ሥነ - ትምህርት

4/56

ምዕራፍ 3—መልካሙንና ክፉውን ስለማወቅ

«እግዚአብሔር በአእምሮአቸው ውስጥ
እንዲኖር እልፈቀዱምና ኃጢአት
ያልነበረው ልባቸው ጨለመ»
EDA 20.1

ምንም እንኳ ንፁህና ቅዱስ ሆነው የተፈጠሩ ቢሆንም ኃጢአት መሥራ እንደማይችሉ ሆነው ደግሞ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የርሱን ትዕዛዝ የማይተላለፍ ኃይል ሰጥቶ ሊፈጥራቸው በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ካደረገ ደግሞ ባሕሪያቸው ሁሉ የማይዳብር ውስጥ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ አገልግሎታቸውም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን የግዳጅ ሥራ በሆነ ነበር፡፡ ስለዚህም የመምረጥ ችሎታ ሰጣቸው፡፡ ትዕዛዙን የማክበር ወይም መተላለፍ የሚያስችላቸው ኃይል ሲያድላቸው፣ ያሰበላቸውን በረከቶች በሙሉ ከመስጠቱ በፊት ደግሞ የነሱ ፍቅርና ታማኝነትም መፈተን ነበረበት፡፡ EDA 20.2

በኤደን ገነት ውስጥም «ክፉና በጐውን የምታስታውቅ ዛፍ ነበረች፡፡ …. እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡፡ «ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ አትብላ» (ዘፍ 2፡9-17)፡፡ አዳምና ሄዋን ክፉውን እንዳያውቁ የእግዚአብሔር ፍላጐት ነበር፡፡ መልካሙን ሁሉ ያውቁ ዘንድ በነፃ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ስለ ክፉውና ስለ ኃጢአት ውጤቶች የድካምን፣ የጥረትና የግረት ዕውቀት፣ ጭንቀት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የሃዘንና የስቃይ እንዲሁም የሞት ዕውቀት እግዚአብሔር ለነሱ በነበረው ፍቅር ታቅቦባቸው ነበር፡፡ EDA 20.3

እግዚአብሔር ለሰው መልካሙን ሲያስብለት ሰይጣን ደግሞ ጥፋትን ይመኝለት ነበር፡፡ ሄዋን እግዚአብሔር የተከለከለችውን ዛፍ በሚመለከት የሚኖረውን ቁጣ ችላ በማለት ለመቅረብ ስትሞክር ከጠላቷ ጋር ተገናኘች፡፡ ፍላጐቷና ጉጉቷ ተነሳስቶ ስለነበረ ሰይጣን ቀስ ብሎ በዘዴ የእግዚአብሔርን ቃል ለማስካድ ቀደመ፡፡ ጥበቡንና ቸርነትን አንዳታምን ለማድረግ ፈጠነ፡፡ ክፉውን የምታሳውቀውን ዛፍ በሚመለከት «እግዚአብሔር አለ …… እንዳትሞቱ ከእርሷ አትብሉ፡፡ አትንኳትም» ብሏል ስትለው ፈታኙ እንዲህ ሲል መለሰ «ሞትን አትሞቱም፡፡ ከርሷ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ መልካምና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡» (ዘፍ 3፡3-5) EDA 20.4

ሰይጣን መልካምና ክፉውን አንድላይ ማወቅ ማለት በረከት ማግኘት ማለት እንደሆነ ለማስመሰል ፈለገ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ከዚያች ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ መከልከሉ በብዙ በጐ ነገሮች ላይ ማዕቀብ እንዳደረገ ለማስመሰል ሞከረ፡፡ ድንቅ የሆነውን ጥበብና ኃይል ቀምሰው እንዳይካፈሉበት እግዚአብሔር እንደከለከላቸው ለማስመሰል ተጣደፈ፡፡ ወደ ተቀደሰው የእድገት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ፣ ትልቁን ደስታም እንዳያገኙ ሆን ብሎ ያደረገው ለማስመሰለ ፈለገ፡፡ ሰይጣን ራሱ የተከለከለችውን ፍሬ እንደተመገበና ይኸንን በማድረጉም የመናገር ኃይል እንዳገኘ ገለፀላቸው፡፡ እነሱም እንደሱ ከዚች ዛፍ ፍሬ ቢበሉ እጅግ ወደበለጠ ከፍተኛ የመኖሪያ ስፍራ ሊገቡ እንደሚችሉና ወደበለጠ ሰፊ ዕውቀት ውስጥ ዘልቀው እንደሚገቡ አስመስሎ አቀረበላቸው፡፡ EDA 21.1

