ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ

20/27

ምዕራፍ 10 - እግዚአብሔርን ማወምዕራፍቅ

እግዚአብሔር ለእኛ ራሱን ለማስተዋወቅና ከእርሱ ጋር ሕብረት እንዲኖረን የሚጠቀምባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ ተፈጥሮ ያለማቋረጥ ለሕሊናችን እግዚአብሔር መኖሩን ይነግረናል፡፡ ልቡን ከፍቶ ያስተዋለ ሰው ሁሉ በእጁ ስራ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅርና ክብር በማየት ይደነቃል፡፡ ጆሮውን ከፍቶ ያዳመጠ ሰው ሁሉ ደግሞ እግዚአብሔር በተፈጥሮ አማካኝነት ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልዕክት ለመስማትና ለማስተዋል ይችላል፡፡ የለመለሙት መስኮች፣ ረዣዥም ዛፎች፣ ቡቃያዎች፣ አበቦች፣ የሠማይ ደመናዎች፣ የሚዘንቡት ዝናቦች፣ ፈሳሽ ውሃዎች እና በሠማይ ያሉ ፍጥረቶች ሁሉ ለልቦቻችን መልዕክትን ያስተላልፋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እኛን ከፈጣሪ ጋር ለማስተዋወቅ ይጋብዙናል፡፡ ክየመ 78.1

አዳኛችን ጠቃሚና ክቡር ትምህርቶቹን በፈጠረው ፍጥረት ውስጥ አስቀመጠ፡፡ በሥራ ብዛት የተወጠረውን ማንኛውም ሰው እንኳን ቢሆን የእግዚአብሔርን ትምህርት ሁልጊዜ ማስታወስ እንዲችል ብሎ ከዛፎች፣ ከወፎች፣ በሸለቆ ውስጥ ካሉት አበባዎች፣ ከኮረብታዎች፣ ከባሕሮች፣ ከኩሬዎች፣ ከሚያምሩት ሠማያት እንዲሁም በዙሪያችን ካሉት በእግዚአብሔር ቃል ከተፈጠሩት ፍጥረቶች ሁሉ ጋር የእውነትን ቃል አያይዞታል፡፡ ክየመ 78.2

እግዚአብሔር ባማረ ውበት ያስጌጣትን ምድራዊ ቤታችንን በማየት ልጆቹ እንዲደሰቱና እንዲያደንቁ ይፈልጋል፡፡ እርሱ ውበትን ይወዳል፡፡ በውጪ ከሚታዩት ነገሮች ሁሉ ይልቅ ግን ልጆቹ ያማረ ባሕርይ ፣ ንፅህና፣ ገርነት፣ እና በአበቦች ላይ የሚታየው አይነት ግርማ ሞገስ እንዲኖራቸው ይወዳል፡፡ በማስተዋል ካዳመጥን የእግዚአብሔር ፍጥረታት ስለመታዘዝና ስለመታመን ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ይሰጡናል፡፡ ክየመ 78.3

ኮቴ በሌለው መንገዳቸው በሕዋው ውስጥ ከዘመናት እስከ ዘመናት በተመደበላቸው መንገድ ከሚጓዙት የሠማይ ከዋክብት ጀምሮ በጣም ትንሽ እስከሆነችው ነገር (አተም) ድረስ ፍጥረት ለፈጣሪው ፈቃድ ይታዘዛል፡፡ እግዚአብሔር ለፈጠረው ሁሉ ያስባል፣ የሚያስፈልገውንም ሁሉ በሰዓቱ ይሰጠዋል፡፡ ከማስተዋል በላይ በሆነው ኃይሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ዓለማት የያዘው አምላክ ትሁት ዜማውን ለሚያዜመው ትንሹ ወፍ እንኳን ይጠነቀቃል፤ የሚሻውንም ይሰጠዋል፡፡ ሰዎች የዕለት ስራቸውን ለመስራት ከቤታቸው ሲወጡ፣ ፀሎት ሲፀልዩ፣ በሌሊት ሲተኙም ሆነ በጠዋት ሲነሱ፣ ሃብታም ሰው በደስታ ሲበላና ሲጠጣ፣ ደሃውም ሰው በትንሹ ገበታው ዙሪያ ልጆቹን ሲሰበስብ እያንዳንዱ ነገር በሠማይ ባለው ሩህሩህ አባት ዓይን ታይቷል፡፡ እግዚአብሔር ያልተመለከተው የፈሰሰ እንባ የለም፣ የማያስተውለው ፈገግታም የለም፡፡ ክየመ 79.1

