ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ
ምዕራፍ 6 - እምነትና ተቀባይነት ማግኘት
ህሊናዎ በመንፈስ ቅዱስ ሲነቃቃ የኃጢአትን ክፋት፣ ኃይል፣ ክስ እንዲሁም ዋይታውን ማስተዋል ይችላሉ:: ኃጢአትንም መጸየፍ ይመለከቱታል፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር የለየዎት መሆኑንና በክፉው ኃይል ግዞት ስር መውደቅዎን ያስተውላሉ፡፡ ከዚህ ግዞት ለማምለጥ በታገሉ ቁጥር ረዳት አልባነትዎን አብልጠው ያስተውላሉ፡፡ የሃሳብዎ መነሻም ሆነ በልብዎ ያሉት ነገሮች ንጽህና የጎደላቸው እንደሆኑና፡፡ ህይወትዎ በስስትና በኃጢአት የተሞላ መሆኑን ይመለከታሉ፡፡ በመሆኑም ይቅር ለመባል፣ ከበደል ለመንጻት እንዲሁም ነጻ ለመውጣት ይናፍቃሉ፡፡ ታዲያ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት የመፍጠርና ዳግም በአምሳሉ የመቀረጽ ዕድል ያገኙ ዘንድ ምን ማድረግ ይችላሉ? ክየመ 46.1
አጥብቀው የሚሹት ነገር ቢኖር ሰማያዊውን ይቅርታና ሰላም እንዲሁም ፍቅርን ነው:: ይህን ነገር ገንዘብ ሊገዛው፣ አእምሮ በጥረቱ የግሉ ሊያደርገው ወይም ጥበብ ሊያገኘው አይችልም፡፡ እነዚህን ነገሮች ከእግዚአብሔር በስጦታ መልክ ይቀበሏቸዋል እንጂ በግል ጥረትዎ የራስዎ ለማድረግ በፍጹም ተስፋ ማድረግ አይችሉም:: እግዚአብሔር ግን «ያለገንዘብ ያለ ዋጋ» (ኢሳ. 1:18) በስጦታ መልክ ያበረክትልዎታል በመሆኑም እጆችዎን ዘርግተው መቀበል እስከ ቻሉ ድረስ በእርግጥም የእርስዎ ናቸው:: ጌታ አምላክ እንዲህ ይላል «ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጻል» (ኢሳ. 1፡18)፡፡ «አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ» (ሕዝ. 36:26)፡፡ ክየመ 46.2
ኃጢአትዎን ተናዝዘዋል፤ ከልብዎም አርቀውታል፡፡ እራስዎን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ወስነዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ በመሄድ ኃጢአትዎን እንዲያጥብልዎና አዲስ ልብ እንዲሰጥዎ ይጠይቁት፡፡ ከዚያም በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የጠየቁትን እንደተቀበሉ ይመኑ፡፡ እግዚአብሔር ቃል የገባልንን ስጦታ የራሳችን ለማድረግ፣ እንደተቀበልነው መቁጠር እንዳለብን ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ያስተምር የነበረው ትምህርት ነበር፡፡ ክየመ 47.1
ሕዝቡ በኢየሱስ ኃይል ባመነ ጊዜ ከደዌአቸው ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ማየት የሚችሉትን ነገር በማሳየት (አካላቸውን በመፈወስ) ፤ ማየት የማይችሉትን ይኼውም የኃጢአት ይቅርታን ለመስጠት የሚችልበት ኃይል እርሱ እንዳለው እንዲያምኑ ይረዳቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ ሽባውን በፈወሰ ጊዜ ይህን ሁኔታ በግልጽ ጠቅሶታል፡- «ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን የማስተሰረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው» በማለት ሽባውን «ተነሳ! ቃሬዛህንም ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ» አለው» (ማቴ. 9:6፡፡ እንዲሁም ኢየሱስ ያደረገውን አስመልክቶ ወንጌላዊው ዮሐንስ ሲናገር «ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ እንድታምኑ ዘንድ ፧ አምናችሁም በስሙ ህይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል» (ዮሐ. 20፡31)፡፡ ክየመ 47.2