ሰይጣን የተከለከለችውን ፍሬ በመብላቱ ታላቅ በረከት እንዳገኘ አድርጐ ሲናገር ሕግን በመተላለፉ ከሰማይ እንደተጣለ ግን እንዳይታወቅ አደረገ፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነበረ ውሸቱ፡፡ ሔዋን በከፍተኛ የማወቅ ጉጉት፣ እጅግ ተደንቃ፣ አሁን እውነት በማስመሰል ሸፋፍኖ ያቀረበውን አሳሳች ድብቅ መንገድ ለይታ መገንዘብ አልቻለችም፡፡ እግዚአብሔር የከለከለውን ለማግኘት ተመኘች፡፡ የርሱንም ታላቅ ጥበብ ካደች፡፡ የእውቀት ሁሉ ቁልፍ የሆነውን እምነቷን አውጥታ ጣለች፡፡ EDA 21.2

«ሴቲቷም ዛፉ ለምግብነት ያማረ እንደሆነ ለዐይንም እንደሚያስጐመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች፡፡ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፡፡»; እጅግ ጣፋጭ ነበር፡፡ ወዲያውኑ እንደበላችውም የተለየ ኃይል ተሰማት፡፡ እጅግ ወደላቀ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረች መሰላት፡፡ ራሷ ሕግን ተላለፈች ለባሏም ፈታኝ ሆነችበት፡፡ «እሱም ከርሷ ጋር በላ፡፡» ዘፍ 3፡6 EDA 22.1

ጠላትም «ዐይናችሁ ይከፈታል፣ እንደ እግዚአብሔርም መልካምና ክፉውን የምታውቁ ትሆናላችሁ፡፡» ብሏቸው ነበር፡፡ (ዘፍ 3፡5) በእርግጥ ዐይኖቻቸው ተከፈቱ ነገር ግን ምንኛ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሕግን መተላለፋቸው ያስገኘላቸው ነገር ቢኖር የሀጢአት መርገም የሆነውን ክፉውን ማወቅ ብቻ ነው፡፡ ፍሬው በራሱ መርዛማነት የለውም፡፡ የፍሬውን መልክና ቀለም አይቶ ለመመገብ ከመውደዱ ላይም አይደለም ኃጢአትነቱ፡፡ የእግዚአብሔርን አምላክነት ካለማመን ላይ ነው እንጅ፡፡ የመጀመሪያ ወላጆቻችንን ሕግ ተላላፊ ያደረጋቸውና ወደዚህ ዓለምም የክፋትን ዕውቀት ያመጣው የእርሱን ቃል አለማመንና ሥልጣኑንም አለመቀበለ ነው፡፡ ለውሸትና ለስህተት ዓይነቶች ሁሉ በር የከፈተውም ይኸው ነበር፡፡ EDA 22.2

የሰው ልጅ እውነት ወደሆነውና ማስተዋልም ሁሉ በርሱ ዘንድ የሆነውን አምላክ ከማዳመጥ ይልቅ አሳሳቹ ሰይጣን የሚለውን ለመስማት በመምረጡ ሁሉንም ነገር አጣ፡፡ ክፉውንና በጐውን በማደባለቁ ሐሳቡ ተምታታበት፡፡ ሕሊናውና መንፈሳዊ ኃይሉ ደነዘዘ፡፡ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ያጐናፀፈውን በጐ ነገር ማድነቅና ማመስገን አልቻለም፡፡ EDA 22.3

አዳምና ሄዋን ክፉውን ለማወቅ መረጡ፡፡ ስለዚህም ያን ያጡትን የቀድሞውን ደረጃ እንደገና ለማግኘት ከፈለጉ ራሳቸው በራሳቸው ላይ ባመጡት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ ግድ ሆነባቸው፡፡ ከዚያ ወዲያ በኤደን መቆየት አልቻሉም ምክንያቱም ፍፁም የሆነችው ኤደን አሁን ላሉበት ደረጃ የሚሆን ትምህርት ልትሰጣቸው አትችልምና፡፡ እናም ሊነገር በማይችል ሀዘን ያችን ግሩም ድንቅ የሆነች ሥፍራና አካባቢዋን ተሰናብተው ወጡ፡፡ የሀጢአት እርግማን በወረደባት መሬት ላይም መኖር ጀመሩ፡፡ EDA 22.4

እግዚአብሔርም ለአዳም እንዲህ አለው፡፡ «የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፡፡ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝኩህም ዛፍ በለተሃልና ምድር ካንተ የተነሳ የተረገመች ትሁን፡፡ በሐይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ከርሷ ትበላለህ፡፡ እሾህና አሜኬላን ታበቅልብሃለች፡፡ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ ወደመጣህበት መሬት እስክትመለስ በፊትህ ወዝ እንጀራ ትበላለህ፡፡ አፈር ነህና ወደአፈር ትመለሳለህና፡፡ (ዘፍ 3፡17-19) EDA 23.1