በማስተዋል ካዳመጥን የእግዚአብሔር ፍጥረታት፣ ስለመታዘዝና ስለመታመን ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ይሰጡናል።

ይህንን እውነት ሙሉ በሙሉ ብናምን ተገቢ ያልሆነው ስጋትና ሽብር ሁሉ ከኛ በራቀ ነበር፡፡ ሕይወታችንም እንደ አሁኑ ተስፋ መቁረጥ አይታይበትም ነበር፡፡ በዛ ፈንታ ትንሽም ሆነ ትልቅ የችግራችን ብዛት በማያስጨንቀውና የክብደቱ መጠን በማያስቸግረው በእግዚአብሔር እጅ ላይ ሁሉን እንተወዋለን፡፡ ከዚያም ብዙ ሰዎች ለብዙ ዘመናት ያላገኙትን የነፍስ እረፍት በማግኘት እንደሰታለን፡፡ ክየመ 79.2

የስሜት ህዋሳቶቻችን በምድር ውበት የሚደሰቱ ከሆነ እንግዲያውስ ኃጢአትና ሞት ያላቆሸሸውንና፣ የእርግማን ጥላ የማያጠላበትን ወደ ፊት የሚመጣውን ዓለም እናስብ፡፡ በምናባችሁ የጻድቃንን መኖሪያ ሳሉት፡፡ የፈለገ ብሩህ አእምሮ ቢኖረን እኛ ከምንገምተው በላይ እንደሆነ ግን እናስታውስ፡፡ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ውስጥ በሰጠን የተለያዩ ስጦታዎች ማየት የምንችለው የእግዚአብሔርን የክብሩን ብልጭታ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።›› (1 ቆሮ. 2፡ 9)፡፡ ክየመ 80.1

አዎ፣ ደራሲዎችና የተፈጥሮ ተመራማሪዎች ስለተፈጥሮ ውበት ብዙ የሚፅፉትና የሚናገሩት ይኖራል፡፡ በተፈጥሮ ውበት በእጅጉ የሚደሰተው ግን ክርስቲያን የሆነ ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ የአባቱ የእግዚአብሔር ድንቅ የእጅ ስራና በእያንዳንዱ አበባ፣ ቁጥቋጦና ዛፍ ላይ ደግሞ ፍቅሩ ሲንጸባረቅ ይመለከታልና፡፡ ተራራዎችና ሸለቆዎች ወንዞችና ባሕሮች የእግዚአብሔር ፍቅር መግለጫዎች እንደሆኑ የማያስተውል ሰው የተፈጥሮን ውበት ሙሉ በሙሉ ለማድነቅ አይችልም፡፡ ክየመ 80.2

አዳኙን ለመተዋወቅ ከፈለጋችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ።

እግዚአብሔር አስደናቂ በሆነው እንክብካቤውና ጥበቃው እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለልባችን ብዙ ይናገራል፡፡ ልባችንን ከፍተን ማስተዋል ከቻልን በሚያጋጥሙን የየዕለቱ ገጠመኞችና በአካባቢያችን በሚከሰቱት ክስተቶች ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን፡፡ ስለ እግዚአብሔር ዘወትር የሚያሰላስለው ዘማሪ እንዲህ በማለት ፅፏል፡- ‹‹የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።›› ‹‹ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።›› (መዝ. 33፡ 5፤ 107፡ 43)፡፡ ክየመ 80.3