የኃጢአትን ይቅርታ እናገኝ ዘንድ እንዴት በእርሱ ማመን እንዳለብን፣ኢየሱስ የታመሙትን እንዴት እንደፈወሰ ከሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንኳን ሳይቀር መማር እንችላለን፡፡ በቤተሳይዳ ወደ ነበረው ሽባ ሰው ታሪክ እንመለስ፡፡ ይህ በሥቃይ ላይ የነበረ ምስኪን አንዳችም የሚረዳው ሰው አልነበረውም፤ እንዲሁም ላለፉት 38 ዓመታት አንዴም እንኳ እግሮቹን ተጠቅሞባቸው አያውቅም:: ነገር ግን ኢየሱስ «ተነሳ ቃሬዛህንም ይዘህ ሂድ» ሲል ተናገረው:: ምናልባትም ይህ ህመም የደቆሰው ሰው «ጌታ ሆይ የምታድነኝ ከሆነ ለቃልህ እታዘዛለሁ» ማለት ይችል ነበር፡፡ ምስኪኑ ሰው በዚህ ፋንታ ከክርስቶስ አንደበት በወጡት ቃላት በማመን ወዲያውኑ ማድረግ ያለበትን አደረገ፡፡ ለመራመድ ፈቃደኛ ሆነ ተራመደም፡ክርስቶስ የተናገረውን ቃል ተከትሎ ተንቀሳቀሰ፤እግዚአብሔርም ኃይል ሰጠው:: ከህመሙም ተፈወሰ፡፡ ክየመ 47.3
ከዚህ ሽባ ጋር የሚያመሳስልዎት ነገር ቢኖር፣ እርስዎም እንደ እርሱ ኃጢአተኛ መሆንዎ ነው፡፡ ላለፈው ኃጢአትዎ ስርየት ማግኘት ወይም በራስዎ ብርታት ልብዎን ማንጻት አይችሉም:: ነገር ግን እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል እነዚህን ሁሉ ያደርግልዎ ዘንድ ቃል ገብቶአል፡፡ በዚህ ተስፋ በማመን ኃጢአትዎን ይናዘዙ፣ እራስዎንም ለእግዚአብሔር ያስረክቡ፡፡ እርሱንም ለማገልገል ፈቃደኛ ይሁኑ:: እርስዎ ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ፣ እግዚአብሔርም ቃል የገባውን ለእርስዎ ይፈጽማል፡፡ ይቅር እንደተባሉና እንደነጹ በማመን የተስፋው ቃል በእርስዎ ሕይወት እንደተፈጸመ ቢያምኑ፣እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን እምነትዎን እውን ያደርገዋል:: ልክ ኢየሱስ ለሽባው ሰው እንደተፈወሰ ባመነ ጊዜ የሚራመድበትን ኃይል እንደሰጠው፣ እርስዎም ይድናሉ፡፡ ክየመ 48.1
እንደዳኑ እስኪሰማዎት ድረስ አይጠባበቁ፤ ይልቁንም «አምናለሁ፤ ድኛለሁ፤ ይህንንም የምለው ስሜቴ መስክሮልኝ ሳይሆን እግዚአብሔር ቃል ስለገባልኝ ነው::» ይበሉ፡፡ ክየመ 48.2
ላለፈው ኃጢአትዎ ስርየት ማግኘት ወይም ደግሞ በራስዎ ብርታት ልብዎን ማንጻት አይችሉም።
ኢየሱስ «ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል» (ማር. 11:24) በማለት ይናገራል፡፡ይህን ተስፋ ለመቀበል የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ ያለ ሲሆን ይኼውም በጸሎት የምንለምነው ነገር ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የተስማማ እንደሆነ ነው። በመሆኑም እነዚህን በረከቶች መጠየቅና እንደተቀበልናቸው ማመን እንዲሁም ስለተደረገልን ነገር እግዚአብሔርን ማመስገን የእኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የተስማማ እንደሆነ ነው። በመሆኑም እነዚህን በረከቶች መጠየቅና እንደተቀበልናቸው ማመን እንዲሁም ስለተደረገልን ነገር እግዚአብሔርን ማመስገን የእኛ ፋንታ ነው። ወደ ኢየሱስ በመቅረብ ከኃጢአት እንድንነጻ እንዲሁም ከሕጉ ፊት ያለ ጸጸት ወይም ሐዘን እንቆም ዘንድ ዕድል ተሰጥቶናል «ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም» (ሮሜ 8፡1)፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ ይመላለሳሉና። ክየመ 48.3
ስለዚህ እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋልና፡፡« . . . የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ:: ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፧ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው፡፡» (1ኛ ጴጥ. 18-19)፡እንዲህ እግዚአብሔርን በማመን ብቻ፣ መንፈስ ቅዱስ በልብዎ ውስጥ አዲስ ሕይወት እንዲወለድ አድርጓል፡፡ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ እንደተወለደ አዲስ ሕጻን ይቆጠራሉ:: እግዚአብሔርም አንድያ ልጁን በሚወድበት ፍቅር እርስዎንም ይወድዎታል፡፡ ክየመ 49.1
