልኩትም ጊዜ ከእነርሱ መካከል በመገኘት ሊባርካቸውና ሊያጽናናቸው እንዲሁም ልባቸውን በደስታና በፍቅር ሊሞላ ይፈልጋል፡፡ ጌታ ልጆቹ እርሱን በማገልገላቸው ብዙ መጽናናት እንዲያገኙና ከችግር ይልቅ ደስታን እንዲለማመዱ ይፈልጋል፡፡ እርሱን ለማምለክ የሚመጡ ሰዎች ሁሉ፣ ስለ እርሱ ጥንቃቄና ፍቅር የከበሩ አሳቦችን ይዘው እንዲመለሱ በየዕለት ተግባራቸውም ደስተኞች እንዲሆኑ፣ በነገር ሁሉ በእውነተኝነትና በታማኝነት መጋፈጥ የሚችሉበትን ጸጋ እንዲያገኙ ይፈልጋል፡፡ በመስቀሉ ዙሪያ ልንሰበሰብ ይገባናል፡፡ ክርስቶስና ስቅላቱ በአእምሮአችን የምናስበው ነገር፣ የንግግራችን፣ እንዲሁም የደስታችን ሁሉ ማእከል ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን መልካም ስጦታዎች ሁልጊዜ ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ ፍቅሩንም ስናስተውል በመስቀል ላይ ስለ እኛ በተቸነከሩት የጌታ እጆች ላይ ሁሉንም ነገራችንን ለማስረከብ ፈቃደኞች እንሆናለን፡፡ ነፍስ በምስጋና ክንፍ ወደ ሰማይ ትበራለች፡፡ በላይ በሰማይ አደባባዮች እግዚአብሔር በመዝሙርና በሙዚቃ ይመለካል፡፡ እኛ ደግሞ በዚህ ምድር ላይ ምስጋናችንን በመግለጥ ስናመልክ የሰማይ ሠራዊትን አምልኮ እየተጠጋን እንሄዳን፡፡ «ምስጋናን የሚሰዋ ሁሉ» እግዚአብሔርን ያከብራል፡፡ መዝ. 50፡ 23፡፡ «በምስጋናና በዜማ ድምጽ» በአክብሮት በተሞላ ደስታ ወደ ፈጣሪያችን እንቅረብ፡፡ ኢሳ. 51፡3፡፡ ክየመ 99.1