እግዚአብሔር በቃሉ አማካኝነትም ይናገረናል፡፡ ስለ ባሕርይውም፣ ለእኛ ስላለው ዓላማ እና የጠፋውን ሰው ለማዳን ስላላው እቅድ ቃሉ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ይነግረናል፡፡ በቃሉ ውስጥ የአበው፣ የነብያት እንዲሁም የሌሎች ቀደምት ቅዱሳን ታሪክ ተፅፎ እናነባለን፡፡ እነርሱም ‹‹እንደኛ ሰው ነበሩ›› ያዕ. 5.17፡፡ እንደኛ ከተስፋ መቁረጥ ጋር የታገሉ በፈተናም ውስጥ የወደቁ ነበሩ፤ ቢሆንም እንደገና ድፍረትን በማግኘት በእግዚአብሔር ፀጋ አማካኝነት አሸናፊዎች ሆኑ፡፡ በእነርሱ ምሳሌነት እኛም በጽድቅ ጎዳና በምንሮጠው ሩጫ መበረታትን እናገኛለን፡፡ እነዚያ የእግዚአብሔር ልጆች ስላሳለፏቸው ድንቅ ልምምዶች ስናነብ፣ በተገለጠላቸው ብርሃን፣ ፍቅርና በረከት አማካኝነት ያገኙ ስለነበረውም ደስታ ስናነብ፣ በተሰጣቸው ፀጋ አማካኝነት ያደርጉ ስለነበረው ስራ ደግሞ ስንሰማ፤ ያ በእነርሱ ውስጥ ይሰራ የነበረው መንፈስ ቅዱስ እኛም እንደነርሱ አይነት ባሕርይን እንድንላበስ በልባችን ውስጥ የተቀደሰ ፍላጎት እሳትን ያቀጣጥላል፡፡ ክየመ 81.1

ኢየሱስ ስለ ብሉይ ኪዳን እንዲህ በማለት የተናገረው መግለጫ ለአዲስ ኪዳንም ገጣሚ ነው፡- ‹‹እነርሱ ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው›› (ዮሐ. 5፡39) ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ አዳኙ፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋችን መሠረት ስለሆነው ይመሰክራሉ፡፡ አዎ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ይናገራል ‹‹ያለእርሱ ምንም ነገር አልተፈጠረም›› (ዮሐ. 1፡3) ከሚለው ከፍጥረት ታሪክ ጀምሮ ‹‹እነሆ በቶሎ እመጣለሁ›› (ራዕይ 22፡12) እስከሚለው የመጨረሻ ተስፋ ቃል ድረስ በቃሉ ውስጥ ስለ እጁ ስራ እናነባለን፣ ድምፁንም እንሰማለን፡፡ አዳኙን ለመተዋወቅ ከፈለጋችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ፡፡ ልባችሁን በእግዚአብሔር ቃል ሙሉት፡፡ ጥማታችሁን ሊያረካ የሚችል ሕያው ውሃ ነውና፡፡ ከሠማይ የወረደ ሕያው እንጀራ ነውና፡፡ ኢየሱስ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።›› (ዮሐንስ 6፡53) አለ፡፡ ምን ለማለት እንደፈለገ ሲያብራራም፡- ‹‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።›› (ዮሐ. 6፡63) ብሎ ተናገረ፡፡ ሰውነታችን ጥንካሬን የሚያገኘው ዕለት ዕለት በሚመገበው ምግብና በሚጠጣው ውሃ ነው፡፡ ለተፈጥሮአዊ ሰውነታችን ምግብና ውሃ እንዲህ ወሳኝ ከሆነ ለመንፈሳዊውም ህይወታችን እንደዚያው ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ተፈጥሮአችን ጥንካሬንና መልክን የሚሰጠው የምናሰላስለው ነገር ነው፡፡ ክየመ 81.2

ኃጢአተኛውን ሰው በመቤዠት እግዚአብሔር የሰራው ሥራ መላእክት በጥልቅ ሊመረምሩት የሚመኙት ርዕስ ነው፡፡ ይህ የድነት ሚስጢር የዳኑት ፃድቃን ለዘለዓለም የሚመረምሩት ሳይንስ እንዲሁም የውዳሴ መዝሙራቸው ዋና ርዕስ ይሆናል፡፡ ታዲያ ይህንን ጠቃሚ ርዕስ ዛሬውኑ በሰፊው ልናጠናው አይገባምን ወሰን የለሹ የኢየሱስ ምህረትና ፍቅሩ በእኛ ፈንታ የከፈለው መስዋትነት፣ ስለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ በደንብ እንድናስብበት ጥሪ ያቀርቡልናል፡፡ አዕምሮአችንና ሃሳባችን ሁሉ ስለአዳኛችን እና ስለአማላጃችን ባሕርይ እንዲሁም ሕዝቡን ከኃጢአት ለማዳን ስለመምጣቱ ዓላማ ማሰብና ማሰላሰል አለበት፡፡ ስለ እነዚህ ሰማያዊ ነገሮች በበለጠ በምናሰላስልበት ጊዜ እምነታችንና ፍቅራችን የበለጠ እየጠነከረ ይሄዳል፣ ፀሎታችንም በእምነትና በፍቅር የተሞላ ስለሚሆን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ያገኛል፡፡ በመሆኑም በኢየሱስ ላይ ያለን እምነት የበለጠ ይጠነክራል፣ ዕለት በዕለትም የኢየሱስን የማዳን ኃይል በሕይወታችን እንለማመዳለን፡፡ ክየመ 82.1