እራስዎን ለኢየሱስ ከሰጡ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ ወይም እራስዎን ከእርሱ መነጠል የለብዎትም፡፡ ይልቁንም በየቀኑ «እኔ የክርስቶስ ነኝ፤እራሴን ለእርሱ አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ» በማለት እርሱ መንፈሱን እንዲስጥዎና በጸጋው ዙሪያ ይጠብቅዎ ዘንድ ይጠይቁት:: የእግዚአብሔር ልጅየሆኑት ራስዎን ለእርሱ በመስጠትና በእርሱ በማመን እንደሆነ፣ በእርሱ መኖርንም መቀጠል ይኖርብዎታል፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- «እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ» (ቆላ. 2፡6)፡፡ ክየመ 49.2
አንዳንዶች ‹የእርሱን በረከት ከመጠየቃችን በፊት ሕይወታችን የተለወጠ መሆኑን ለእግዚአብሔር ለማሳየት ለተወሰነ ጊዜ ልንፈተሽ ይገባናል» ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን የጌታን በረከት አሁኑኑ መጠየቅና የግላቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ድካማቸውን ለማሸነፍ የእግዚአብሔር ጸጋና የክርስቶስም መንፈስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ክፉን ማሸነፍ አይችሉም፡፡ ኢየሱስ ከነኃጢአታችን፣ ረዳተቢስና ጥገኛ እንደሆንን፣ ባለንበት ሁኔታ ወደ እርሱ እንድንመጣ ይወዳል፡፡ ከነደካማነታችንና መተላለፋችን በንስሓ እግሮቹ ስር መውደቅ እንችላለን፡፡ እርሱም በፍቅር እጆቹ ያቅፈናል፤ ቁስላችንን ይጠርግልናል፤ ከእርኩሰታችንም ሁሉ ያጠራናል፤ ይህንንም ማድረግ ለእርሱ ክብሩ ነው:: ክየመ 49.3
በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ውድቀት አንዱ መንስዔ ኢየሱስ በግል ይቅር እንደሚላቸው አለማመናቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ቃል የገባውን በቀጥታ አይቀበሉትም፡፡ ይቅርታ ለእያንዳንዱ ኃጢአት በነጻ የመሰጠቱን ዕድል ሁሉም ለራሱ ሊያውቅና ሊቀበል ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ ለሌሎች እንጂ እርስዎን እንደማይጨምር አድርጎ የማሰቡን ጥርጣሬ ያስወግዱ፡ተስፋዎቹ የተሰጡት በንስሓ በፊቱ ለሚቀርቡ ሁሉ ነውና! በክርስቶስ አማካኝነት ብርታትና ጸጋ በአገልጋይ መላእክቱ በኩል ለእያንዳንዱ አማኝ ነፍስ እንዲሰጡ ተደርጎአል፡፡ በመሆኑም በሞተለት በኢየሱስ በኩል ብርታትን፣ ንጽህናንና ጽድቅን ማግኘት የማይችል አንድም ኃጢአተኛ የለም:: እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ ልመናውን የሚያቀርበው ጌታ በኃጢአት የተበከለውን ልብሳቸውን አውልቆ ነጩን የጽድቅ ሸማ ሊያለብሳቸው እየጠበቃቸው ይገኛል፡፡ ክየመ 50.1
ሰብአዊ ፍጡራን አንዳቸው ሌላቸውን በሚያስተናግዱበት አይነት መንገድ እግዚአብሔር እኛን አያስተናግደንም፡፡ የእርሱ ሐሳብ የምህረት፣ የፍቅርና በርህራሄ የተሞላ አሳብ ነው:: እንዲህም ይላል «ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው:: ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ይደረግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና» (ኢሳ.55:7) «መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ ጠርጌ አስወግጃለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ» (ኢሳ. 44 :22) ክየመ 50.2