ምንም እንኳን ምድር ብትረገምም ተፈጥሮ የሰው ለጅ የትምህርት መጽሐፍ እንደሆነች እንድትቀጥል ተደርጐ ነበር፡፡ አሁን ግን በጐ ነገርን ብቻ የምትወክል አልሆነችም፡፡ ምክንያቱም ክፉውን በየሥፍራው ሞልቶ ነበርና፡፡ ምድርን አበላሽቷታል፣ ባህሩንም አየሩንም ሁሉ በክሎታልና፡፡ ባንድ ወቅት የእግዚአብሔር ባህሪይና በጐ ዕውቀት ብቻ ተጽፎበት የነበረው ሥፍራ ሁሉ አሁን የሰይጣን ባህሪና ክፉው እውቀት ተጽፎበታል፡፡ በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ክፉና በጐውን እንዲሁም የኃጢአትን ውጤት በማያቋርጥ ማስጠንቀቂያ ከተፈጥሮ ይማር ጀመር፡፡ EDA 23.2

አዳምና ሄዋን ከሚወድቁ አበባዎች ከሚረግፉ ቅጠሎች የፈራሽነትን ምልክት ተማሩ፡፡ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ሞት እንዳለበት በጉልህ አእምሮአቸው ውስጥ ተቀረፀ፡፡ ዋና የሕይወታቸው መተማመኛ የነበረው አየር እንኳን ሳይቀር የኃጢአትን ዘር ፍሬ እንደያዘ ተረዱ፡፡ EDA 23.3

ጥለውት ስለመጡት ያ የጥንቱ ግንዛታቸውም ያለማቋረጥ ማስታወሻ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አነስተኛ ፍጥረታት መካከልም አዳም ለእግዚአብሔር ታማኝ እስከሆነ ድረስ እንደ ንጉሥ እንዲሆንና ፍጥረታት ሁሉ እርሱ ለሚለው ሁሉ እንዲታዘዙ ተደርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕግን ሲተላለፍ ያ ሁሉ ግዛት ተወሰደበት፡፡ እሱ በሩን የከፈተለት የአመጽ መንፈስ በፍጡር እንስሳት ሁሉ ላይ ተስፋፋ፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአራዊት ፀባይ፣ የዱር ዛፎች ባህሪ፣ በየሜዳው ያለው ሳር፣ ለእስትንፋስ የሚያገለግለው አየርም ሁሉ የክፉውን ዕውቀት አሳዛኝ ትምህርት ይናገሩ ጀመር፡፡ EDA 24.1

ይሁንና የሰው ልጅ ራሱ የመረጠው የክፉ ነገርን ውጤቶች ማግኘት አልተተወም፡፡ «በህይወት ዘመንህ ሁሉ ትበላለህ ባንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፡፡ እሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፡፡» ዘፍ 3፡15 ይህ የመጀመሪያ ወላጆቻችን እየሰሙ የተነገረው ዓረፍተ ነገር ለእነሱ የተስፋ ቃልም ነበር፡፡ እጣ ፈንታቸው ስለሚሆነው ስለ እሾክህ አሜኬላ፣ ስለ ላብ ማፍሰስ ጣርና ስለ ሐዘን ወይም በኋላ ተመልሰው ስለሚገቡበት አፈር ከመስማታቸው በፊት ተስፋ የሚሰጠውን ቃል ሰሙ፡፡ ወደ ሰይጣን በማዘንበላቸው ምክንያት ያጡትን ሁሉ በክርስቶስ እንደሚመለስላቸው ተገነዘቡ፡፡ EDA 24.2

ይኸንን ማበረታቻ ተፈጥሮ ራሷ ደግማ ታቀርበዋለች፡፡ ምንም በሀጢአት ብትበላሽ ስለ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን ስለ መዳንም በሚገባ ትናገራለች፡፡ ምንም እንኳን የእርግማን ማስረጃ ምስክርነቷን በሚበሰብሱ ነገሮች ምልክት ብታሳይም ሕይወትና ኃይል በሚሰጡ አስደሳች ነገሮች የተሞላች ነች፡፡ ዛፎች ቅጠላቸውን ያረግፋሉ፡፡ ይህም አዲስ ቀምበጥ ለማውጣት እንደያስችላቸው ነው፡፡ አበባዎችም ይሞታሉ ይህም ሌላ ልዩ ውበት ያለው አዲስ አበባ ለማውጣት ነው፡፡ እናም በእያንዳንዱ ነገር ውስጥ የመፍጠር ኃይሉ መግለጫ ያለና እኛም እንደገና ተመልሰን በአዲስ መልክ «በጽድቅና በእውነት ቅድስና» (ኤፌ 4፡24) እንደምንፈጠር ማረጋገጫ ተቀርጾበታል፡፡ ስለዚህም ይህ ተጨባጭ የተፈጥሮ ለውጥ ወደ አዕምሮአችን በግልጽ የሚያመጣልን ለዚያ ሁሉ ላጣነውና ላመለጠን ታላቅ ነገር ሁሉ የተስፋ መልክተኛ ወይም አስታዋሽ ሆኖ ነው የቀረበልን፡፡ EDA 24.3

ክፉ ነገር በተስፋፋ ቁጥር የአባታችን ድምጽ ልጆቹ ኃጢአትና ውጤቶቿን እየተመለከቱ እንዲርቋትና በጐውን እንዲቀበሉ በመጋበዝ ሲማፀን ይሰማል፡፡ EDA 25.1