የጥሞና ጊዜ ወስደን ስለአዳኛችን ፍፅምና በምናሰላስልበት ጊዜ አዲስ ፍጡር ለመሆንና እርሱን ለመምሰል በልባችን ምኞት ይቀሰቀሳል፡፡ የምታመልከውን አምላክ ለመምሰል ነፍሳችን ትራባለች፤ ትጠማለች፡፡ ልባችን የበለጠ በክርስቶስ እየሞላ በሄደ ቁጥር ስለእርሱ ማንነት የበለጠ ለሌሎች እንናገራለን፣ በዓለምም ላሉት እንመሰክራለን፡፡ ክየመ 82.2

መጽሐፍ ቅዱስ ለተማሩ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ተራ ለሚባሉት ሰዎች ታስቦ ነው የተጻፈው፡፡ ለድነታችን አስፈላጊ የሆኑት እውነቶች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ቀትር ፀሐይ ግልፅ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ግልፅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቃድ ትቶ በራሱ አስተሳሰብ ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊሳሳትና ትክክለኛውን መንገድ ሊስት አይችልም፡፡ ክየመ 83.1

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን በተመለከተ ማንም ሰው የሚለንን ተከትለን መሄድ የለብንም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በግላችን ልናጠናው ይገባል፡፡ ራሳችን በመመርመር ፈንታ ሌሎች ስለእኛ እንዲመረምሩልን በምንፈቅድበት ጊዜ አዕምሮአችንን እያዳከምን መሄድ ብቻ ሳይሆን የማገናዘብ ችሎታችንም እየመነመነ ይሄዳል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የጠለቀ ትርጉም የማይመረምር አዕምሮ አያድግም፡፡ አዕምሮአችን እየበሰለ የሚሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በተመለከተ አንድን ጥቅስ ከሌላው ጥቅስ ጋር እያጣቀስን ፣ መንፈሳዊ ነገርን ከመንፈሳዊ ነገር ጋር እያነፃፀርን በምናጠናበት ጊዜ ነው፡፡ ክየመ 83.2

መጽሐፍ ቅዱስን እንደማጥናት የአእምሮእንን የማገናዘብ ችሎታ የሚያጠነክር ሌላ ነገር የለም፡፡ አሳባችንን ከፍ የሚያደርግ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያለ ሰፊና የከበሩ እውነቶችን የያዘ ሌላ መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱ እንደሚገባ ተጠንቶ ቢሆን ኖሮ በዚህ ዘመን ብርቅ የሆኑትን የአእምሮ መስፋት፣ የባሕርይ ክቡርነትንና የዓላማ ጽናትን ሰዎች መቀዳጀት በቻሉ ነበር፡፡ ክየመ 83.3

መጽሐፍ ቅዱስን በጥድፊያ በማንበብ ምንም ጥቅም አይገኝም፡፡ አንድ ሰው በውስጥ ውበቱን ሳያይ ወይም ጥልቅና የተሰወረውን ትርጉሙን ሳያስተውል መፅሀፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው ገፅ እስከ መጨረሻው ገፅ ሊያነብ ይችላል፡፡ ትርጉሙ ምን እንደሆነ እስኪገባንና ከድነት እቅድ ጋር ጥቅሱ ያለውን ግንኙነት እስክናስተውል ድረስ የምናጠናው አንድ ጥቅስ፣ ያለ ዓላማና ከውስጡም ለእኛ የሚሆን ምንም መመሪያ ሳናገኝበት ከምናነበው የብዙ ምዕራፎች ንባብ ይሻላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ ሁልጊዜ ከእናንተ አይለይ፡፡ በአገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ አንብቡት፤ ጥቅሶቹንም በቃላችሁ ያዙ፡፡ እንዲያውም በመንገድ ስትጓዙ አንድ ክፍልን አንብቡና በዚያ ክፍል ላያ አሰላስሉ፡፡ በዚህ መልኩ ቃሉ በአዕምሮዎ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ክየመ 84.1