«ማንም እንዲሞት አልሻምና፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና ሕይወት ኑሩ» (ሕዝ. 18:32)፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የተረጋገጠ በረከት ለመስረቅ ዝግጁ ነው:: እርሱ እያንዳንዱን የተስፋ ጭላንጭልና የብርሃን ጨረር ከነፍሳችን ሊወስድ ይመኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ምኞቱ እውን ይሆን ዘንድ ልንፈቅድለት አይገባም:: ጆሮዎችዎን ለፈታኙ በመስጠት ፋንታ እንዲህ ይበሉት «እኔ ህያው እሆን ዘንድ ኢየሱስ ሞተልኝ! ይወደኛል፣ እንድጠፋ የእርሱ ምኞት አይደለም፡፡ በርኅራኄ የተሞላ ሰማያዊ አባት አለኝ፡፡ ምንም እንኳ ፍቅሩን ባበላሽና በረከቱን ባባክንም ነገር ግን ተነስቼ ወደ አባቴ ቤት በመሄድ እንዲህ እለዋለሁ “አባቴ ሆይ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቁጠረኝ»፡፡ ይህ ተምሳሌት ተቅበዝብዞ የነበረው ልጅ እንዴት ተቀባይነት እንዳገኘ ያወሳል፡፡ «ነገር ግን እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፤ አባቱ አይቶት ራራለት ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ አቅፎ ሳመው» (ሉቃ. 15፡18-20)፡፡ ክየመ 50.3
ይህ ልብ የሚነካ ምሳሌ እንኳ፣ የሰማያዊውን አባት ወደር የለሽ ርኅራኄ ለመግለጽ ብቁ አይደለም:: ጌታ በነቢያቱ አማካኝነት «በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህም በርኅራኄ ሳብሁሽ» (ኤር. 31:3) በማለት ይናገራል፡፡ የጠፋው ልጅ ከአባቱ ቤት ርቆ በባዕድ አገር የነበረውን ሁሉ ያባክን በነበረበት ጊዜ የአባቱ ልብ እርሱን ይናፍቅ ነበር፡፡ ይህ የአባቱ መናፈቅ ልጁ ወደ እግዚአብሔር ይመለስ ዘንድ ነፍሱን ያነቃ፣ ያባብል እንዲሁም በፍቅር ወደ ተሞላው የአባቱ ልብ ይስበው ነበር፡፡ ክየመ 51.1
ይህ ሲነገር በማይቻል ፍቅር የተሞላው ልብ፣ ስፍር ቁጥር በሌለው ግዙፉ አምላካዊ ርኅራሄ ኃጢአተኛውን ወደ ራሱ ይስባል፡፡
በተስፋ የተሞሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ከፊትዎ ተገልጠው እያሉ ለጥርጥር ቦታ ሊኖርዎ ይችላል? ኃጢአቱን ለመተውና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚናፍቀው ምስኪኑ ኃጢአተኛ በንስሐ ወደ እግሮቹ ስር እንዳይመጣ ጌታ ይከለክለዋል ብለው ያምናሉ? ከእንዲህ ያለው አስተሳሰብ አጥብቀው ይራቁ! ሰማያዊውን አባትዎን በዚህ መልኩ ከማሰብ በላይ ነፍስዎን ሊጎዳ የሚችል አንዳች ነገር የለም፡፡ ኃጢአትን የሚጠላውና ኃጢአተኛውን የሚወደው አምላክ ሁሉም ይድኑና በክብር መንግሥት ዘላለማዊ በረከት ያገኙ ዘንድ በክርስቶስ ውስጥ ሆኖ እራሱን ሰጠ፡፡ እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ከመረጠበት መንገድ ውጪ ምን ዓይነት የጠነከረ ወይም ይበልጥ በርኅራኄ የተሞላ ቋንቋ መጠቀም ይችል ነበር? «እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፤ እኔ ግን አልረሳሽም» (ኢሳ. 49፡15)። ክየመ 51.2
በጥርጣሬና በፍርሃት ወጀብ ውስጥ እየዋለሉ ከሆነ ቀና ብለው ይመልከቱ እነሆ አማላጃችን ኢየሱስ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር የተወደደውን ልጁን ስለሰጠ ያመስግኑት:: ደግሞም የእርሱ መሞት በእርስዎ ሕይወት ዋጋ እንዳያጣ ይጸልዩ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዛሬውኑ ግብዣውን ያቀርብልዎታል፧ በሙሉ ልብዎ ወደ ኢየሱስ ይምጡና በረከቱን ይውሰዱ፡፡ ክየመ 52.1
የተስፋ ቃሎቹን ሲያነቡ እነዚህ ቃላት ሊገለጽ በማይቻል ፍቅርና ርኅራኄ እንደተሞሉ ያስታውሱ:: ይህ ሊነገር በማይቻል ፍቅር የተሞላው ግዙፉ አምላካዊ ልብ፤ ስፍር ቁጥር በሌለው ርኅራኄ ኃጢአተኛውን ወደ ራሱ ይስባል «በደሙ በተደረገ ቤዛነት የኃጢአትን ይቅርታ አገኘን» (ኤፌ. 1፡7)፡፡አዎ እግዚአብሔር ረዳትዎ መሆኑን ብቻ ይመኑ፡፡ እርሱ አምላካዊውን ግብረገባዊ አምሳል በሰብዓዊው ፍጡር ውስጥ ሊያኖር ይሻል፡፡ ኃጢአትዎን በመናዘዝና በንስሓ ወደ እርሱ ሲመጡ፤ በምህረትና በይቅርታ ይቀርቦታል፡፡ ክየመ 52.2