መጽሐፍ ቅዱስ ለተማሩ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ‹‹ተራ›› ለሚባሉት ሰዎች ታስቦ ነው የተጻፈው፡፡

በማስተዋልና በፀሎት ካላጠናነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ እውቀትን ማግኘት አንችልም፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግልፅ በመሆናቸው ምንም አያሳስቱም ቢሆንም ትርጉማቸው ሙሉ በሙሉ ግልፅ ያልሆኑ በጥንቃቄ ሊጠኑ የሚገባቸው አንዳንድ ጥቅሶች አሉ፡፡ እነዚህን ጥቅሶች ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ማነፃፀር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ መፀለይና በጥንቃቄ መመርመር ግድ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከመረመርን ትልቅ ሽልማት እናገኝበታለን፡፡ ልክ አንድ ማዕድን ቆፋሪ በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኘውን የከበረ ድንጋይ በጥልቀት ቆፍሮ እንደሚያወጣ፣ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተደበቁትን እንቁዎች ለማግኘት ተግቶ የሚፈልግ ማንም ሰው ለሕይወቱ እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን ያገኛል፡፡ ላይ ላዩን ለሚያነብ ሰው ግን እነዚህ እውነቶች አይታዩትም፡፡ ወደ ልባችን የምናስገባቸውና የምናስቀምጣቸው የእግዚአብሔር ቃሎች ከሕይወት ፏፏቴ እንደሚፈስ ምንጭ ይሆኑልናል፡፡ ክየመ 84.2

መጽሐፍ ቅዱስን በምንም ዓይነት ያለፀሎት ማጥናት የለብንም፡፡ ገፆቹን ከመግለጣችንና ከማንበባችን በፊት መንፈስ ቅዱስ ቃሉን እንዲገልጥልንና እንድናስተውል እንዲረዳን ልንጠይቀው ይገባል፡፡ እግዚአብሔርም ይገልጥልናል፡፡ አንድ ጊዜ ናትናኤል ወደ ኢየሱስ ሲመጣ አዳኛችን ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ «ተንኮል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ» ናትናኤልም ሲመልስ «ከወዴት ታውቀኛለህ;» አለው፡፡ ኢየሱስ ሲመልስ «ፊሊጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ» አለው፡፡ (ዮሐ. 1፡ 47-48)፡፡ ዛሬም ኢየሱስ የእውነትን ብርሃን ለማግኘት በስውር ሆነን ወደእርሱ ስንፀልይ እያንዳንዳችንን ያየናል፡፡ ቅዱሳን መላዕክት እራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትህትና የእግዚአብሔርን አመራር ከሚሹ ሁሉ ጋር ይሆናሉ፡፡ ክየመ 85.1

መንፈስ ቅዱስ አዳኛችንን ያከብረዋል ከፍ ከፍም ያደርገዋል፡፡ በክርስቶስ በኩል ያገኘነውን አስደናቂ ድነት፣ የጌታን ፍፁምነትና ፅድቁን የሚገልፅልን ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ኢየሱስ ሲናገር «ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል» አለ (ዮሐ. 16፡14)፡፡ መለኮታዊ እውነትን ሊገልፅልን የሚችል ብቸኛ እና ብቁ አስተማሪ የእውነት መንፈስ ነው፡፡ ኦ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች የሰጠው ዋጋ ምን ያህል ትልቅ ነው! አንድያ ልጁን ለኛ ሲል እንዲሞት አድርጎ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የእኛ አስተማሪ እና የማያቋርጥ መሪ እንዲሆን ያደረገልን! ክየመ 85.2